>

በአቶ እስክንድር ነጋ ላይ ስለተፈጸመው ከባድ ድብደባ ጠ/አ/ህግ አስቸኳይ ማብራሪያ እንዲሰጠን እንጠይቃለን!!! 

በአቶ እስክንድር ነጋ ላይ ስለተፈጸመው ከባድ ድብደባ ጠ/አ/ህግ አስቸኳይ ማብራሪያ እንዲሰጠን እንጠይቃለን!!! 
     በግፍ እስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ፕሬዚደንት አቶ እስክንድር ነጋ በሚኖሩበት ቂሊንጦ ወህኒ ቤት ውስጥ ጥቅምት 11/2014 ዓ.ም. ንጋት 12፡20 ደቂቃ ላይ ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል፡፡
    ከአቶ እስክንድር ነጋ ጋር አብረው በእስር ላይ ያሉት የፓርቲው የአደረጃጀት ጉዳዮች ሓላፊ አቶ ስንታየሁ ቸኮል ጥቅምት 11 ቀን 2014 ዓ.ም. በነበረው የፍርድ ቤት ቀጠሮ የተገኙ ሲሆን የባልደራስ ፕሬዘዳንት ወህኒ ቤት ውስጥ በተደራጀ የውንብድና ቡድን መደብደባቸውን ተናግረዋል። በዚህም ምክንያትም አቶ እስክንድር ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳልቻሉ ገልጸዋል።
   ከችሎት መልስ የአቶ እስክንድር ጠበቆች፣ ቤተሰቦቻቸው፣ የባልደራስ አመራሮችና አባላት ወደ ቂሊንጦ ወህኒ ቤት ሄደው ለመጠየቅ ቢሞክሩም አቶ እስክንድር ከታሰሩበት ክፍል ወጥተው ማነጋገር አልቻሉም። ሆኖም በተፈጸመባቸው ድብደባ ግንባራቸው፣ ዓይናቸው አካባቢ እና  ጉልበታቸው ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ፓርቲያችን አረጋግጧል። ነገር ግን ለደረሰባቸው ጉዳት የተደረገላቸው ህክምና አለመኖሩም ታውቋል። ስለዚህ በአስቸኳይ ቤተሰቦቻቸው ወደ መረጡት ሆስፒታል ተወስደው እንዲታከሙ እንጠይቃለን።
    ድብደባው በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና መሥሪያ ቤቱን በቀጥታ በሚቆጣጠረው ጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ ሊፈጸም እንደቻለ መገመት አስቸጋሪ አይሆንም። ይህም የኅሊና እስረኞችን በተለይም የአቶ እስክንድር ነጋን ህይወት ለመቅጠፍ የሕብረተሰቡን አስተሳሰብ ማለማመጃ ምዕራፍ እንደሆነ ባልደራስ ይረዳል። በመሆኑም ስለተፈጸመው ከባድ ድብደባ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በቀጥታ ለሕዝብ መግለጫ እንዲሰጥ እንጠይቃለን።
    ፓርቲያችን ይህንን የሚለው አቶ እስክንድር ነጋ ከዚህ በፊት በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ፣ በቃሊቲ ወህኒ ቤት እንዲሁም ሰኔ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በወታደር ቁጥጥር ስር በዋሉበት ጊዜ እና ቢሯቸው ውስጥ የደረሱባቸውን በመጠን የተለያዩ ድብደባዎች ሁሉ በማስታወስ ነው።
    ከዚህ ጋ በተያያዘም ጥቅምት 11/2014 ዓ.ም. በነአቶ እስክንድር ነጋ የፍርድ ሂደት ችሎት ታድመው የነበሩ 42 የፓርቲያችን አባላት ታፍሰው ልደታ ክፍለ ከተማ የፖሊስ መምሪያ  ከቆዩ በኋላ አመሻሹ ላይ 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው እንዲታሠሩ ተደርገዋል። ከታሠሩት ውስጥ 12ቱ ሴቶች መሆናቸውም ተረጋግጧል፡፡ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የታሠሩት አባሎቹ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ ይጠይቃል።
ድል ለዴሞክራሲ!!!
Filed in: Amharic