መገላገል የምንፈልገው መምዕላዩ ከሚመራው ቆሻሻ ሥርዓት ነው
ከይኄይስ እውነቱ
ሳይገላ*ባቸውና ሳይገጠ*ባቸው ሥልጣን ላይ ይንጠላጠሉና የለመዱትን እርምጥምጥ ተግባር ሲፈጽሙ ይገኛሉ፡፡ የሙከራ ግድያው ትርኢት ቅንብር ‹ውይ! ሊገድሉት ነው? ምን ይሻለናል? እንድንል ነው? እንደማናቸውም አርቲ ቡርቲ ጉዳዮች ንቄ ልተወው ፈልጌ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አገዛዙ በለመደው የአሸባሪነት መንገድ (አንዴ ‹ተከበብኹ› ሌላ ጊዜ ራሳቸው ይፈጽሙና ‹ዘፋኛችን› ተገደለ በሚል) በንጹሐን ላይ እልቂት የሚፈጸምበት ሁናቴ መቀጠል አይኖርበትም በሚል ሃሳብ ይህንን አስተያየት ለማቅረብ ተገድጄአለሁ፡፡
ግድያ ብርቅ ባልሆነበት አገር ያውም ንጹሓን ሕፃናት፣ ሴቶችና አዛውንት በነገድ ማንነትና በሃይማኖታቸው ምክንያት በሚዘገንን ሁናቴ በአገዛዙና ግብር አበሮቹ በሚጨፈጨፉበት አገር አንድ ጐሠኛ መምዕላይ (tribal/ ethno-dictator) ላይ የግድያ ሙከራ ተደረገበት የሚል የፈጠራ ወሬ ምን ያስደነግጣል? እንኳን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን የሚጠሉ፣ ራሳቸውን ለአገራቸውና ለሕዝባቸው አሳልፈው የሰጡ ደጋግ ነገሥታት አልፈው ኢትዮጵያም ሕዝቧም ቀጥለዋል፡፡ በእግዚአብሔር ፊት የሁሉም ሰው ነፍስ እኩል ነው፡፡ ያም ሆኖ የእግዚአብሔር ‹መንሽ› ፍሬውን ከገለባው/ስንዴውን ከእንክርዳዱ በሚገባ ይለያል፡፡ የሚያስደነግጠው የፈጠራውን መልእክት ሰጭዎቹ ይህን ጥግ አድርገው በለመዱት መንገድ የሚጠሉትን ሕዝብ ለመጨፍጨፍ ያሰቡት ውጥን እንጂ፡፡ የታቀደው እልቂት ተረኞች አዲስ አበቤዎች እንደሆንን ሰማን፡፡ ሞክሩን!!! ከፈለጋችሁ ቄሮው ሽመልስ ዕብዲሳ ሠላሳ ዙር ያሰለጠናቸውን ‹አውሬዎች› አምጥታችሁ ሞክሩን፡፡ የታላቁ መጽሐፍ ቃል ‹ኢይድኅን ንጉሥ በብዝኀ ሠራዊቱ› (አገዛዝ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም) ነው የሚለን፡፡
እኛ እኮ የጐሣው ሥርዓት እስከ ‹ሕገ አራዊቱ› እና እስከነ መዋቅሩ ለሁላችን አይበጀንም ብለን ለዓመታት የሞገትነው ለሁላችን የሚበቃ የጋራ ሀገር (ኢትዮጵያ) እና የጋራ ርእሰ ከተማ (አዲስ አበባ) አለን በሚል ነው፡፡ እንዲወገድም የምንፈልገው ይኸው ከሰው በታች ያዋረደን የተረኞች መንደርተኞች አገዛዝ ሥርዓት ነው፡፡ ይህም በሠለጠነ መንገድ በንግግር/በውይይት ይፈታል በሚል እምነት ነው፡፡ እናንተ የመረጣችሁት የድንቁርናና የዕብደት መንገድ መጨረሻው የጋራ ጥፋት