>
5:28 pm - Wednesday October 9, 5461

የአበበ ገላው “የሚስጥሩ ቁልፍ” ምርመራ ሲፈተሽ  (አቻምየለህ ታምሩ)

የአበበ ገላው “የሚስጥሩ ቁልፍ” ምርመራ ሲፈተሽ 

አቻምየለህ ታምሩ

ጋዜጠኛ አበበ ገላው የዐቢይ አሕመድን Academic Achievement ለማጣራት ያካሄደውን ምርመራ ለፈተሸ የሚገኘው እውነት አበበ ሊነግረን እንደፈለገው የዐቢይ አሕመድ  የትምህርት ማስረጃ ትክክለኛ መሆኑን  የሚያሳይ ሳይሆን ዐቢይ አሕመድን ያለው የAcademic Record የሐሰት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። አበበ ገላው የዐቢይ አሕመድ Academic Achievement ትክክለኛ መሆኑን ለማስረጋገጥ ያቀረባቸው የመጀመሪያው ማስረጃ ዐቢይ አሕመድ የመጀመሪያ ዲግሪውን ተምሮበታል የተባለው የማይክሮ ሊንክ ኮሌጅ ባለቤት ናቸው።
የማይክሮ ሊንክ ኮሌጁ ባለቤት  የሆኑት ሰው በኮሌጃቸው ይገኛል ያሉትን የዐቢይ አሕመድን Academic Record ዋቢ በማድረግ ለአበበ ገላው ምስክርነታቸውን እንደነገሩት ዐቢይ አሕመድ የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን የጨረሰው በ1996 ዓ.ም. ሲሆን በማይክሮ ሊንክ ኮሌጅ ውስጥ ገብቶ በኮምፑዩተር ኢንጅነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪውን መማር የጀመረው ደግሞ በ1997 ዓ.ም. ነበር። እኒህ የአበበ ገላው ምስክር ጨምረው እንደነገሩን ዐቢይ አሕመድ ከማይክሮ ሊንክ ኮሌጅ በኮምፒዩተር  ኢንጅነሪንግ የተመረቀው በ2001 ዓ.ም. ነው።
አበበ ገላው የዐቢይ አሕመድን Academic Record ትክክለኛ መሆኑን ያረጋግጥልኛል ያለውን ይህንን የማይክሮ ሊንክ ኮሌጅ ባለቤት ምስክርነት ይዘን ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ፓርላማ ቀርቦ ቃለ መሐላ በፈጸመበት እለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ጉዳዮች ተጠሪ ሚኒስትር በሆነው በሺፈራው ሽጉጤ  ለፓርላማው የተነበበውን የዐቢይ አሕመድ ትክክለኛ የAcademic Achievement ስንመረምር  በሁለቱ መካከል የ7 ዓመታት ልዩነት እናገኛለን። ሺፈራው ሽጉጤ ለፓርላማ ባቀረበው ኦፊሻላዊ የዐቢይ አሕመድ የትምህርት ማስረጃ መሰረት ዐቢይ አሕመድ ከማይክሮ ሊንክ ኮሌክ በኮምፒዩተር ኢንጅነሪግ በዲግሪ የተመረቀው በ1994 ዓ.ም. ነው።
አበበ ገላው የዐቢይ አሕመድ የትምህርት ማስረጃ ትክክለኛ መሆኑን ያስረግጡልኛል ብሎ ያቀረባቸው በኮሌጃቸው ይገኛል ያሉትን የዐቢይ አሕመድን Academic Record ዋቢ በማድረግ ለአበበ ገላው ምስክርነታቸውን የሰጡት የማይክሮ ሊንክ ኮሌች ባለቤት እንደነገሩን ደግሞ ዐቢይ አሕመድ  በ1996 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል  ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ  በ1997 ዓ.ም. ማይክሮ ሊንክ ኮሌጅ ውስጥ ገብቶ  በ2001 ዓ.ም. በኮምፑዩተር ኢንጅነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪው አግኝቷል። ይህ የሰባት ዓመታት ልዩነት የሚያሳየን አበበ ገላው ሊንግረን እንደፈለገው የዐቢይ አሕመድ  Academic Achievement ትክክለኛ እንደሆነ ሳይሆን ባቋራጭ የተገኘ መሆኑን ነው።
