>

ደራሲና ጋዜጠኛ ጋሽ ታዲዮስ ታንቱ ከነበሩበት እስር ቤት አውጥተው ሰወሯቸው....!!!  (ወንድወሰን ተክሉ)

ደራሲና ጋዜጠኛ ጋሽ ታዲዮስ ታንቱ ከነበሩበት እስር ቤት አውጥተው ሰወሯቸው….!!!
 
 ይድረስ ለኢትዮጲያ ህዝብ በሙሉ !!!
 
 ወንድወሰን ተክሉ

 
ደራሲና ጋዜጠኛ ጋሽ ታዲዮስ ታንቱ ከታሰሩበት የኦሮሚያው ገላን እስር ቤት አውጥተው ወደ አልታወቀ ቦታ እንዳዛወራቸው ባለቤታቸው ወ/ሮ ጸጋ ዛሬ በጭንቀት የገለጹልን ሲሆን ህይወታቸው በከፍተኛ አደጋ ላይ ወድቌልና የኢትዮጲያ ህዝብ አቤት ይበልልኝ ሲሉ ተናግረዋል በማለት የጋሽ ታዲዮስ ጉዳይ የሚከታተለው በጎፈቃደኛ ኮሚቴ አሳውቀዋል።
ደራሲና ጋዜጠኛ ጋሽ ታዲዮስ ታንቱ ለሶስተኛ ጊዜ ወደ አልታሰቀ ስፍራ መወሰዳቸውን ማወቅ የቻሉት ዛሬ ለጥየቃ ወደ ታሰሩበት ገላን ፖሊስ ጣቢያ ባተጔዙበት ወቅት ሲሆን እጅግ በሚደንቅ ሁኔታ በጥበቃ ስራ ላይ የተሰማሩት የፖሊስ ጣቢያው ፖሊሶች ስለጋሽ ታዲዮስ በማንና መቼ እንደተወሰዱ የማያውቁ መሆናቸውን በመግለጽ የት እንዳሉ አናውቅም ብለው ለባለቤታቸው የመለሱበት ሁኔታ የጋሽ ታዲዮስን ህይወት በአደጋ ላይ ስለመሆኑ አማላካች ሆኖ አግኝተነዋል።
በወ/ሮ ጸጋ በኩል የጣቢያውን ኋላፊዎችን አግኝቶ ባለቤታቸው ያሉበትን እስር ቤት ለማወቅ ያደረጉት ሙከራ ያልተሳካላቸው ሲሆን ከጋሽ ታዲዮስ ጋር በአንድ እስር ክፍል ታስሮ ካለ እስረኛ አንደበት ባለቤታቸውን ፖሊሶች መጥተው ወስደዋቸዋል በማለት እንደነገራቸውና ጋሽ ታዲዮስን በገላን ፖሊስ ጣቢያ ሊያገኙ እንዳልቻሉ በከፍተኛ ጭንቀትና ስጋት ገልጸዋል።
ደራሲና ጋዜጠኛ ጋሽ ታዲዮስ ታንቱ በመዓልተ ለሊት ከመኖሪያ ቤታቸው የፌዴራል ፖሊስ ነን ባሉ ወታደሮች ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ በኦሮሚያ ክልል በአዋሽ እስር ቤት ከማንም ጋር እንዳይገናኙ ተደርገው ለብቻ ወደ ሃምሳ ቀናት ያህል እንዲሰቃዩ ከተደረጉ በኋላ ወደ ገላን ፖሊስ ጣቢያ እንዲዛወሩ በማድረግ ከቤተሰብ ጋር እንዲገናኙ ተደርጎ ነበር።
ከወር በፊት የጋሽ ታዲዮስ ቤተሰብ በገላን ፖሊስ ጣቢያ ሲያገኛቸው ከራሳቸው አንደበት በተነገረ የታሰሩበትን መንስኤ ፈጽሞ እንደማያውቁ ቃል እንዳልሰጡ፣ እንዳልተጠየቁና ፍርድ ቤትም እንደማያውቃቸው ማወቅ በመቻሉ ቤተሰባቸው ፍርድ ቤት ቀርበው ክስ ካለባቸውም በይፋ የሚከሰሱበትን የሚከሰሱበት ክስ ከሌላቸውም ከአፈናዊው እስር የሚለቀቁበትን ሁኔታ ለመፍጠር ጉዳያቸውን ይዞ ፍርድ ቤት ክስ መክፈት ችሎ ነበር።
በዚህም የቤተሰባቸው ጥረት ፍርድ ቤቱ ከአንዴም ሁለት ሶስት ጊዜ ለገላን ፖሊስ ጣቢያ በጻፈው የማዘዣ ደብዳቤ ደራሲና ጋዜጠኛ ጋሽ ታዲዮስ ታንቱን ለችሎት እንዲያቀርብ ብሎ ቢያዝም ጣቢያው ግን እኔ በእሳቸው ላይ የማዘዝ ፍርድ ቤት የማቅረብም ሆነ ያለማቅረብ ስልጣን የሌለኝ የአደራን እስረኛን ጠባቂ ነኝ እያለ በመመለስ የፍርድ ቤቱን ትእዛዝ ሳይፈጽም ቀረ።