እንደሆነ ሰለምናምን ነው፡፡ የጋራ አገርም የጋራ ዋና ከተማም አይኖረንም ካላችሁ፣ መልካም! ሁላችንም ምንም አይኖረንም፡፡ ዞሮ ዞሮ የጐሣ ሥርዓት መጨረሻው አገር ማሳጣት ነው፡፡ ሀገር አልባ የሚሆነው ግን ኢትዮጵያ የምትባለ አገር አለችኝ የሚለው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ከአገር ይልቅ መንደርን የመረጣችሁት ጐሠኞች ሁሉ ሀገር ብቻ ሳይሆን መንደር አልባም ትሆናላችሁ፡፡ ግለሰብ አለቃም ሆነ ጭፍራ እንደ ሥራው ዋጋውን ያገኛል፡፡ ፍርድ አደላዳዩ ያውቅበታል፡፡ ልብን የሚመረምር ኩላሊትን የሚፈትን ጌታ ከመጋረጃ ጀርባ የሐሰት ምስክር አይፈልግም፡፡ በምድር የብዙዎችን መምዕላይ ተዋርዶ አሳይቶናል፡፡ ታሪክም መዝግቦታል፡፡
ግብዐተ መሬቱ እንደተፈጸመው ወያኔ የአገርን ህልውና መያዣ አድርገን እያስፈራራን የአንድ ጐሣ የበላይነትን አንግሠን እንገዛለን ብላችሁ አስባችሁ ከሆነ ግፉበት! ግን የማትወክሉት የኦሮሞ ሕዝብ ይህንን እንድታደርጉለት ጠይቋችኋል? የሥልጣንና የንዋይ ፍትወታችሁን ለማርካት፣ ሥር የሰደደ ደዌ ሆኖ የሚያሰቃያችሁን የበታችነት እና የተበዳይነት ስሜት ለመሸፈን ስትሉ የምትጠቀሙበት ሕዝብ ግን ብትነግዱበትም ፈቃዱን አልሰጣችሁም፡፡ ሊሰጣችሁም አይችልም፡፡ ከሰውነት የተለዩት ሎሌዎቻችሁ እና ተጠቅማችሁ እንደምትጥሉት ዕቃ (disposable item) ለጥፋት የምትጫወቱባቸው ወጣቶች ምን ድረስ እንደሚያዛልቋችሁ አብረን የምናየው ይሆናል፡፡ ለካስ ያልዘሩት አይበቅልም፡፡ ክፉ ልጅ ከአባቱ ክፋት ልቆ ለመገኘቱ ዓይነተኛ ምሳሌ የወያኔ ወራሽ የሆነው ኦነጋዊው ኦሕዴድ አይመስላችሁም? በእኔ እምነት የሐሰት ግድያ ወሬውን በመንዛት የአገዛዙ አለቃ ያተረፈው ተጨማሪ ጥላቻን ነው፡፡ ሰይጣናዊው ተልእኮ ያልታሰበ ውጤት እንዲመጣ (backfire) ያደረገ ይመስለኛል፡፡ ውሸትን ዘርቶ ክብርን መወደድን ማጨድ አይቻልምና፡፡
እነ እስክንድርን ባስቸኳይ ልቀቁ!!! ነፃነት ለኅሊና እስረኞች!!!
ኦነግ ያገታቸው ልጃገረድ ተማሪዎች የሚገኙበትን ሁናቴ ለቤተሰቦቻቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሳውቁ፡፡
ሕወሓትን እና ኦነግን ሕገ ወጥ በማድረግና በአሸባሪነት በመፈረጅ የኢትዮጵያን የፖለቲካ መልክዐ ምድር አስተካክሉ፡፡
(የምርጫ ቦርድ የሕወሓት ሕጋዊ ሰውነትን መሠረዙ አንድ የሚያበረታታ ጉዳይ ሆኖ፣ በአሸባሪነት ሊፈረጅ ይገባዋል፤ ትጥቅ ይዞ አገርንና ሕዝብን እያሸበረ ያለው ኦነግም ላይ ባስቸኳይ ሕጋዊ ርምጃ ሊወሰድ ይገባል፡፡)