>
5:08 pm - Sunday February 22, 6184

የትህነግ ስትራቴጂ <መፅሐፍ> - ቅኝት {መስፍን ማሞ ተሰማ - ሲድኒ አውስትራሊያ}

የትህነግ ስትራቴጂ <መፅሐፍ> – ቅኝት

{መስፍን ማሞ ተሰማ – ሲድኒ አውስትራሊያ}


መነሻ፤

በ86 ገፆች የተዋቀረው የናዚስት ትህነግ <የትግል ልዩ ምዕራፍ እድገቶችና የምከታችን ቀጣይ ስትራቴጂዎች፣ ስልቶችና አቅጣጫዎች> በሚል ርዕስ መስከረም 30፣ 2013 ዓ/ም የህወሃት ፅ/ቤት ለአባላቱ ያሰራጨው (በጥብቅ የሚያዝ የሚል አፅንዖት የተሰጠው) የድርጅቱ ስትራቴጂ ራሱን የቻለ መፅሐፍ ነው። ይህ ስትራቴጂ በሁለት ክፍሎች ተዋቅሮ በርካታ ንዑሳን ርዕሶችን አካቷል። ይህ የናዚስት ትህነግ የቀብር ዘመን ዋዜማ ኑዛዜ ዶክመንት ነው።

የአዶልፍ ሂትለርን Mein Kampf (my struggle) መፅሐፍ ይዘት ያለውና የትህነግን የህይወት ታሪክና መፃዒ ግብ የጠቀለለ ቅፅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። Mien kampf የሒትለር ከፊል ግለ ታሪክና የናዚ ፓርቲ ርዕዮት መመሪያ ነው። መፅሐፉ በሶስት ምሶሶዎች ላይ የቆመ ነው። (1) ፀረ ሴሜቲዝምን ያራምዳል (2) በዘረኝነት (በጀርመን አርያን ዘር) ላይ የተዋቀረ ሥርአትን ይሰብካል (3) በምሥራቅ አውሮፓ ነፃ መሬትን ለማጋበስ (aggressive foreign policy for living space) መከተልን ያራምዳል፤ ወራሪ ፖሊሲን ይከተላል። እኒህ ሶስቱ የናዚ ፓርቲ መርሆዎች በትህነግ ፓርቲ የስትራቴጂ መፅሐፍ ላይ በሚገባና በማያሻማ ቋንቋ ተብራርተው ይገኛሉ።

እንደ ሒትለር Mien Kampf ሁሉ ይህ የናዚስት ትህነግ ዶክመንት (1) ተጀምሮ እስከሚጨረስ ትምክህተኛና ጠባቦች በሚል ቅፅል አሃዳውያን ብሎ በፈረጃቸው ኢትዮጵያውያን የተገነባችውን ሀገረ መንግሥት ለትግራይ ህልውና ሲባል መስበርና ማፈራረስ አስፈላጊ ስለመሆኑና በተለይ ደግሞ አማራው የአሃዳውያን ጎሬና መገለጫ ስለመሆኑ ያብራራል፣ «በአማራው ላይ ሂሳብ ማወራረድ» የሚለውን የዘር ማጥፋት መርሆውን ልብ ይሏል። (2) ዶክመንቱ ተጀምሮ እስከሚጨርስ የትግራይን የበላይነት ለማረጋገጥ ትህነግ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የወታደራዊ የበላይነትን በአብዮታዊ ዲሞክራሲ መርሆ እውን ለማድረግ መከተል ያለበት ብቸኛው መፍትሄ ስለመሆኑ ይተነትናል። (3) የትግራይን ሀገረ መንግሥትነት ለመመስረትና ለማረጋገጥ እንደ አዶልፍ ሒትለር የውጪ ፖሊሲ – (aggressive foreign policy geared to gaining living space in East Europe) ሁሉ ትህነግም – buffer zone – ብሎ በሰየመው በትግራይ አጎራባች (አማራ እና አፋር ክልል) እንደ ሒትለር (aggressive foreign policy geared to gaining living space in Amhara and Afar Region) እውን ይሆን ዘንድ ወደ  ተግባር የተተረጎመ መጠነ ሰፊ ወረራ በሲዖል ሠራዊቱ እያካሄደ መሆኑን ያስተውሏል። 

ከላይ እንደቀረበው ትንታኔ በአጠቃላይ ይዘታቸው ተመሳሳይነት ያላቸው ትህነግና ናዚዝም አፍሪካዊና አውሮፓዊ መሆናቸው ብቻ ነው ልዩነታቸው። ይህንን ጥቅል ምልከታ ለመንደርደሪያ ካሰፈርኩ ዘንዳ የትነግ ስትራቴጂ ዶክመንት የያዛቸውን አንዳንድ ነቁጦች ወደ ማስቀመጡ ላምራ። 

