* እኛ እንደ እነሱ አንተባበርማ አንተባበርም ምቀኞች፣ ክፉወች ለወንድሙ ጉድጓድ ቆፋሪ እንደ እኛ ማን አለ?
• እኛ እንደ እነሱ አንተባበርም እንጂ ብንተባበር አይችሉንም ነበር። ቢያንስ ለቅሶህን አሳምረው ነበር። እጮህልህም ነበር። እለምንልህም ነበር። እሟገትልህም ነበር። ይኸው ነው።
~ በእኔ በኩል ያልተዘጉ 99 ወለል ብለው ተከፍተው የሚጠብቁኝ በሮች ስለሚታዩኝ በሁለት በተዘጉብኝ ትናንሽዬ መስኮቶች አልጨነቅም።
•••
በቀደም ዕለት ከፌስቡክ መንደር ገፍትረው ዩቱዩብ መንደር ጣሉኝ። አሁን ደግሞ ከዩቲዩብ መንደር ገፍትረው አውጥተውኛል። ሳስበው ግን ወይ ሳታላይት ላይ አውድቃለሁ። ወይ ደግሞ የሆነ የራሴ መንደር መሥርቼ አርፈዋለሁ። ጠብቁ። ቱ ምን አለ ዘመዴ በሉኝ።
•••
ይድረስ ለዩቲዩብ ተከታታይ ወዳጆቼ በሙሉ። ዛሬ ደግሞ በእግዚአብሔር ኃይል ሌላ ድል በዩቲዩብ ላይ ተቀዳጅቻለሁ። ስሙት።
•••
እነሆ ዛሬ ደግሞ ዩቲዩብ ሆዬም ልክ እንደ አጅሬ ፌስቡክ ያለምንም ማስጠንቀቂያና ያለአንዳች ማሳሰቢያ እኔ ዘመዴን በዩቲዩብ ቪድዮ እንዳልሠራ ሳይሆን ቪድዮ ራሱ እንዳላይ አድርጎ በድርጅቱ አሠራር መሠረት ባልተለመደና ከሕግ አግባብ ውጪ በሆነ መንገድ ከባልቦላው አጥፍቶ ቻናሉን ጭምር እንዳልጠቀም ማድረጉን በጻፈልኝ ደብዳቤ አሳውቆኛል። ቪዲዮዎቼንም በሙሉ ዘግቶባቸዋል። ቆልፎባቸዋልም።
•••
እኔ ዘመዴ የሥላሴ ባርያ፣ የድንግል አሽከር ሁሌም ዘወትርም አሸናፊ ነኝ። እኔ ዘመዴ የድል አድራጊው የይሁዳ አንበሳ የኢየሱስ ክርስቶስ የመድኃኔዓለም የአማኑኤል ልጅ እኮ ነኝ። አሁንም አሸናፊ ነኝ። አሸንፌዋለሁ። ይሄንን ወራዳ ዓለም አሸንፌዋለሁ። በንግግር፣ በውይይት፣ በእውነት የማያምነውን ዓለም አሸንፌዋለሁ።
•••
በዩቲዩብ ታሪክ በሰዓት ውስጥ 55 ሺ ሰው ቁጭ ብሎ የሚያየው እንደ እኔ ተራ የሆነ ሰው አይቼም ሰምቼም አላውቅም። እኔ ግን አድርጌዋለሁ። በዩቲዩብ ታሪክ በሰዓት ውስጥ 20 ሠላሳ ሺ ሰው ላይክ ሼር የሚያደርገው ተራ ሰው አይቼ አላውቅም። በእኔ ግን ታይቷል። በዩቱዩብ ታሪክ በባዶ ሜዳ 17ሺ ሰብስክራይበርስ፣ በአንድ ቪድዮ ሞኒታይዝድ የተደረገ ሰው አላየሁም። በ3 ወር 155 ሺ ሰው ሲከተለው፣ 7 ሚልዮን ሰዓት የታየም አልሰማሁም። ይሄ ሁሉንም አስደንግጧል። ጀርመኖቹንም ጭምር።
