>
5:28 pm - Sunday October 9, 6196

እውን ግብጽ የሱዳን እውነተኛ ወዳጅ ናትን ? ኢትዮጵያ ምን ማድረግ ይበጃታል ? ደረጀ መላኩ (የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

እውን ግብጽ የሱዳን እውነተኛ ወዳጅ ናትን ? ኢትዮጵያ ምን ማድረግ ይበጃታል ?

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com

መግቢያ

ግብጽ ሱዳንን ለአንድ መቶ አመታት እንደገዛቻት ከታሪክ እንማራለን፡፡ ከ19ኛው ክፍለዘመን መጀመሪያ አንስቶ የናይል ወንዝን መስመር ተከትላ እስከ ደቡብ ሱዳን ጫፍ ድረስ ይቺን ሀገር ገዝታለች፡፡ ግብጽ የሡዳን ዋና ከተማ ካርቱምን ሳይቀር ገዝታለች፡፡ ግብጾች ሱዳንን የወረሩትና የገዙት  በኢስማኤል ካሚል ፓሻ( Ismail kamil Pasha ) ሶስተኛ ልጅ በሆነው መሀመድ አሊ (Mohammed Ali)  ሱዳንን ካሸነፉ በኋላ እንደነበር የሚታወቅ ነው:: ይህ በታሪክ የተቀመጠ እውነት ስለሆነ የሚያከራክር አይመስለኝም፡፡ የኢስማኤል ጦር ተዋጊና አደገኛ ነበር፡፡ ኢስማኤል የአባይን ወንዝ ለመቆጣጠር ፍላጎትና ምኞት ስለነበረው ጦር ሰብቆ ሱዳንን የተቆጣጠረው እንደጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ከ1920- 1924 ነበር፡፡ በግዜው አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ አገዛዝ ነጻ ለመውጣት ሲታገሉ የነበረ ቢሆንም ግብጽ ከታላቋ ብሪታንያ ጋር በመተባበር ሱዳንን የጋራ መኖሪያ ቤቷ ለማድረግ ትጥር ነበር፡፡ ወይም በሌላ አነጋገር ከታላቋ ብሪታንያ ጋር በማበር ሱዳንን ለመግዛት ችላ ነበር፡፡ ሱዳን በብሪታንያና ግብጽ የጋራ አገዛዝ ምክንያት በብዙ ተሰቃይታ ቆይታለች፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ግብጽ ከቅኝ ገዢ  ብሪታንያ ጋር ህብረት በመፍጠሯ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ግብጽና ታላቋ ብሪታንያ በጋራ ሆነው ሱዳን የገዙት እንደጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር  ከ1899- 1955 እንደነበር ማወቁ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሱዳን በእንግሊዝ ግብጽ ጥምር ቅኝ ግዛት ስር በነበረችበት ጊዜ ለደረሰባት ስቃይና መከራ ሁሉ በዋነኝነት ተጠያቂዋ ግብጽ ናት፡፡ ግብጽ ሱዳን ከግማሽ ክፍለዘመን በላይ በእንግሊዞች ቅኝ እንድትገዛ ሁነኛውን ሚና ተጫውታለች፡፡ እንደማናቸውም በቅኝ እንደተገዙ የአፍሪካ ሀገራት ሁሉ ሱዳንም ማንነታቸውን፣ሀብታቸውን፣ መንፈሳዊና ቁሳዊ ሀብታቸውን አጥተዋል፡፡ ጥንታዊ ብሔራዊ ማንነታቸውን ተነጥቀዋል፡፡ ወይም እንዲረሱ ተደርገዋል፡፡ መሬታቸውም በቅኝ ገዢ ባለሀብቶች ተወስዷል፡፡ በሌላ አነጋገር ሱዳናውያን የሀገራቸው ባለቤት መሆን አልተቻላቸውም፡፡ በቅኝ መገዛት ትርፉ ( ጥቅሙ) ጥቅም አለው ከተባለ ማለቴ ነው፡፡ በሀገር ላይ ባይተዋር መሆን ነው፡፡ ሱዳን ከቅኝ አገዛዝ መዳፍ ስር ከወጣችም በኋላም ቢሆን  ግብጽ ለሱዳን ምንም አይነት ክብር ሰጥታ እንደማታወቅ በርካታ የሱዳን የፖለቲካ ሰዎች የሄሱት ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህም እልፍ በማለት ሁለቱን ሀገራት በሚያገናኘው ሰሜናዊ ክፍል ድንበር ላይ የትንኮሳ ባህሪዋን እንደቀጠለች ነው፡፡ ግብጽ የሱዳንን አንድነት እና ሉአላዊነት ለማናጋት በሁለቱ ሀገራት ሰሜናዊ ክፍል ትንኮሳ ከጀመረች አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሱዳን በተደረጉ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራዎች የግብጽ እጅ ከጀርባ እንዳለበት የአካባቢው የፖለቲካ ተንታኞች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው፡፡ እንዲሁም ሱዳን የውስጥ አንደነቷ እንዲላላ ተዋጊ ሚሊሻዎችን በመርዳት ትታወቃለች፡፡