  • ኢትዮጵያ እየፈራረሰች ነው

በትህነግ ዶክመንት መሰረት ኢትዮጵያ እየፈራረሰች ነው። እንዲህ ይላል፤ «የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት፣ አይሲጂ፣ ፍሪደም ሀውስ፣ ታዋቂ ግለሰቦች ወዘተ እያካሄዱት ያለው ተቃውሞ እና እንቅስቃሴ የዚህን ቡድን ቅቡልነት  በእጅጉ ሊያወርድ እና ራቁት ሊያስቀረው የሚችል ነው። ከእነዚህ አዳዲስ እውነታዎች ተነስተን አሜሪካ ከአብይ ጋር ለመቀጠል እየፈለገች አይደለም። በአውሮፓ አብዛኞቹ ሀገሮች ኢትዮጵያ እየፈረሰች ነው የሚል ሰፊ ስጋት አለባቸው። እኛ የያዝነውን አቋምና መፍትሄም መስማት ጀምረዋል። ከዚህ በመነሳትም ብዙ የአውሮፓ መንግሥታት ሆነ የሩቅ ምሥራቅ ሀገራት ከኢትዮጵያ ውጪ ከእኛ ጋር የመገናኘት ፍላጎት እያሳዩ ነው።» (ገፅ 7/8) 

ይህ የትህነግ ዶክመንት መስከረም 30/2013 የተሰራጨ ይሁን እንጂ በናዚስቶቹ ምክር ቤት መቀሌ ከመሸጉበት 2010 ዓ/ም ጀምሮ ሲወያዩበትና ሲያዳብሩት የቆዩት፣ ብዙም ሥራ (በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጪም) ሲሰሩ የከረሙበትና በመጨረሻም የህወሃት ስትራቴጂ ሰነድ ሆኖ የወጣ መሆኑን ልብ ይሏል።

በዚህ ስትራቴጂያቸው መሠረትም በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ስምንት ጊዜ አውሮፓውያንን እና አሜሪካን በኢትዮጵያ ላይ (ይህ ፅሁፍ እስከወጣበት ድረስ) አዝምተዋል። እንዳሰቡት ባይሳካላቸውም ግን ጥረታቸውን ቀጥለዋል፤ ኢትዮጵያ በመንግሥታቱ ማህበር እንድትገለልና በማዕቀብ ወጥመድ እንድንትንበረከክ። አሜሪካ በእነ ሱዛን ራይስ ግንባር ቀደም አስተባባሪነት ለትህነግ በመወገን ለኢትዮጵያ የጀርባ ተባይ ሆናባታለች። በባይደን አስተዳደር የተሰገሰጉት ነጭ ህወሃታውያን በየጊዜው ኢትዮጵያ ላይ የሚጎስሙትን ነገረኛ አዋጅና ፉከራ እያየው ነውና! የናዚስት ትህነግ ስትራቴጂ Mien kampf እንዲህ ይላል፤ «ባይደን ከተመረጠ የኦባማ ሰዎች ወደ ሥልጣን እንደሚመጡ ይገመታል። (ስለዚህም) የተሻለ ግንኙነት ለመፍጠር ዕድል ይኖረናል። ከዶናልድ ትራምፕ በኋላም ቢሆን የአብይን ቡድን ሊሰማው የሚችል አይኖርም» (ገፅ 7) ዶናልድ ቢሸነፍም ዲሞክራቱ ባይደን ከኦባማ በሚወርሳቸው አፍቃሪ ህወሃት ሃይላት በኢትዮጵያ ላይ ለሚወስደው የጥፋት ሴራ ትህነግ በአሜሪካ መንግሥት ተባባሪ ሀይል እንደሚኖረው በስትራቴጂ ሰነዱ ላይ በርግጠኝነት አስቀድሞ አስፍሯል።

በናዚስት ትህነግ Mien kampf ሰነድ መሰረት ኢትዮጵያ በመባል የምትታወቀው ሀገረ መንግሥት የተመሰረተችው በ19ነኛው ክፍለ ዘመን በተለይም በ1881 ዓ/ም ከሰሜን ሸዋ በተነሳው የምኒልክ «ጨፍላቂ» ኢምፓየር ግንባታ ነው ይላል። አያይዞም በድምሩ 102 ዓመት ዕድሜ ያለው አሃዳዊ ኢምፓየር (እስከ 1983 ዓ/ም ድረስ ይላል ሰነዱ) ከመበታተን የዳነው ትህነግ በ1983 ዓ/ም ስለታደገውም መሆኑን በፀፀት ስሜት ይገልፃል። ከገፅ 68 እስከ ገፅ 86 በዘለቀው መንዘባዘብ ኢትዮጵያ እንደ ዩጎዝላቪያ የመሆን ዕድሏ ሰፊ ሲሆን ከጦርነት በመለስ በሰላማዊ መንገድ እንድትፈርስ «የሽግግር/ባለአደራ መንግሥት» ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑንና ለዚህም አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያትታል። ሠላማዊ መበታተኑን (ምናልባት አንቀዕ 39ኝን በመጠቀም) የሽግግር/ባለአደራ መንግሥት በሚመሰርተው ሸንጎ በሚለው አካል በኩል ተፈፃሚ ሊያደርገው እንደተዘጋጀ ያለ ሃፍረት ይደሰኩራል። በዚህ ዙሪያ የትህነግን Mien Kampf ለመበለት መድከም ከቶም አስፈላጊ ስላልመሰለኝ ወደ ሌላ ነቁጥ ላምራ። 