ጋዘጠኛ አበበ ገላው የዐቢይ አሕመድ Academic Record ትክክለኛ መሆኑን ለማሳየት የሄደበት ርቀት እሱ ራሱ በወያኔ ዘመን የወያኔ ሹሞች የነበራቸው ዲግሪ የተገዛ መሆኑን ለማጋለጥ የሰራቸውን ምርጥ ስራዎች አፈር ድሜ የሚያበላ ነው። አቤ እ.ኤ.አ. በ2015 ዓ.ም. “Exposed: “Honorable” Speaker Abadula Gemeda has fake degrees” በሚል ባዘጋጀው ጽሑፍ ውስጥ አባ ዱላ አሉኝ ከሚላቸው የማስትሬት ዲግሪዎች ውስጥ አንዱ እ.ኤ.አ. በ2009 ዓ.ም. እንግሊዝ አገር ከሚገኘው Greenwich University ገዛው ያለውን MA in International Relations መሆኑን ነግሮን ነበር። የዐቢይ አሕመድ Academic Achievement ትክክለኛ መሆኑን ለማሳየት  አበበ ገላው ባካሄደው ምርመራ ግን አባ ዱላ ማስተሩን ከገዛበት ከGreenwich University የተገዛውን የዐቢይ አሕመድ ማስትሬት ትክክለኛ ማስትሬት መሆኑን ሊነግረን ይቃጣዋል!  ከዚህ በተጨማሪ አበበ ገላው ለወያኔ ሹማምት የውሸት ድግሪና ማስተር ይሸጣል እያለ ሲያብጠለጥለው የነበረውን ፓስተር ባደግን የዐቢይ አሕመድ Academic Record ለማጣራት ሲሆን ግን  ፓስተሩን ዶክተር ባደግ በቀለ አድርጎ በማቅረብ  ሲሸጠው የኖረውን የውሸት ዲግሪ ደግሞ ወደ እውነተኛ የትምህርት መመዘኛ አድረገው።  የፓስተር ባደግ የውሸት ዲግሪ  ወደ እውነት ያደገው የዐቢይ አሕመድ  Academic Record ሲጣራ መሆኑ በእውነቱ ያስተዛዝባል።
አበበ ገላው ዐቢይ አሕመድ ጎበዝ ለማድረግ ብዙ ጥሯል። አበበ ገላው ዐቢይ አሕመድ ጎበዝ ተማሪ እንደነበር ለማሳየት ያቀረበው መከራከሪያ  አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መማሩን ነው። ዐቢይ አሕመድ የዶክትሬት ዲግሪውን አገኘበት የተባለው Institute for Peace and Security Studies  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር ይሁን እንጂ ተቋሙ  እ.ኤ.አ. በ2007 ዓ.ም. የተቋቋመው የወያኔ ካድሬዎች ሊሰለጥኑበት ነው። በዚህ ተቋም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፊት ኢትዮጵያን ወክሎ  ቀርቦ ባደረገው ንግግር እንግሊዝኛን ባፍጢሙ የደፋው  uneducated and uneducable የሆነው ወርቅነህ ገበየሁ ሁሉ እንደ ዐቢይ አሕመድ አይነት የዶክትሬት ዲግሪ አግኝቶበታል። አበበ የተቋሙ ኃላፊ ወደሆኑ ሰው ደውሎ  ዐቢይ ለዶክትሬት ማሟያ ዐቢይ ያቀረበው ወረቀት የተሰጠውን  ውጤት ጠይቆ ነበር። ኃላፊው የዐቢይ ወረቀት ያገኘው ውጤት “Very Good” ነው ቢሉትም አበበ ገላው ግን ዐቢይ አሕመድን ጎበዝ ለማድረግ ስለፈለገ “ባግባቡ A አግኝተው ነው የተመረቁት?” ሲል በተደጋጋሚ አቅርቧል። ሆኖም ግን ዩኒቨርሲቲ እናስተምር ለነበርን ሰዎች በዲግሪ የአንድ ተማሪ ዲግሪ ማሟያ ወረቀት A ወይም A+ ግሬድ  የሚሰጠው  ወረቀቱ  “Excellent” የተባለ እንደሆነ  ነው እንጂ  “Very Good”  ሲሆን  አይደለም። “Excellent” የተባለ ወረቀት A ግሬድ የሚያገኘው ተማሪው ከመቶ ያገኘው ውጤት ከ83-90 ሲሆን  “Excellent” የተባለ ወረቀት A+ ግሬድ የሚያገኘው ተማሪው ከመቶ ያገኘው ውጤት ከ90-100  ሲሆን ነው።   “Very Good”  የተባለ  ወረቀት ግሬዱ B ወይም B+ ነው። “Very Good”  የተባለ ወረቀት ግሬዱ B+  የሚሆነው ተማሪው  ከመቶ ያመጣው ውጤት ከ75- 80 ያገኘ እንደሆነ ሲሆን  “Very Good”  የተባለ ወረቀት ግሬዱ B የሚሆነው ተማሪው ከመቶ ያገኘው ስጤት ከ68- 75 ሲሆን ነው።  በClass Descriptionም “Excellent” እና “Very Good”   የተባሉ ወረቀቶች ይለያያሉ።  “Excellent”  የተባለ ወረቀት Class Descriptionኑ First class with Great distinction ሲሆን  “Very Good”  የተባለ ወረቀት Class Descriptionኑ First class with Distinction ነው።