ግብጽ መልካም የሱዳን ጎረቤት ሀገር አይደለችም

ሁለቱ ሀገራት 1200 ኪሎሜትር የሚረዝም የጋራ ድንበር እንዳላቸው፣ በዚሁ የጋራ ድንበራቸው መሃል ላይ ከ2.5 ሚሊዮን በላይ የሁለቱ ሀገራት ህዝብ እንደሚኖር ይነገራል፡፡ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1956 ጀምሮ በሱዳን ግዛት ስር ያለው ድንበር መጠሪያ ሃሊያብ (Haliyab) የተሰኘ ሲሆን፣ ይህ በማእድን ሀብት የበለጸገ የሱዳን ድንበር በግብጽ ቁጥጥር ስር የወደቀ ስለመሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በዚህ አካባቢ በማግኒዝየም ማእድን የበለጸገ፣ እንዲሁም በተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ የታደለ አካባቢ ነው፡፡ ስለሆነም ሱዳን ወታደራዊና ዲፕሎማቲክ ትግል በማካሄድ አካባቢውን ለመቆጣጠር ጥረት ብታደርግም አሁን ድረስ አልተሳካላትም፡፡ ግብጽ ታካዊ ተጽእኖ ስለምታርግ፣ የሱዳንን ሉአላዊነት ስለምትጻረር ሁለቱም ሀገራት መልካም ጎረቤታሞች አይደሉም በማለት መደምደም የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በግብጽ መንግስት ብቸኛ ውሳኔ በሁለቱ የጋራ ድንበሮች ላይ ይካሄድ የነበረው የንግድ እንቅስቃሴ ለብዙ ጊዜያት ይዘጋ ነበር፡፡ ይህ የንግድ እንቅስቃሴ መቆም በእጅጉ ሲጎዳ የነበረው በሁለቱ ሀገራት የጋራ ድንበር ላይ የሚኖሩትን የኑቢያ ነገዶችን(The <<Nubian>> tribes ነው፡፡ ምንም እንኳን ተመሳሳይ ቋንቋ ቢናገሩም አንድ አይነት ሀይማኖትና ዝርያ ቢኖራቸውም( የእስልምና ሀይማኖት ተከታይ ቢሆኑም) በግብጽ የሚኖሩት የኑቢያ ነገዶች መገለል ይደርስባዋል፡፡ በአጭሩ በቆዳቸው ቀለም ምክንያት( የቆዳ ቀለማቸው ጥቁር ስለሆነ ብቻ ማለቴ ነው) ከሌሎች የግብጽ ዜጎች እኩል አይታዩም፡፡ ሀቢብ መሀመድ የተባሉ ሱዳናዊ ጸሃፊ ካቀረቡት የእንግሊዥኛ ጽሁፍ ለአስረጂነት የሚከተለውን እውነት አቀርባለሁ፡፡

‹‹Nubian >> tribes living along the border of the two countries, though they share the same language ,religion and race, the Nubians in Egypt also faced marginalization because of their blacks skin color and are not treated equal citizens of Egypt>>

ምንግዜም ቢሆን ግብጽ የራሷን የእድገት እቅድ የምታወጣው በሱዳን ኪሳራ ነው

እነ አንዋር ሳዳት እና ጃማል አብዱል ናስርን ጨምሮ  አሁን ድረስ ግብጽን የገዙ መሪዎቿ እንደሚያስቡት ከሆነ የግብጽን  ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ሱዳን የራሷን አንድ አይነት ጥቅም ማጣት አለባት፡፡ ( ለአብነት ያህል ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር አለኝ የምትለውን የድንበር ውዝግብ ለመፍታት የሄደችበት የሰሞኑ መንገድ ከጀርባው እነማን አይዞሽ በርቺ እንደሚሏት ለብዙዎቻችን ግልጽ እየመጣ መሰለኝ፡፡ ከዚህ ባሻግር የግብጽ ዲፕሎማቶች ሱዳንን የዲፕሎማሲ ወጥመድ ውስጥ በመዶል በታላቁ አባይ ግድብ ግንባታ አጠቃላይ ሁኔታ የሱዳንን አቋም ለማዛባት የሚያደርጉት ጥረት ሲታሰብ ያማል፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ ሱዳን ግብጽ በምትጎነጉነው የፖለቲካ ሴራ ምክንያት ኢትዮጵያን ማጣት ያለባት አይመስለኝም፡፡ ግብጽ የራሷ ብሔራዊ ጥቅም እስከተጠበቀ ድረስ ሱዳን በግጭት ውስጥ ብትዘፈቅ የሚደማ ልብ የላትም፡፡ በነገራችን ላይ እንዲህ አይነት ፣ የአንድን ሀገር ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ብቻ ( የግብጽን ማለቴ ነው) ዛሬ እንደ ድንገት የተጀመረ አይደለም፡፡ የቆየ ታሪክ አለው፡፡ የግብጽ ገዢዎች ከትላንት እስከዛሬ ያላቸው አቋም ተመሳሳይ ነው፡፡ ምንግዜም ቢሆን በሌሎች ሀገራት ኪሳራ ግብጽ መጠቀም አለባት፡፡ ( ለአብነት ያህል በታላቁ የአባይ ጉዳይ ዙሪያ የምታነሳቸው ክርክሮች ጭብጡ በኢትዮጵያ ኪሰራ እኔ መጠቀም አለብኝ ባይ ናት፡፡)

ለአብነት ያህል እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1960 ግብጽ የታላቁን አስዋን ግድብ በሱዳን ድንበር አቅራቢያ ስታስገነባ እንደው ዝም ብላ አልነበረም፡፡ የራሷን ጥቅም ለማስጠበቅ እቅድ አውጣታ ከጨረሰች በኋላ ነበር ግድቡ እውን እንዲሆን ያስደረገችው፡፡ የአስዋን ግድብ ተገንብቶ ካበቃ በኋላ የጣለቁ ናስር ሀይቅ የተኛው በሱዳን ድንበር ላይ ነው፡፡ ሁላችንም እንደሚገባን አንድ ታላቅ ፕሮዤ ገቢራዊ ሲሆን በአካባቢው የነበረው ህብረተሰብ መፈናቀሉ አይቀሬ ነው፡፡ ደግና ዲሞክራት መንግስት ከሆነ ተፈናቃዩን ህብረተሰብ ወደ ተሻለ ስፍራ በመወሰድ አዲስ ኑሮ እንዲጀምር ያደርጋል፡፡ የታላቁ አስዋን ግድብ በተሰራበት የሱዳን ድንበር ላይ ነዋሪ የነበሩት ከሁለት መቶሺህ (200000 ) በላይ ነባር ነዋሪዎች ከለም መሬታቸው ላይ ከተፈናቀሉ በኋላ የሰፈሩት በበረሃማ አካባቢ ነበር፡፡ 

