>

የዛሬዋ ኢትዮጵያና የነገ ውሎዋ! (በአንዱ ዓለም ተፈራ)

የዛሬዋ ኢትዮጵያና የነገ ውሎዋ!

ነፃ አስተያየት፤    አንዱ ዓለም ተፈራ

(ክፍል ፩)


በጠባብ የዛሬ ጥቅምና ስኬት የተሸፈነ ዓይን፤ ነገ የሚጠብቀውን ገደል መመልከት ይራባል።

አንድ አገር እንድትመሠረትና አገር ሆና እንድትቀጥል፤ ብዙ የታሪክ ሁኔታዎች መገጣጠምና መሳካት አለባቸው። ይህ ደግሞ ብዙ ዘመን የሚወስድ ክስተት ነው። በአንፃሩ አንድን አገር ለማፈራረስ፤ አውቀው ሆን ብለው የተነሱት፤ በጉልበትና በተንኮል! ወይንም ሳያውቁት በተለያየ ጠባብና ጥቃቅን የጥቅም ስሌት ተመርኩዘው ለተነሱት፤ በድንቁርና ሊከናወን ይችላል። ለዛሬዋ ኢትዮጵያ ችን፤ የኒህ ሁለቱ መንገዶች መንትያ ሀቅ ከፊታችን ተደቅኗል። ልትቀጥል ነው ወይንስ ልትፈርስ! ዝም ብሎ “ኢትዮጵያ አትፈርስም!” ማለት፤ መደረግ ያለበትን ዝግጅት ዘንግቶ፤ ለማያውቁት ኃይል ኃላፊነትን መዳረግ ነው። ውጤቱ ሲያምር፤ “አላልኳችሁም!” ለማለት። ውጤቱ ሳያምር ደግሞ አንገትን ለመድፋትና ለመደበቅ ነው። ውጤቱ ምንም ሆነ ምንም፤ የራሳችንን ኃላፊነት ሳንወጣ ለሌሎች አሳልፈን በሠጠነው ጉዳይ፤ የዉጤቱ ባለቤትና ወሳኝ ልንሆን አንችልም። የአገራችን የነገ ውሎዋ አስተማማኝ አይደለም። ማየት ተስኖን፤ ከተጨባጩ እውነታ ርቀን፤ በራሳችን የግል ጥቅም ላይ ባተኮርን ቁጥር፤ ትልቁ ዕይታ ካይናችን ይሰወራል። እንኳንስ የነገውን ሀቅ ይቅርና፤ ዛሬ እግራችን የሚረግጥበትን መሬት ማየት ይሳነናል። የአገር ሕልውና የሚጠበቀው፤ ትክክለኛ ሕገ-መንግሥት ኖሮ፣ ሕዝቡ አመኔታውን በሕግና ስነ ሥርዓት ላይ አሳድሮ፣ በሥልጣን ላይ የሚቀመጡት ኃላፊዎች፤ እንደሌላው ግለሰብ ለሕጉና ስነ ሥርዓቱ ተገዝተው ሲገኙ ነው። ይህን መሠረት አድርጎ ነው፤ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ያለውን ሀቅ ይህ ጽሑፍ የሚፈትሸው።

