ኦነጋውያኑ እያደር እየባሰባቸው ነው
ከይኄይስ እውነቱ
ሰሞኑን በብሔራዊ መለያችንና ኩራታችን በሆነው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ የተፈጸመውንና እየተፈጸመ ያለውን ባጠቃላይ ኢትዮጵያን፣ በተለይ ደግሞ የአገር ምልክቶችን የማጥፋት ደባ ከኢትዮ – 360 ሜዲያ በዝርዝር አደመጥኹ፡፡ ጥፋቱ ከተነገረውም በላይ እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ ለተቋሙ ደኅንነትና ለአየር ሥርጭት እንዲስማማ ተደርጎ ተቈጥቦ የቀረበ ይመስለኛል፡፡ በተቋሙ ላይ እየደረሰ ያለውን ጥፋት በጥቅሉ ብናውቀውም ‹አጽሙን› ሥጋ በማልበስ በኩል እና መረጃዎቹን ከማስረጃ ጭምር በየጊዜው እየተከታተሉ ለባለቤቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲደርስ ያደረጉት ሜዲያውና አባላቱ እንዲሁም ሕይወታቸውን አስይዘው መረጃውን ላስተላለፉ ዜጎች ላቅ ያለ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡
ነባር ተቋማትን የማፍረስ ተግባር ኦሮሙማ የሚባለውና በዐቢይና የኦሮሞ ጐሠኞች የሚመራው አገር አጥፊ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ አገር የማጥፋቱ እንቅስቃሴ ቀደም ሲል በወያኔ የተጀመረ መሆኑ ቢታወቅም በሙሉ ኃይል እየተፈጸመ የሚገኘው ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ የሆነን ሁሉ አጥብቀው ለሚጠሉት አማራ የሚባል ሕዝብ ሰጥተው በጥላቻና ሥር በሰደደ የበታችነት ስሜት የሚሰቃዩት፣ በዚህም ምክንያት ዘግናኝ ነውሮችን ባለፉት 3 ዓመታት በመፈጸም ላይ በሚገኙት የኦሮሞ ጐሠኞች ወር ተረኝነት ወቅት ነው፡፡ ዐቢይና የዓላማ ተጋሪዎቹ ተመክረው ተዘክረው እምቢ በማለት ይቅርታ በሌላቸው ወንጀሎችና ነውሮች ራሳቸውን እንደ ዕርድ ከብት እያሰቡጠ የሚገኙበት ምክንያት ምን ይሆን?
የዛሬው ርእሰ ጉዳዬ አየር መንገዳችንን በ21ኛው ክ/ዘመን የተረኞች ጐሠኞች መፈንጫ በማድረግ ውድቀቱን ለማፋጠን በዐቢይና በአባ ዱላ ተልእኮ ተሰጥቶት በአካውንት ሥራ አመራርነትና በሠራተኛው ማኅበር ፕሬዚዳንትነት ተመድቦ ተቋሙን እያመሰ የሚገኝ ተሊላ ጉተማ የሚባል ‹ቄሮ›፣ በተጠቀሰው የኢትዮ – 360 ፕሮግራም ላይ ካንድ ሜዲያ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ስለ ኦሮሞ ማንነት የተናገረውን ቃል ይመለከታል፡፡ ዐውዱም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ስለሚነገረው የሥራ ቋንቋ ይመለከታል፡፡ ቃሉም የሚከተለው ነው፤
