>

ብሄርተኝነት ታሪክን እና የድሮ በደልን እየቆሰቆሱ በቂም ማያያዝን እንደርእዮተ-አለም የሚጠቀም ነው!!! (ሙክታሮቪች) 

ብሄርተኝነት ታሪክን እና የድሮ በደልን እየቆሰቆሱ በቂም ማያያዝን እንደርእዮተ-አለም የሚጠቀም ነው!!!

(ሙክታሮቪች)
ኢትዮጵያን የምንል ሰዎች ከኢትዮጵያ የተለየ ጥቅም ስለምናገኝ አይደለም:: ኢትዮጵያ በአንድነቷ እንደታሪኳ ቀና ብላ በአለም ላይ ብትደምቅ ብትበለፅግ ለእኛ የተለየ ድርሻ ይኖረናል ብለን አይደለም። የሁላችንም ጥቅም ጎልቶ ስለሚታየን ብቻ ነው።
.
ተዉ አንድ እንሁን፣ ተዉ ቂም በቀል አንፈልፍል፣ ተዉ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ማንም ኢትዮጵያዊ ያሻው ቦታ ላይ ሠርቶ የማፍራት፣ መርጦ የመኖር ነፃነት እና መብቱ ይጠበቅለት ማለታችን ፣ ማረፊያ መውደቂያ ስላጣን አይደለም፣ የአባት የእናት የዘመድ አዝማድ የትውልድ ቦታ አጥተን አይደለም:: አንድ እንሁን አንለያይ ማለት መነሻ የሌለን ወፍዘራሽ ስለሆን አይደለም። የሀገርና የፖለቲካ ትርጉም ስለገባን ነው። የዜግነት ፅንሰሀሳብ የሚመሰረተው በሁሉ እኩልነት ላይ መሆኑ ስለገባን ነው። የእኔ ብሄር ብቻ ያስተዳድር በሚል የሚጀመር ፖለቲካ በየትኛውም መስፈርት ኃላቀር ፖለቲካ መሆኑ ስለገባን ነው።
.
ኢትዮጵያን ያልን በዚህች ሀገር ከመጎዳት ውጪ ያተረፍነው የለም። ብሔራችንን ያላልን በሀገራችን ተገፍተናል፣ ባይተዋር ሆነናል፣ ተበደልናል፣ ከንቀትና የቀድሞ ስርዓት በደል ተሸካሚ ከመሆን ውጪ ያተረፍነው የለም። ተናቅን እንጂ አልተከበርንም:: አጣን እንጂ አላገኘንም::
መታገሳችን እኛ ጀግንነትና ድፍረቱን አጥተን፣ ብሔሬን ያሉት ስለጀገኑም አይደለም:: ብሄርተኝነት መንገድ የሚመጣውን መዓት መተንበይ ስለቻልን ነው። አለም በብሄርተኝነት የት መቀመቅ እንደገባች፣ ሀገራት እንዴት እንደፈረሱ ስላጠናን፣ ከአዋቂዎች አንደበት ቁጭ ብለን ስለተማርን፣ በግል ከመጠቀምና ለስልጣንና ክብር ከመስገብገብ የሀገርና የህዝብን ሰላምና ቀጣይነት ስለፈለግን ነው።
ጥቂቶች አይደለንም። በሀገራችን ባይተዋር የሆን ሚልዮኖች ነን። የሚወክለን ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት አጥተን የምንብሰለሰል ሚልዮኖች ነን።
ለምን ይህን አቋም መረጥን?
የሀገር ፍቅር በጥቅም ስለማይመዘን ነው:: ትሥሥራችን እያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ የዘለቀ ስለሆነ ነው:: ሀገር ከመንደር ስለሚሻል ነው:: ሠርተን፣ ለፍተን በላባችን አፍርተን፣ አንገታችንን ቀና አድርገን የምንኖርባት ሰላማዊ ሀገር ለመፍጠር ነው:: ደስታም ስኬትም፣ ዝናም ክብርም፣ ሀብትም ፍቅርም፣ ትዳር ጥሪትም፣ ዕምነት ተስፋም፣ ሰርግ ቀብርም…ሁሉም በሀገር እንደሚያምር ስለገባን ነው:: መስከናችን፣ ዝም ማለታችን ለሀገር የሚበጅ ከሆነ ግዴለም ይሁን ብለን እንጂ እውነት ከኛ ጋ መሆኗን አጥተን አይደለም።
.