ታሪክ፤ ሰዎች ፈልገው በተለሙት መንገድ የሚወርድ ፈሰስ ሳይሆን፤ ከሰዎች ፍላጎትና ስሌት ውጪ፤ በቦታው ላይ ባለው ሀቅ የሚነዳ ጎርፍ ነው። አገር፤ ሆን ብለው ሊያፈርሷት በተነሱ ወይንም ሳያውቁት፤ ዓይኖቻቸው የአገር ዜግነት ምንነትንና የአገር ትልቅነት ላይ ማተኮር ያለበትን በዘነጉት ልትፈራርስ ትችላለች። በመጀመሪያው መንገድ፤ ምስሌ ቢጠቀስ፤ ከውጪ የመጣ ጠላት የሚያካሂደው ወረራ ነው። ይህ በታሪካችን በተደጋጋሚ ተከስቷል። የጣሊያን መንግሥት፤ የቱርክና የግብፅ መንግሥታት፤ የድርቡሽ ወራሪዎች፣ የሶማሊያ ተስፋፊዎች የሚጠቀሱ ናቸው። በሁለተኛው መንገድ ደግሞ፤ የእንግሊዝ ወራሪ ኃይል በናፒየር እየተመራ በመጣ ጊዜ መንገድ በመሩትና፤ በጣሊያን ወረራ ጊዜ ባንዳ ሆነው ባገለገሉት ተተግብሯል። በሁለቱም መንገድ የተቃጣብንን ጥቃት፤ ውድ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ተከላክለውና አክሽፈው፤ አገራችንን ለኛ እንድትቆይ አድርገውልናል።

አገርን አገር ሆና እንድትቀጥል፤ ሰላም በአገር እንዲኖርና ሕዝቡ ለልማት እንዲሰማራ፤ መሠረቱ ትክክለኛ ሕገ-መንግሥት ነው። ይህ፤ የአገራችን ዋናው ገዥ ሰነድ ነው። የባለሥልጣናትም ተግባርና ኃላፊነት የተወሰነው በዚሁ ሰነድ ነው። ይህ ሰነድ፤ ያለ አማራጭና ያለ ማወላወል ሕዝቡ የኔ ብሎ የተቀበለውና ያመነበት መሆን አለበት። የዚህ ሰነድ ምንጭና አዘገጃጀት፤ ለተቀባይነቱም ሆነ ለተግባራዊነቱ ወሳኝ ነው። የሕገ-መንግሥት መኖር ብቻውን በራሱ በቂ አይደለም። ሕገ-መንግሥቱ ትክክለኛ ሲሆን ነው ገዢ የሚሆነው። ባሁኑ ሰዓት ባገራችን ላይ ያለው ሕገ-መንግሥት፤ ምንጩም ሆነ አዘገጃጀቱ ኢትዮጵያዊነትን ያቀፈ አይደለም። እናም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ፤ አትከፋፍሉን! በያለንበት ሁላችንም እኩል ኢትዮጵያዊያን ነን! ዘርና ሃይማኖትን መሠረት አድርጎ የተነሳ ሂደት ያፋጀናል! ታሪካችን ይሄን አይፈቅድም! በማለት ሰላማዊ ሰልፍ አድርጓል። ለዚህም ከፍተኛ መስዋዕት ከፍሏል። አሁን በአገራችን ለተከሰቱት ብዙዎቹ ችግሮቻችን መንስዔው ይሄው ሕገ-መንግሥት ነው። መነሻው ይሄ ሆኖ፤ ከዚህ መንጭተው አገራችንን በማተራመስ ላይ ያሉ ብዙ ጉዳዮች አሉ።

ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያዊያንን ሲገድሉ፣ በትክክል መግለጥ በማይቻል አረመኔነት ሲጨፈጨፉ፣ ቤት ንብረት፣ ሰፈር መንደር ትርጉም አጥተው ሕይወትን ለማትረፍ ሩጫ ሲያቸንፋቸው፣ መኖር ማለት በፍርሃትና በድንጋጤ ተከቦ መደንበር ሲሆን፣ እኛ ማነን? አገራችንስ ምንድን ነች? ይሄ በአንድ ምሽት የተከሰተ ጉዳይ አይደለም። ብዙ የታሰበበትና በዕቅድ የተተገበረ እውነታ ነው። እናም በደንብ መመርመርና መጠናት አለበት። ኢትዮጵያ ለኛ የደረሰችን፤ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በየዘመናቸው በከፈሉት ሕይወት ነው። የኛ ዘመን ኃላፊነት፤ ኢትዮጵያን ለነገ ኢትዮጵያዊያን ከተቀበልንበት አሳምረን ማሳደር ነው። በአገር መኖር ማለት ለግል፤ ዛሬ ብቻ ሆድን ሞልቶ ወደ መኝታ መሄድ ማለት አይደለም። በአገር ላይ ካሉ ሰዎች ጋር የጋራ ኃላፊነት አለብን። “አባት የሞተ ዕለት ባገር ይለቀሳል። እናት የሞተች ዕለት ባገር ይለቀሳል። አገር የሞተ ዕለት ወዴት ይደረሳል!” የተባለው የአገርን ቦታ በግልጥ ለማሳየት ነው።