‹‹…ይህ ግቢ[አየር መንገዱ] ዓለም አቀፍ የሥራ ቋንቋው የታወቀ ነው፡፡ እንግሊዝኛ ነው፡፡ ነገር ግን ባለፉት ጊዜያቶች አብዛኛው ሰው የሚጠቀመው ሁለቱን ቋንቋዎች ብቻ [እንግሊዝኛና አማርኛ] ነው፡፡ በዚህ ግቢ የኦሮምኛ ቋንቋ መናገር የማይሞከር ነው፡፡ የዚህ ግቢ የሥራ ቋንቋ እንግሊዝኛ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ባብዛኛው የሚነገረው አማርኛ ነው፤ እንግዲህ በሕግ የግቢው ቋንቋ እንግሊዝኛ ነው ከተባለና ከዚህ ውጭ ሌላ ቋንቋ የሚነገር ከሆነ የኦሮምኛ ቋንቋም፣ የጉሙዝ ቋንቋም፣ የሶማሊኛ ቋንቋም ከአማርኛ እኩል መነገር አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ እኔን ደግሞ እግዚአብሔር ነው ኦሮሞ አድርጎ የፈጠረኝ፡፡ መርጬ አይደለም ኦሮሞ የሆንኩት፡፡ እግዚአብሔር በሰጠኝ ነገር ደግሞ ደስተኛ ነኝ፤ እኮራለሁ፡፡ ይህንን ደግሞ ለማየት ኦሮምኛ ተናጋሪ ወንድሞቼን የትም ቦታ ቢሆን፣ በስብሰባም ቦታ ቢሆን በእንግሊዝኛና በአማርኛ አላናግራቸውም፤ በኦሮምኛ ብቻ ነው የማናግራቸው፤ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሚሠሩ አብዛኛው ሠራተኞች ምሳሌ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡››
ግለሰቡ የአምላክን ስም እግዚአብሔር ብሎ በመጥራቱ የየትኛውም ክፍል ይሁን የክርስትና አሊያም የይሁዲ እምነት ተከታይ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ለነዚህ እምነቶች መሠረት ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት አስረግጠው የሚነግሩን ደግሞ እግዚአብሔር በራሱ መልክና ምሳሌ የፈጠረው ሰውን ነው፡፡ ወንድና ሴት አድርጎ፡፡ አባታችን አዳምንና እናታችን ሔዋንን፡፡ ዛሬ በዓለሙ ሁሉ በዝቶ ተባዝቶ እንደምናየው የተለያየ ኅብረ መልክዕ (ነጭ፣ ጥቁር፣ ወዘተ.) ይዞ፡፡ በየትኛውም የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍል፣ በትርጓሜም ሆነ በሥነ መለኮት ትምሕርት እግዚአብሔር እገሌ የሚባል ነገድ ወይም ጐሣ ፈጠረ የሚል አናገኝም፡፡ ነገድ/ጐሣ ሰው አይደለም፡፡ ነገድ/ጐሣ ሰዎች በማኅበር መኖር ሲጀምሩ የፈጠሩት ስያሜ ነው፡፡ ባጭሩ ሰው ሠራሽ ነገር ነው፡፡ ጥንታዊ ፣ ኋላ ቀርና ዝቅተኛ ለሆነው የሰዎች ስብስብ አወቃቀር/አደረጃጀት የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ በመሆኑም እግዚአብሔር ኦሮሞ፣ ጉራጌ፣ ትግሬ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ወዘተ. እያለ የፈጠረው ፍጥረት የለም፡፡ ነገድ/ጐሣ ቋንቋን ወይም ቦታን ወይም የሰው ስምን ተከትሎ በሰው ልጅ ወይም በኅብረተሰብ ስምምነት የተፈጠረ ስያሜ ነው፡፡ ስለዚህ ተሊላ ሆይ! እግዚአብሔር አንተን ኦሮሞ አድርጎ አልፈጠረም፡፡ ለቋንቋው ከሆነ ማንኛውም ሕፃን ያደገበትን ቦታ ወይም የሚኖርበት ማኅበረሰብ የሚናገረውን ቋንቋ እየተናገረ ያድጋል፡፡ ካንድም ሦስት አራት ቋንቋዎች ሊናገር ይችላል፡፡ ሆኖም የሚናገራቸው ቋንቋዎች የሚወክሉት ማኅበረሰብ ካለ፣ እግዚአብሔር እነዛን ማኅበረሰቦች አድርጎ ፈጠረኝ ሊል አይችልም፡፡ ሰው ሰራሽ የሆነው የአንድ ነገድ/ጐሣ አባል ሆኖ መገኘት በግል ጥረትና ድካም የሚገኝ ባለመሆኑ የሚያኮራም