•••
እኔ እንደዜጋ ሃገሬን፣ እንደ አማኝ የጥንታዊቷን፣ የብሔራዊቷን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያኔ ክብሯን እገልጣለሁ፣ ሞገሷን አሳያለሁ፣ ትውፊቷንን፣ ቀኖናዋንና ዶግማዋንም ሳልፈራ፣ ሳልሳቀቅ ለዓለሙ ሁሉ እመሠክራለሁ። ወደፊትም እመሰክራለሁ። እኔ ዘመዴ ፍጹም፣ የማልሳሳት፣ በሁሉ ነገር ትክክል ነኝ ማለትም አይደለም። እስታለሁ። እሳሳታለሁም። እንዲያ ማድረጌ የሚያስከፋው ካለ ግን በአናቱ ይተከል። ገደል እንጦሮጦስም ይግባ። ጉዳዬም አይደለም። ኬሬዳሽ።
•••
ዩቲዩብ ሠርቼ ያገኘሁትን ገንዘቤን፣ እናንተ የሠጣችሁኝን ገንዘብም ጭምር ሁሉ ዩቱዩብ ሙሉ በሙሉ አልሰጠኝም። ሲቲከር ገዝታችሁ፣ የረዳችሁኝን ገንዘቤን ጭምር አልሰጠኝም። ከሳሹ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሆነ መረጃው ደርሶኛል። የእኛው ጉዶችም ጭምር አሉበት አሉ። እኔ ግን እውነትን ከመግለጥ በቀር ያጠፋሁት ጥፋትም የለም። አንዳች ጥፋት አላጠፋሁም። ስለዚህ ከዳስታ በቀር፣ ከድል አድራጊነት በቀር ሌላ ነገር አይሰማኝም።
•••
ስለቤተ ክርስቲያኔ፣ ስለተጨቆኑ ነገዶች፣ ከመጮህ፣ ከማልቀስ በቀር ያጠፋሁት ጥፋት የለም። ደግሞም ጥፋት እንኳን ባጠፋ ዩቲዩብ ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጥ አውቃለሁ። ማስጠንቀቂያ ሲሰጥም ደግሞ ያስጠነቀቀበትን ምክንያትም አብሮ እንደሚጽፍ አውቃለሁ። በእኔ ላይ ግን የተደረገው የተገላቢጦሽ ነው። በቃ ዘጉት፣ ዘጉት።
•••
ይሄ ማለት በቃ መንገዶች ሁሉ ተዘጉ ማለት አይደለም። የተዘጋው የዩቲዩብና የፌስቡክ ደጆች ብቻ ናቸው። ገና ያልተዘጉ 98 ሺ በሮች ከፊቴ አሉ። ሁሉንም በሮች አንኳኳቸዋለሁ። ዌብሳይትና የሳታላይት ሚዲያ በፊቴ ቆመው የሚታዩኝ ናቸው። አንኳኳቸዋለሁ። እስትንፋሴ እስኪቆም። ወደ አፈር እስክገባ እጅ አልሰጥም።
•••
ዩቲዩቤን ካዘጉትና ካመለከቱት መሃል የራሳችን ቤት ጉዶችም እንዳሉበት ሰምቻለሁ። በለጠን፣ ሸፈነን ባዮችም አመልካቾች እንደነበሩ ሰምቻለሁ። እስቲ ይድላችሁ። እስቲ ይስፋችሁ። እኔ ግን የዩቲዩብ ብር እንኳ እስከአሁን ከአንድ ጊዜ በላይ አልደረሰኝም። አልተቀበልኩምም። ምድረ ምቀኛ ሁላ !!