  • ደህንነት፣ ሠላም ፣ ዲፕሎማሲ፤

ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮኻል እንዲሉ ትህነግ ከአራት ኪሎ ወደ መቀሌ ተዛውሮ ከመሸገ ወዲህ ከትግራይ በቀር በመላዋ ኢትዮጵያ በወኪሎቹ አማካኝነት የንፁሃን ደም እንደ ጎርፍ እንዲፈስ አድርጓል፣ መጠን አልባ ንብረት አውድሟል፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል።ይህንን ዕኩይ ሥራውን በቅርብ እየተከታተለ ሲገመግም የሰነበተው ናዚስት ትህነግ በመስከረም 30/2013 የስትራቴጂ ሠነዱ ላይ እንዲህ ይላል፤ « በፀጥታ፣ ደህንነት እና ሠላም ዙሪያ ያሉ ክስተቶች/ዕውነታዎች ሌሎች ጠቃሚ ጉዳዮች ናቸው። በዚህ ወቅት በዚህች ሀገር አብዛኛው አካባቢ ሠላም የለም። ግጭት፣ ግፍ፣ የጅምላ ግድያና እስር ከነበረበት በእጅጉ ተባብሷል። በኦሮሚያ፣ ደቡብ (ወላይታና ሲዳማ) ቤንሻንጉል፣ ጋምቤላ በየቀኑ የሚያልፍ ህይወት ለጉድ ነው። በእንዲህ አይነት ተግባራት ምክንያት ህዝብ በፀጥታ መዋቅሩ ላይ ዕምነት እያጣ እየተገለለ እየሄደ ነው። በሀገር መከላከያ የመሰላቸትና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት እያደገ ነው።» (ገፅ 17/18) 

ይገርማል። ትህነግ ከቤተመንግሥት ከወጣበት ጊዜ አንስቶ በመላው ኢትዮጵያ ከትግራይ በስተቀር የነበረውን ትርምስ በሪሞት እየመራው ቆይቶ የደረሰበት ድምዳሜ ዓላማው ሕዝብንና መከላከያውን መለያየትና በመጨረሻም በስንጥቁ መኻል ገብቶ ቀቢፀ ተስፋውን ዕውን ለማድረግ መሆኑን ይህ የስትራቴጂ ሰነዱ በገሀድ ይናገራል።

ናዚስት ትህነግ መቀሌ ከመሸገበት ደቂቃ ጀምሮ ያለመታከት እረፍት አልባ ሆኖ ሲሰራ ቆይቷል። ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ያለውን ትግራዋይ በሙለ በዘርፈ ብዙ አደረጃጀት በጃንጥላው ሥር አሰልፏል። ኢትዮጵያ በአመፅ ትነድ ዘንድ ትህነግ እንዲህ ይላል፤

«የተደራጁ ሀገራዊ አመፆችን ማቀጣጠል፤ ጠላትን ለማሰናበት/ለማጥፋት ትልቅ መሳሪያ ሊሆን የሚችለው በትጥቅ የታገዙ አመፆችና ድርድር ነው። የትግሉ መስክ ሀይል የታከለበት የተደራጁ አመፆችንና ብጥብጦችን ማዕከል ማድረግ አለበት። የተደራጁ አመፆች ወደ ወታደራዊ ጦርነት መሸጋገር እንደሚችል ታሳቢ ያደረገ፤ ይህንንም የሚፈፅም ግልፅና ህቡዕ አደረጃጀትና ተልዕኮውን በመግለፅ ሊሰራበት የሚገባ ነው።» (ገፅ 60) 

ኢትዮጵያን ለ27 ዓመት ረግጦ ሲገዛት የኖረው ትህነግ በሚገርም እና በሚያሳዝን መልኩ የሠነደው ስትራቴጂ ተጀምሮ እስኪያበቃ ኢትዮጵያን እንደምን አድርጎ አንቆና ትንፋሽ አሳጥቶ እንደሚገድላት ያለ ሀፍረት የሚተነትን ሠነድ ነው።