ሆነ የሚያሳፍር ጉዳይ አይደለም፡፡ ስለሆነም ሰዎች ርስ በርስ በሚያደርጉት ግንኙነት በመረጡትና በሚያውቁት ቋንቋ መነጋገር ከማንም ፈቃድ የማይሹበት ተፈጥሯዊ መብታቸው ነው፡፡ ይህ መብት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኝ በየትኛውም የመንግሥት መ/ቤትና ድርጅት እንዲሁም የግል ድርጅቶች ውስጥ የተከለከለበትን ጊዜ አላውቅም፡፡ ሊከለከልም አይችልም፡፡ በአንፃሩም ዓለም አቀፍ የሥራ ጠባይ ያላቸው መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ሀገር-በቀል ድርጅቶች ዓለም አቀፍ ቋንቋዎችን ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ ይህ ማለት ግን እነዚህ ተቋማት ባገር ውስጥ የሚያደርጓቸውን የሥራ ግንኙነቶች በማዕከላዊው መንግሥት በሕግ የሥራ ቋንቋ ተብሎ በተደነገገው አይጠቀሙም ማለት አይደለም፡፡ እንደውም ግዴታ አለባቸው፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በከሳሽ ወይም ተከሳሽነት ፍርድ ቤት የሚያደርገውን ሙግት የሚያቀርበው በአማርኛ ይሆናል፡፡ ምሳሌውን ከፍ ለማድረግ ኢትዮጵያ እንደ አንድ ሉዐላዊ አገር በተባበሩት መንግሥታት ወይም በሌሎች መንግሥታዊ ዓለም አቀፍ ተቋማት የምታደርገውን ግንኙነት በብሔራዊ ወይም ይፋ በሆነው የሥራ ቋንቋዋ አማርኛ የማቅረብ ሙሉ መብት አላት፡፡ ተግባራዊ ስታደርግም ኖራለች፡፡ ዓፄ ኃይለሥላሴ በመንግሥታቱ ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽን) ጄኔቫ ያደረጉትን ንግግር ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህንን የማትተው በጥላቻ ልብና ጆሯቸው ለተደፈነው ኦነጋውያን ሳይሆን እነሱ በሐሰት ትርክት ውዥንብር ውስጥ ለከተቱት ወጣት ትውልድ እንጂ፡፡
ይህ አጠቃላይ እውነታ እንዳለ ሆኖ፣ በዓለም የሚገኙ አገራት የሥራ ቋንቋ/ዎች በበላይ ሕግጋታቸው ይወስናሉ፡፡ አሁን ባለው የወያኔ ማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› በኢትዮጵያ የማዕከላዊው መንግሥት የሥራ ቋንቋ አማርኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ጥናትን፣ ብሔራዊ ፍላጎትን እና የጋራ ስምምነትን መሠረት አድርጎ ይህንን የሥራ ቋንቋ ባዲስ ሕገ መንግሥት ወይም ያለውን በማሻሻል እንደ አስፈላጊነቱ ወደ 4/5 ከፍ ማድረግ ይቻላል፡፡ የዐቢይ አገዛዝ ‹የሚኒስትሮች ምክር ቤት› ያደረገው ማሻሻያ ግን (በማን አለብኝነት ተግባራዊ ለማድረግ ከሚሞከር በቀር) ሕገ ወጥ ነው፡፡ ቢያንስ አይነካብን ያሉትን የወያኔ ‹ሕገ መንግሥት› የሚፃረር ድርጊት ነው፡፡