ደቡብ ሱዳን እንደ አዲስ ሀገር ሆና ስትፈጠር የግብጽ እገዛ ከፍተኛ ነበር

ግብጽ በአንዲት ጠንካራና ሉአላዊት ሱዳን መኖር ተጠቃሚ አይደለችም፡፡ የተለያዩ የግብጽ ዜጎች አንዲት ሱዳንን ወደ በርካታ ሀገራት ለመከፋፈል በብዙ ባጅተዋል፡፡ ይህ የግብጽ መንግስታት የታሪክ ሌጋሲ ቅብብሎሽ አሁን ግብጽን እየገዙ እሰከሚገኙት አብዱለፈታህ አልሲሲ አገዛዝ ገቢራዊ እየሆነ ነው፡፡ እንደ ብዙ የሱዳን ፖለቲካ ተንታኞች የጥናት ወረቀት ውጤት ከሆነ የግብጽ ሚስጥራዊ እቅድ ሱዳንን ወደ ብዙ ትናንሽ ክፍልፋይ ሀገራት መቀየር ሲሆን ይህንንም ገቢራዊ ለማድረግ ሁለት ስትራቴጂዎችን ነድፈው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ዘመናት ተቆጠሩ፡፡

  1. የመጀመሪያው በሱዳን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ነው፡፡ እንደ አፍሪካው ቀንድ የፖለቲካ ጠበብቶች ጥናት ውጤት ከሆነ ግብጽ የሱዳን አማጺ ሚሊሻ ለሆኑት እና በዳርፉር፣ በደቡብ ኮርዶፋን፣ በብሉ ናይል ግዛት ለሚንቀሳቀሱ ሀይሎች የመሳሪያ እርዳታ ታደርጋለች፡፡ ለአማጺዎችን ወታደራዊ ስልጠና ትሰጣለች፡፡ እንዲሁም ለእነኚሁ አማጺዎች የዲፕሎማቲክ ከለላ እንደምትሰጣቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
  2. ሌላው ሁለተኛው  ደግሞ ሱዳን በሌሎች ሀገራት ጣልቃ እንድትገባ የምትጎነጉነው የፖለቲካ ሴራ ነው፡፡ ይህ ከሱዳን የግዛት ክልል ውጪ የምታደርገው መሰሪ ተግባሯ መሆኑ ነው፡፡ በቅርብ ግዜ ውስጥ ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ገፍታ የገባችው እንደው ዝም ብላ እንዳልሆነ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በአንክሮና በሰከነ መንፈስ መመርመር ይገባናል፡፡ የግብጽ እጅ ከጀርባው አለ፡፡ ኢትዮጵያ የታላቁን አባይ ወንዝ እየገነባች በመሆኗ ግብጽ ተቆጥታለች፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያን ለማዳከም የምትተኛ ሀገር አይደለችም፡፡ የታላቁን አባይ ማዘግየት ከቻለችም ማስቆም የግብጽ አላማ ነው፡፡ ይህን አለማዋን ለማሳካት ደግሞ ኢትዮጵያን ማስጨነቅ በጦርነት ውስጥ ለመዶል መሞከሯ የሚጠበቅ ነው፡፡ ስለሆነም በአሁኑ ጊዜ ሱዳንና ኢትዮጵያ በድንበር ይገባኛል ምክንያት የጀመሩትን መለስተኛ ግጭት ወደለየለት ጦርነት ውስጥ ለመዶል ስትል የማትቆፍረው ጉድጓድ፣ የማትመሰው ቅጠል የለም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ኢትዮጵያና ሱዳን በድንበር ይገባኛል ምክንያት ግጭት ውስጥ የገቡት ለብዙ ጊዚያት ነበር፡፡ ላለፉት መቶ አመታት በተለያዩ ጊዜያት በድንበር አካባቢ የሚገኙ የሁለቱ ሀገራት ዜጎች በግጦሽ እና እርሻ መሬት ይገባኛል አለመግባባት ምክንያት ተጋጭተዋል፡፡ ስለሆነም በእኔ የግል አስተያየት እንዲህ አይነት የተለመዱ ግጭቶች ሁለቱንም ሀገራት  ወደለየለት ጦርነት ማስገባት የለባቸውም ብዬ አስባለሁ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና እንዲህ አይነት የተለመደ መለስተኛ ግጭት በአሁኑ ግዜ ለምን ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆነ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ መልሱ በአጭሩ ግብጽ የሁለቱን ሀገራት የተለመደ የድንበር ላይ ግጭት በታላቁ አባይ ግድብ ግንባታ ላይ ተጽኖ ለመፍጠር በሚያስችላት መንገድ በረቀቀ ዘዴ ለመጠቀም እየሰራች ነው የሚለው ይሆናል፡፡ ከዚህ ባሻግር አንዳንድ የሱዳን ወታደራዊ ሀይል ከፍተኛ የጦር ጄኔራሎች የግብጽን ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሚሰሩ ፣ ከሌሎች የአረብ ሀገራት እንደ ሳኡዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትሰ መንግስታት ድጋፍ እንደሚደርግላቸው ነጻ መንፈስ ያላቸው የሱዳን ፖለቲካ ተንታኞች በጥናት ወረቀታቸው ላይ ጠቅሰውታል፡፡ 

