>

የዳንኤል ክብረት ነገር (አቻምየለህ ታምሩ)

የዳንኤል ክብረት ነገር

 

 

አቻምየለህ ታምሩ
የውሸት ታሪክ ጽፎ እነ አቶ በላይ መኮንንን በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ላይ ያስነሳው ዳንኤል ክብረት፣ የዐቢይ አሕመድ እልፍኝ አስከልካይ ከኾነ ወዲህ ኦሮማይዝ ለማድረግ ያልሞከረው የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ዐቢይ ክስተት ያለ አይመስለኝም። ዳንኤል ከሰሞኑ የካቲት 12 ቀን የተከበረውን የሰማዕታት ዝክር  አስመልክቶ አዲስ አበባ ውስጥ በአንድ መድረክ ላይ ተገኝቶ በግራዚያኒ ላይ የግድያ ሙከራ ስላደረጉ ሰዎች ሲተርክ የአርበኝነት ተጋድሎውን ኦሮማይዝ ለማድረግ ያልፈነቀለው ድንጋይና ያልበጠሰው ቅጠል የለም። ዳንኤል የታሪኩ ባለቤት የኾኑ ሰዎችን ማንነት እየለወጠ ኦሮማይዝ ለማድረግ ያን ያህል ሲራኮት በግራዚያኒ ላይ የተካሄደውን የየካቲት 12ቱን የግድያ ሙከራ የመሩትና ያንን አስደናቂ ተጋድሎ የጠነሰሱትን የአማራ ጀግኖች ማንነት ግን ጠርቶ ስለ ውለታቸው ሊያወሳቸው አልፈለገም።
 ‹ውሻ በበላበት ይጮኻል› እንዲሉ ዳንኤል ይህንን የሚያደርገው አለቆቹ እነ ዐቢይ አማራን እንዲያወግዝ እንጂ የዚያ አስደናቂ የአርበኝነት ተግባር ምሳሌ ተደርጎ እንዲጠቅስ እንደማይፈልጉ ስለሚያውቅ ነው።
ዳንኤል በዝክረ በዓሉ ላይ ያደረገውን ዲስኩር የጀመረው የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ግራዚያኒን ለመግደል በተደረገው የአርበኝነት ተጋድሎ ላይ ዋነኛ ተዋንያን ነበሩ ያላቸውን ሰዎች በማውሳት ነበር። በመጀመሪያ ደረጃ ያወሳውም የሐረር ሰው ያደረገውን ስብሐት ጥሩነህን ነበር። በግራዚያኒ ላይ የፈነዳውን ቦንብ የጣሉት እነ አብርሃ ደቦጭ፣ እቅድ ያወጡትና የመከሩትም ስብሐት ቤት ውስጥ እንደኾነ ዳንኤል ነግሮናል። ይህ የዳንኤል አተራረክ በጭምጡም ኾነ በታሪካዊ እውነታው የተሳሳተ ነው። ዳንኤል ልብ ወለድ ፈጥሮ ያልተደረገና ያልኾነ ታሪክ ሊነግረን የተነሳው እንደለመደበት ታሪካችንን ለአለቆቹ መተያያ አቅርቦ አሰላለፉን የበለጠ ሊያሳምር ስለፈለገ ነው።
ዳንኤል ወደ ጌቶቹ ነገድ ግንድ ለማስጠጋት የሐረር ሰው አድርጎ ያቀረበው ስብሐት ጥሩነህ የበጌምድር አማራ እንጂ እሱ ሊያደርገው እንደሞከረው የሐረር ኦሮሞ አይደለም። ስብሐት ጥሩነህ የተወለደው በሰኔ ማርያም ዕለት በ1900 ዓ.ም. ደብረ ታቦር ሲኾን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በስዊድን ሚሽን በአስተማሪነት ሲሠራ ቆይቶ በ1923 ዓ.ም. ሀርማንስቡርግ ሚሽን ወደሚባለው የጀርመን ሚሽን ተዛውሮ በአማርኛ አስተማሪነት ይሠራ በነበረበት ወቅት ነበር ጥሊያን ኢትዮጵያን የወረረችው። (ምንጭ፡ Campbell, I. (2017). The Addis Ababa Massacre: Italy’s National Shame. Oxford University Press; Page 246) ስለዚህ ስብሐት ጥሩነህ የደብረ ታቦር አማራ እንጂ ዳንኤል በመተያያው እንዳቀረበው የሐረር ኦሮሞ አለመኾኑ መታወቅ አለበት። ስብሐት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ደብረ ታቦር ውስጥ የሚኖር ታደሰ ጥሩነህ የሚባል ወንድም ነበረው። የስብሐት ጥሩነህን ታሪክ ያጠናው ኢያን ካምቤል ስለ ስብሐት የሕይዎት ታሪክ የጻፈው ወንድሙን ታደሰ ጥሩነህን ቃለ መጠይቅ በማድረግ እንደኾነ ቀደም ብዬ በጠቀስኩት መጽሐፉ ነግሮናል።