እንግዲህ አሁን ላለንበት ሀቅ ተጠያቂው ማነው? መነሻው ይሄን ተጠያቂ ለይቶ ማወቁ ነው! አማራ ነህ፣ ወላይታ ነህ፣ ዶርዜ ነህ፣ አኙዋክ ነህ፣ ተብሎ አንድ ኢትዮጵያዊ ከታረደ፤ አገራችን ወደ የት እየሄደች እንደሆነ መገመቱ ከባድ አይደለም። ይህ የልብ ወለድ ትረካ አይደለም። እውነት፣ ታሪክ፣ ምንነትና አገር ትርጉማቸው ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። በፈጠራ የተመላ ታሪክ በሥልጣን ጥመኞች ተለፎ፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በጠሉ ባለሥልጣናት ሕገ-መንግሥቱ ረቆና ጸድቆ፣ ይሄን ያልተቀበለ ጠላት ተብሎ ተፈርጆ፤ ነገ ኢትዮጵያ ትኖራለች ብሎ መመኘት አጉል ነው! ይህ ያለንበት የፖለቲካ ሀቅ ነው። ይሄን ያለንበትን የፖለቲካ ሀቅ በግልጥና በትክክል መናገር ካልቻልን፤ እየኖርን አይደለም! ይሄን መናገር ታሪካዊ፣ ኢትዮጵያዊና ትውልዳዊ ግዴታ አለብን። ባንዳ ሰባራ ጠርሙስ በከሰከሰበት መንገድ ባዶ እግራቸውን ተጉዘው ፋሽስቱን እንደተጋፈጡት ቀደምቶቻችን ባንበረታም፤ በያለንበት በአገራችን በተጨባጭ ያለውን ሀቅ በትክክል መናገሩ፤ በጣም ቀላሉ ኃላፊነት ነው። በርግጥ መናገሩ ብቻ በቂ አይደለም! በደልን መዘርዘሩ በዳዩን ከመበደል አያቆመውም። ተበዳይ በቃኝ ብሎ መነሳት አለበት። ያ ብቻ ነው መፍትሔ የሚያመጣው። አትበድሉኝ ብሎ መነሳት ወንጀል ሳይሆን፤ የተፈጥሮ ግዴታ ነው።

አገራችን በተፈጥሮ የታደለች ነች። ብዙ የተጠራቀመ ንብረት አላት። ከነኚህ ዋናውና አውታሩ ሕዝቧ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ነው። ፍላጎቱ በሰላም ውሎ መግባቱ፣ እርሻው መሳካቱ፣ ገበያው መድራቱና አብሮ መኖሩ ነው። ታዲያ ይኼ በምኞትና ቁጭ ብሎ በማየት የሚሳካ ሳይሆን፤ ሁልጊዜም ነቅተው የሚጠብቁትና የሚቆሙለት መሆን አለበት። ለዚህ ደግሞ በሥልጣን ላይ ያሉት ብቻ ሳይሆኑ፤ እያንዳንዳችን የግዴታ መቆም አለብን። ጥቃቅን ልዩነቶች ወሰን አላቸው። የኢትዮጵያዊያን አደጋ ላይ መውደቅና የአገር ሕልውና ከፊታችን ሲገረጥ፤ አንድነት መነሳት አማራጭ የለውም። ምርጫው ሆነ የየቡድን ፖለቲካው፣ የአባይ ግድብ ሆነ የግብጥ መንደፋደፍ፣ የዚህ ጉዳይ ንዑስ አካላት ተደርገው መወሰድ አለባቸው። ኢትዮጵያዊያን እያለቁ ነው! መጀመሪያ ኢትዮጵያዊያን ሆነን፣ በሕገ-መንግሥቱ ተከብረን ስንገኝ ነው ምርጫ ትርጉም የሚሠጠው። ምርጫን ማድረግ የያዙትን ሥልጣን ሕጋዊ ለማድረግ ከሆነ፤ እስከዛሬ በታሪካችን ብዙ ምርጫዎች ተደርገዋል። ትክክለኛ ግን አንዳቸውም አልነበሩም።