የግብጽ ስውር አገዛዝ በሱዳን

ሱዳናዊው የፖለቲካ ተንታኝ ሚሰትር ሀቢብ አህመድ እና ሌሎች የሱዳን ፖለቲከ ተንታኞች ባቀሩበት ጽሁፍ መሰረት ሱዳን በአስር ሺህ (10000 ) የሚቆጠሩ ወታደሮቿን በየመኑ ጦርነት እንዲካፈሉ የላከችው በዋነኝነት በግብጽ የዲፕሎማቲክ ሴራ ምክር ወይም ትእዛዝ ነበር፡፡ ከዚህ ባሻግር በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ያገረሸውን የድንበር ላይ ግጭት ተከትሎ ግብጽ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ወደለየለት ጦርነት እንድትገባ የማታደርገው ሴራ የለም፡፡ ግብጽ የኢትዮጵያን የውስጥ አለመረጋጋት ተገን በማድረግ ፣ እንዲሁም የድንበር ላይ ግጭቱን ለማባባስ ከሞከረች አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ግብጽ የሱዳንን ሽግግር መንግስት እና ኢትዮጵያ ያለችበትን አስጨናቂ የፖለቲካ አጣብቂኝ ተሞርክዛ ሱዳንን ጦር አውርድ ብላ ብታዝ የሚስገርም አይደለም፡፡ ከዚህ ባሻግር አጠቃላዩ ስእል የሚያሳየን ነገር ቢኖር ግብጽ ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያን ወደ ግልጽ ጦርነት ከአስገባች አካባቢውን ወደለየለት ትርምስ ውስጥ አስገበዋለው ብላ ስትራቴጂ ያወጣች ይመስላል፡፡ የዚህ የለየለት ትርምስ ደግሞ ውጤቱ የናይልን ወንዝ ያለምንም ተቀናቃኝ የአንበሳውን ድርሻ ለመጠቀም ያስችላታል፡፡ 

ሱዳን አሁን መረዳት ያለባት ቁምነገር ምን ይሆን ?

ኢትዮጵያ እውነተኛ የሱዳን ጎረቤት ናት፡፡ የሁለቱ ሀገራት ህዝብ ለዘመናት የቆየ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ያላቸው ህዝቦች ናቸው፡፡ የዝነኛው የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ አቀንቃኝ የነበረው ጋሼ ጥላሁን ገሠሠ ( አፈሩን ገለባ ያድርግለት) በሱዳናውያን የሙዚቃ አፍቃሪያን ልብ ውስጥ ለዘለአለም ሲንቀለቀል እንደሚኖረው ሁሉ ሱዳናዊው ዝነኛ የሙዚቃ ሰው ያጥኡም ድምጹ በኢትዮጵያውያን እዝነ ልቦና ውስጥ በተመሳሳይ መልኩ ሲንቀለቀል ይኖራል፡፡ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ስደተኞች በሱዳን መሬት ላይ እንደሚጠለሉት ሁሉ የሱዳን ስደተኞችም ኢትዮጵያ ሁለተኛ ቤታቸው ሆና ቆይታለች፡፡ ወደፊትም ይሄው እውነት ይቀጥላል፡፡ ስለሆነም ሱዳን ከግብጽ ይልቅ ኢትዮጵያ ትበልጥባታለች ብዬ አስባለሁ፡፡ ጊዜያዊ የፖለቲካ ስካር ያልፋል፡፡ የሚያዋጣው የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ዘለቄታዊ ህይወት ማሰቡ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር ኢትዮጵያ በሱዳን የሚከሰቱ የርስበርስ ግጭቶችን ለማብረድ በተባበሩት መንግስታት የጸጥታ አስከባሪ ጦር ስር ሆና ወደ ሱዳን መሬት ገባች እንጂ የሱዳንን መሬት ወራ አታቅም፡፡ ኢትዮጵያ የራሷን የማትሰጥ ፣ የሰው ማትነካ ሀገር መሆኗ መታወቅ አለበት፡፡ ስለሆነም ሱዳን የራሷን ሉአላዊነት መጠበቅ አለባት እንጂ በሶስተኛ ወገን ግፊት ከጎረቤቷ ኢትዮጵያ ጋር ግጭት ውስጥ መዶል የለባትም፡፡ ሱዳን ለሌሎች ሀገራት ጥቅም ብላ ህዝቧን መጉዳት ያለባት አይመስለኝም፡፡

የሱዳን ስውሩ ኃይል ማን ነው ?

ልብ በል፤ በጎንደር በኩል ሱዳን ድንበር ጥሳ፣ ሰተት ብላ ወደኢትዮጵያ የገባችው ለምን ይመስልሃል? በነፍስ ሔር ከሱዳን ጀርባ ስውር የሴራ እጆች አሉ፡፡   ግብጾች ይኸን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በኢትዮጵያ ውስጥ ትርምሱ እንዲቀጥል በውስጥና በውጭ ቅጥረኛ ኃይላት ፊት ለፊት መጥተው ስለመታየታቸው በብዙ የፖለቲካ ተንታኞች የተነገረ ጉዳይ ነው፡፡

የሱዳን ጦር ሰራዊት አንዳንድ ሙሰኛ አመራሮች ከግብጽ ጋር ባላቸው የኢኮኖሚ ጥቅም ትስስር ተገን በማድረግ  “አሁን ጊዜው ጥሩ ነው፣ አመቺ ነው” ባሉበት ጊዜ በድንበር ይገባኛል ጥያቄ ስም ምስኪን የኢትዮጵያ ገበሬ ላይ ጦር መዝዘው ሉዐላዊነታችንን በጠራራ ጸሐይ ደፈሩ፡፡

ዕቅዱ የተጠናና የተናበበ እንደነበር የሚለተሪ ሳይንስ አዋቂዎች ሲናገሩ ይሰማል፡፡ በነገራችን ላይ የወያኔ ቡድን በኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ ተኩስ በመከፈቱ ምክንያት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ግዛት ውስጥ ጦርነት መቀስቀሱን እናስታውሳለን፡፡ ህወሓቶች ጥቅምት 24 ቀን ጦርነቱን ሲለኩሱ፣ የግብጽ የውክልና ጦርነት የሚያስፈጽመው የሱዳን ጦር ከአምስት ቀናት በኋላ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ድንበራችን ጥሶ ገባ፡፡

