>

ሳቅና ለቅሶም በፈረቃ፤ የግፍ አዙሪት...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ሳቅና ለቅሶም በፈረቃ፤ የግፍ አዙሪት…!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

*… ትላንት አብረን አልቅሰን ቢሆን ኖሮ ዛሬ አብረን እንስቅ ነበር። ትላንት አብረን ስቀን ቢሆን ኖሮ ዛሬ አብረን እናለቅስ ነበር…!
 
አዎ ኢትዮጵያ ውስጥ መብራት እና ውሃ ብቻ ሳይሆን ሳቅና ለቅሶ፣ ሃዘን እና ፌሽታ፣ ስኬትና ውድቀት፣ ዝርፊያና መዘረፍ፣ ገፊና እና ተገፊነት፣ ሃብት ማካበት እና መቆርቆዝም፤ ባጭሩ ግፍ፣ ግፈኛነትና ተገፊነት በፈረቃ ናቸው። ትላንት ህውሃት የከፋ የሰብአዊ መብቶችን ሲጥስ የሚያለቅሱ ግፉሃን የነበሩትን ያህል፤ ሕውሃትን አበጀህ እያሉ ከበሮ ይደልቁ የነበሩ፣ ሕጻናት በግፍ ተገደሉ ስንል ባንክ ሊሰርቁ ሲሞክሩ ነው ይበላቸው ይሉ የነበሩ፣ በዜጎች መፈናቀል፣ መሰቃየት እና እንግልት ያተርፉና ይሳለቁ የነበሩ ሰዎች ነበሩ። ግፍ ይብቃ ብለን በአለም አደባባዮች ስንጮኽ እና ስንሰለፍ በማዶ ቆመው ይሳለቁ የነበሩ ሰዎች ዛሬ በአለም አቀፍ ተቋማት ደጃፍ በእኛ እግር ተተክተው ሜዳ ለሜዳ ሲንደባለሉ፣ በበረዶ እና ዝናብ ሲጉላሉ ሳይ ከልቤ አዘንኩ። ያዘንኩት ለነሱ ሳይሆን አገራችን የገባችበትን አረንቋ እና አዙሪት አስቤ ነው። ትላንት አብረን አልቅሰን ቢሆን ኖሮ ዛሬ አብረን እንስቅ ነበር። ትላንት አብረን ስቀን ቢሆን ኖሮ ዛሬ አብረን እናለቅስ ነበር ብዮ ክፉኛ ቆዘምኩ።
ኢትዮጵያን ጨምዶ የያዛት የግፍ አዙሪት በአሥርት አመታት ግፈኛና ግፉአንን ቦታ እያቀያየረ፤ አንዱ ሲስቅ ሌላውን ደም እያስነባና እያስለቀሰ፤ አንዱ ማቅ ሲለብስ ሌላው የክት ለብሶ እያሽካካ፤ የትላንት ግፈኞች የዛሬ ግፉአን፤ የዛሬ ግፏንን ደግሞ የነገ ግፈኞች እያደረገ መቀጠሉን ሳስብ የነገው ሁኔታችን ያስፈራኛል።
ግፍን ስለማንጠየፍ ስንገፋና ስንረገጥ የምንመኘው ተራችን ደርሶ ገፊ የምንሆንበትን ቀን ነው። በግፈኝነት እንቀናለን። በስርቆት እንቀናለን። በሥልጣን መባለግ እንቀናለን። ገፊ ስንሆን በኛ የሚቀኑ እንዲሁ ተራ ይጠብቃሉ። ግፍም፤ ግፈኝነትም በፈረቃ ይጎበኙናል። ግፍን የሚጠየፍ ማህበረሰብ ግን ግፈኝነትንም ሆነ ተገፊነትን አንዴ ወይም ከበዛ ሁሌቴ ቢጎበኙት ነው። ከዛ ጥሩ ትምህርት ስለሚወስድ ሁለቱንም ያነጥፋቸዋል። ገፊም፤ ተገፊም የሌለበትን ሥርዓት ይገነባል። ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል የሚሆንበትን፣ ሰዎች በሰውነታቸው ብቻ መብታቸው ተጠብቆ የሚኖሩበትን፣ አጥፊዎች በየትኛውም ጠርዝ ላይ ይቁሙ እኩል ተጠያቂ የሚሆኑበትን እና ማህበራዊ ፍትህን የተላበሰ፤ ሰው ሰው የሚሸት አገር እና የፖለቲካ ሥርዓትን ይገነባል። ብሶቶች በዘር፣ በኃይማኖት ወይም በሌላ መድሎ የሚመነዘርበት አገር ግፍን በፈረቃ ይቀበላል፣ ይሸኛል።