ናዚስት ትህነግ ኢትዮጵያን ለመምታትና ለመበታተን ጎረቤት ብሎ በሚጠራቸው ክልሎች አማራና አፋር እንዲሁም የመውጫ በር (ኮሪዶር) በሚላት ሱዳን ተወርዋሪ ሀይል ማዘጋጀትን አስመልክቶ በነደፈው ዕኩይ ስትራቴጂ ይህንን አስፍሯል፤ «በጎረቤቶቻችን ዘንድ መጠነ ሰፊ ባፈር ዞን በመፍጠር ከዚህም ተሻግሮ የሚዘልቅና ራሱን የቻለ የተለየ ዝርዝር ዕቅድ የሚሰራበት ነው።…ባፈር ዞን ማስፋትና ማጠናከር፤ ከጫፍ እስከ ጫፍ አጎራባቾቻችን ከሆኑት ሕዝቦች አፋር፣ አገው፣ ቅማንት እና አማራ አካባቢዎች የምከታውን አቅሞች ለማድረግ ልንረባረብበት የሚገባ ነው።» (ገፅ 61) እነሆ እንግዲህ ዛሬ በጎንደር፤ በወሎ፤ በአፋር ትህነግ የሚያደርገው የሞት የሽረት ጦርነት ከዚህ ባፈር ዞን ከሚለው ስትራቴጂ የመነጨ ስለመሆኑ ራሱ ምሥክር ነው። 

በዚህ የትህነግ 86 ገፅ Mien Kampf ሠነድ እንደምንረዳው ናዚስት ትህነግ ወደ ለየለት ጦርነት ከመግባቱ በፊት ሰፊ ዕቅድና የውስጥ ለውስጥ ሥራ (ለምሳሌ በቅማንትና በቤንሻንጉል ታጣቂዎችን ማደራጀት) በትጋት ሲሰራበት የቆየ ለመሆኑ አስረጅ ነው። በወሎ፤ በጎንደር እና በአፋር ትህነግ ሺህ በሺዎች እየደራረበ ለጦርነት የሚያግተለትለው የሲዖል ሠራዊቱ ቀዳሚ ተልዕኮም ትግራይን ከጦርነት ቀጠና በማውጣት የጥይት አብራጅ (አማራና አፋርን የጦርነት አውድማ በማድረግ) ባፈር ዞን ማስፋትና ማጠናከር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። በትህነግ የሲዖል ሠራዊት በመካሄድ ላይ ያለው ዝርፊያው ውድመቱና ናዚስታዊ ጭካኔው (ይህ ቅኝታዊ ፅሁፍ ለንባብ በበቃበት ወቅት) የዚህ የባፈር ዞንን የማስፋት ዕቅድ ዋና አካል መሆኑም ሊጤን ይገባል።

እፍረት አልባው ትህነግ እንዲህ ይላል፤ «በኦሮሚያ ሲካሄድ የቆየው እና ያለው ትግል የሕዝቡ ነው። የቄሮ ንቅናቄ ሕዝባዊ ንቅናቄ ነው። ወደ ኋላ ሊመለስ አይችልም። (ገፅ 19) እንግዲህ አዛኝ ቅቤ አንጓች ይሏል እንዲህ ነው። ትህነግ አዲስ አበባ ላይ በተቀመጠበት የሥልጣን ዘመኑ በስንትና ስንት ሺህ የሚቆጠር የኦሮሞ ወጣትን (ቄሮን) በእስር እንዳላንገላታ፤ ብዙዎችን እንዳልገደ፤ እናትን በልጇ ሬሳ ላይ እንዳላስቀመጠ፤ በእሬቻ በዓል በመቶዎች የሚቆጠሩትን እንዳልፈጀ ሁሉ እነሆ በዚህ አይን ባወጣ የሴራ ሰነዱ የኦሮሞ ሕዝብና የልጆቹ (የቄሮ) ተቆርቋሪ ሆኖ ቀርቧል። ትህነግ ይሉኝታ እንኳን የሌለው የአካይስቶች ድርጅት ነው። እንቀጥል የክህደት ሰነዱን፤

«በቤንሻንጉልም ጫካ ገብተው የአቅማቸውን ትጥቅ ይዘው፣ ባህላዊ መሳሪያ ተጠቅመው ከፀጥታ ሀይሎች ጋር ወደ ተከታታይ ትግል ገብተዋል። በአመፅ እየተደረገ ካለው ንቅናቄ/እንቅስቃሴ በተጨማሪ   በኦሮሚያ ቄሮ እና ኦነግ ሸኔ፣ አፋር እጉጉመ እና ሌሎችን በትጥቅ በመደገፍ ለሚ,ደረገው ትግል የተሻለ ዕድል እየተከፈተ ነው።» (ገፅ 19)

አዎ! ኢትዮጵያ ከትግራይ በመለስ ለጆሮ ዘግናኝ፣ ለዕይታ እብደትን የሚያስከትሉ በግፍና በጭካኔ በተፈጁት ልጆቿ ደም እንድትሞላ ከ2010 ዓ/ም ጀምሮ ከመቀሌ በሚቆጣጠራቸው አምሳለ ፍጡራኑ (ኦነግ/ኦነግ ሸኔ፣ ቅማንትና ቤንሻንጉል ጉምዝ) ከደቡብ እስከ ሰሜን ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ዘግናኝ የዘር ማፅዳት ጭፍጨፋዎች መፈናቀሎችና የከተሞች ውድመቶች እንዲካሄዱ በማድረግ መመሪያ ሲሰጥ፣ በፋይናንስና በትጥቅ ሲረዳ ለመቆየቱ ይህ ሰነድ በማያሻማ የስትራቴጂ ቀመሩ በራሱ ላይ አስረጅ ምሥክር ሆኖ ይገኛል። ለዚህም ነው ኦነግ ሸኔ እና ፈጣሪው ትህነግ በወታደራዊ መስክ ማዕከላዊ መንግሥቱን ለመጣል ስምምነት ማድረጋቸውን በይፋ ያወጁት። ስልቻ ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎ ስልቻ!!!

