>

እግዚአብሔር ለምን መቅሰፍት ያመጣል?!? (አባ ገብረኪዳን)

እግዚአብሔር ለምን መቅሰፍት ያመጣል?!?

አባ ገብረኪዳን
 ማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል
በልብ መታሰቡ በቃል መነገሩ ስሙ ይክበርና ቸሩ አምላካችን እግዚአብሔር ፍጥረቱን ለመጥቀም ስለ ሦስት ነገር መቅሰፍትን ያመጣል።
፩. ” ከመ መቃብር ክሡት ጎራዒቶሙ – ጉረሯቸው እንደተከፈተ መቃብር ነው ” ለሚላቸው ሰዎች። ማለት መቃብር ቢቀብሩበት ቢቀብሩበት በቃኝ እንደማይል ኃጢአትን በቃኝ ለማይሉ ፥ መመለስን ለማያስቡ መመለስንም ለማይፈልጉ ሲል መቅሰፍትን ያመጣል። ሰው ኃጢአትን ከመደጋገሙ የተነሣ ኃጢአት ወደ ልማድ ይለወጣል። በልማድ ከመታሰሩ የተነሣ ልቡ ይደነድናል። ልቡ ከመደንደኑ የተነሣ ጽድቅን ይጠላል ፥ ኃጢአት ይጣፍጠዋል ። ከዚህ በኋላ ጽድቅን ሁሉ ይቃወማል። ” እስመ ግዘፈ ልብ ዘልፈ ይትቃዎሞ ለጽድቀ እግዚአብሔር – የደነደነ ልቡና ዘወትር የእግዚአብሔርን እውነት ይቃወማል ” እንዲል ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ። ከዚህ ሲያልፍ ምሕረት እንኳ ያስጠላዋል። መጨረሻ ላይ ለማይረባ አእምሮ ተላልፎ ይሰጣል ። ከዚህ ወዲያ በግብሩ አውሬ ወይም ሰይጣን ይሆናል ። አንድ ሰው በዚህ ግብር ለመያዙ የደዌው ምልክት ምንድን ነው ቢሉ በኃጢአት አለማፈርና በግፍ መደሰት ፤ ከዚህም አልፎ በግፍ መኩራት ይታይበታል። ቀደም ብለን እንዳነሣነው እጁጉን በሽታው እንደጸናበት የፍጻሜ ምልክቱ ደግሞ ምሕረትን መስማትም አለመፈለግ ነው ። እንዲህ አይነት ሰው ደግ መሥራትቱስ ይቅርና ሃይማኖቱን እንኳ እስከማጣት ይደርሳል። “የሌለውን ያንኑ ይወስዱበታል ” የተባለው ይኸው ነው።
ሊቁም ” ኢይትከሃሎ ለብእሲ ለእመ ኢያግኀሰ ርእሶ እምግዕዘ ልማድ – ሰው ከፈቃደ ልማድ ማእሰር ራሱን ካላራቀ ሃይማኖታዊ ምእመን መሆን አይቻለውም ” ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትርጓሜ ዕብራውያን ፳፪ መመለስን ለማይሻ ፣ ምሕረት ለማይፈልግ ፣ ልቡ ለደነደነ ፣ አእምሮው ለተነሣው ፣ ሕሊናው ለከዳው ” እሰማው ዘንድ እግዚአብሔር ማን ነው ” በሚል እንቢተኛ ልብ ለጸና ሰው መቅሰፍት ይታዘዝልታል ። ለምን ቢሉ ምሕረተ እግዚአብሔርን ላልተጠቀመባት ሰው ፍትሑ ትፈርድበታለችና።
ይህ ሰው ሞቱ ሁለት ጥቅም አለው። መጀመሪያ “ወባሕቱ በአምጣነ ኢትኔስሕ ትዘግብ መቅሰፍት ለርእስከ – ነገር ግን ንስሐ እንዳለመግባትህ ለራስህ ፍዳን ታከማቻለህ ” እንዳለው ሐዋርያው ቆይቶ ፍዳን ከሚጨምር መሄዱ ይሻለዋልና ስለዚህ ነገር እግዚአብሔር ይቀስፈዋል። ሌላው ደግሞ ንስሐ ለመግባት ያለቀውን የተሰጠውን ዘመንና ትምህርት ላልተጠቀመበት ሰው መቆየቱ ለሌላው ስቃይ እንዳይሆን ስለዚህም ይቀስፈዋል። አሥር ምክር ተሰጥቶት ላልተመለሰ ፈርዖን ቢቆይ በሕዝበ በእስራኤል ላይ ስቃይ ከመጨመር በቀር እርሱ እንደማይመለስ ባወቀ ገንዘብ እግዚአብሔር በባሕር ውስጥ እንዳሰጠመው ማለት ነው። እኛንም ” ወይእዜኒ አመ ሰማዕክሙ ቃሎ ኢታጽንዑ ልበክሙ – አሁንም ቃሉን ብትሰሙ ልባችሁን አታጽኑ ” ያለን ዕድል ፈንታችን ጽዋ ተርታችን እንዲህ እንዳይሆን ነው።