እንደ የገላን ፖሊስ ጣቢያ ምላሽ ጋሽ ታዲዮስ ታንቱን አንዴ አዲስ አበባ ሜክሲኮ  በሚገኘው ወንጀል ምርመራ እስር ቤት ለጥቆም በኦሮሚያ በሚገኘው አዋሽ እስር ቤት ቀጥሎም በገላን እስር ቤት እያቀያየር አፍኖ በማሰር ላይ ያለው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን በቤተሰብ ብርቱ ያላሰለሰ ጥረት ፍርድ ቤቱ የገላን ፖሊስ ጣቢያ ጋሽ ታዲዮስ ማቅረብ ካልቻለ የጣቢያው አዛዥም ታስሮ ይቅረብ እስከማለት ደረጃ በደረሰበት ሁኔታ የፊታችን ማክሰኞ መስከረም 18ቀን ቁርጣ የሆነ የፍርድ ቤት ቀጠሮ ተይዞላቸው ሳለ ዛሬ ከገላን ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው መሰወራቸውን ነው ኮሚቴው ከባለቤታቸው ማረጋገጥ የቻለው።
በዚህ ሳምንት አጋማሽ ላይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በኦነግ ሸኔ መሪነቱ በከፍተኛ ወንጀል ተግባር የተሳተፈንና ብሎም በፓርላማው አሸባሪ የተባለን ሰው በምህረት ይቅርታ ተቀበልኩ የሚል ዜናን ባስደመጠን ሁኔታ በአንዲት ወንጀል ነክ ተግባር ላይ ተሰማርተው የማያውቁትን የእድሜ ባለጸጋ ደራሲና ጋዜጠኛ ጋሽ ታዲዮስ ታንቱን ግን ከእስር ቤት እስር ቤት እያንከራተተ ይህንን መሰል ግፍና ስቃይን የኦሮሚያው ፖሊስ ኮሚሽነር ለምንከንደሚፈጽምባቸው በግልጽ ባይታወቅም የጋሽ ታዲዮስ እውነተኛነት እውነተኛ የታሪክ ምስክርነት እና ብሎም ስለኢትዮጲያ ስለአዲስ አበባና ስለአማራው እውነተኛ ታሪክን በግልጽና በአደባባይ በማሰማታቸው እንደሆነ ጥያቄ የሚያስነሳ እንዳልሆነ እናውቃለን።
አሸባሪ ነፍሰ ገዳይን በምህረት ተቀብያለሁ የሚለን አቢይ መራሹ መንግስት ለእስር እንኴን የማይመቹትን ጎምቱ አዛውንትን ደብዛ እያጠፋ የሚያሰቃይ በቀልተኛ አረመኔ መሆኑን የጋሽ ታዲዮስ ስቃይ ከቃል በላይ ይገልጻል።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር በፍርድ ቤት በኩል እየቀረበለት ያለውን ተደጋጋሚ የማዘዣ ጥሪን ለማስቀረት በሚያስችል መልኩ የግሉ እስረኛ ያደረጋቸውን ጋሽ ታዲዮስ ታንቱን ከነበሩበት የገላን ፖሊስ ጣቢያ አውጥቶ ደብዛቸውን ማጥፋት እንደ አማራጭ መፍትሄነት እየተጠቀመ መሆኑን መረዳት የሚቻል ሲሆን በዚህም ምክንያት የጋሽ ታዲዮስ ህይወት በከፍተኛ አደጋ ላይ የወደቀ መሆኑን ስለሚያሳይ መላው ኢትዮጲያዊያን በሙሉ ስለእኚህ አዛውንት ድምጽ ሆኖ ማስተጋባት ይኖርባቸዋል።
ይህንን አይን ያወጣን አረመኔያዊነትን ኢትዮጲያዊ ሁሉ በአንድ ድምጽ በማውገዝ የጋሽ ታዲዮስ ድምጽ መሆን ይገባዋል።

ፍትህ ለጋሽ ታዲዮስና ለህሊና እስረኞች በሙሉ!!!

Filed in: Amharic