•••
ከፌስቡክ መንደር በበለጠ የዩቲዩብ መንደር ብዙ ሺ ወዳጆችና ምሁራን ሁሉ አገናኝቶኛል። ባለሃብቶች፣ አማኞች፣ ባለሙያዎችም ጭምር አገናኝቶኛል። እናም በዪቲዩብ ሲበዛ ደስተኛ ነበርኩ። በእውነት አንድ ቪድዮ ከሠራሁ በኋላ ከሚደውሉልኝ ተላላቅ ሰዎች ጋር እውያይ የነበረው ነገር እንዴት ያለ ደስታና ሃሴት ፈጥሮልኝ እንደነበረ መድኃኔዓለም ነው የሚያውቀው። አሁንም እጅ አልሰጥም። ሌላ መንገድም እፈልጋለሁ። በዚያም ከች እላለሁ።
•••
እናንተ ግን አይዟችሁ። እንዳሸነፍን ቁጠሩት። ሃገር በገነባን፣ ይቅርታን፣ ፍቅርን በሰበክን፣ እርቅን ባወጅን፣ ራስን መከላከልን በሰበክን፣ ከሱሉልታ እስከ ሚኒሶታ እንዲህ የሚያንዘረዝራቸው ከሆነ አይዟችሁ፣ ደስም ሊላችሁ ይገባል። አሸናፊዎች ነን። አትዘኑ፣ አትበሳጩ። ዓለም ገዢዋ የታወቀ ነው። በሜዳቸው ነው ያንጠባጠብናቸው። በሜዳቸው ነው የገረፍናቸው። በሜዳቸው ነው ነጥብ ያስጣልናቸው። እናም እንዲች ብላችሁ እንዳትበሳጩ። ነገርኳችሁ። እንዲህ ብላችሁ እንዳትበሳጩ።
•••
ዩቲዩብ ላይ OMN በነጻነት እየሠራ እኔ ዘመዴ ስከለከል ምን ያህል አሸናፊ እንደሆንኩ ማወቅ መረዳት አለባችሁ። አዎ አሸናፊ ነኝ። የዩቲዩብ ቻናሌ መዘጋቱ በራሱ ራሱን የቻለ ዜና የሚሆንላቸው እኮ ብዙዎች ናቸው። ከመንግሥት ውጪ፣ ከመንግሥት በቀር ሊያዘጋብኝ የሚችል ማንም የለም።
•••
በአሜሪካ ጠበቃ እፈልጋለሁ። ለብር አልሠራሁም ነገር ግን ብሬን እንዲሰጠኝ ዩቲዩብን በሕግ እጠይቀዋለሁ። ማብራሪያም ጭምር እጠይቀዋለሁ። እጅማ አልሰጥም። እስከ ጥግ ድረስ እሄዳለሁ።
•••
በተረፈ ጠብቁኝ። ሰሞኑን ደግሞ በዚህች አስራአምስት ቀን ውስጥ በሌላ መንገድ እመጣለሁ። 60 ዎቹም የዩቲዩብ ቪድዮዎቼን ዩቲዩብ ቢያወርድብኝም ወዳጅ አይጥፋ ሌላ ሰው ደግሞ በሙሉ ቀድሞ አውርዶ ይዞልኛል። እናም በሌላ መንገድ በሌላ ገጽ እንደገና እጭናቸዋለሁ። ይኸው ነው። አሁን ስሰማ ዩቲዩብ በዓለም ላይ 666 ን የሚቃወሙ ነጮችንም ጭምር አካውንታቸውን እንደዘጋ ሰምቻለሁ። እንዲህ በዩቲዩብ የተጎዱ ፀረ ኢሉሚናንቲዎች የዩቲዩብ አቻ የሆነ ተመሳሳይ ቻናል እንደከፈቱም ሰምቻለሁ። ዘመቻውን በዚያ ተቀላቅለን መሟገት ነው። አለቀ።
•••
ሚድያ ደግሞ ሌላ አማራጭ ነው። የጀርመንን የሚዲያ ሕግ እንዲያዩልኝ ዛሬውኑ ለታላላቅ ኢትዮጵያውያን ነግሬአለሁ። ሰሞኑን መልስ ይነግሩኛል። እሱንም እንሞክራለን። ለጊዜው እስከአሁን ያልተዘጋብኝ http://t.me/ZemedkunBekeleZ
የቴሌግራም ቻናሌ ነው። ቴሌግራም የራሺያ ኦርቶዶክሶች ነው ስለተባለ እስከአሁን አልተዘጋብኝም። እሱን ሰብስክራይብ እያደረጋችሁ ተከታተሉኝ። ይኸው ነው።
•••
ሻሎም ! ሰላም !
መስከረም 28/2012 ዓም
ከራየን ወንዝ ማዶ።