የሱዳን ወረራ ዓላማው ምን እንደሆነ በጥልቀት ለመረዳት በርካታ መግፍኤ ምክንያቶችን መመርመር ግድ ይላል፡፡ ድንበር ለማስከበር ወረራና ጉልበት አዋጪ አለመሆኑን ሱዳኖች ይስቱታል ተብሎ አይገመትም፡፡ በእኔ አስተያየት የኢትዮጵያን ጦር ጎትቶ በድንገት ጦርነት ውስጥ መዶል ተፈልጎ የነበረ ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያ በውስጣዊ የፖለቲካ ችግር ውስጥ የምትዳክር ሀገር በመሆኗ ሀገሪቷን የበለጠ የትርምስ መድረክ ለማድረግ ታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች አስበው አቅደው የከፈቱት ጦርነት ይመስላል፡፡ ከዚህ ባሻግር የታላቁን አባይ ወንዝ ግድብ ስራ ከቻሉ ማስቆም ካልቻሉ ደግሞ የታላቁን አባይ ወንዝ ግድብ ስራ ለማስተጓጎል አልመው ነበር የተነሱት፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ዘሎ ወደለየለት ጦርነት ውስጥ አለመግባቱ የብልህ መሪ ውሳኔ ቢሆንም የሱዳን ወታደሮች ከግዜ ወደ ግዜ ይዞታቸውን እየገፉ ከመጡ ለኢትዮጵያ ህለውና አደጋን ይጋብዛል፡፡  ስለሆነም የግዜው የኢትዮጵያ መንግስት በመጀመሪያ የዲፕሎማቲክ ተጋድሎ በዲፕሎማቲክ አዋቂዎች በማድረግ መሞከር ይህ አልሆነ ካላ ግን ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በማሰለፍ የኢትዮጵያን ዳርድንበር ለማስከበር በታሪክ ፈተና ፊት ወድቋል፡፡ በነገራችን ላይ የሱዳን ወረራ እንደው ዝም ብሎ ድንገት የተፈጸመ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በውስጥ የፖለቲካ ችግሮች ተተብትባለች ብለው ታሪካዊ ጠላቶቻችን አስበዋል፡፡ ኢትዮጵያን ወደለየለት የርስበርስ ጦርነት ውስጥ ለመዶል ሁኔታዎች ሊመቻቹ ይችላሉ ብለው አስበዋል፡፡ ከዚህ ባሻግር ህወሓት ላይ የሚደረገውን የሕግ የማስከበር ስራ እንዲላላ ለማድረግ የታለመም ነበር፡፡ በዚህም ሕወሓቶች ትንፋሽ አግኝተው እንዲያንሰራሩ የታቀደ ግልጽ ማበርም ይመስላል፡፡ በዚህም አጋጣሚ የህወሓት የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች ኢትዮጵያን ሲከዱ የመጀመሪያቸው እንዳልሆነ የአሁኑ ትውልድ መገንዘብ አለበት፡፡ የወያኔ መሪዎች ሶማሊያ ኢትዮጵያን በ1969 ዓ.ም. ስትወር ድጋፍ ሰጥተው ነበር፡፡ ከሱዳንም ጋር አያብሩም ብሎ ለማመን ይቸግራል፡፡ እነርሱ ለኢትዮጵያ የሚደማ ልብ የላቸውም፡፡ ኮሎኔል በላይ አስጨናቂ፣ አጼ ዮሃንስን፣ ሻምበል ምሩጽ ይፈጠርን፣ ዶክተር ሀይሉ አርአያን፣አቶ ገብረመድህን አርአያን፣ዶክተር ዮሀንስ አበራን በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ጀግኖቸን ያፈራው ሰሜን ኢትዮጵያ የትግራይ መሬት የወያኔ መሪዎችን ማፍራቱ ሲታሰብ በእውነቱ ያስደነግጣል፡፡ ያሳዝናል፡፡ ማሳዘን ብቻ አይደለም፡፡ ህሊናን ያደማል፡፡ ሆድንም ይበጠብጣል፡፡ የትግራይ ወንድሞቻችን፣ አህቶቻችን፣ ወንድሞቻቸችን ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድሞቻቸው……. ሁሉ ለኢትዮጵያ ዳርድንበር መከበር የከፈሉት ከባድ መስእዋትነት በወያኔ የሀገር ክደት የተነሳ በፍጹም ከል ሊለብስ አይቻለውም፡፡ ወያኔ ሀገርን እስከመሸጥ የደረሰ ቅሌትዋ ፍንትው ብሎ ቢታይም የትግራይን ህዝብ ኢትዮጵያዊነት መንፈስ በፍጹም አያናጋውም፡፡

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ለሚዲያ ሰዎች ሲናገሩ “ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያለውን ችግር ማጉላት ያልፈለገችው ጉዳዩን ቀጠናዊ ላለማድረግ ነበር” ብለዋል፡፡ በእርግጥም ህወሓት ሮኬት ወደአስመራ ስትተኩስ ብቸኛ ዓላማዋ ጉዳዩን ቀጠናዊ በማድረግና በማወሳሰብ የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት መሳብ ነበር፡፡ አሁንም ግብጾች ሱዳናውያንን ከጀርባ እየጋለቡ ወደኢትዮጵያ ድንበር ገስግሰው የገቡት ጦርነቱን ቀጠናዊ በማድረግ ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ላይ ያላትን ትኩረት መቀነስ እና ቢቻል ስራውን ማስተጓጎል መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

እናም የግብጾች ሴራ ድንበር ከመውረር ሊሻገር ያልቻለው በኢትዮጵያ በኩል ሕጋዊ አካሄዶች ብቻ በመመረጡ ነው፡፡ ዘሎ ወደጦርነት አለመገባቱ የዲፕሎማሲ ዋጋው ከፍተኛ ነው፡፡

በዚህ የተበሳጩት ግብጾች በውክልና ጦርነታቸው አሁንም ወደኢትዮጵያ ድንበር በጣም ዘልቀው እየገቡና ጉዳት እያደረሱም ስለመሆኑ ተሰምቷል፡፡

