>

የ ህወሀት የክህደት ጥግ...!!! በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን)

የ ህወሀት የክህደት ጥግ…!!!

በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን)


*… የቀድሞ የህወሓት ነባር ታጋይ አይተ ገብረመድህን አርአያ በአንድ ወቅት ስለ ጌታቸው አሰፋ ተጠይቀው ሲመልሱ… ጌታቸው ደስታው የሚመነጨው ከሰው ልጆች ስቃይና መከራ ነው ። በጭካኔያዊ ድርጊት የሚደሰት SADIST ነው ። ከቀድሞው የወያኔ የደህንነት ኃላፊ ጋር በመሆን ብዙ ሰላማዊ ሰዎችን የጨረሰ ወንጀለኛ ነው። ከመነሻው አንስቶ እጁ በንፁሀን ደም የጨቀየ ነው ። የህወሓት መሪዎች በትግራይ ሕዝብ መካከል የበቀሉ አረሞች እንጅ ከትግራይ ሕዝብ አብራክ የወጡ አይደለም

የካቲት 11 ቀን ፣ 1967 ዓ ም በ11 ሰዎች በምዕራብ ትግራይ ቆላ በሽሬ አውራጃ ልዩ ስሙ ደደቢት በተባለ ስፍራ የተመሰረተው እና የቀዳማይ ወያኔ ቅርሻ የሆነው “ ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ “ / ተሓህት / ወደ አማርኛ ሲመለስ የትግራይ ሕዝብ አርነት ግንባር ፤ የዛሬው አሸባሪው ህወሓት ስንክሳር ሲገለጥ ደምቀው ከሚታዩት ባህሪዎቹ ውስጥ አሪዎስነት፣ ክህደት፣ ሴረኝነትና እስስታዊነት ይገኙበታል ። ስለከሀዲነቱ ፣ ሴረኝነቱ ፣ መርህ አልባነቱ ስለሚገለጥበት እስስታዊነቱ በዚሁ ጋዜጣ በተደጋጋሚ ስለጻፍሁበት የዛሬው መጣጥፌ ትኩረት በአሪዎስነቱ ፣ በአረመኔነቱ፣ በጨካኝነቱ ፣ በጭራቅነቱ/በቡልቡልነቱ/ላይ ነው ። አሸባሪው ህወሓት ርህራሄና ሰብዓዊነት የሚባል ነገር ያልፈጠረበት ጨካኝ አረመኔ ነው ። የጭካኔው ጥግ የሰው ልጅ ይፈጽመዋል ተብሎ የማይታመን ነው ። በተለይ በአቦይ ስብሀትና በመለስ የሚዘወረው ቡድን የፖለቲካና የወታደራዊ ትርፍ እስካስገኘለት ድረስ ምንም ከማድረግ አይመለስም ። ይህ በላኤ ሰብነቱ ዛሬ ወይም ትላንት የተጀመረ ሳይሆን አብሮት ያደገና ጥርሱን የነቀለበት ነው ። በዚያ ሰሞን ለንባብ የበቃው የጋዜጠኛ አርዓያ ተስፋማርያም ፣ “ከህወሓት ጓዳ”ይሄን ማንነቱን ፍንትው አድርጎ ያሳያል ።