ዳንኤል ለአድማጩ የተናገረው ሌላው የተሳሳተ ታሪክ በግራዚያኒ ላይ ቦንብ ለመጣል እነ አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ያሴሩ የነበረው ስብሐት ቤት ውስጥ እንደነበረ አድርጎ ያቀረበው ታሪክ ነው። በመጀመሪያ በግራዚያኒ ላይ ቦንብ የመጣል ሐሳብ የተጠነሰሰው በስብሐት ጥሩነህም ኾነ በነ አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም አይደለም። በግራዚያኒ ላይ ቦንብ የመጣልና ግራዚያኒን የመግደል ሐሳብ የተጠነሰሰው በንጉሠ ነገሥቱ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ነው። ከማይጨው ሽንፈት በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ ጀኔቭ ሄደው የኢትዮጵያውያንን አቤቱታ በመንግሥታቱ ማኅበር ፊት በየጊዜው እየቀረቡ ለማሰማት (በተለይም ፋሽስት ጣሊያን አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ) የገጠማቸው ፈተና፣ ፋሽስት ጥሊያን ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ስለተቆጣጠረች የመንግሥታቱ ማኅበር ውስጥ የነበረው የኢትዮጵያ ወንበር ለጥሊያን ተላልፎ መሰጠት አለበት የሚለው የአባል ሀገራቱ ውሳኔ ነበር። ኢትዮጵያ በሊግ ኦፍ ኔሽን የነበራት የአባልነት ወንበር ለፋሽስቶቹ ተላልፎ እንዳይሰጥ ለማድረግ ንጉሠ ነገሥቱ የነበራቸው አንድ አማራጭ አዲስ አበባን የተቆጣጠረውን የፋሽስት መሪ በመግደል የኢትዮጵያ አርበኞች አዲስ አበባን መልሰው ለመያዝ በመዋጋት ላይ መኾናቸውን ለማኅበሩ በማሳወቅና በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል ብቻ ሳይኾን በዋና ከተማዋ በአዲስ አበባ ውስጥም አርበኞች ትግል ላይ እንደኾኑ ጥሊያን ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥራ እየገዛች አለመኾኗን ማሳየት ነበረባቸው።
ባጭሩ ንጉሠ ነገሥቱ በዋና ከተማቸው ላይ እንዲደረግ ያሰቡትን ጉልህ ተጋድሎ ለዓለም በማሳየት ኢትዮጵያ በጀኔቭ የነበራት ወንበር ለፋሽስቶች ተላልፎ እንዳይሰጥ ለመከራከር ሲሉ ነበር የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. በኢጣሊያ ንጉሣዊ ቤተሰብ አንድ ልዑል መወለዱን ምክንያት በማድረግ በግራዚያኒ ትእዛዝ በቀድሞው የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቅጽር ግቢ) በተዘጋጀው የድግስ ፕሮግራም ላይ የሚገኙ የፋሽስት ከፍተኛ ሹማምንት በሙሉ እንዲገደሉ በውጭ ጉዳይ ሚንስትራቸው በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ በኩል ወደ አዲስ አበባ ትእዛዝ ያስተላለፉት። (Campbell, I. (2007). “Yekatit” 12 Revisited: new light on the strike against Graziani. Journal of Ethiopian Studies, 40 (1/2), 135-154; Page 142)