የብሄርተኝነት መንገድ ለሰጥቶ መቀበል የማያመች፣ መነጋገር የሌለበት፣ እኛ እና እነሱ በሚል ግጭት ቀስቃሽ ቁርሾና ጥላቻ በመፈልፈል ህዝብን ከህዝብ ስለሚያጋጭ ነው የምንርቀው። ብሄርተኝነት ታሪክን እና የድሮ በደልን እየቆሰቆሱ በቂም ማያያዝን እንደርእዮተአለም የሚጠቀም፣ በፍርሃትና በስጋት ህዝብን እያመሰ ድጋፍ የሚሰበስብ የጥቅመኞች መንገድ ስለሆነ ከግል ጥቅም ጥቅም ሀገርን መርጠን ነው የራቅነው።
በብሄር እየተቧደኑ ደም መፋሰስ ያረጀ ያፈጀ፣ ሗላ ቀር፣ እንስሳዊ ባህሪ ስለሆነ ነው የራቅነው:: መጫረስ የኢትዮጵያ ጠላቶች ያቀዱልን እና ማዳከም ማልፈስፈስና አቅመቢስ ማድረግ የፕሮጀክታቸው ግብ ስለሆነ ነው ብሄርተኝነትን የምንጠየፈው። የብሄር ፅንፈኝነት አሸናፊ የማይኖርበት ሁላችንንም መቀመቅ ይዞን የሚወርድ የጋራ ውድመት መንገድ ስለሆነ ነው የምንርቀው።
.
ማንም ማንንም ለፍቶ ካቀናው ሀገር፣ ተወልዶ ካደገበት ከተማ፣ ከአባቱ ርስት በዋዛ ሲነቀል ዝም ስለማይል መተላለቅ ደጃችን ላይ መሆኑን ፈርተነው ከልዩነት አንድነትን የምንመርጠው። ማንም በማንም ላይ የበለጠ ጀግና ስላይደለ የእልህ ፖለቲካ ያዳክመናል ብለን ነው ጎሰኝነትን የራቅነው። ማንም በየትም ቦታ መኖር መክበርና ወልዶ መሳም አለበት ብለን ስለምናምን ነው የብሄር ፖለቲካ ዘመናዊውን አለም የማይጥን አደገኛ ስለሆነ ነው የማንከተለው።
ይህ ማለት ብዛኻነትን የምንክድ ሆነን አይደለም። አንድነት ልዩነትን ማሰሪያ አማራጭ የለሽ መፍትሄ እንጂ ጨፍላቂነት እንዳልሆነ እናውቃለን። አንድነት የልዩነት ማሰሪያ ብርቱና ወርቃማ ገመድ መሆኑን እናውቃለን። ልዩነት የአንድነት ጌጥ መሆኑን እናውቃለን። ሀገር በአንድነት ላይ ተመስርታ ልዩነታን ማቀፍ እንዳለባት እናምናለን። ከልዩነት መነሳት ወደ አንድነት ሳይሆን ወደ የባሰ መከፋፈል እንደሚወስደን ስለገባን ነው አንድነትን የምናስቀድመው እንጂ ልዩነት አይኑር ብለን አይደለም።
.
በሀይማኖትና በጎሳ የሚለያዩን በችግር ጊዜ ከእኛ ጋ እንደማይሆኑ ስለሚገባን ነው የማንፈልጋቸው። የግጭትና ሞት ነጋዴ ስለሆኑ ነው የምንርቃቸው። የሰው ህይወት መጥፋት ስለሚያመን ነወ የማንወዳቸው። በሞት ስለሚያተርፉ ነው የማንከተላቸው።
ኢትዮጵያን እና ህዝቦችዋን የምናስቀድመው ሁሉ ኢትዮጵያዊ ሰው መሆኑ ተከብሮ፣ እኩል ሆኖ፣ በተከበረችና በበለፀገች ሀገር ላይ ብሄሩ፣ ቋንቋውና ታሪኩ እንደሚከበርና እንደሚበለፅግ ስለምንተልም ነው አንድነትን የምንሻው። የስርዓት ችግር ስርዓቱን በማረምና በማዘመን ይታረማል ብለን ስለምናምን ነው ወደ ኋላ ከማየት ወደ ፊት እያየን ነገአችንን በመመካከረ በእኩልነትና በነፃነት ላይ ሀገር እንገንባ የምንለው። ከትናንት ተምረን ነገን እናሻሽል በማለት ነው የትናንቱን ታሪክ መጥፎ መጥፎውን ብቻ ሳይሆን መልካሙንም እንያዝ የምንለው።
እኛ ይህን ነው የምናስበው። በዚህ እሳቤ ሀገር ያድጋል እንጂ ማንም አይጨፈለቅም። ማንም አይዋረድም። የአለም ሀገራት የሚሄዱበትም መንገድ ይህ ነው።
.
ኢትዮጵያ ከነህዝቦችዋ ከነልዩነቷ ለዘላለም በአንድነቷ ትኑር!
Filed in: Amharic