አሸባሪው ህወሓት ገና ከጅምሩ በአቋምና በአመለካከት የተለዩትን ፤ ለስልጣኔ ያስገኛል ያላቸውን እንደ ድመት እየበላ ያደገ ጨካኝ አረመኔ ነው ። እነ ገሠሠው አየለ/ስሁል/ ፣ ዩሐንስ ገብረመድህን/ዋልታ/ ፣ ዘርኡ ገሰሰ/አግአዚ/ እና ሌሎች በሴራ ገድሎ በመቃብራቸው የተረማመደ አሪዎስ ነው ። በተለይ በትግራይ ክልል ፊውዳል ብሎ የፈረጃቸውን ከ40ሺህ በላይ ትግራዋይን ደመ ከልብ አድርጎ ያስቀረ ጭራቅ ነው። አምነውት ለድርድርና ለእርቅ የቀረቡትን በውድቅት ሌሊት በተኙበት የጨፈጨፈ አውሬ ነው ። በትግራይና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ባቋቋማቸው ዘግናኝ ከምድር በታች እስር ቤቶች “ሀለዋ ወያኔ” ወይም “ባዶ ስድስት” ያለቁ ኢትዮጵያውያንን ብዛትማ ቤቱ ይቁጠረው ። ከ1971/72 አንስቶ በወልቃይት ፣ በጠገዴና በጸለምት አማሮች ላይ የተፈጸመ ግፍ ለመስማት ይሰቀጥጣል፤ ለማየት ይዘገንናል ። ማንነታችን የአባቶቻችን ሀገር ርዕስት ይከበር ባሉ በግፍ ተገድለዋል። ተሰቃይተዋል ። በጅምላ ተግዘዋል። ተሰደዋል። ጭው ባለ በርሀ በተሰሩ የምድር ቤት እስር ቤቶች ወገን በወገኑ ላይ ይፈጽመዋል ተብሎ ለማሰብ በሚከብድ ህልቆ መሳፍርት የሌለው ግፍ ተፈጽሞባቸዋል ። በቁማቸው ተቀብረው ከብት ተነድቶባቸዋል ። እስከ አንገታቸው ተቀብረው ራሳቸው ላይ ጨው ተነስንሶ ከብት እንዲልሳቸው ተደርጓል ። እነሱን ገለውና አስረው ሚስቶቻቸውን ልጅ በማስወለድ ዘር ለማጽዳት ጥረዋል ። በማንነቱ እንዲሸማቀቅ በገዛ ሀገሩ ሁለተኛ ዜጋ እንዲሆን ተደርጓል ። ዜጎችን ኦነግ በሚል የፈጠራ ክስ ፈርጆ ለማሰር የደህንነት መዋቅሩን ተጠቅሞ በፒያሳው ትግራይ ሆቴል ፣ በሚኒባስና ሕዝብ በሚሰበሰብበት አደባባይ ፈንጂ የሚያፈነዳና ንጹሐንን የሚፈጅ እፉኝት ነው።

የቀድሞ የህወሓት ነባር ታጋይ አይተ ገብረመድህን አርአያ በአንድ ወቅት ከ” ኢትዮጲስ “ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ስለ ጌታቸው አሰፋ ተጠይቀው “…ጌታቸው ስለ ፈፀመው ግፍና ያጠፋው የንፁሀን ነፍስ ላይ በግልፅ ጥናት ቢደረግ ፤ …ከሂትለር ባለሟሎች ተርታ የሚሰለፍ ነው ። በአንድ ወቅት ከፍየል ውሃ ሁለት ገበሬዎችን አፍኖ ወደ ሀዋላ ወያኔ አስገባቸዋለሁ ብሎ መንገድ ላይ ገሎ ጥሏቸው አስከሬናቸው በጅብ ተበልቶ የራስ ቅላቸው ወድቆ ተገኝቷል ። የጌታቸው አሰፋ ደስታ የሚመነጨው ከሰው ልጆች ስቃይና መከራ ነው ። በጭካኔያዊ ድርጊት የሚደሰት SADIST ነው ። ከቀድሞው የወያኔ የደህንነት ኃላፊ ጋር በመሆን ብዙ ሰላማዊ ሰዎችን የጨረሰ ወንጀለኛ ነው። ከመነሻው አንስቶ እጁ በንፁሀን ደም የጨቀየ ነው ። የህወሓት መሪዎች በትግራይ ሕዝብ መካከል የበቀሉ አረሞች እንጅ ከትግራይ ሕዝብ አብራክ የወጡ አይደለም ።

ህወሓት ፀረ ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን ፤ ፀረ ትግራይም ነው ።… ይላሉ ። ዛሬ አሸባሪው ህወሓት ሸለቆ ለሸለቆ እየተሽሎከለከ የሚፈጽመው ግፍ አብሮት ያደገ እንጂ ዛሬ የተጀመረ አይደለም ። ስለጌታቸው አሰፋ አረመኔያዊ ማንነት የተገለጸው የአሸባሪው ህወሓት መገለጫ ነው ። ይህ ክፉ መንፈስ በዛሬው የአሸባሪው ህወሓት ርዝራዥ የሰራ አካላት ተሰራጭቶና ተዋህዱ ያለ በመሆኑ ዛሬም ትግራዋይ ታፍነው እየተወሰዱና እየተገደሉ የጅብ ሲሳይ እየሆኑ ነው ። ሕዝባቸውን በዚህ ክፉ ቀን ማገልገላቸው እንደ ወንጀል ተቆጥሩ ሰሞኑን የጊዜያዊ አስተዳደሩ አንድ ከፍተኛ የስራ መሪ በግፍ መገደላቸው ሳያንስ አስከሬናቸው እንኳ አፈር ተነፍጎ አውሬ በልቶታል ። በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ የሚገኙ የጊዜያዊ አስተዳደሩ በርካታ አመራሮች በዚሁ አሸባሪ ርዝራዦች ተገድለዋል። ሰሞኑን ደግሞ ስፔናዊ የድንበር የለሽ የሀኪሞች ድርጅት ከእነ ሁለት ኢትዮጵያዊ ባልደረቦቿ ተገድለዋል ። ቀደም ሲል በተመሳሳይ ሁኔታ 12 የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ባልደረቦች በግፍ ተገድለዋል ። በዚህ በኩል ደግሞ መንግስት ርሀብን እንደጦር መሳሪያ እየተጠቀመ ነው ሲል የፈጠራ ክስ ይደርታል ።