  • ቅጥፈትና ዲፕሎማሲ 

ትህነግ እንዲህ ይላል፤ «በሀሰት አጀንዳ የጠላት ምርጫ ማንኛውም አይነት ፋታ እንዳያገኝ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ጠላትን ለመጣል ወይም ለማሰናበት አንድ እርምጃ የሚያራምድ ቁልፍ መሪ ቃል ጋር አቀናጅቶ የፖለቲካ ሥራችን ማዕከል እንዲሆን ማድረግ» (ገፅ 61)

መስከረም 30/2013 ዓ/ም ይፋ (ለአባላቱ?) የተደረገው ይህ ሰነድ እንደሚገልፀው ማዕከላዊው መንግሥት ህጋዊ መንግሥት ባለመሆኑ (ምርጫ ዘመኑ ያለቀበት) ፌዴራሊስት ሀይሎችን አሰባስቦና ማንኛውንም የሀሰት አጀንዳም በመጠቀም መጠነ ሰፊ ፕሮፓጋንዳ ማካሄድ የስትራቴጂው አንዱና ዋናው የፕሮፓጋንዳው አካል ሆኖ ተቀምጧል።

ናዚስት ትህነግ በስትራቴጂው ላይ «ጊዜያዊ መንግሥት/የባላደራ መንግሥት» በማለት በስፋት የተነተናቸው ዕቅዶችና ሊተገበሩ የሚገባቸው ግቦች ብሎ የለያቸውን ነቁጦች ስንመለከትና በሚቋቋመው ጊዜያዊ/ባላደራ መንግሥት ውስጥ የባለድርሻ አካለቱን ማንነትና የሸንጎውን አወቃቀር ስንረዳ ትህነግ ምን ያህል ሩቅ ትልም እንዳቀደና ኢትዮጵያን ለመበተን እስከምን ድረስ በየዘርፉ እንደተጓዘ ፍንትው ብሎ ይታያል። እንደ ትህነግ የጊዜያዊ/ባላደራ መንግሥት ዕቅድ ከሆነ ኢትዮጵያን በሠላማዊ መንገድ መበታተን የሚቻል ሲሆን ለዚህም ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የተካተቱበት ሸንጎ ማዋቀር አስፈላጊ ስለመሆን በስፋት ተንትኗል። የፋሽስት ጣሊያንን ዕቅድ ለመፈፀም የተነሳው ትህነግና ተባባሪ ባንዳ ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ መሆናቸውን ታሪክ ያረጋግጠው ሀቅ ሆኗል። 

ትህነግ በ27 ዓመት የሥልጣን ዘመኑ ከዲፕሎማቶች እስከ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት በቁልፍ ሀላፊነቶች ባስቀመጣቸው አባላቱና ቅጥረኞቹ በኩል ዓለም ዐቀፍ ዲፕሎማሲውን ለራሱ የስትራቴጂ ግብ ጠቃሚነት እንዲረዱት ስለማዋል በሰነዱ ላይ እንዲህ ይላል፤ «በሶስተኛ ወገን የግንኙነት መስክ በኩል እየሰሩ የቆዩ የተሻለ ዕውቀትና በሳል ተሞክሮ ያላቸው አመራሮቻችንን በበይነ መንግሥታት ፅ/ቤት እየተመራ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ አሁን ያስቀመጥነው የምንገኘውን መሠረታዊ ተግባራትን እና ተልዕኮዎችን ለመፈፀም በሚያግዝ/በሚደግፍ ቅኝት ተጣጥሞ/ተስተከክሎ ከውጪ ማግኘት የሚገባን የፍትሃዊ ጥያቄያችን እና አካሄዳችን ደጋፊ በጠላቶች ላይ ተፅዕኖዎችን የሚፈጥር መሰባሰብ፣ ጥያቄያችንና አካሄዳችን ግልፅ ያልሆነላቸውን ማብራራት፣ የጠነከረ ተቃውሞ ያላቸውን ወደ ማግባባት እንዲመጡ ማድረግ…

«የዓለማችን ትልልቅ ሀገራትም እንደየባህሪያቸውና ትስስራቸው ለተመሳሳይ ዓላማ መስራት። ከአሜሪካን ፕላን<ኤ> እና ፕላን <ቢ> በዲሞክራቶችና ሪፐብሊካኖች ከምርጫው ጋር አዛምደን (የጆ ባይደን የመመረጥ ዕድል የሰፋ ይመስላል) የአውሮፓ ህብረት፣ እንግሊዝንና ራሺያን ጨምረን አላማችንን እና አመለካከታችንን፣ የእነርሱን ጥቅማ ጥቅሞች የሚጎዳ እና ሀገርን እያፈረሰ ያለው ቡድን ለመግራት የሚያግዝ መግባባት/ውይይቶችን ማድረግ» (ገፅ 67) 