እንግዲህ ትግእስትም ልክ አለው እንዲሉ ኢትዮጵያ ደጃፍዋ ድረስ የመጣን ወራሪ ቆንጥጣና አስተምራ መመለስን ድሮም የተካነችው ጥበብ ነውና ዛሬም ለመተግበር የምትገደድበት ሰዓት እነሆ ደርሷል፡፡

የትሮይ ፈረሶቹን ሱዳናውያን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ድንበር የማስከበር ስራው የመንግስት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ብሔራዊ ግዴታ መሆኑን በመረዳት ለአይቀሬው ግዳጅ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ግን ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከጎሳ ከረጢት ውስጥ በመውጣት ኢትዮጵያን ማስደቀም ግዴታችን ነው፡፡ በእኔ የልጅነት እድሜ ሀገር በባእድ ተደፈረች ከተባለ እነ እትዬ ማሚቴ ሳይቀሩ ማማሰያቸውን ይዘው ሲፎክሩ እያየሁ አድጌአለሁ፡፡ በወያኔ አገዛዝ ወደታሪክ ትቢያነት የተቀበሩት እድሜ ቀጥል ጠጅ ቤት፣ መምሩ ጠጅ ቤት፣ አራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ጠጅ ቤቶች ጥምቢራቸው በጠጅ የዞር ጠጪዎች ሳይቀሩ በቁጭት ይነዱ ነበር፡፡ ይንጨረጨሩ ነበር፡፡ ፉከራው አይጣል ነበር፡፡ የወታደሩ፣ ገበሬውና ወዛደሩ ተደፈርኩ ስሜት ደግሞ አስገራሚና ከፍተኛ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ድንበር ተደፈረ በተባለ ማግስት ሚስቴን፣ልጄን፣ ስንቄን ሳይል ወዲያው ነበር ወደ ጦር ማሰልጠኛ የሚገባው፡፡ ወደ ጦር ሜዳ የሚተመው፡፡ ከ750 ኪሎ ሜትር በላይ ዘልቆ ወደ ኢትዮጵ ድንበር የገባውን የአብሪተኛውን የመሃመድ ሲያድባሬ ጦር አሳፍሮና ቀጥቅጦ የመለሰው ከኢትዮጵያ ገበሬ የተመለመለው ህዝባዊ ሰራዊትና በሀገር ፍቅር ስሜት የነደደው የኢትዮጵያ መለዮ ለባሽ መደበኛ ጦር ነበር፡፡ ምስጋና ለወያኔ የጎሳ ፖለቲካ የሀገር ፍቅር ስሜት ላልቷል፡፡ ያለምንም መቀባባት  ኢትዮጵያ በብሄራዊ ውርደት ውስጥ ብትዶል፣ ምንም ደንታ የማይሰማው ትውልድ ተፈጥሯል፡፡ በአጭሩ መንፈሱ የተሰበረ ትውልድ ተፈጥሯል፡፡ ዛሬን ብቻ በምቾትና ተድላ ከኖረ ለነገ ግድ የለውም፡፡ የሀገር ፍቅር ነጻነት ምን እንደሆነ መገንዘብ አልቻለም፡፡ ጥሩ ልብስ መልበስ፣ መዝናናት፣ መደሰት፣ መሳቅ መጫወት ብቻ ከተሟሉለት ግድ የለውም፡፡ ጋሼ ጥላሁን ገሠሠ ገና ድሮ በጠዋቱ ነበር ጥሩ ልብስ ለብሰን አምሮብን ተውበን የምንታየው፣ ሀገር በነጻነት ተከብራ ስትኖር ነው፡፡ በማለት በዛ ግሩም ጥኡም ድምጹ አዚሞ ህያው ሆኖ ያለፈው፡፡ የዛሬው ትውልድ በአብዛኛው ልቡ የሚሸፍተው ወይ ለፈረንጅ ዘፈን ግፋም ካለ አካባቢያዊ ስሜት ለሚቀሰቅሱ ዘፈኖች ተብሎ ቢጻፍ ስህተት አይመስለኝም፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ የማእከላዊው መንግስት ስራ እጅግ ሰፊ መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያዊ ስሜትን በትውልድ ውስጥ ከማስረጽ አንጻር ማለቴ ነው፡፡

እንደመደምደሚያ

በ1969 / 70 ዓም የዚያድ ባሬን ወረራ በሕይወት ያሉቱ በግብር ያዩትን ተጋድሎና የተከፈለውን መስዋዕትነት ሲያስተምሯችሁ ክልልን ወዳችሁ ጆሮ ነፈጋችሁ ። 

ባልነበረባችሁበት ዳኝነት ለመስጠትም አፋችሁን አሾላችሁ ። 

መስዋዕትነቱን እንደ ታሪክ ለመዘከር ቋቅ አላችሁ ።

በ1983 ዓ.ም. በዳግማዊ ምኒሊክ ቤተመንግስት ዘው ብላችሁ የገባችሁት ወያኔዎችና አጋሮቹ የኢትዮጵያን ዳርድንበር ሲያስከብሩ ከተገንጣዮችና አስገንጣይ ሀይሎች ጋር ሲፋሉም አካል እና በመንፈስ የተጎዱትን ዘማቾች የደርግ ወታደሮች ነበሩ በሚል የጥላቻ መንፈስ ተነሳስታችሁ ለመንከባከብ ነፍጋችሁ ለስቃይ ዳረጋችሁ ። 