ባለቤቷን (ዐቢይና አባዱላን) የተማመነች በግ እንዲሉ አቶ ተሊላ የማዕከላዊው መንግሥት ተቋም በሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ በስብሰባ ላይ ወይም ለሥራ ጉዳይ በኦሮምኛ እናገራለሁ ማለቱ በተረኛነት ድንቁርናና ማንአለብኝነት ካልሆነ በቀር ሕገ ወጥ መሆኑ ሊነገረው ይገባል፡፡ በመሠረቱ የጐሣ/ማንነት ፖለቲካ መሣሪያ ሆኖ እንጂ ቋንቋ ከመግባቢያነት ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡ እላይ እንደገለጽኹት ኦሮምኛም ሆነ ሌሎች ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነገሩ ቋንቋዎች ሕጋዊ መሠረት እስካላቸው ድረስ ይፋዊ ለሆነ የሥራ ጉዳይ በማዕካለዊ መንግሥት መጠቀም ይቻላል፡፡ ከዛ ውጭ አሁን ባለው የጐሣ ሥርዓት በቋንቋና በጐሣ በተዋቀሩት ክፍላተ ሀገራት ውስጥ ባሉ ሕጎች መሠረት በየአካባቢው የሚነገሩ ቋንቋዎች በዛው ክ/ሀገር ለሥራ አገልግሎት በጥቅም ላይ መዋላቸው ይታወቃል፡፡
የቋንቋው ጉዳይ የኦሮሙማ ዓላማ አራማጆች ለአማርኛ ካላቸው መሪር ጥላቻ የመነጨ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ አሠራርን፣ ዘመናዊ አመራርን ገንዘቡ ያደረገ፣ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የሚጠይቀውን ተቋም የኦሮሞ ጐሠኞች በጐሣ ኮታ እየቀየሩ የሚገኙበት ሁናቴ ግን እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ብሔራዊ መለያችን የሆነውን አየር መንገዳችንን በእነዚህ በጥላቻ ካበዱ ደናቁርት ለመታደግ ብርቱ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
እኔ አልገባ ያለኝ እነዚህ የጐሣ ፖለቲካ ቸርቻሪዎች ከኢትዮጵያ ሌላ አገር አላቸው ወይ? አገር የተመሠረተበትን መሠረት እየናዱ፣ ማዕዝናቱንም እያወላለቁ ከቶውንም ‹ሌላ› አገር መገንባት ይቻላል? እነዚህ በሥልጣንና በስግብግብነት ያበዱ ተረኛ ጐሠኞች የኦሮሞን ሕዝብ እንዴት ቢንቁት ነው ከቀረው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር በማለያየት ለተጨማሪ ጉዳት ሊዳርጉት የሚሯሯጡት? አገርንና ሕዝብን የመጥላት አስከፊ መጨረሻ እንዴት ከጌታቸው ወያኔ አይማሩም? ዛሬ ወያኔ ለትግራይ ሕዝብ ያተረፈው ምንድን ነው?
በትግራይ፣ በመተከል፣ በወለጋ፣ በኮንሶና በሌሎችም የኢትዮጵያ ግዛቶች የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ባስቸኳይ ይቁሙ!!! በሁሉም አካባቢ አደጋ የደረሰባቸው ወገኖቻችንን ፈጥነን እንርዳ!!!
እነ እስክንድርን ባስቸኳይ ልቀቁ!!! ነፃነት ለኅሊና እስረኞች!!!
ኦነግ ያገታቸው ልጃገረድ ተማሪዎች የሚገኙበትን ሁናቴ ለቤተሰቦቻቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሳውቁ፡፡
ሕወሓትን እና ኦነግን ሕገ ወጥ በማድረግና በአሸባሪነት በመፈረጅ የኢትዮጵያን የፖለቲካ መልክዐ ምድር አስተካክሉ፡፡ (የምርጫ ቦርድ የሕወሓት ሕጋዊ ሰውነትን መሠረዙ አንድ የሚያበረታታ ጉዳይ ሆኖ፣ በአሸባሪነት ሊፈረጅ ይገባዋል፤ ትጥቅ ይዞ አገርንና ሕዝብን እያሸበረ ያለው ኦነግም ላይ ባስቸኳይ ሕጋዊ ርምጃ ሊወሰድ ይገባል፡፡)