>

አቶ ባጫ ጊኒ ንግድ ባንክን ለከፍተኛ ኪሳራ ዳርጎ አምባሳደርነት ተላከ!!! (ጌታቸው ሽፈራው)

አቶ ባጫ ጊኒ ንግድ ባንክን ለከፍተኛ ኪሳራ ዳርጎ አምባሳደርነት ተላከ!!!

ጌታቸው ሽፈራው
ባጫ የጀመረውን የቁልቁለት ሩጫ ሊያስቀጥል ከኦሮምያ ባንክ ሌላ ሰው መጥቷል
አቶ ባጫ ጊኒን ወደ ንግድ ባንክ እንዳመጡት ብዙ ጩኸት ተሰምቶ ነበር። አልሰሙም። በእርግጥ  የኢትዮጵያን ሐብት ለማጋበስ ለሚፈልጉት ባለ ጊዜዎች  የባጫና የታከለ ኡማን ያክል  የጠቀማቸው የለም።
አቶ ባጫ የቀድሞ የንግድ ባንክ አመራሮችን እያባረረ ከኦሮሚያ ባንኮች ሲያመጣ ዝም ተባለ። በማንነት የሚቀርቡትን ባለሀብቶች ከሌሎች የግል ባንኮች የተበደሩትን ብድር ወደ ንግድ ባንክ አስመጣ ሲባል ዝምታን መረጡ። የሌሎች ብድር ወለድ እስከ 17 በመቶ ሲሆን የንግድ ባንክ እስከ 12 የሚደርስ ነው።  ሌሎችን እያከሰረ የራሱን ሲጠቅም ዝም ተባለ።
ዋዜማ ራዲዮ ዛሬ እንደዘገበው ባንኩ ከደንበኞች 24 ቢሊዮን ብር ሰብስቧል። በተቃራኒው 40 ቢሊዮን ብር ብድር ሰጥቷል። ብድሩ የተሰጠው ደግሞ በማንነት  መሰረት መሆኑን ዋዜማ ዘግቧል። ይህን ሁሉ ነውር ሲሰራ ስልጣን ላይ ያሉ አካላት  “አበጀህ” ብለውት ባይሉት ማስቆም ይችሉ ነበር።
በእርግጥ ዘመነኞቹ ከቀደሙት የተማሩትን ነው እያደረጉ ያሉት። ልማት ባንክ የትግራይ ባለሀብቶችን ብቻ  ሲያበድር እንደነበር ይታወቃል። ጋምቤላ ውስጥ መሬት ተቀብለው እናለማለን በማለት ብረት ሲያስመጡበት ኖረዋል። ልማት ባንክ በማንነት ብቻ ሲያበድር ኖሮ ከስሯል። ገዥዎቹ ንግድ ባንክን የአማራ ባንክ ነው ብለው ሲፈርጁት ኖረዋል። ለዚህም አመራሩን እየቀነሱ የራሳቸውን ሰው አስገብተው እንዳልነበር አድርገውታል።  ትህነግ በልማት ባንክ በኩል በርካቶችን መልቲ ሚሊየነር እንዳደረገው ሁሉ እነ ባጫ ጊኒም ማንነትን መሰረት ያደረገ ብድር ሰጥተው የአማራ ነው ያሉትን ንግድ ባንክ ወደ ውድቀት መርተውታል። ሁለቱም ግን ብድር ሲከለክሉ የኖሩት አማራውን ነው።  አማራውን እንዲህ በአድሎ ገፍተው ገፍተው የራሱን ባንክ እንዲመሰርት አድርገውታል።
ባጫ ጊኒ ታዲያ ይህን ሁሉ አድርጎ አምባሳደርነት ተላከ።  መንግስት የሚባለው የወንጀለኛ መደበቂያ ሆኗል የሚባለው ለዚህ ነው። ይህን የመሰለ ወንጀል የሰራን ግለሰብ እንዳይጠየቅ የተከበረውን አምባሳደርነት ስም ደርቦለት ወደ ውጭ ልኮታል። በእሱ ቦታ ደግሞ ከኦሮሚያ ባንክ ሌላ ሰው አምጥቷል። ባጫ የጀመረውን ሊያስቀጥል  ካልሆነ ሌላ ስራ ሊሰራ አይችልም። የሰራውን ሰርቶ እሱንም ጫና ሲበዛ ወደ አንዱ ያዞሩታል።  የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዲህ መጫዎቻ ሆኗል።
Filed in: Amharic