ቤተሰቡን ከአዘቅት ውስጥ ጣላችሁ ።

የልጆቹን ተስፋ ከወዲሁ አጨለማችሁ ።

የደርግ ወታደር እያላችሁ ቅፅል ስም ሰጥታችሁ አገልግሎታቸውን አራከሳችሁ ።

የሚገባቸውንም ጥቅም ከራሳችሁ ፍላጎት በመነጨ ሥልጣናችሁ ከለከላችሁ ።

የመንግሥትም ሆነ የህወሃት ኢሕአዴግ የድርጅት አባል የነበረ ሁሉ በሰራው እርኩስና መጥፎ ምግባር ይጠየቃል ።

የወያኔ ቡድን ብቻ ሳይሆን የሴራው ተካፋዮችና አስፈፃማዎች የነበሩና ከደሙ ንፁህ ያልነበሩ ሌሎች የኢህአዲግ አባላት የነበሩ ይመለከታቸዋል ! በታሪክና ህሊና ፊት መጠየቃቸው አይቀርም፡፡

እነሆ ዛሬ ኢትዮጵያ በታሪክ ፊት ከባድ ፈተና ላይ ወድቃ ትገኛለች፡፡

አይነጋ መስሏት …. አሉ አበውና እመው

 አሁን ወያኔ አፈርድሜ አስግጦት የነበረውን ኢትዮጵያዊ ብሔራዊ ስሜት ለማንሰራራት እንዲችል ለማድረግ የግዜው የኢትዮጵያ መንግስት በታሪክ ፈተና ፊት የወደቀ መሰለኝ፡፡ ክልል ማለት አገር ማለት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ሁሉንም የኢትዮጵያ ክልሎች በኢትዮጵያዊ ብሄራዊ ስሜት ለማንቀሳቀስ  ግዜው ግድ ብሎታል፡፡ ፈተናው ቀርቧልና የፖለቲካው ፊታውራሪዎች ሆይ እስቲ እንያችሁ ?

ከየት ትጀምሩ ? ከአለም የመገናኛ ብዙሃን እንደተሰማው የኢትዮጵያ ዳር ድንበር በሱዳን ወታደሮች ተደፍሯል፡፡

በአሉታዊ ብሔር ብሔረሰብ ጠባብ ፖለቲካ አንዱን በዳይ ሌላውን ተበዳይ ፍረጃ ቅስቀሳ መርህ ተጉዛችሁ ሳለ አገር መጉዳታችሁንና በሕዝብ መሐል አድልዎ መፈፀማችሁን ዛሬ በዚህ ወሳኝ ወቅት ገብቷችሁ ይሆን ? እብሪተኛውን የመሃመድ ሲያድባሬ ጦር ኢትዮጵያውያን ያሸነፉት በህብረት ስለቆሙ ነበር፡፡ ድር ቢያብር አንበሳ ያስር እንዲሉ ዛሬ ኢትዮጵያውያን ሁሉ አንድነታቸውን ማጠበቅ አለባቸው ተብሎ ሲነገር እንደው ወሬ ለማሳመር አይደለም፡፡ የገጠማቸውን የህልውና ፈተና ለማለፍ የግድ አንድነት ስለሚበጃቸው ነው፡፡ ከታሪክ እንማር፡፡ ኢትዮጵያ ጠላቶቿን ያሸነፈችው በአንድነቷ ነው፡፡ አንድነታችን ከላላ የማንም መፈንጫ ሆነን እንቀራለን፡፡

ዳር ሲነካ መሐል ዳር ይሆናል ።

ወራሪ ጦር ወሰንም ክልልም አያቅም ።

የሚገታው ከሌለ መሬት በነፃ ካገኘ ይገሰግሳል ።

ስግብግብ አያቆምም !

ኢትዮጵያ ምን ይበጃታል ?

የማቀረብው የመፍትሔ ሀሳብ እንደ አዋቂ ወይም እንደ የዲፕሎማቲክ ሰው ሆኜ አይደለም፡፡ እውቀትም አለኝ ብዬ አይደለም፡፡ የመፍትሔ ሃሳብ ለመሰንዘር የምሞክረው እንደ አንድ ሰው፣ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ፣ የኢትዮጵያ መጻዒ እድል እንቅልፍ ከነሳቸው ዜጎች አንዱ ነኝ ብዬ በማሰቤ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በታሪክ ውስጥ አይታው የማታውቀው ከባድ የህልውና ፈተና ውስጥ ስለመዶሏ ኢትዮጵያውያን ሁሉ መገንዘብ አለባቸው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ፈተና ውስጥ ስትድወቅ ደግሞ ዜጎች ተመልካች መሆን የለባቸውም፡፡ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የመፍትሔው አካል መሆን አለባቸው፡፡ እኔም እንደ አቅሚቲ ኢትዮጵያ ለገጠማት ፈተና መፍትሔ ይሆናል የምለውን ሃሳብ ሰንዝሬአለሁ፡፡ ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ጨምሩበት፡፡

በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ትክክለኛ መስመር ላይ ነች ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ  ሰላምንና ትእግስትን መምረጧ ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያ በጣሊያን ፋሺስቶች በግፍ ስተወረር፣ በእብሪተኛው መሃመድ ሲያድባሬ ጦር ስትወረር ትእግስቷ ወደር አልነበረውም፡፡ ዛሬም የሱዳንን ወረራ በትእግስት የምታየው ጀግኖችን አጥታ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ምንግዜም ቢሆን የሚሞቱላት፣ የሚደሙላት፣ የሚያለቅሱላት፣ የሚጸልዩላት ልጆች ሞለተው ተርፈዋታል፡፡ ኢትዮጵያ ለሰላሳ አመታት ከዚያም በላይ የወያኔ አገዛዝን በትእግስት ተሸክማ ኑራ ቆይታ  የሀገር ውስጥ ባንዳዎችን በትክክለኛ ጊዜ ድል መንሳትዋ የታወቀ ቢሆንም ሀገራችን ስለፈለገች ብቻ ሰላም ትሆናለች ማለት አይደለም። ትእግስትም ልክ አለው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የሰላም አማራጩን ግን አሟጦ መጠቀም ያስፈልጋል። በነገራችን ላይ በቤኒሻንጉል የሚፈጸመው የንጹሃን ግድያ መዘዙ ብዙ ነው፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በተለይ መተክል ዞን የሚፈጸመው አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መጨረሻው ምን ይሆን የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ መልስ እንቅል ሊነሳን ይገባል፡፡ ጥቃቱን የሚፈጽሙት የጉሙዝ አማፂ የሚሰለጥኑት የት ነው ማን ነው የሚያሰለጥናቸው ከጀርባቸው ያሉ የውጭ ሀይላት እነማን ናቸው ወዘተ ወዘተ በርካታ ራስምታት የሆኑ ጥያቄዎች መልሳቸው ከባድ ነወስ፡፡እነኚህ የኢትዮጵያን ሰላምና መረጋጋት የማይፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶቻችን  የመጨረሻው ግባቸው የህዳሴው ግድብና ቤኒሻንጉል ክልልን መቆጣጠር ይሆን ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው፡፡ በእኔ አስተሳሰብ አይሆንላቸውም እንጂ ሀገራችንን መንግስት አልባ ከማድረግ የሚተኙ አይደሉም። ሴራው ብዙ ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታችንን ማጥበቅ አለብን፡፡ 