ጉድ ነሽ ያንኮበር ቅጠል፣ ከመፋጀትሽ የመለብለብሽ – አሉ። ትህነግ ራሱ ሀገር አፍራሽ ሆኖ ሀገር አፍራሽ መንግሥት የሚለውን ለማስወገድና እራሱን መልሶ አራት ኪሎ ለማስገባት በዚህ ሰነድ መሰረት በምን ያህል ጥልቀትና ስፋት፣ ከሀገር ዐቀፍ እስከ ዓለም ዐቀፍ አቅዶ እንደሰራና እየሰራ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። 

ከዓለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተሩ የትህነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ቴዎድሮስ አድሃኖም ጀምሮ በየሀገራቱ ኤምባሲዎች፣ የእርዳታ ድርጅቶች፣ ዓለም ዐቀፍ የሚዲያ አውታራት፣ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች፤ ኤንጂኦዎች ወዘተርፈ ውስጥ በሚገኙት አባላቱና ተቀጣሪ ወኪሎቹ ዓለም ዐቀፍ ፀረ ኢትዮጵያ ዘመቻው እስከ ተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ድረስ እንደዘለቀ በተደጋጋሚ የታየ ሀቅ ነው። ትህነግ ከስምንት ወር የተንቤን ሽሽቱ ከተመለሰ ወዲህም እንኳን ቢሆን በቀጥታ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የገባው በዚሁ መቀሌ ላይ መስከረም 30/2013 ዓ/ም ባወጣው የስትራቴጂ መመሪያው መሰረት መሆኑን አፅንዖት ሰጥቶ ማንጠብ ግድ ይላል። በጎንደር፣ በወሎ እና አፋር በትጋት እየተገበረው የሚገኘው ኢትዮጵያን <ሲዖል እስከማውረድ> የዘለቀ ዘግናኝ ዘመቻው በሰነዱ «ባፈር ዞን» መፍጠር ብሎ ባስቀመጠው ስትራቴጂ መሆኑን በአንክሮ ያጤኗል።

በመኻል ሀገር (አአ) ስለሚኖሩ ትግራዋይ የትህነግ Mien Kampf እንዲህ ይላል፤ «በመኻል ሀገር የሚኖር ትግራዋይ በሙሉ ጠላትን የመጣል/የመገርሰስ ትግል እንደ አንድ አካል ደህንነቱን ማረጋገጥ ሆኖ ተጠናክሮ እንዲወጣ በበቂ ትኩረት መሰራት አለበት። በዚህ መሰረት አደረጃጀቶች ተልዕኮዎች እና አሰራሮችን በሚያመች መልኩ አድሰን (አሳድሰን) እንረባረባለን፤ በውጪ የሚኖሩ ተጋሩ ባለፈው ባስቀመጥነው የሥራ ዕቅድ አቅጣጫ እና አሁን በተጀመረው ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል መሥራት ነው። (ገፅ 66/67)

ከላይ ባቀረብኩት የሰነዱ አካል ውስጥ በሽፍንፍን የቀረበ ነገር ግን በቅርበት ሲመረመር እጅግ ከባድ የሆነ ምሥጢር የያዘ ፍንጭ (ክሉ) እናገኛለን። ትህነግ በሰነዱ በቅንፍ ውስጥ (አሳድሰን) ብሎ ያስቀመጠው የአዲስ አበባው የተጋሩ መዋቅር ጉዳይ ነው።  ከመቀሌው የትህነግ ማዕከላዊ አመራር በተጓዳኝ (parallel) በአዲስ አበባ ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስ <ኮማንድ ፖስት> ያለው አደረጃጀት ስለመኖሩ የምናገኘው ፍንጭ በአዲስ አበባ «ተልዕኮዎችንና አሰራሮችን በሚያመች መልኩ (አሳድሰን) እንረባረባለን» ይላል። «አሳድሰን» ማለት በአዲስ አበባው አደረጃጀትና አመራር ጉዳይ የአዲስ አበባው የጁንታ መዋቅር ሀላፊ መሆኑን አስረግጦ ያሳየናል። 

ኢትዮጵያ ከመቀሌ ትግራይ በሚተላለፍ መመሪያና ዕቅድ ብቻ ሳይሆን አዲስ አበባ በተቀመጠ የናዚስት ህወሃት የሽብርና የጥፋት ቡድን መሪና አቀነባባሪ፣ እጅግም መሰሪና ዘርፈ ብዙ መዋቅር ያለው፣ በፋይናንስ፣ በሰው ሀይልና በማቴሪያል የተደራጀ አጥፊ ሀይል በጉያዋ ሆኖ ሲለበልባት የኖረና ያለ መሆኑን መገንዘብ ግድ ይላል። ይህ በመኻል አዲስ አበባ የመሸገው የትህነግ ገዳይ ስብስብ መዋቅሩንና አባላቱን ከቁንጮው እስከ ቁርጭምጭሚቱ መመታት፤ መበተንና ዳግም እንዳያንሰራራ ሆኖ ማምከን የነገው የኢትዮጵያ ሠላም ህልውና ጉዳይ በመሆኑ የመቀሌውን ቁንጮ ከመምታትና የሲዖል ሠራዊቱንም ከመበተን ባልተናነሰ ሊሰራበት ይገባል!!! 

