>

እኛን ማን ፈራጅ አደረገን የኛን ቆሻሻ ማን በነገረን!?! (ጌትነት አየለ)

እኛን ማን ፈራጅ አደረገን የኛን ቆሻሻ ማን በነገረን!?!

 

ጌትነት አየለ
☞ በየሶሻል ሚዲያው ስፔኖች እንዲ ስለሆኑ ነው ጣሊያኖች እንዲህ ሰለሆኑ ነው ኮሮና የፈጃቸው የምትሉ ኢትዮጵያውያን የኛን አጥያትና ቆሻሻ ማን ይንገረን?
☞ በእውኑ ፈጣሪ የሚቀጣው ቃሉን አውቆ ለሚያጠፋው ወይስ ሳያውቁ ለሚያጠፉት?
☞ እውነት እንነጋገር ከተባለ እንደኛ 97% ፐርሰንት አማኝ በሆነው የአሏህ/የእግዚሀብሔርን ቃል እያወቅን ቃሉን የተላልፈን እልፍ አእላፍ ሚሊዮኖች የለንም ወይ?
☞ እኛኮ መስጂዳችንን ያቃጠልን፣ ቤተክርስቲያን ያቃጠልን፣ የእምነት ሁለማዎችንና ቀሳውስቶችን የደበደብን አልፎም ጋዝ አርከፍክፈን ያቃጠልን እኮ ነን።
 ☞ ለአንድ ተራ አክቲቪስት ብለን ወንድማችንን በአደባባይ ገድለን በመሰላል ወጥተን በሺዎች ፊት በመብራት ፖል ላይ ዘቅዝቀን ሰቅለን ሰልፊ የተነሳን እኮ ነን።
☞ ወንድሞቻችንን  በብሔራቸው ወደው ባላመጡት የታፔላ ስም እስከነ ህይወታቸው ጋዝ አርከፍክፈን በአደባባይ ስጋቸው እስኪሸተን ድረስ አቃጥለናቸው የሞቅን እኮ ነን።
☞ለሰው ልጆች የህይወት ድህነት ፈጣሪ የሰጣቸውን የህክምና ጥበብ ወገኖቻቸውን ሊፈውሱ የሄዱ የህክምና ባለሙያዎችን በድንጋይ ወግረን በሀሰት ፍርድ የገደልን እኮ ነን።
☞ እኛ አማራ፣ኦሮሞ፣ትግሬ፣ሲዳማ,,,ወዘተ,,,እያልን  የሰው ጓጉንቸር ሆነን እርስ በእርሳችን ውጣልኝ ክልሌ፣ባንዲራዬ ገለመኔ እያልን አባትና ልጅን ሆስፒታል ድረስ ሄደን የገደልን። አባትና ልጅን በብሔርና በዘር መዝነን ገለን የወንድማችን አስክሬን ላይ ሸምቀቆ አስገብተን አስፋልት ለአስፋልት የጎተትን ፣የሴት እህቶቻችን ጡት በሜጫ ቆርጠን የጣልን ሴት እህቶቻችን የደፈርን ከዛም አልፎ ወንድ ህፃናት ሰዶም የሚፈፀምባቸው፣በድንጋይና በአጠና ከነ ባለቤቷ ጨፍጭፈን የገደልን አራስ ሴት የገደልን።
☞ ወንድምና እህቶቻችንን ህፃናቶችን ሳይቀር በዘርና በብሔር በማሳደድ በቀስት ነድለን የጣልን እኮ ነን።
ኮሮና መጣ ሲባል የ5 ብር እቃ 300 ብር የሸጥን የ100 ብር ደሞዝ ተጨመረ ሲባል የሶስትና የአራት መቶ ብር የቤት ክራይ የምንጨምር አረ ስንቱን ልዘርዝረው,,,ታዲያ ከኛ በላይ በአጥያት የቆሸሸና በብሔርተኝነትና በዘረኝነት የጠነባ በጭካኔ ልቡ የታወረ አለ ወይ?  97% አማኝ በሆነው ህዝብ መሀል የሚገኝ ከወዴት አለ።
እውነት ፈጣሪ ምክንያት ኖሮት እንጂ እኛ ኢትዮጵያውያን ሌላው ቢቀር በዚህ 2 አመት ውስጥ የፈፀምነው ግፍና በደል እምነት ኖሯቸውም ሳይኖራቸውም እድሜ ልካቸው ካጠፉት የሌሎች አገራት ይልቅ የኛ አጥያትና በደል አይበልጥም ትላላቹን?  ደርሶ ፈራጅ አንሁን የራሳችንን ቆሻሻና እድፍ አጥያት አረመኔነት ጨካኝነት ማን በነገረን መጀመሪያ የራሳችንን አጥያትና በጥላቻና በዘረኝነት በብሔርተኝነት ከመቆሸሽ አልፎ የከረፋውን ማንነታችንን እናፅዳ።
አሏህ እዝነትን እንዲሰጠን እግዚሀብሔር ይቅር እንዲለን።
ኢትዮጵያዊነት ከዘር በላይ ነው
Filed in: Amharic