 እናት አባት ቢሞት በሀገር ይለቀሳል፣

 ወንድም እህት ቢሞት በሀገር ይለቀሳል፤

 ሀገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል ፡፡ እንዲሉ ከጎሳ ከረጢት ውስጥ ወጥተን ኢትዮጵያን እናስቀድም ለማናቸውም  የሚከተሉትን ምክረሃሳብ ለማቅረብ እሞክራለሁ

– በመላው አለም እንደ ጨው ዘር የተበተኑት ኢትዮጵያዊ ምሁራንና በሀገር ውስጥ ያሉ ታዋቂ የጶለቲካ መሪዎችና ምሁራን  ሌሎችም ከምእራባዊያን ጋር የሚተዋወቁ ታዋቂ ባለሙያዎች መንግስትን በዲፕሎማሲ እንዲደግፉ ማድረግ ያስፈልጋል።

– ከቻይና፣ ከሩሲያ፣ ከባይደን አስተዳደር፣ ከአውሮጳ ህብረት እንዲሁም ከግብፅ ጋር የማይስማሙ እንደ ቱርክ ካሉ አካላት ጋር ለመስራት በየጊዜው መረጃ የሚሰጥ ካውንስል በአስቸኳይ ማቋቋም ቢቻል።

– ኢትዮጵያዊ ብሔራዊ ስሜትን በትውልድ ውስጥ ለማስረጽ ኢትዮጵያዊ ፍልስፍናን በሰፊው ማስተማር ፡፡

– የክልል ልዩ ሀይሎች ወደ መከላከያ ውስጥ ገብተው የሚጠረነፉበት የህግ ማእቀፍ አዘጋጅቶ ከወዲሁ ልምምድ ማድረግ ቢጀምሩ። መከላከያችንም ከትግራይ ተልእኮ በኋላ መልሶ የማደራጀት ስራ መስራት ቢቻል።

– ዘመኑ የዋጀውን ወታደራዊ ቴክኖሎጂ አቅም በፈቀደ መጠን ለመከላከያ ሰራዊት ማስተማር 

– አሁን የማንፈልገው ጦርነት ውስጥ እንደሆንን አስቦ መንግስትና ህዝብ ከአይምሯዊ ዝግጅት ያለፈ ስራ መስራት ቢቻል

– ሊቢያ ውስጥና ቀይባህር አካባቢ ስራ መስራት ይገባል። ከተጠቃን በሱዳን እግረኛና የጦር ጄት ሳይሆን በግብፅ የባህር ሀይል ነው። ስለዚህ ቀይባህር አካባቢ የባህር ሀይል በውሰትም ቢሆን ማሰማራት። ( የቀድሞው የኢትዮጵያ የጦር አታሺዎች እውቀቱና ክህሎቱ ስላላቸው እነርሱን ማማከር ይበጃል፡፡)

– የሚሊተሪ ጄቶች ሳንጠቀም በኢትዮጵያ የህዝብ ማመላለሻ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ሰፊ ስምሪት መስጠት።

– እንደ ዳርፉር የግጭት ስበት ማእከሎችን መጠቀም።

–  ከአረብ ሀገራት መካከል ደጋፊ ለመፍጠር መጣር።

– ቤኒሻንጉል ሙሉ ለሙሉ ለጠቅላይ ሚኒስተር ተጠሪ በሆነ ኮሚቴ እንዲተዳደር ተደርጓል። ትልቅ ስራ ነው። አሁን የህዳሴ ግድብ የጥቃት ኢላማ እንዳይሆንና ስራ እንዳይስተጓጎል በደንብ የተዘጋጀ አንድ ብርጌድ/ሻለቃ መከላከያ ሰራዊት ስምሪት መስጠት።

 እንደተሰማው ከሆነ  የግብፅ  የጦር መኮንኖች ከባለፈው ህዳር ጀምረው ለሱዳን ሰራዊት ስልጠና እየሰጡ ናቸው። በኛ በኩልም ዝግጅት ማድረግ።

– ጦርነት የማይቀር ከሆነ የኛና የወራሪዎች የጥቃት ኢላማዎችን መለየትና ጦርነቱ በኛ ግዛት እንዳይሆን ማድረግ።

– ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያና የባይደን አስተዳደር በቴክኖሎጂና በዲፕሎማሲ እንዲያግዙን ማድረግ። ደግሞም ጉዳዩ ከአፍሪካ ህብረት እጅ ወጥቶ ለአለም አቀፍ ሴክዩሪቲ ካውንስል መቀረቡ ስለማይቀር ከወዲሁ ሰነድ ዘዘጋጅቶ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቂ መረጃ መስጠት።

ኢትዮጵያዊነት አሸናፊነት ነው! ሰለፍ የጅግና ነው ድል ግን የእግዜአብሔር ነው፡፡

Filed in: Amharic