አፈና በማንም የትም ቢደረግ ልንቃወመው ልናወግዘው ይገባል…!!!!
አደባባይ ሚድያ
* የመምህር ዘመድኩን የዩቲዩብ ቻነል መዘጋት “ኢትዮጵያን እና ኦ.ተዋሕዶን” እንወዳለን የሚሉ ሰዎችን አፍ የማዘጋት አንዱ የዘመቻ አካል..
—————————— ————-
የአደባባይ ሚድያ አዘጋጆች የመምህር ዘመድኩን ዩቲዩብ ቻናል በመዘጋቱ ማዘናችንን መግለጽ እንፈልጋለን። ከዚህ ቀደም የመምህር ዘመድኩን ፌስቡክ በተዘጋበት ወቅት መዘጋቱ ትክክል አለመሆኑን በግል ፌስቡካችን እና በአደባባይ ሚድያ ዋና ገጽም መጻፋችንን እናስታውሳለን። አሁንም ብዙዎች የሚከታተሉት ቻነል መዘጋቱ ኢትዮጵያን እና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን የሚወዱትን በሙሉ በአያሌው እንደሚጎዳ እንገነዘባለን። ጉዳቱ በዚህ ቻነል አማካይነት ርዳታ የሚሰበሰብላቸውና ችግራቸው ለተቀረፈላቸው ወገኖች ጭምር ነው። ሕግ ባለበት ሀገር እንደመኖራችንና ዩቲዩብም በሕግ የሚመራ ተቋም እንደመሆኑ ቻነሉ በሕግ አግባብ ድጋሚ እንደሚከፈት እናምናለን።
የዩቲዩብ ቻነሉ መዘጋት የሚያሳየው ጉዳይ “ኢትዮጵያን እና ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን” እንወዳለን የሚሉ ሰዎችን አፍ ለማዘጋት የመሞከሩ ጉዳይ ለወደፊቱም እንደሚቀጥል ይገመታል። መምህር ዘመድኩን ዘንድ የመጣው የሌሎችንም በር እንደሚያንኳኳ ምንም ጥርጥር የለውም። በቅርቡ የግል ፌስቡካችንን መግቢያ (ፓስወርድ) ሳይቀር ለመስበር ተደጋጋሚ ሙከራ በመደረግ ላይ መሆኑን እንደጻፍን ይታወሳል። ለማንኛውም ነገር መመካከርና መዘጋጀት ጥሩ ነው። ሥራ እንሥራ እስካልን ድረስ የጥንተ ጠላት ፈተናም መነሣቱ የታወቀ ነው። ፈታኝም ፈተናውን ይቀጥላል፣ እኛም ርምጃችንን ከመቀጠል ውጪ ሌላ ዕድል ፈንታ የለንም።
ዓላማችን ለቤተ ክርስቲያናችን እና ለሀገራችን የአቅማችንን ማበርከት ነው።
እግዚአብሔር ይርዳን።
አደባባይ ሚዲያ