አሸባሪው ህወሓት አገዛዝ ላይ እያለም ሆነ በመማጸኛ ከተማው መቐሌ መሽጎ ያልጣሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የለም ። ገልብጦ ገርፏል ። አካል አጉድሏል። ዘር እንዳይተኩ አድርጓል ። ወንድ ልጅ ሳይቀር እንዲደፈር አድርጓል ። ጥፍር ነቅሏል ። በወንድ ልጅ ብልት የሁለትና የሶስት ሊትር የላስቲክ ውሀ አንጠልጥሏል ። በደረሰባቸው ስቃይ ብዙዎቹ ለአእምሮ ህመም ተዳርገዋል ። ሽባ ሆነዋል ። እግራቸው ተቆርጧል። በማዕከላዊ ፣ በቃሊቲ፣ በቅሊንጦ ፣ በሽዋ ሮቢትና በሌሎች “ማረሚያ” ቤቶችና ስውር ማሰቃያ ቦታዎች ህልቆ መሳፍርት የሌለው ግፍ ፈጽሟል ። አስፈጽሟል። በእስክንድር ነጋ ፣ በአንዷለም አራጌ፣ በሀብታሙ አያሌው ፣ በከፍያለው ፣ በዳባ ገሬ ፣ በወልቃይት ሕዝብ፣ በዋልድባ አባቶች እና በሙስሊም ወንድሞቻችን ለይ ለመስማት የሚሰቀጥጥና ለማየት የሚዘገንን ግፍ ፈጽሟል ። ከሁለት ዓመታት በፊት”የፍትሕ ሰቆቃ”በሚል በኢቲቪና በሌሎች ቴሌቪዥኖች የተላለፈው ዘጋቢ ፊልም ፤ የጌታቸው ሽፈራው”የሰቆቃ ድምጾች”፤ የአንዳርጋቸው ጽጌ”የታፋኙ ማስታወሻ”፤ የአንዷለም አራጌ ፤ የሀብታሙ አያሌው ፤ ወዘተረፈ ግለ ማስታዎሻዎች ዛሬም ህያው እማኝ ናቸው ።

ከስቃዩ ሰለባዎች አንዱ የሆነው ዳባ ገሬ በዚሁ ዘጋቢ ፊልም ፤ በዜጎች ላይ ይፈፀም የነበረው ግፍ ወገን በወገኑ ላይ ይፈፅመዋል ተብሎ የማይታመንና ልጅ ሆነን ወላጆቻችን ያስፈራሩበት በነበረው ጭራቅ/ቡልቡል/የሚፈፅም ይመስለኝ ነበር ያለው ይሄን ያረጋግጣል ። የህወሓት መራሹን ግፍ በ”የፍትሕ ሰቆቃ”የተመለከትሁ እለት ማንባቴን አስታውሳለሁ። ለእራሴ እውን እነዚያ አረመኔዎች ፣ አውሬዎች ከሰው ዘር የተፈጠሩ ናቸው? ብያለሁ። መልሱ የስቃዩ ሰለባ ዳባ እንዳለው ጭራቆች ናቸው። ሕገ መንግስቱን ለሽንት ቤት ተጠቀምበት እያሉ ይሄን ዘግናኝ ስቃይ በወገናቸው ለፈፀሙ አረመኔዎች ነው እንግዲህ እነ ሱዛን ራይስናአንቶኒ ብሊከን ጠበቃ ሆነው ብቅ ያሉት !? በዛ ዘጋቢ ፊልም የስቃዩ ሰለባ ሆነው የቀረቡ እህት ወንድሞቼን ባሰብሁ ቁጥር ዓለምአቀፉ ማህበረሰብና ምዕራባውያን በሀሰተኛና ሆን ተብሎ በተዛባ መረጃ ከትህነግ ጭፍራና ርዝራዥ ጎን መቆማቸውን ስመለከት በእነሱ ቁስል ላይ እንጨት እየሰደዱ እንደሆነ ስለሚሰማኝ ህመማቸው ያመኛል። በሮማውያን ዘመን የነበሩ ገዥዎች ሰውን ከአንበሳ ፣ ከነብር ጋር እያታገሉ በሰው ልጅ ስቃይ ይዝናኑ እንደነበር ከታሪክ ድርሳናት አንብበን እንዳልተደነቅን ፤ በሀገራችን አብዲሌ በሶማሊያ ክልል ጅግጅጋ በ” ጄል ኦጋዴን “ ! ?ዜጎች ከአንበሳ ፣ ከነብር ፣ ከጅብ ጋር ይታሰሩበት የነበረ ምን አልባት በዓለማችን በ21ኛው መ/ክ /ዘ የመጀመሪያም ፣ የመጨረሻም የሆነ ማሰቃያ አዘጋጅቶ ህልቁ መሳፍርት የሌለው ግፍ ይፈጸም የነበረው በአሸባሪው ህወሓት ቡራኬ መሆኑን ያስተዋለ በዜጎች ይፈጸም የነበረ ግፍ ተቋማዊ እንደነበር ያረጋግጣል ። ሆኖም ከሀዲውና እፉኝቱ ትህነግ የጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓም የሰሜን ዕዝ ጥቃት እና የጥቅምት 30ን የማይካድራን ትውልድና ታሪክ ይቅር የማይለውን የክፍለ ዘመኑን ታላቅ ክህደትና ጭፍጨፋ ለመፈጸም ዝግጅቱንና ልምምዱን የጀመረው ከደደቢት ውልደቱ ከየካቲት 11 ቀን 1967 ዓም አንስቶ ነው ። ለግማሽ ክፍለ ዘመን በዝግ የተዶለተበት የክህደት ደባ ። የጭካኔ ልምምድና ዝግጅት ውጤት ነው ።

