>

ሀሳብ አልባ ወንበሮች...!!! (ዮሀንስ መኮንን)

ሀሳብ አልባ ወንበሮች…!!!

ዮሀንስ መኮንን

*….በተደጋጋሚ እንደገለጽነው ብልጽግና ከሀሳብ ክርክር ሲሸሽ የመጀመሪያው አይደለም። “እመጣለሁ” ብሎ ይቀራል። “ቀኑ ይቀየርልኝ” ብሎ ቀኑ ተቀይሮለት ይቀራል። ታዛቢዎች እና ባለሙያዎች በሚታደሙበት “አልከራከርም” ይላል፣ በቀጥታ ስርጭት በሚተላለፍ ክርክር ለመሳተፍ አሻፈረኝ ይላል። ለእኔ ከሌሎቹ ተጨማሪ ሰአት ይጨመርልኝ፣ ሌሎቹ አንድ አንድ አባል ሲወክሉ እኔ ብቻ ሁለት ተከራካሪ ይፈቀድልኝ ብሎ ችክ ይላል… ሰበቡ ማለቂያ የለውም…!
ዛሬ ኢቲቪ (EBC) አምስት ፓርቲዎችን በመጋበዝ በባህል እና ቱሪዝም ላይ የምርጫ ክርክር ለማድረግ ቀጠሮ ነበረን። አራት ፓርቲዎች (ኢዜማ፣ እናት፣ አብን፣ ነጻነት እና እኩልነት) በቀጠሮአችን ሰአት ኢቲቪ ስቱዲዮ ተገኝተን ነበር። እኔ እና ዶ/ር ሙሉዓለም ኤዜማን ወክለን ቀድመን ተገኘን። ሀሳብ አልባው ብልጽግና ፓርቲ ግን ቢጠበቅ ቢጠበቅ የውኃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል።
የአራቱ ፓርቲዎች ተወካዮች ይህ የብልጽግና ተደጋጋሚ ነውር ተቀባይነት እንደሌለው እና ብልጽግና ቀረ ተብሎ ክርክሩ ከሚሰረዝ የመጣነው ፓርቲዎች ክርክራችንን መቀጠል አለብን የሚል አቋም ያዝን። ኢቲቪ ግን ጌቶቹን በመፍራት “ብልጽግና በሌለበት ክርክሩ አይካሄድም” አለ።
(በነገራችን ላይ ኢቲቪ ራሱ ከዚህ ቀደም አብን ፓርቲ በሌለበት ሌሎች ፓርቲዎችን ያከራከረ ሲሆን ፋና ቲቪ ደግሞ በተመሳሳይ ርእስ ትናንት ባዘጋጀው ክርክር እናት ፓርቲ በሌለበት አከራክሯል)
ከአንድ ሰአት በላይ ተጨቃጭቀን ኢቲቪ ሀሳቡን እንደማይቀይር ስንረዳ ከኢዜማ የተወከልነው እኔ እና ዶ/ር ሙሉዓለም ለመጡት ፓርቲዎች አንድ ሀሳብ አቀረብን። “ስቱዲዮ ውስጥ ገብተን በየቦታችን እንቀመጥ የሀሳብ አልባው የብልጽግና ወንበሮች ለታሪክ ባዶ ሆነው ፎቶ እንነሳ” አልን። ፓርቲዎቹ ተስማሙ። እነሆ ይህንን ፎቶ አስቀረን።
እውቁ ደራሲ በዓሉ ግርማ “ከአድር ባይ ብዕር ባዶ ወረቀት ብዙ ይናገራል” እንዲል እኔ ደግሞ “ከካድሬ ጭንቅላት ባዶ ወንበሮች ሀሳብ አላቸው” እላለሁ።
Filed in: Amharic