፪. ሁለተኛ መቅሰፍት የሚመጣው ” ቅን ልቡና ላላቸው ፣ የተንኮል ጥበብ ለሌለባቸው ፣ እግዚአብሔርን ለማይሸነግሉ ፣ በብልጠት መጽደቅ ለማይፈልጉ ፣ በቅን መንገድ ሆነው ፣ ድካማቸውን ተረድተው ” ኢታብአነ እግዚኦ ወስተንሱት – አቤቱ ወደ የፈተና አታግባን ” ለሚሉ ሰዎች እግዚአብሔር ደዌውን ሞትን ያመጣል። የፈተና ቀን ምንድን ነው ቢሉ መከራ ፈርተው ክርስቶስን የሚክዱባት ቀን ናት ይላሉ አበው። ስለዚህ በጭንቅ ቀን የእምነት ትጥቃችን እንዳይላላ በክንፈ ርድኤትህ ከልለን ፤ ለሚሉና “አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዛ ዓለም ወከአዉ ደሞሙ በእንተ እግዚአብሔር ፥ ወተዐገሡ ሞተ መሪር በእንተ መንግሥተ ሰማያት ተሣሃለነ በከመ ዕበየ ሣሕልከ – ሰማዕታት በእውነት የዚህችን ዓለም ጣዕም ናቁ ። እግዚአብሔርን ስለ መውደድም ሰውነታቸውን ለሕማም ለሞት አሳልፈው ሰጡ፤ ደማቸውንም አፈሰሱ። ስለ ጣዕመ መንግሥተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሡ። አቤቱ እኛ ግን እንደ ሰማዕታት እሳቱን ስዕለቱን ፥ እንደ ባሕታውያን ድምፀ አራዊቱን ጸብዓ አጋንንቱን ፥ እንደ መነኮሳት ዕፀብ ገዳሙን ፣ ፍትወታት ርኩሳት ኃጣውእ ርኩሳቱን ታግሠን መጽደቅ አይቻለንምና እንደ ምሕረትህ መጠን ማረን ” እያሉ የሚለምኑትን እግዚአብሔር በመከራ ጽናት እንዳይናወጹ በጊዜው ይወስዳቸው ዘንድ መቅሰፍትን ያመጣል። ይህን የሚያደርገው መቆየታቸው ያለቻቸውን ጥቂት ምግባር እንዳያሳጣቸው ሃይማኖታቸውን እንዳያስክዳቸው ነው።
ከኢትዮጵያውያን ጻድቃን አንዷ እናታችን ቅደስት ወለተ ጴጥሮስ ይህንን አድርጋለች። በሚቀጥሉት ጊዜያት መከራ እንደሚመጣ በጸጋ አውቃ ከመንፈሳዊ ልጆቿም ጥቂቶቹ በድካማቸው ካሉበት መንፈሳዊ ሕይወት መከራው እንዲያናውጻቸው በተረዳች ጊዜ ፤ አርድዕቶቿን በሞት እንዲወስድላት እግዚአብሔርን ለምና እንዲሞቱ አድርጋለች። ቆይተው በመከራው ተናውጸው ሲዖል ከሚወርዱ ያለቻቸውን በጎ ሕይወት ይዘው የምድሩ ዕድሜ ቀርቶባቸው ዘለዓለም ቢኖሩ የተገባ ነውና ። እግዚአብሔርንም እንዲህ በሚለው የቅዱስ ዳዊት መዝሙር ነበር የለመነችው ” እስመ ይኄይስ እምኀይው ሣህልከ – አቤቱ ከሕይወት ቸርነትህ ይሻላል “። ይህ ማለት በምድር ኃጢአት ሊጨምሩ ከመኖር የምድሩ ዕድሜ ቀርቶ አጥሮ በቸርነትህ የዘለዓለም ሕይወትን መውረስ ይሻላልና ማለት ነው ። ነቢዩ በሌላም ስፍራ ” አቤቱ በኃጥኣን ድንኳን ከመኖር ይልቅ በአንተ ቤት መጣል ይሻላል”። በዚህ ዓለም ቆይተን ኃጢአትን ጨምረን ከሚፈረድብን በሞት ተጥለን ዘለዓለም ብንኖር በእውነት ይሻለናልና ። ይህንን ማድረግ የሚቻለው ግን እርሱ ባለቤቱ ሕያው እግዚአብሔር እንጅ ማንም አይደለም ። ራሱን የፈጠረ ሰው እንደሌለ ማንም ራሱን ቢገድል ራሱን ጣዖት ማድረጉ ነው።