ይኽንን በፋሽስት ከፍተኛ ሹማምንት ላይ የታቀደውን የግድያ ኦፕሬሽን እንዲያስፈጽሙ የታዘዙት ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ የነበሩት ደጃዝማች ለጥይበሉ ገብሬ ነበሩ። ደጃዝማች ለጥይበሉ ገብሬ የመርሃቤቴ አማራ ናቸው። ልብ በሉ! ትእዛዙን ወደ ደጃዝማች ለጥይበሉ ገብሬ በጽሑፍ የላኩት ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር በጀኔቭ አብረዋቸው የነበሩት የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ናቸው። (Ibid)
ብላቴን ጌታ ኅሩይ ለደጃዝማች ለጥይበሉ ገብሬ በጻፉት ደብዳቤ ያስተላለፉት መልዕክት ግራዚያኒና ታላላቅ የፋሽስት የአዲስ አበባ ሹማምንት እንዲገደሉ ብቻ ሳይኾን፣ ይኽንን ኦፕሬሽን በተሳካ ኹኔታ እነማን ሊፈጽሙት እንደሚገባ የሰዎችን ስም በመዘርዘር ነው። ብላቴን ጌታ ኅሩይ በነግራዚያኒ ላይ የታቀደውን ግድያ በተሳካ ኹኔታ ሊፈጽሙ ይችላሉ ብለው ከዘረዘሯቸው ሰዎች መካከል በወቅቱ የፋሽስት አገልጋዮች የነበሩት አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም የሚገኙበት ሲኾን ከተማ ውስጥ ከነበሩት ደግሞ ስምዖን አደፍርስና ጢንቄሳ ኬሎ (የጃጋማ ኬሎ ወንድም) እንዲመለመሉና ኦፕሬሽኑ እንዲካሄድ መክረዋል። (Ibid)
እንግዲህ ደጃዝማች ለጥይበሉ ገብሬ አብርሃ ደቦጭን፣ ሞገስ አስገዶምንና እነ ስምዖን አደፍርስን ለታቀደው ኦፕሬሽን የመለመሉት የንጉሠ ነገሥቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ብላቴን ጌታ ኅሩይ ከጀኔቭ በሰጡት ጥቆማ መሠረት ነው። የደጃዝማች ለጥይበሉ ገብሬ ቀጣዩ ከባድ ሥራ የታዘዙትን ጥቃት ለመፈጸም የፋሽስት ጥሊያን አገልጋዮች የነበሩትን አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶምን አግባብተው ለታሰበው ኦፕሬሽን ማሰልጠን ነበር። ሞገስ አስገዶምንና አብርሃ ደቦጭን ለመመልመል ከተጠቀሟቸው ሰዎች መካከል የወንድማቸው ልጅ በኾኑት በፊታውራሪ ደምሴ ኃይለ ማርያም በኩል የተወዳጁት የሀርማንስቡርግ ሚሽን የሥራ ጓደኛው የኾነው ስብሐት ጥሩነህ ቀዳሚው እጩ ነበር። ሁለተኛው እጩ መልማይ ደግሞ የሁለቱም የተማሪ ቤት ጓደኛ፣ የደጃዝማቹ ወዳጅ ስምዖን አደፍር ነበር።  ልክ እንደ ስምዖን ሁሉ ስብሐትም የታጨበት ምክንያት የአብርሃና ሞገስ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ጓደኛ ስለነበር ነው። ጀግኖቹ ስብሐትና ስምዖን ደጃዝማች ለጥይበሉ የጣሉባቸውን ከባድ የቤት ሥራ በመወጣት የፋሽስቶች ቤተኛ የነበሩትን አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገደሞን በማሳመን ለታቀደው ኦፕሬሽን ተፈጻሚነት ከደጃዝማች ለጥይበሉ ጋር አስተዋወቋቸው። (Campbell, I. (2017).The Addis Ababa Massacre: Italy’s National Shame. Oxford University Press; Page 247)