አዎ ዛሬ የህውሃት ደጋፊዎች በመላው አለም ብቻቸውን ሲጮኹ ሳይ ከልቤ አዘንኩ። ያዘንኩት ለእነሱ አይደለም ለአገራችን ነው። መቼ ነው ሳቃችንም፤ ክፌታችንም፣ ደስታችንም፣ ስኬታችንም በጋራ የሚሆነው ብዮ ከራሴ ጋር ሙግት ገጠምኩ። የሙስሊሙ ማህበረሰብ ሲገፋ እና ድምጻችን ይሰማ እያለ ሲጣራ ስንቶቻችን አብረን ቆመናል? የኦሮሞ ወጣቶች የኦነግ አባላት እየተባሉ በየማጎሪያ ቤቱ ሲሰቃዩ ስንቶቻችን አብረን ጮኸናል፣ የአማራ ወጣቶች ትምክህተኛና ነፍጠኛ እየተባሉ ከአገር ሲሳደዱና በየሜዳዊ ሲደፉ ስንቶቻችን አውግዘናል፣ የሱማሌ ክልል ሰዎች በአብዲ ኢሌ ማጎሪያቤት ከአውሬ ጋር ሲታሰሩ እና ሴቶቻቸው ሲደፈሩ ማን ድምጹን አሰምቷል፣ ጋምቤላ ውስጥ አኝዋኮች ሲጨፈጨፉ ማን ደርሶላቸዋል፤ እንዲህ እያልኩ አንዳችን በተገፊነት ሌላቸን በታዛቢነት ያሳለፍናቸውን መከራዎች መቁጠር ይቻላል።
ግፍ ቀኑን ቆጥሮ በየተራ ይጎበኘናል። እኔ ጋር አይደርስም ያልነው እሳት ሌላውን አቃጥሎ ሲጨርስ እኛን መለብለብ ይጀምራል። እኛ ግን ዛሬም ለመማር ልቦናችንም ሆነ አይምሯችን የተከፈተ አይመስለኝም። ዛሬም የአንዱ ቁስል ለሌሎቻችን ምንም ነው። ዛሬም የአንዱ የስቃይና የጣር ድምጽ ላንዳንዶቻችን ሙዚቃ ነው። ትላንት የአንዳችን ስቃይ የሌላው የጥንካሬ መገለጫ መስሎ ይታይ እንደነበር ሁሉ። እንደ ሕዝብ መክሸፋችን ሁሌም ግፈኞች እንዲበረቱ እድል ይፈጥራል። እንደ ሕዝብ ግፍን ተጠያፊዎች አለመሆናችን አገራችንን ግፍ የማይነጥፍባት፤ የግፍ ቋት አድርጓታል።
ያ አዙሪት ዛሬም ቀጥሏል። ትላንት ዜጎችን ከመሬታቸው፣ ከቤታቸው፣ ከሥራቸው፣ ከቀያቸው ያፈናቅሉ የነበሩ ሰዎች ዛሬ ተፈናቃ ሆነው ሳይ ያመኛል። ትላንት ብህውሃት ካድሬዎች ጫማ ስር ወድቀው ሲሽቆጠቆጡ የነበሩ እና ተላላኪ ሆነው የገዛ ሕዝባቸውን ሳይቀር ሲያሰቃዩ የነበሩ ሰዎች ዛሬ ያንን የህውሃት ጫማ ሲለኩ ሳይ ነጋችን ያሰፈራኛል። ግፈኞች የግፈኛውን ጫማ መለካት ሲጀምሩ የዙሩን አቅጣጫ ወዴት እንደሚሔድ ይገባሃል። አዎ ትላንት የተገፉ ሰዎች የገፊዎቹን ጫማ እየለኩ ለመሆኑ አንድ ሺ አንድ ምሳሌ ላቀርብ እችላለሁ። ሕውሃት የደርግን ጫማ ከመለካት አልፋ ተጫማችው። ውድቀቷም ያው ከደርግ የከፋ ሆነ። ዛሬ የህውሃትን ጫማ የምትለኩ ሰዎች ከህውሃት የከፋ ነገር ሊጠብቃችሁ እንደሚችል የተረዳችው አይመስለኝም። የግፍ ተግባር ግፉአኑን ክፉኛ ቢጎዳና ቢያስለቅስም መጨረሻው ግን ግፈኛውንም ነው ይዞ የሚጠፋው። የአለም ታሪክም የሚያሳየው ይሄንኑ ነው።
ትግራይ ላይ ጦርነቱን ተከትሎ የተከሰተው አስከፊ የሆነ ሰብአዊ ቀውስ አብዛኛውን ሰው ክፉኛ ያሳስበዋል። ይህ ግፍ ትላንት ከሕውሃት ጎን በቆሞ የወያኔ ጀሌዎች መነገሩ ግፍነቱን አያስቀረውም። ዛሬም በእውነተኝነት እና በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርተው ትግራይ ክልል ውስጥ ያለውን ችግር ከሚገልጹ ወገኖቻችን ጋር አብረን ልንቆም ይገባል። የዛኑ ያህል ከግፍ ተግባር አትራፊ ሆነው የዜጎችን ችግር ለፖለቲካ ግባቸው ሊጠቀሙ የሚፈልጉ የሕውሃት ካድሬዎችን ልክ እንደ ትላንቱ ልንጠየፋቸው ይገባል።
ግፍን እንጠየፍ፣ አዙሪቱን እናስቁም፣ ከግፏን ጎን እንቁም፣ ግፈኞችን ለፍርድ እንዲቀርቡ እንታገል። ያኔ ሳቅና ደስታችንም ሆነ ሃዘንም ከመጣ በጋራ እናስተናግደዋለን። የአንዳችን መከራ የሁላችንም ስለሚሆን እዳው ገብስ ይሆናል። የአንዳችን ስኬትም እንዲሁ የሁላችንም ሃሴት ይሆናል።
አብረን የምንስቅበትን ቀን ያምጣልን!
Filed in: Amharic