፫. ሦስተኛው ደግሞ እግዚአብሔር በሚያመጣው መቅሰፍት የሚጠቀሙ ሰዎች ዕድሜ ለንስሐ የተሰጣቸው ናቸው ። ክብር ይግባው ስሙ ይመስገንና አቡሃ ለምሕረት እግዚአብሔር ካልዘራበት አያጭድም፤ ካልበተነበት አይሰበስብም ። ማለት ሳያስተምር አይፈርድም። ስለዚህ ሰውን በብዙ መንገድ ለድኅነት ይጠራል ። መምህራንን ለሚሰማ በመምህራን ፥ በትሑት ሰብእና በቅን ልቡና በበጎ ሕሊና ሆነው ሊሚፈልጉት በመጻሕፍት ፥ ይህ ሁሉ ላልተሳካላቸው በሥነ ፍጥረት ” ወኩሉ ዘተፈጥረ ለመፍቅደ ነባብያን ቦ እምኔሆሙ ለምሕሮ ወቦ እምኔሆሙ ለአንክሮ ወቦ እምኔሆሙ ለተዘክሮ – የተፈጠረው ፍጥረት ሁሉ በነፍስ ለባውያን ነባብያን ሕያዋን ሆነው ለተፈጠሩ ለሰዎች የተፈጠረ ነው። ከተፈጠሩትም ፍጥረታት ለትምህርት የተፈጠሩ አሉ። ለአድናቆት የተፈጠሩ አሉ፤ እግዚአብሔርን ለማሰብ የተፈጠሩ አሉ”። እንዳለ አረጋዊ መንፈሳዊ በሥነ ፍጥረት ላልተማረም በአእምሮ ጠባይዕ ያስተምራል። በዚህ ሁሉ ለላልተመለሰም በተአምራት ያስተምረዋል ።
ይህንን ሁሉ አልፎ ወደ እግዚአብሔር ያልተመለሰ ሰው በመቅሰፍት ይማራል ። ፈጣሪ የለም የሚል ሰነፍ ልቡ እንኳን ቢሆን በመቅሰፍት እግዚአብሔር እንዳለ ያውቃል። ለሚጨነቁት የማያዝኑ ሲጨንቃቸው ርኅራኄን ይለምዳሉ ። ፍርድ አጉድለው ድኻ ተበደለ የማይሉ ባለሥልጣናት ፈራጅ እንዳለ ያውቁ ዘንድ መቅሰፍት ይመጣል። ክንደ ብርቱ ነን ብለው ቋንጃ የሚቆርጡ ፥ ደም የሚያፈሱ፣ ቤት የሚተኩሱ ፦ ከእግዚአብሔር ጸባዖት – ከአሸናፊው የሠራዊት ጌታ ከሕያው እግዚአብሔር ክንድ በታች መሆናቸውን ተረድተው ይመለሱ ዘንድ መቅሰፍት ይመጣል ። ሞትን ዘንግተው በሚሞት ሥጋቸው ርኵሰትን ያነገሧት ሰዎች ሥጋቸው ፈራሽ ብስባሽ ነገር ግን ትንሣኤ ያለው መሆኑን ተረድተው ከዝሙታቸው ይመለሱ ዘንድ መቅሰፍት ያታዘዛል። ቀማኞችና ስግብግቦች በአንድ በሁለት ቀን የዕድሜን ዛላ የሚቆርጥ ደዌ ሲመጣና ገንዘባቸውን ለዕድን እንደሚያጠራቅሙ ተረድተው ቸሮች ለጋሶች ይሆኑ ዘንድ መቅሰፍት ይታዘዛል። ደፋሮች በመቅሰፍት ይለዝባሉ ። ፈሪዎች የእግዚአብሔርን ከሃሊነት አይተው በሃይማኖት ይጸናሉ ። ለምን ቢሉ ከእነ እገሌ እጅ ማን ያስጥለናል? ብለው የሚሸበሩ ሁሉ እነዚያ ኃያላን ሁሉ በኃይለ እግዚአብሔር ሲብረከረኩና ኃይላቸውና ምሽጋቸው አንዳች የማይጠቅም መሆኑን አይተው ይበረታሉ ። በሰው የሚመኩት ሁሉ ፥ በእነ እገሌ እናሸንፋለን እያሉ የሚደነፉት ሁሉ አሁን መመኪያዎቻቸው ራሳቸውን ማዳን የማይቻላቸው ባለ መድኀኒቶች መሆናቸውን ይረዳሉ ። ስለዚህም እንዲህ ብለው ይዘምራሉ ” ወከንቱ ተአምኖ በሰብእ በእግዚአብሔር ንገብር በኃይለ ወውእቱ የኀስሮሙ ለእለ ይሳቅዩነ – በሰው መታመን ከንቱ ነው፤ በእግዚአብሔር ኃይልን እናደርጋለን እርሱም አስጨናቂዎቻችንን ያዋርዳቸዋል”።