አበበ ገላው  የዐቢይ አሕመድ Academic Achievement ትክክለኛ መሆኑን ለማሳየት በሰራው ዶክመንተሪ ዳግማዊት ሞገስ የምትባል የነውረኛው ብአዴን ባለሟል  ፈጸመችው ስላለው plagiarism ነግሮናል። የዳግማዊትን plagiarism የነገረን አበበ ገላው  የሚከላከለው ዐቢይ አሕመድ የፈጸመውን plagiarism ግን  ሊነግረን አልደፈረም። ዐቢይ አሕመድ እ.ኤ.አ. በ2016 ዓ.ም. ከአትላንቲክ ማጋዚን ጋር አደረግሁት ባለው ቃለ ምልልስ አሜሪካዊው የፖለቲካ ሳይንቲስት Joseph Samuel Nye Jr. እ.ኤ.አ. በ2004 ዓ.ም. “Soft Power: The Means to Success in World Politics” በሚል ካሳተመው መጽሐፍ ቃለ በቃል በመቅዳት፤ እ.ኤ.አ. በ1973 የአሜሪካው ውጭ ጒዳይ ሚንስትር የነበረው ሔንሪ ኪሲንጀር የሰጠውን ቃለ ምልልስና በራስለንድ ብራንድ መጽሔት ከወጣ አርቲክል የሚችለውን ያህል ዝቆ በመውሰድ እንደራሱ አድርጎ  ማቅረቡንና  plagiarize አበበ ገላው ያውቃል። የድምጽና የምስል ማስረጃው አለው።  የዳግማዊትን plagiarism  የነገረን አበበ ገላው ግን ይህንን የድምጽና የምስል ማስረጃ የሚገኝበትን  የዐቢይ አሕመድን plagiarism  ሊነግረን አልደፈረም።
ከታች የተያያዘው የቪዲዮ ማስረጃ  የመጀመሪያ ክፍል ዐቢይ አሕመድ ፓርላማ ቀርቦ ቃለ መሐላ በፈጸመበት ወቅት ለፓርላማ የቀረበውንና ዲግሪውን በ1994 ዓ.ም. ከማይክሮ ሊንክ ኮሌጅ እንዳገኘ የሚያረጋግጥ ሲሆን ሁለተኛው ክፍል ደግሞ አበበ ገላው የዐቢይ አሕመድ Academic Record ትክክለኛ መሆኑን ለማረጋገጥ ባደረገው ምርመራ ዐቢይ አሕመድ የመጀመሪያ ዲግሪውን አገኘበት የተባለው የማይክሮ ሊንክ ኮሌጅ ባለበት  በኮሌጃቸው ይገኛል ያሉትን የዐቢይ አሕመድን Academic Record ዋቢ በማድረግ ዐቢይ አሕመድ የመጀመሪያ ዲግሪውን ከኮሌጃቸው  ያገኘው በ2001 ዓ.ም. እንደሆነ ምስክርነታቸውን የሰጡበት የድምጽ ማስረጃ ነው።
___________
ማሳሰቢያ፡ 
ከታች የታተመውን የማይክሮ ሊንክ ባለቤት የሆኑት ሰው ለአበበ ገላው የሰጡትን ንግግር  እስከ መጨረሻው ድረስ ላደመጠ  የኮሌጁ ባለቤት ያቀረቡት ማስረጃ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር መሆኑን ራሳቸው  መናገራቸውን ይገነዘባል። ሺፈራው ሽጉጤም  ለፓርላማ  ባቀረበው ንግግር ያቀረበው የዐቢይ የትምህርት  የትምህርት ማስረጃ የተደራጀው እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ነው። ሺፈራው  ሽጉጤ ያቀረበው ሙሉ ንግግር  ያላቀረብሁት ስለረዘመብኝ  ነው። ሙሉ ንግግሩ ወረድ ብዬ  ያያዝሁትን ትር በመጫን ማድመጥ ይቻላል።  ሽፈራው ሽጉጤ  ባቀረበው በዚህ ንግግር ዐቢይ አሕመድ የተወለደበትን ዘመን 1968ን  ጭምሮ የተማረበትን ዘመን ሁሉ ያቀረበው በኢትዮጵያ አቆጣጠር ነው። ለምሳሌ  ዶክትሬቱን በ2009 ዓ.ም. እንዳገኘ ይናገራል።  በ2010 ጠቅላይ ሚኒስትር የሆነው ዐቢይ ዶክትሬቱን ያገኘበት ዓመት  2009 ዓ.ም. የፈረንጅ አቆጣጠር  ሊሆን አይችልም። እነሆ የሺፈራው ሽጉጤን ሙሉ ንግግር የያዘው ትር፤
Filed in: Amharic