እንደ መውጫ

አዎ አሸባሪው ህወሓት ጭራቅ ፣ ቡልቡል ወይም ዙምቢ እንጂ በፈጣሪ አምሳል የተፈጠሩ ሰዎች ስብስብ አይደለም ። ዙምቢ ሲመለከቱት አስፈሪ ፤ ባህሪው ደግሞ ጨካኝ አረመኔ ነው ። በላዔ ሰብዕና ደም መጣጭ ነው ። የአሸባሪው ህወሓት በገዛ ዜጎቹ ላይ ለ27 አመታት ይፈፅመው በነበረ ግፍና ስቃይ የተነሳ እንደ ዙምቢና ጭራቅ መፈራት ጀምሮ ነበር ። በገዛ እህት ወንድሞቹ ላይ የፈፀማቸው ለመስማት የሚሰቀጥጡ ፣ ለማየት የሚዘገንኑ ግፎችን መለስ ብለን ባሰብን ቁጥር በአምላክ አምሳል የተፈጠረ የሰዎች ስብስብ ያደረጋቸው ሳይሆን የሰውነትና የኢትዮጵያዊነት ባህሪ ባልነበረው ዙምቢ ቡድን የተፈጸሙ ነበሩ ። በገዛ ወገኑ ስቃይ ፣ ግፍ ፣ በደል ፣ ርሀብ ፣ እርዛት ፣ ቸነፈር ፣ እልቂት ፣ ግጭት ፣ ወዘተረፈ እንጀራውን የሚያሰፋና የሚደሰት የህወሓት ዙምቢ ብቻ ነው ። አንዱን ብሔር ከሌላው ብሔር ፤ አንዱን ሀይማኖት ከሌላው ሀይማኖት በማጋጨት የደም ምሱን የሚያገኝ ። ዛሬም ለዚህ የደም ምሱ ርዝራዡ ቀን ከሌት እዚህም እዚያም እየዛከረና እየተንቀዠቀዠ ነው ። በአጠቃላይ የአሸባሪው ህወሓት ባህሪም ሆነ መልክ ከኢትዮጵያውያን የስነ ልቦና ውቅርና ማንነት ያፈነገጠ መሆኑን የሴራ ፣ የደባ ፣ የጭካኔና የግፍ ጥጉ ጥሩ ማሳያ ነው ። ባለፈው በሰሜን እዝ ላይ የፈጸመው ትውልድም ሆነ ታሪክ ይቅር የማይለው ክህደትም ሆነ በማይካድር ከተማ በአማራ ላይ የፈጸመው የዘር ማጥፋት በሀገሪቱ የዘመናዊ ፖለቲካ ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ እንደማያውቅ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል ። ወደፊትም በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ይፈጠራል ተብሎ አይታሰብም ።

ሀገራችን ኢትዮጵያ በሀቀኛና ጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !

አሜን ።

Filed in: Amharic