በሥልጣን ላይ ያለ አካል፤ በሥልጣኑ ላይ ለመቆየት፤ የሚቀምመው ተንኮል፤ አገርን ሊያፈርስ ይችላል። “ሥልጣን ያባልጋል። ፍጹም ሥልጣን ደግሞ፤ ፍጹም ጠቅልሎ ያባልጋል!” ይባላል። ሹሞች በሥልጣን ላይ የተቀመጡት፤ አገራቸውን ለማገልገል እንጂ፤ ራሳቸውን ለማበልጠግና የግል ዓላማቸውን ለማራመድ አይደለም። ያ ሲሆን አገር አደጋ ላይ ትወድቃለች። ሥልጣንን እና ጉልበትን የተማመነ ክፍል፤ ከሕዝብ ኃላፊነት ይወጣል። ባለሥልጣናት እውነትን ክደው፣ በራሳቸው እብሪት ተመርኩዘው፣ ጉልበታቸውን ተማምነው፣ በሥልጣን ላይ ለመቆየት፤ ሕዝቡን ሰርዘው፣ ራሳቸውን የአገራችን የኢትዮጵያ ብቸኛ ወካይ አድርገው ያቀረቡ ጊዜ፤ የአገራችን የወደፊት ዕጣ አደጋ ላይ ይወድቃል። በሥልጣን ላይ ያለ አካል፤ ከራሱ ድርጊት ሌላ፤ ሌሎችን አሰባስቦ፣ ከመንግሥት ውጪ ያሉ ሕገ-ወጥ አካላት የሚያካሂዱት ድርጊት በማስመሰል ሕዝባዊ በደልን ሲፈጸም፤ የአገር ሕልውና አደጋ ላይ ይወድቃል።

አሁን በአገራችን በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው አማራውን በያለበት መጨፍጨፍ ወዴት ይወስደናል? መላ ኢትዮጵያዊያን ምን ማድረግ ይገባናል? የሰብዓዊ መብት ጠባቂዎች በየጊዜው ዋጋ እየከፈሉ ይሄንን ዘግበዋል። የአማራ ወጣቶች ባደባባይ ይህ እንዲታወቅ ጮኸዋል። አሁንም ከፍተኛ ዋጋ በመክፈል ላይ ናቸው? ይሄንን በአማራው ላይ እያደረሰ ያለው ክፍል፤ ሌሎች ይከተላሉ እያለ ነው። ይህ ክፍል ፀረ-ኢትዮጵያዊያን እና ፀረ-ኢትዮጵያ ነው። በዚህ ክፍል የሚጠቃለሉት የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርና ኦነግ ሸኔ ብቻ አይደሉም። ከግለሰብ እስከተደራጀ አካል ድረስ አቅደው የተንቀሳቀሱበት የፖለቲካ ስሌት ነው። ይሄንን መረዳት አለብን።

ኢትዮጵያ በልጆቿ አንድነቷ ተጠብቆ፣ ዛሬም ወደፊትም ትከበራለች።

ክፍል ፪ ይቀጥላል።

Filed in: Amharic