ብዙ ሰው አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ከየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. በፊት በዱር በገደሉ ሲንከራተቱ የነበሩ አርበኞች ይመስሉታል፤ ይህ ስህተት ነው። አብርሃ ደቦጭ ከወረራው በፊት ከተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ከተመረቀ በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ ሲኖር ለጥሊያን መንግሥት ሲሰልል ተገኝቶ በሀገር ክዳት ተፈርዶበት ግራዚያኒ አዲስ አበባን እስኪቆጣጠር ድረስ በእስር ላይ የነበረ ሰው ነው። ግራዚያኒ አዲስ አበባ ሲገባ በስለላ ሲያገለግለው የነበረው የፋሽስት አገዛዝ ከእስር እንዲወጣ አድርጎት መጀመሪያ የዲቦኖ በመቀጠል የግራዚያኒ የፖለቲካ አማካሪ ኾኖ ተሾመ። ሞገስ አስገዶም ደግሞ የግራዚያኒ አስተርጓሚ የነበረ ታማኝ አገልጋይ ነበር። ታላላቆቹ ስብሐት ጥሩነህና ስምኦን አደፈርስ  አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶምን የትምህርት ቤት ወዳጅነታቸውን ተጠቅሞ ለትልቁ ኦፕሬሽን የመለመሏቸው  በዚህ አኳኋን ታማኝ የፋሽስት አገልጋዮች እያሉ ነው።
በዚህ ኹኔታ በስብሐት ጥሩነህ የተመለመሉት እነ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ፊታቸውን እየተሸፈኑ በመግባት ስለ ኦፕሬሽኑ ሥልጠና ይሰጣቸው የነበረው ዳንኤል ኦሮሞ ሊያደርገው በሞከረው በስብሐት ጥሩነህ ቤት ሳይኾን በመርሃቤቴው አርበኛ በደጃዝማች ለጥይበሉ ቤት ውስጥ ነበር። አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የቦንብ ጥቃት የፈጸሙ ዕለት (የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም) መነሻቸው የደጃዝማች ለጥ ይበሉ ቤት ነበር። (ibid Page 141) ከዚህ በተጨማሪ በግራዚያኒ ላይ የተወረወረውን ቦንብ የገዙትና ለአብርሃና ሞገስ እንዴት እንደሚፈታ አሰልጥነው የሰጧቸው ታላቁ አርበኛ ደጃዝማች ለጥይበሉ ገብሬ ናቸው። (Greenfield, R. (1965). Ethiopia፡ a New Political History. FA Praeger; Page 240])
ዳንኤል ከየካቲት 12ቱ የአርበኝነት ጀብዱ ጋር በተያያዘ ያነሣው ሌላው ሰው እነ አብርሃና ሞገስን ደብረ ሊባኖስ ድረስ በታክሲ የሸኛቸውን፣ ሐረር መወለዱን ተጠቅሞ ወደ ባለጊዜዎቹ የነገድ ማንነት ሊያስጠጋው የሞከረውንና የታክሲ ሾፌር ያደረገውን ስምዖን አደፍርስን ነው። ዳንኤል፣ ስምዖን አደፍርን የታክሲ ሾፌር አድርጎ በማቅረብ በ1966 ዓ.ም. ተካሄደ ብሎ ያሞካሸውን ዐቢዮት ያመጡትን የኢትዮጵያ ታክሲ ሾፌሮች ወክሎ ሐውልት እንዲቆምለት ብዙ ደስኩሯል። እውነታው ግን ስምዖን አደፍርስ የናጠጠ ነጋዴና ወጣት ባለሀብት ነበር እንጂ የታክሲ ሾፌር አልነበረም፤ ስምዖን በዚያ ወቅት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከነበረው ቢዝነስ መካከል ሁለት ታክሲዎች አሰማርቶ የታክሲ አገልግሎት ይሰጥ እንጂ እሱ ራሱ የታክሲ ሾፌር አልነበረም፡፡ ስምዖን ሐረር ይወለድ እንጂ በነገድ ማንነቱም ዳንኤል ወደ ጌቶቹ ሊያስጠጋው እንደፈለገው ኦሮሞ ሳይኾን እናትም አባቱም የአንኮበር አማሮች ናቸው። (Campbell, I. (2017).The Addis Ababa Massacre: Italy’s National Shame. Oxford University Press; Page 247)
