>
5:13 pm - Wednesday April 19, 8828

"በወለጋ በኦነግ/ሸኔ ታግተው ሲፈለጉ  የሰነበቱ አባት  አስክሬናቸው በእሳት ተቃጥሎ ተገኘ....!!!" (ጌጥዬ ያለው)

“በወለጋ በኦነግ/ሸኔ ታግተው ሲፈለጉ  የሰነበቱ አባት  አስክሬናቸው በእሳት ተቃጥሎ ተገኘ….!!!”

ጌጥዬ ያለው

አቶ ዓለም ይብሬ ይባላሉ። በአማራነታቸው ፈርጆ በአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት እንደሚደገፍ የዓይን ምስክሮች የሚናገሩለት ኦነግ/ሸኔ አግቶ ከወሰዳቸው ቀናት አልፈዋል። “የወረዳው ባለሥልጣናት እንዲያፋልጉን ብንናመለክትም፤ አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ ሆኑብን” ይላሉ ከጅምላ ጭፍጨፋ የተረፉ ቤተሰቦቻቸው።
ሲፈለጉ የሰነበቱት አቶ ዓለም  በሚኖሩበት በኦሮሚያ መስተዳድር ሆሮጉድሩ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ ሀርቡ ነጋሶና ደርጌ ኮትቻ ቀበሌ ባለፈው የካቲት 5 ቀን 2014 ዓ.ም. አስክሬናቸው በእሳት ተቃጥሎ ተገኝቷል። እንደ ቤተሰቦቻቸው ገለፃ ሽብርተኛው ቡድን ከእነ ነፍሳቸው ያቃጥላቸው ወይም ከሞቱ በኋላ የሚታወቅ ነገር የለም። ወንድማቸው አቶ ቃሲም ይብሬ ደግሞ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ታግተው እንደተወሰዱ ደብዛቸው ጠፍቷል።
በእሳት ተቃጥሎ የተገኘው የአቶ ዓለም ይብሬ አስክሬን ከፊል አጥንቶች የተለያየ ቦታ ተበታትነው እንደተገኙ የዓይን እማኞች ተናግረዋል። አጥቶቹን ለመሰብሰብ የሞከሩ የቤተሰብ አባላትም እንዳይሰበስቡ ተከልክለዋል። በሁለተኛው ቀንም በጅምላ ታስረዋ። ከየካቲት 6 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ ፖሊስ ፅ/ቤት ታስረው የሚገኙት የቤተሰብ አባላት የሚከተሉት ናቸው፦
1- አብዱል ፈታህ ይመር (የ1 ዓመት ሕፃን)
2- ዘይነባ ሰይድ (እናታቸው ለገበያ ወጥተው ስለነበር ልጁ አዝላ የነበረች አዳጊ)
3-ፈለቄ ይመር (ሴት አዛውንት)
4- ሞሚና ሰይድ (የ5 ዓመት ልጅ)
5- ሐዋ ሰይድ (የ7 ዓመት ልጅ)
6- ተስፋዬ ገሰሰ (የ70 ዓመት አባት)
7- ኡስታዝ አረቡ ያሲን (የሃይማኖት አባት)
በአካባቢው የሚገኙ ሌሎች አማሮችም በኦነግ/ሸኔ ላይ “ጥቃት ሰንዝራችኋል” በሚል መታሰራቸውን ምንጮች ገልፀዋል።  “መንግሥት በሽብርተኛነት በፈረጀው ሃይል ላይ ‘ጥቃት አድርሳችኋል’ ተብሎ ሰው አይታሰርም። አድርገውትም ቢሆን መቀጣት የለባቸውም” በማለት የሞገቱ አማራ የፌዴራል ፖሊስ አባላትም አብረው ታስረዋል።
Filed in: Amharic