  • ጦርነት ሠላም ነው።

ዓለማችን ካፈራቻቸው ትውልድና ዘመንን የሚሻገሩ የፅሁፍ ሥራዎቻቸውን ካበረከቱ ደራሲያን መካከል አንዱ ጆርጅ ኦርዌል (አርተር ብሌር) ይባላል። የኦርዌል መፃህፍት በተለይም ሁለቱ አበርክቶዎቹ የሰው ልጅና መንግሥታዊ ሥርዐተ መዋቅሮቹ በምድር እስካሉ ድረስ ሲጠኑና ሲዘከሩ ይኖራሉ። ስለምን ቢሉ – ምድር ከአምባገነን (ፋሽስት፣ ናዚስት ወዘተ) መንግሥታት መሪዎችና ፓርቲዎቻቸው ትፀዳ ዘንድ አይቻላትምና!   

የኦርዌል ሥራዎች የአምባገነኖችን (ፋሽስት፣ ናዚስት ወዘተ) ምንነት፣ ማንነትና መገለጫዎቻቸውን እንደ ንጋት ፀሀይ ፍንትው አድርገው ስለሚያሳዩ፣ በየትኛውም ዘመን፣ በየትኛውም የዓለም ዳርቻ በሚገኝ ሀገር አምባገነኖች ሲከሰቱ ማንነታቸውንና ዓላማቸውን ማጋለጫና መታገያ መሳሪያ ሆነው ይገኛሉ። እኒህ የፋሽስቶችና ናዚስቶች መቅሰፍት የሆኑት የኦርዌል ሥራዎች በተለይ ሁለቱ መፃህፍት «አኒማል ፋርም» እና «1984» ይባላሉ። «አኒማል ፋርም» የሚለውን የኦርዌል ሥራ የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ «የእንስሳት አብዮት» በሚል ርዕስ ተርጉሞት ለንባብ አብቅቷል። «1984» የተባለው ታላቁ ድርሰቱ በሶስት ፅንሰ ሀሳቦች ላይ የቆመ ነው፣ የአምባገነን ሥርዐቶችን፣ አይዲዮሎጂያቸውንና መሪዎቻቸውን አብጠርጥሮ ያሳያል።

ጦርነት ሠላም ነው። ነፃነት ባርነት ነው። ድንቁርና ጥንካሬ ነው። War is peace. Freedom is slavery. Ignorance is strength. የ«1984» መፅሐፍን እኒህ ሶስት ምሶሶዎች ወደ መሬት አውርደን ወደ ሀገራችን ስናመጣቸው በሶስቱም ፅንሶች ላይ ከውልደት እስከ እርጅናው የህልውናው መሠረት ሆኖ የኖረውን ናዚስት ትህነግን እናገኛለን። ትህነግ በህይወት ለመኖር ጦርነት መኖር አለበት። ጦርነት ለትህነግ ህልውና ሠላም ነውና! በባርነት መግዛት ለትህነግ ነፃነትን ማረጋገጥ ነውና! ደናቁርትን በዙሪያው ማሰለፍና ማሰማራት ለትህነግ የጥንካሬው ምንጭ ነውና! የኦርዌላዊውን ጥቅል ምልከታ በዚሁ ልግታና ወደ ናዚስት ትህነግ የስትራቴጂ ሰነድ Mien Kampf ልመለስ። 

  • ክተት ሠራዊት ምና ነጋሪት

«ጠላትን የምናሰናብትበት አመት፣ ወር፣ ቀን እና ሰዓት አሁን ነው። ጎን ለጎን መኖር አይቻልም። እንደ ሀገርም ከባድ አደጋ ውስጥ ነን። ይህ አምባገነን እያለም ሆነ ከዚያ በኋላ ይህች ሀገር ልትፈርስ ትችላለች። ወደ ሌላ አማራጭ የምንገባበት ሁኔታ/እውነታ ላይ ነው የደረስነው። ጠላት በብዙ መልኩ ተዛብቷል። የተዛባውም ጠላት ዕድል ሳያገኝ ሙሉ በሙሉ መሰናበት/መገርሰስ አለበት። እኛ የጀመርነው ትግል በሁሉም መልኩ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ገፅታዎቹን አቀናጅተን በሰፊው ከተሰማራንበት/ከዘመትንበት ሀገር ደረጃ ለሚኖር ውጤት ጠቃሚ ሚና መጫወታችን አይቀሬ ነው። አሁን ባለንበት ደረጃ ለረጅም ጊዜ መቆየት አይኖርብንም። (ገፅ 23/24)

