>
5:13 pm - Thursday April 19, 2503

እፍረተ ቢሱ ንጉሱ ጥላሁን !!! (አቻምየለህ ታምሩ)

እፍረተ ቢሱ ንጉሱ ጥላሁን !!!

አቻምየለህ ታምሩ
ንጉሱ ጥላሁን የሚባለውን አይነት የአማራ ሕዝብ ነቀርሳ የሆነ፣ ሆዱን ብቻ የሚያሰላ፣ የአማራ ህመም የማያመው፤ የአማራ በደል የማይሰማው፤ የአማራ ግፍ እንደሰው የማያሳዝነው እርመ በል ፍጡር ያለ አይመስለኝም።  በስምና አድራሻ የተጠቀሱ 17 የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ  የአማራ ተወላጅነት ያላቸው ተማሪዎች በአሸባሪው ኦነግ መታገታቸውን ተከትሎ እንዲለቀቁ ከአንድ ወር በላይ ስንጮህ ከርመን ሕዝቡ የልጆቹ ሁኔታ አሳስቦት በከፍተኛ ሁኔታ መነሳሳት ሲጀምር  አጀንዳ ለማስቀየር ጥር 2 ቀን 2012 ዓ.ም. በአገዛዙ ልሳን ብቅ ብሎ  በሰጠው መግለጫ አገዛዙ 21 ተማሪዎችን  ማስለቀቁንና 6 ተማሪዎች ብቻ ታግተው  ሳይለቀቁ እንደሚገኙ ገልጾ ነበር።
በዚህ በእርመ በሉ ንጉሱ ጥላሁን መግለጫ መሰረት ታገቱ ብለን በስም፣ በፎቶና በአድራሻ ስንጮህላቸው ከነበሩት 17 ተማሪዎች መካከል ሳይለቀቁ የቀሩ ስድስት ተማሪዎች ብቻ ነበሩ ማለት ነው። ስድስት ብቻ ታጋቾች ሳይፈቱ እንደቀሩ በጥር 2  መግለጫው  የነገረን  ፍጡር ትናንትና በሰጠው ሌላ መግለጫው ጥር 2 ቀን አገዛዙ አስለቀቃቸው ብሎ የነገረን የ21 ተማሪዎች ጉዳይ እውነት መሆኑን ሳያፍር በመድገም ሊያሳምነን ሞክሯል።
በሌላ በኩል ደግሞ በመታገታቸው ስንጮህላቸው ከነበሩት ተማሪዎች መካከል ስድስት ተማሪዎች ብቻ ታግተው እንደሚገኙ የነገረን ሰውዬ ትናንትና ዐይኑን በጨው አጥቦ ስንጮህላቸው የነበሩት 17 ተማሪዎች በሙሉ ታግተው እንደሚገኙ ስጥ እንደቀመሰ ዶሮ ክንፉን ዘርግቶ ፤ በሚሰፈርለት ቀለብ የሰባውን ኩልኩልቱን እያሳዬ ፤ እንደ መቃበር በተከፈተው ጉሮሮው ሲጋት ያደረው ካቲካላ ያጎረነነውን ላንቃውን እያሟሸ ፤ ሰው መሳይ ያደረገውን ኮቱን እንደ ክንፍ ዘርግቶ ፤ እየተከፈለው በሚሞላው ቀፈቱ ላይ ያሳረፈውን ክራባቱን እያስተካከለ ሳይሰቀጥጠው ሲናገር ተደምጧል።
ይህ ኅሊናውን ብቻ ሳይሆን ነፍሱንም ጭምር የሸጠ ፍጡር ለመሆኑ ልጆች አሉት? ሌላው ቢቀር ለልጆቹ ሲል ትንሽ እንኳ ከሆዱ ቀንሶ አያስብም? ነገ ልጆቹ ብቻ ሳይሆን ዘሮቹ  ባጠቃላይ ተሸማቅቀው፣ ከሰው በታች ሆነው እንዲኖሩ የዛሬው ስራው ምስክር ሆኖ እንዲኖር እየሰራ መሆኑ አልታወቀው ብሎት ይሆን? ፋሽስት ወያኔና ናዚ ኦነግ በአማራ ላይ ያሰቡትን ክፋትና ጥፋት ሆዳሞቹ እነ  ንጉሱ ግንባር ቀደም መሳሪያ ሆነው ያላስፈጸሙበት ጊዜና ቦታ ኖሮ ያውቃልን?
Filed in: Amharic