በነገራችን ላይ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ኾነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ብፁዕ አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ፣ የስምዖን አደፍርስ ታናሽ ወንድም ልጅ ናቸው። የብፁዕ አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ ዓለማዊ ሥማቸው ደምረው ሱራፌል አደፍርስ ነው። የስምዖን አደፍርስ የካፒታል ምንጭ በወቅቱ ጅቡቲ ይኖር  የነበረው  አጎናፍር አደፍርስ  የሚባል ታላቅ ወንድሙ ነው።  የአደፍርስ ወንድማማቾችን ታሪክ የበለጠ ማወቅ የሚሻ ቢኖር ብፁዕ አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ ከሸገር ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ያዳምጥ።
ዳንኤል የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. በግራዚያኒ ላይ ከተቃጣው የግድያ ሙከራ ጋር በተያያዘ ማንነቱን በትክክል ያነሳው የወለጋ ተወላጁን ዻባ ብሩን ብቻ ነው። ዳንኤል የዻባ ብሩን ስም በግራዚያኒ ላይ ከተካሄደው የግድያ ሙከራ ጋር አያይዞ ያነሳው ታሪኩን ኦሮማይዝ ለማድረግ እንጂ ዻባ ብሩ በግራዚያኒ ላይ በተካሄደው የግድያ ሙከራ እጁ ስላለለበት አይደለም። ዳንኤል፣ ዻባ ብሩን ያነሳው አብርሃና ሞገስ ያፈነዱትን ቦንብ በግል ገንዘቡ እንደገዛው አድርጎ ነው። ይህ ፈጽሞ ነጭ ውሸት ነው። ቀደም ሲል እንዳየነው ቦንቡን የገዙት ደጃዝማች ለጥይገሉ ገብሬ ናቸው። ‹እፍኝ ቆሎ ይዞ ወደ አሻሮ መጠጋት› እንዲሉ ዳንኤል፣ ዻባ ብሩን በግል ገንዘቡ ቦንቡን እንደገዛ አድርጎ ያቀረበው ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ለደጃዝማች ለጥይበሉ ገብሬ ስለ ኦፕሬሽኑ በጻፉት ደብዳቤ ላይ ለኦፕሬሽኑ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ሁሉ ከገንዘብ ያዤ ከዻባ ብሩ ውስድ ብለው የሰጡትን ትእዛዝ ቆልምሞ ነው። (Campbell, I. (2007). “Yekatit” 12 Revisited: new light on the strike against Graziani. Journal of Ethiopian Studies, 40 (1/2), 135-154; Page 142)
ባጭሩ ዳንኤል የወለጋውን ዻባ ብሩን በግራዚያኒ ላይ የተወረወረውን ቦንብ በግል ገንዘቡ የገዛው አድርጎ ሊያቀርበው የፈለገው፣ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ገንዘብ ያዥ የነበረው ዳባ፣ ደጃዝማች ለጥይበሉ ለኦፕሬሽኑ መሳካት ገንዘብ ቢያስፈልጋቸው እንዲሰጣቸው የታዘዘውን የመንግሥት ገንዘብ ነው። ዻባ ብሩም በግራዚያኒ ላይ በተቃጣው የግድያ ሙከራ ዳንኤል ሊነግረን እንደፈለገው እንኳን ገንዘብ አውጥቶ ቦንቡን ሊገዛ እሱ ራሱ ኦፕሬሽኑ በተካሄደበት ወቅት ኢሉባቦር ውስጥ ጎሬ ከተማ ስለነበር ብላቴን ጌታ ኅሩይ ለኦፕሬሽኑ መሳካት ገንዘብ ቢያስፈልግ ለደጃዝማች ለጥይበሉ ብር እንዲሰጥ ያዘዙትን ለማድረግ የሚችልበት ኹኔታ ላይ አልነበረም። (Ibid)
