>
5:13 pm - Wednesday April 19, 3752

"መቼ ታሰርክና ነው የምትፈታው?" - ፖለቲካዊ ቧልት!!! (አሳዬ ደርቤ) 

“መቼ ታሰርክና ነው የምትፈታው?” – ፖለቲካዊ ቧልት!!!

 

አሳዬ ደርቤ 
እሜቴ ‹‹ከዚህ በኋላ እኔን የሚመለከት ነገር ጽፈህ ባገኝ ለለውጡ ቀጣይነት ስል እፈታኻለሁ›› ባለችኝ ጊዜ…. ቤቴን ትቼ ወግ ፍለጋ ወደ ፌስቡክ አካውንቴ ስገባ…. ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በአንድ እጃቸው አበባ፣ በሌላ እጃቸው ካሜራ ይዘው ሰው ሲፈልጉ አገኘኋቸው፡፡ ከእሳቸው አጠገብ ደግሞ በላይ በቀለ ወያ ባንድራና ሞባይል ይዞ አካባቢውን ይቃኛል፡፡
ይሄንንም ባየሁ ጊዜ ‹‹ምን ሆናችሁ ነው?›› ብዬ ስጠይቃቸው ‹‹እኔን አንሳኝ፣ እኔን አንሳኝ›› እያሉ ያዋክቡኝ ጀመር፡፡
‹‹ምንድን ነው የማነሳችሁ?›› ባልኳቸው ጊዜም ጠቅላያችን ፈጠን ብለው ‹‹ፌስቡክ ላይ የምንለጥፈው ፎቶ›› በማለት መለሱ፡፡
‹‹ካሜራ ማን አልነበረዎት እንዴ?››
‹‹ነበረኝ! ግን እንደ ስናይፐር ተኳሽ ካሜራ ሌንስ ላይ አጨንቁሬ የምውልበት አንድ ዐይኔ ደከመ ብሎ ሥራ ለቀቀ!›› የሚል መልስ እየሰጡኝ ሳለ ‹‹እንደ’ኔ አንድ ፎቶ ካላችሁ እሱን እያቀናበራችሁ አትለጥፉም?›› እያለ ታየ ቦጋለ መጣና…. እሱ የበላይ በቀለን ሞባይል ሲቀበል፣ እኔ የጠቅላያችንን ካሜራ ተረክቤ…. እስኪደክመኝ ድረስ በርካታ ፎቶዎችን ሳነሳቸው ቆየሁ፡፡ ከዚያም ካሜራቸውን ሰጥቻቸው ጉዞ ስጀምር ያነሳኋቸውን ፎቶዎች አልተመቿቸውም መሰል ‹‹ድሮም እናንተ የሰሜን ሰዎች በመፈንቅለ-መንግሥት መሪን ከሥልጣኑ ማንሳት እንጂ ፎቶ ማንሳት መቼ ታውቁበታለችሁ?›› እያሉ ይቆጡ ጀመር፡፡
/
ለእሳቸው መልስ በመስጠት ፈንታ በዝምታ ወደ ፊት ስጓዝ…. ሥዩም ተሾመ ብትን ብሎ መርቅኖ ‹‹አብን አብን ›› እያለ ሲመጣ አገኘሁት፡፡
‹‹ወዴ’ት እየሄድክ ነው?›› ባልኩት ጊዜም ‹‹ብልጧን ፍለጋ›› እላለሁ ብሎ ‹‹በለጠን ፍለጋ›› ካለኝ በኋላ ‹‹ከለጠፍኩት አፈትላኪ መረጃ ምን ተረዳህ?›› የሚል ጥያቄ አቀረበ፡፡
‹‹መረጃውን ስለ በለጠና ዶክተር ደሳለኝ የሚያወራ ሲሆን… ዓላማው ደግሞ አብንን ማፈራረስ ነው!›› ብየ መለስኩለት፡፡
ይሄንንም ባልኩት ጊዜ ‹‹አዎ አብንማ መፍረስ አለበት›› ብሎኝ ምርቃናውን የሚያፈርስበት ግሮሰሪ በዐይኑ ሲፈልግ ከማል ገልቹ ከአንዱ ግሮሰሪ በረንዳ ላይ ተቀምጦ ከሆነች አስተናጋጅ ጋር ሲጨቃጨቅ ዐየውና ወደ እሱ ዘንድ አመራ፡፡
እናም ወደ ሌላ ስፍራ ከመሄዴ በፊት ጭቅጭቁን ሳዳምጥ….  ከማል በሞቅታ መንፈስ የሆነ ካርታ ከጠረጴዛ ላይ ዘርግቶ በምላጭ እየቀረጸ ‹‹የጠጣህበትን ሒሳብ ክፈል›› እያለች ለምትጠይቀው አስተናጋጅ ‹‹ኦሮሚያን እስክገነጥል ድረስ ፋታ ብትሰጪኝ ምን አለበት›› እያለ ይመልስላታል፡፡
/
ጭቅጭቁን ትቼ የሞባይሌን ስክሪን ሳንሸራትተው እነ ክርስቲያን ታደለ ከቃሊቲ እሥር ቤት ሲወጡ በር ላይ አገኘኋቸውና ሁሉንም እስረኞች ‹‹እንኳን ደስ አላችሁ›› እያልኩ አቅፌ ስስማቸው ቆየሁ፡፡
በዚህ መሃከል ታዲያ አቦ ጃዋር ወህኒ-ቤቱ በር ላይ ቆሞ ማየቴ ትኩረቴን ሰረቀውና ‹‹ይሄ መንግሥት በእነ ክርስቲያን ቦታ ጃዋርን ሊያስገባው ነው እንዴ›› ከሚል ጥያቄ ጋር በትኩረት እከታተለው ጀመር፡፡
ከአፍታ ቆይታ በኋላም…. ጃዋር የእስረኞቹን ማንነት እየመዘገበ ዘር ሲቆጥር ከቆየ በኋላ ‹‹አንድም ኦሮሞ አልተፈታ›› ማለት ሲጀምር ‹‹መቼ ታሰርክና ነው የምትፈታው?›› የሚል ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡
እሱ ግን ለጥያቄ መልስ በመስጠት ፈንታ የታሰሩት የአብን እና የህውሓት አመራሮች በምህረት ተለቅቀው ሲወጡ ኦነግ ባለመሆናቸው ሲበሳጭ ከቆየ በኋላ ‹‹እዚህ ሐገር የኦሮሞ ተጠቃሚነት የሚረጋገጠው መቼ ይሆን?›› እያለ ፊት ለፊት ወዳለው ሥጋ ቤት አመራ፡፡ እሱንም ተከትዮ ዐይኔን ወደ ሥጋ ቤቱ ስወረውረው ‹‹የኩሽ ሉካንዳ ቤት እና ቤተ-ክህነት›› የሚል ታፔላ አነበብኩ፡፡ ከሉካንዳ ቤቱ ውስጥም ቄስ በላይ በመስቀል ፈንታ ቢለዋ ይዘው ‹‹የሙስሊም ነው የክርስቲያን?›› እያሉ ለሚጠይቋቸው ሥጋ ሸማቾች ‹‹እኔ የማርዳቸው በሬዎች ማንነት እንጂ ሃይማኖት የላቸውም›› እያሉ ይመልሱላቸዋል፡፡
Filed in: Amharic