እነሆ ናዚስት ትህነግ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ የዘመተው እንዲህ ባለ በጥቁርና ነጭ ቀለም በግልፅ በሰፈረ የስትራቴጂ ሰነዱ አቅጣጫ መሠረት ነው። ኢትዮጵያን ማፍረሻው ጊዜው ሰዓቱ፣ ቀኑ አሁን ነው። ኢትዮጵያን ማፍረስ የምንጀምረው የሰሜን ዕዝን በመምታትና በመደምሰስ ነው፤ ጊዜው፣ ሰዓቱ፣ ቀኑ ደግሞ አሁን ነው። ይህ ነው ናዚስት ትህነግ ማለት!! ያጎረሰውን እጅ የነከሰ፣ ጠባቂውን ያረደ!!

ትህነግ የርኩሳን ሁሉ እርኩስ ነው። የናዚስት ትህነግ ስትራቴጂ ሰነድ መቀሌ ላይ በጭብጨባ ከተመረቀ ከአንድ ወር በኋላ በጥቅምት ወር መጨረሻ ትህነግ የጨለማ ዘመን ጦርነትን ኢትዮጵያ ላይ በጨለማ ከፈተ። ይህ ፅሁፍ ለንባብ እስከበቃበትም በትህነግ የሲዖል ሠራዊት የጨለማ ዘመን ጦርነት አእላፍ ኢትዮጵያውያን ህይወታቸው እያለፈ ነው። በወሎ፤ በጎንደር፤ በአፋር ከተሞችና መኖሪያዎች በሲዖል ሠራዊቱ ሳጥናኤላዊ ተልዕኮ እየወደሙ ነው። በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል/እየተፈናቀሉም ነው። የናዚስት ትህነግ የሲዖል ሠራዊት እንደ ጎርፍ በላይ በላዩ እየተገማሸረ በወሎ፤ በጎንደር፣ በአፋር የትህነግን የቃል ኪዳን ሰነድ ዕውን ለማድረግ ለእብደት የሚዳርግ ዘግናኝ አረመኔነት እየፈፀመ ነው። …

በዚህ ሁሉ መዓት መኻል ግን ኢትዮጵያ ትህነግ እንዳለመው ከመበታተን አፋፍ ላይ አልደረሰችም። አትደርስምም!! ኢትዮጵያ በዘመናት ታሪኳ ውስጥ በተፈጠሩት ባንዶችና የውጪ ጠላቶች አያሌ ሟርትን ብታስተናግድም በሟርተኞቹ መቃብር ላይ እያበበችና እየጠነከረች እዚህ ለመድረሷ ታሪክና ፈጣሪ ምሥክር ናቸው!! የዘመናት ጠላቷ ትህነግና ያሰማራው የሲዖል ሠራዊት መቀመቅ የሚወርዱበትና የኢትዮጵያ ትንሣኤ የጨለማውን የትህነግ ዘመን እስከ ወዲያኛው የሚቀብርበት ዋዜማ ላይ ትገኛለች – ትላንት፣ ዛሬ፣ ነገም በሕዝቧ ፅናትና አንድነት ሰንደቋን ከፍ አድርጋ የምትቀጥለው ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያችን!!!

  • ማጠቃለያ

ትህነግ ቃላት ሊገልፁት ከሚችሉት በላይ የህይወትና የሠላም ፀር የሆነ ድርጅት ነው። ትህነግ ለኢትዮጵያ ነቀርሳ ነው። ኢትዮጵያ መፈወስ ካለባት ከትህነግ ነቀርሳ መገለገል የህልውና ግዴታዋ ነው። ትህነግ ትንፋሽ እስካለው ድረስ ኢትዮጵያ ትደማለች። የኢትዮጵያን ደም ለማቆም ትህነግ እንደ መዋቅር ፍፁም መደምሰስ አለበት። ትህነግ እንደ ድርጅት እንዳይኖር ማድረግ ፍፁም አማራጭ የሌለው ግዳጅ ነው።

እነሆ የዚህን ዕኩይ ድርጅት የኑዛዜ ሰነድ በየፈርጁ ለመተንተን አያሌ ገፆች ያሉት ጥራዝ ይሆናል። በበኩሌ ጊዜ ወስጄ በተወሰነ ደረጃ ለአቀራረብ አመቺ ይሆናሉ ባልኳቸው ንዑሳን ርዕሶች ሥር ያሰናዳሁት የትህነግ ስትራቴጂ ቅኝት የድርጅቱን የስትራቴጂ ተልዕኮና ግብዐት ለአንባቢ ግንዛቤ ያሲዛል ብዬ እገምታለሁ።

ኢትዮጵያ በነፃነት ለዘለዓለም ትኑር!

ድል ለመከላከያና ለሕዝባዊ ሠራዊት!

ሞት ለትህነግና ለሲዖል ሠራዊቱ! 

Mesfin Mamo Tessema

መስከረም 20/2014

September 30/2021

Sydney, Australia

Filed in: Amharic