በነገራችን ላይ ዻባ ብሩ ከወረራው በፊት የመጀመሪያውን የአማርኛ ቋንቋ መተየቢያ መኪና (Type writer) የፈለሰፈው የኢንጂነር አያና ብሩ ወንድም ነው። ዻባ ለወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ለብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ በአስተርጓሚነት ሲሠራ የነበረ ሲኾን ብላቴን ጌታ ኅሩይ ጃፓንን በጎበኙበት ወቅት ከጃፓኖች ጋር በተነሱት ፎቶ ውስጥ ዻባ በግራ በኩል በመጀመሪያ ረድፍ ላይ ተቀምጦ የምናየው ወጣት ነው።
ዳንኤል ስለ ወለጋው ዻባ ብሩ ጽናት ሊያስረዳ ያልሞከረው ነገር የለም። ዻባ ግን እንኳን ጽናት ሊኖረው ኢሉባቦር ውስጥ እስከ 1929 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ከቆየ በኋላ ገንዘብ የሚልኩለት አለቃው ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ በ1929 ዓ.ም. በስደት እንዳሉ ባዝ ከተማ ውስጥ መሞታቸውን ሲሰማ ሳይውል ሳያድር ለጥሊያን እጁን በመስጠት ፋሽስትን እስኪያልበው ድረስ አገልግሏል። ዳንኤል ግን ዻባ ብሩን የሚፈልገው የየካቲት 12ቱን የአርበኝነት ተጋድሎ ኦሮማይዝ ለማድረግ ስለኾነ ለጥሊያን ገብቶ ባንዳ ኾኖ ሲያገለግል እንደኖረ ሊነግረን አይፈልግም። እስከመጨረሻው ድረስ ከፋሽስት ጋር የተፋለሙትን፣ በግራዚያኒ ላይ የተሞከረውን የግድያ ኦፕሬሽን ያቀዱትንና ያስፈጸሙትን አሊሙን አርበኛ ደጃዝማች ለጥይበሉ ገብሬን ግን አማራ ስለኾኑ ከየካቲት 12ቱ ታላቅ የተጋድሎ መዝገብ ታሪካቸውን ይፍቀዋል።
ኢትዮጵያን ይወዳል የሚባለው ዳንኤል ክብረት፣ ሀገር የፈረሰበትን የ1966 ዓ.ም. የደናቁርት ዐቢዮት በስሜት የገለጸበት አሳፋሪ ውዳሴ እውነተኛ ማንነቱንና ወቅታዊ አሰላለፉን በግልጽ የሚያሳይ ኾኖ አግኝቼዋለሁ። የ1966ቱን ዐቢዮት አስነሡ ያላቸውን የታክሲ ሾፌሮች ከጣራ በላይ በማሞገስ ዐቢዮቱ እንዲፈነዳ ሞተር በመኾን ለከፈሉት መስዋዕትነት ውለታ የሚኾን ሐውልት ሊቆምላቸው ይገባል ሲል ተከራክሯል። የታሪክ ተመራማሪ እየተባለ፣ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የኢትዮጵያ የሦስት ሺህ ዓመታት ብሔራዊ ትርክት ተደምስሶ በጨቋኝና ተጨቋኝ ትክርት በመተካት እስካሁን ድረስ የመጣንበት የቁልቁለት መንገድ የጀመረበትን ዐቢዮት እንደ ለውጥ የሚቆጥር ቢኖር የሰማውን የሚደግም ከእፉዬገላ የቀለለ ብቻ ነው። ዳንኤል በአደባባይ የመታሰቢያ ሐውልት እንዲቆምለት የሚጠይቀው ዐቢዮት፣ ኢትዮጵያ ወደበለጠ ሥልጣኔ፣ ዲሞክራሲ፣ የፓርቲ ፖለቲካ አደረጃጀትና ልማት እያደረገችው የነበረውን ግስጋሴ ባጭር ያስቀረውንና ጥሩንባ እየነፋ የሚገድል፣ ዘርፎና ወርሶ የማይጠረቃ፣ ሕዝብን ወደ ከብትነትና አልፎም ወደ ግዑዝ ድንጋይነት የለወጠ ሰይጣናዊ አገዛዝ የተተካበትን ክፋት የወለደውን ዐቢዮት ነው።
Filed in: Amharic