ዓለማትን ካለመሮር ያመጣቸው ከሃሌ ኩሉ አምላካችን ዓለምን በአንድ ጊዜ ጸጥ ያደርጋት ዘንድ ለእርሱ ተቻለው ። አጉራ ዘላይ ስትሆን ይቆነጥጣት ዘንድ ለእርሱ ብቻ ይቻለዋል ። ስታለቅስ ደግሞ ያጽናናት ይፈውሳት ዘንድም ለእርሱ ብቻ ይቻለዋል። ሊሰብራት ለእርሱ ናት ፥ ሊጠግናት ለእርሱ ናት። ዓለምን የፈጠሯት እስኪመስሉ ድረስ በዚህ ዘመን ለሚመጣው እንዲህ እናደርጋለን የሚሉ ጠበብተ ዓለም ሁሉ አሁን ዝም ይበሉ። በፈለሰፉት መሣሪያ የሚመኩ ሁሉ አሁን የእግዚአብሔርን ጣት መቃወም ሲሳናቸው ነባብያነ ከንቱ በመሆናቸው ይፈሩ ። ስለዚህ አሁን የመጣው ደዌ ” ኮሮና ” ከእግዚአብሔር ወደ እርሱ እንድንመለስ የመጣ የድኅነት ጥሪ እንጅ አስጨናቂያችን አይደለም ። ራሳችንን አስተካክለን በብርሃኑ ከተመላለስን መቆየታችን ብቻ ሳይሆን መሞታችንም ጥቅም ነው ። እኔ ግን ደዌው እንዴት ይለፈን ሳይሆን በዚህ ጊዜ እንኳን ወደ እግዚአብሔር ሳንመለስ እንዳንቀር ነው የሚያስጨንቀኝ ። ቅዱሳን እሳትና ስለትን አክሊል ተቀዳጅተውበታል። እኛም እስካሁን እንኳን ደጋጎች ባንሆን አሁን በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት እንኳ እውነተኛ ክርስቲያን እንሁን! ከዚህ ባለፈ ግን እኔ እላለሁ የአምላካችንን ከሃሊነት አየንበት እንጅ አንዳች የሚያስፈራን የለም ።
” እንግዲህ ክርስቶስን እያየ ሞትን የሚፈራ ማን ነው ” ያለው የመምህራችን የቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ቃል ጉልበት ይሁነን። ኑሯችንንም ሞታችንንም ለድኅነት ያደርግልን! “ማርያም ንጽሕት ድንግል ወላዲተ አምላክ ማእምንት ሰአሊተ ምሕረት ለውሉደ ሰብእ ሰአሊ ለነ ኀበ ክርስቶስ ወልድኪ ይስረይ ኃጢአተነ ሰአሊ ለነ የቅድስት “እመቤታችን ንጽሕናዋ የታመነ ነው፤ አምላክን ለመውለድ በቅታበታለችና ። አምላክን መውለዷ የታመነ ነው ፤ ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ የወለደችው ልጇ ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቷልና። ምሕረት ማሰጠቷም የታመነ ነው፤ በእግዚአብሔር ዘንድ የእናትነት ባለሟልነት አላትና። ስለዚህ እንዲህ ብለህ ግጥም ይላሉ ሊቃውንት ” ወላዲተ አምላክ ማእምንት ሰአሊተ ምሕረት ማእምንት – ያታመነች የአማላክ እናት የታመነች ምሕረት ለማኝ አማላጅ ወይም አምላክን መውለዷ የታመነ ከሆነ ማማለዷማ እንዴታ ማለት ነው “
እንዲህ ከሚያደርገው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኝልን። አእምሮውን ለብዎውን በልቡናችን ሳይልን አሳድሪልን አሜን
በእውነት ያለ የሐሰት ተቆየን!
~~~~~~~~ ~~✞ ✞ ✞ ~~~~~~
መጋቢት ፲፮ -፳፻፲፪ ዓመተ ምሕረት
አባ ገብረ ኪዳን ነባሪሃ ለኪዳነ ምሕረት
Filed in: Amharic