>

ዐብይ አሕመድና የኦሮሞ ልዩ ኃይል (መስፍን አረጋ)

ዐብይ አሕመድና የኦሮሞ ልዩ ኃይል

 

መስፍን አረጋ


የዐበይ አሕመድ አካሄድ በገሃድ የሚያመለክተው መዳረሻው በጦቢያ ፍስራሽ ላይ የኦሮሞ አጼጌ (Oromo empire) መመሥረት ነው፡፡  ወደዚህ መዳረሻው በፍጥነት ለመድረስ ደግሞ  የኦሮሙማ፣ በኦሮሙማ፣ ለኦሮሙማ የሆነ ግዙፍ ሠራዊት ያስፈልገዋል፡፡

በስሙ የጦቢያ መከላከያ የሚባለውን ሠራዊት፣ በግብሩ ግን በራሱ ባብይ አሕመድ ጠቅላይ አዛዥነት፣ በብርሃኑ ጁላ ኢታማዦር ሹምነት፣ በቀንዓ ያደታ መከላከያ ሚኒስትርነት፣ በይልማ መርዳሳ አየር ኃይል አዛዥነት … ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የኦሮሙማ ሠራዊት አድርጎ፣ የኦሮሙማን አጀንዳ እንዲያስፈጽም በመላ ጦቢያ ላይ አሰማርቶታል፡፡ 

የኦሮሙማ መከላከያ ሠራዊት ስለተመሠረተ ደግሞ፣ የሚቀረው በመላው ጦቢያ ላይ የሚሠማራ፣ የኦሮሙማን ሕግ የሚያስከብር የኦሮሙማ የፖሊስ ሠራዊት ነው፡፡  ለዚህ የታጨው ደግሞ የኦሮሙያ ልዩ ኃይል ነው፡፡  

የትግራይ (የወያኔ) ልዩ ኃይል ሙሉ በሙሉ ፈራርሷል፡፡  ያማራ ልዩ ኃይል ደግሞ ከኤርትራ ሠራዊት ጋር እኩል ተኮንኖ በዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲጠረጠር ለማድረግ፣ ዐብይ አህመድ ባሜሪቃ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባንቶኒ ብሊንከን (Antony Blinken) አማካኝነት “ከትግራይ” ባፋጣኝ ለቆ ይውጣ የሚል መግለጫ አውጥቷል፡፡  ከዚህ መግለጫ በኋላ የሚከተለው ደግሞ ያማራ ልዩ ኃይልን በዘር ማጥፋት ወንጀል አስከስሶ፣ “ዘር አጥፊወችን እያደኑ የሚያጠፉት የሰው ዘር ጠበቃወቹ” አሜሪቃ፣ እንግሊዝና ፈረንሳይ ተረባርበው ድምጥማጡን እንዲያጠፉት ማድረግ ብቻና ብቻ ነው፡፡  

የኦሮምያ ልዩ ኃይል በተከታታይ ዞሮች እየሰለጠነ መጠናከሩን ይቀጥልና፣ ልክ እንደ ትግራይ ልዩ ኃይል ያማራ ልዩ ኃይል ድምጥማጡ ሲጠፋ፣ ስሙን ወዲያውኑ ቀይሮ በመላ አገሪቱ ላይ የኦሮሙማን ሕግ የሚያስከብር፣ ምናልባትም ነፍጠኛን በቁማር “በሰበረው” በቁማርተኛው በሽመልስ አብዲሳ ጠቅላይ አዛዥነት የሚመራ የኦሮሙማ ፖሊስ ሠራዊት ይሆናል፡፡

የኦሮሙማ ፖሊስ የኦሮሙማን ሕግ ለማስከበር በመላ ጦቢያ ላይ ሲሰማራ፣ ጦቢያ “ከኦሮምያ ትወጣለች” (Ethiopia out of Oromia)፣ የኦሮሞ አጼጌ (Oromo Empire) ደግሞ በይፋ ይታወጃል፡፡  

ዐብይ አሕመድ ደግሞ በቅሎ መቀመጥን ካበሾች ተምሮ ጃናሞራን ከፈጃት “ምስሌ” ከሚባለው አምስተኛው ሉባ፣ እንዲሁም ላኮምልዛን (ወሎን)፣ ሸዋን፣ ጎዣምን፣ ደምቢያን … በመጨፍጨፍ “ድኾች ሁሉ የሚበለጽጉባቸውን ምድሮች” ምድረበዳ ካደረጉት፣ በተጨማሪም “ባሕር የሚለብሱትን ሲዳማዎች ባሕር ከጨመሯቸው”  ሐርሙፋ ከሚባሉት ከሜልባ ልጆች ቀጥሎ፣ ድፍን ጦቢያን ኦሮሞ ያደረገ ሰባተኛውና የመጨረሻው ሉባ ይሆናል፡፡

ባለመታደል ያገራችን የጦቢያ ጠላቶች ከጊዜ ወደጊዜ የሚሄዱት እየከፉና እየከፉ ነው፡፡  ደርግን ስናማርር ወያኔ መጣ፡፡  ወያኔን ስናማርር ኦሮሙማ ተተካ፡፡  በርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ግን ዐብይ አህመድን የመሰለ ሳይታጠቅ የሚገድል ጠላት አገራችን ጦቢያ መቸም አይታ አታውቅም፣ ወደፊትም የምታይ አይመስለኝም፣ ለዚያውም ደግሞ ዐብይ አህመድ ገድሎ፣ መቸም ስሟ እንዳይነሳ ሶፍ ኡመር ዋሻ ውስጥ ለሃቹ ሳይቀብራት በፊት በሆነ ታምር ከተረፈች፡፡ 

 

አማራና ትግሬ በጥቅል ሐበሻ

ርስበርስ ተዳምተህ በምክኒያት ተልካሻ

ስትዳከምለት በስተመጨረሻ፣

ሥጋህን በጫጭቆ የኦነጉ ውሻ

ለሃች ይቀብርሃል እሶፍ ኡመር ዋሻ፡

 

Mesfin Arega

mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic