>

የአማራ ለምድ የለበሱ የብአዴን ፀራማራ ተኩላወች!   (መስፍን አረጋ)

የአማራ ለምድ የለበሱ የብአዴን ፀራማራ ተኩላወች!

መስፍን አረጋ

 

መንደርደርያ

ወያኔ፣ ኦነግና የብአዴን ፀራማራ ተኩላወች በአማራ ሕዝብ ላይ የሚረባረቡት እየተናበቡ ሲሆን፣ ዋሳኙን ሚና የሚጫወቱት ደግሞ ተኩላወቹ ናቸው፡፡  ለምሳሌ ያህል ወያኔው ጌታቸው ረዳ በትግራይ ቲቪ ላይ በቅርቡ በሰጠው ቃለ መጠይቅ፣ ከአማራ ሕዝብ ጀርባ ለሚደረገው ለወያኔና ለኦነግ ፀራማራ ድርድር እንቅፋት የሆነው ጎንደር ነው በማለት ጎንደርን ነጥሎ በይፋ ከሰሰ፡፡  የጌታቸው ረዳን ክስ ተከትሎ ደግሞ የብል()ግና የደሕንነት አለቃ የሆነው የብአዴኑ ፀራማራ ተመስገን ጥሩነህ ሐይማኖትን ሰበብ ባደረገ በተቀናበረ ቀውጥ (engineered chaos) ጎንደርን ቀወጣት፡፡  የተመስገን ጡሩነህን የተቀናበረ ሐይማኖታዊ ቀውጥ ተከትሎ ደግሞ ኦነጋዊው ዐብይ አሕመድ በፋኖ ላይ በብአዴኑ ፀራማራ በአበባው ታደሰ የሚመራ ዘመቻ  ከፈተ፡፡  

የትም ይወለዱ የትም፣ ደመቀ መኮንንን፣ ተመስገን ጥሩነህንና እና አበባው ታደሰን የመሳሰሉ አማራዊነት የሌላቸው የብአዴን ፀራማራ ተኩላወች ያላቸው ቋሚ ባሕሪ አንድና አንድ ብቻ ሲሆን፣ እሱም እጅግ የከረረ የአማራ ጥላቻ ነው፡፡  ስለዚህም ፀራማራ የሆነን ማናቸውንም ቡድን በሎሌነት ለማገልገል ሙሉ ፈቃደኞች ብቻ ሳይሆኑ፣ ሙሉ ደስተኞችም ናቸው፡፡  በመለስ ዜናዊ ዘመን የወያኔ ታማኝ ሎሌወች እንደነበሩ ሁሉ፣ በዐብይ አሕመድ ዘመን ደግሞ የኦነግ ታማኝ ሎሌወች ሁነዋል፡፡  ከወያኔ ሎሌነት ወደ ኦነግ ሎሌነት በቀጥታ መሻገራቸው ደግሞ ለሌላ ሰው እንጅ ለነሱ ምንም ተቃርኖ የለውም፡፡  ለነሱ የሚታያቸው ፀራማራነት ብቻ ስለሆነ፣ በነሱ ዕይታ መሠረት በወያኔና በኦነግ መካከል አንዱ የትግሬ ሌላው የኦሮሞ ፀራማራ ከመሆኑ በስተቀር ሌላ ልዩነት የለም፡፡  ስለዚህም እነዚህን የብአዴን ተኩላወች ይበልጥ የሚያረካቸው ሁለቱ ፀራማራወች (ማለትም ወያኔና ኦነግ) ባንድነት ተባብረው አማራን ይበልጥ ቢያጠቁላቸው ከቻሉ ደግሞ ሕልውናውን ቢያጠፉላቸው ነው፡፡  ወያኔና ኦነግ በአማራ ላይ ባንድነት እንዳይረባረቡ እንቅፋት የሆኑትን ፋኖን፣ የአማራ ሚሊሻንና ልዩ ኃይልን ለማጥፋት ቆርጠው የተነሱበት ምክኒያትም ይሄውና ይሄው ብቻ ነው፡፡ 

የአማራ ሕዝብ ሕልውናውን ለማስጠበቅ ሲል ብቻ አማራነትን እንዲያቀነቅን ሳይወድ በግዱ ተገዷል፡፡  ስለዚህም ትግሬ በትግሬ፣ አሮሞ በኦሮሞ ተወክሎ እያለ፣ አማራ ግን የአማራ ለምድ በለበሱ ፀራማራ ተኩላወች መወከል የለበትም፡፡  ስለዚህም የአማራ ሕዝብ ሆ ብሎ መነሳት ያለበት እነዚህን ወያኔና ኦነግ በጫንቃው ላይ የጫኑበትን፣ የአማራ ለምድ የለበሱ ፀራማራ ተኩላወች ከጫንቃው ላይ አውርዶ አሽቀንጥሮ ለመጣል ነው፡፡  ይህን ካደረገ ደግሞ የራሱን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ሕልውና እንደሚያስጠብቅ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡  አማራ በአማራዊ መሪ ከተመራ፣ ወያኔና ኦነግ እዳቸው ገብስ ነው፡፡          

የብአዴን ፀራማራ ተኩላወች

ደመቀ መኮንን፣ ተመስገን ጥሩነህ፣ አበባው ታደሰና መሰሎቻቸው፣ እውን አማራን ከድተዋል?

የታላቁ ሊቅ ያለቃ ደስታ ተክለወልድ መዝገበ ቃላት (ገጽ 639) በዝርዝር እንደሚያስረዳው፣ ከዳ የሚለው ቃል የተለያዩ ትርጉሞች አሉት፡፡  ለምሳሌ ያህል ከዳ ማለት አንዳለጠ፣ አንሸራተተ፣ ጣለ፣ አወደቀ ማለት ሊሆን ይችላል፣ መሬቱ ከዳው እንዲሉ፡፡   ከዳ ማለት አመጸ፣ ለጌታው አልታዘዝ አለ፣ ጌታውን ነከሰ ማለትም ሊሆን ይችላል፣ አፍ ሲከዳ ከሎሌ ይብሳል እንዲሉ፡፡  አብዛኛውን ጊዜ ግን ከዳ የሚለውን ቃል የምንጠቀመው አንዱን መወገኑን አቁሞ ተቃራኒውን ወገነ በሚለው ትርጉሙ ነው፡፡  ስለዚህም አማራን ከዳ የምንለው ከአማራ ጋር መወገኑን አቁሞ ከፀራማሮች ጋር የወገነን ግለሰብ ነው፡፡ 

ደመቀ መኮንን፣ ተመስገን ጥሩነህ፣ አበባው ታደሰና መሰሎቻቸው ግን ታሪካቸው በግልጽ እንደሚመሰክርባቸው አማራ መስለው አማራን እንዲያጠቁና እንዲያሰጠቁ በቀንደኛው ፀራማራ በበረከት ስምዖን ለወያኔ ሎሌነት የተመረጡ፣ የአማራ ለምድ የለበሱ ፀራማራ ተኩላቸወች ናቸው፡፡  እነዚህ ፀራማራ ተኩላወች መቸም ጊዜ ቢሆን ከአማራ ጋር ወግነው ስለማያውቁ አማራን ከዱ ሊባሉ አይችሉም፡፡  ስለዚህም ያልከዱትን አማራ ከዱ ተብለው ያለ ኃጢያታቸው መወቀስ የለባቸውም፡፡  

እነ ደመቀን አማራን ከዱ የሚሉ ሰወች ይህን ለማለት የበቁት የነደመቀ ስም አማራዊ ስለሆነ ይመስለኛል፡፡  አማራዊ ስም ግን አማራዊነትን አያመለክትም፡፡  አማራ ሁኖ ለሆዱ ሲል የፀራማሮች ሎሌ የሆነ ሆዳደር አማራ አለ፡፡ አማራን መስሎ አማራን ለመጉዳት ሲል ብቻ፣ አማራ ሳይሆን አማራ ነኝ የሚል የቁጩ አማራ አለ፡፡  አማራ ሁኖ ያማራ ጉዳይ ግድ የማይሰጠው ባይተዋር አማራ አለ፡፡  አማራ ሁኖ አማራነቱን እንዲጠላ የተደረገ ራስጠል አማራ አለ፡፡  አማራ ሁኖ የፀራማሮችን የጭቃ ጅራፍ ስለሚፈራ ብቻ አማራነቱን የሚያድበሰብስ ቱርቂ አማራ አለ፡፡  አማራ ሁኖ ከአማራነት በላይ ነኝ በሚል ውሃ በማይቋጥር ምክኒያት የአማራን ሰቆቃ ዓይቶ እንዳላየ የሚያልፍ ተመጻዳቂ አማራ አለ፡፡  አማራ ሁኖ ጎጠኞች እንዳይቀየሙና ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ አማራ ሲሞት አማራ ሞተ አትበሉ የሚል፣ የኢትዮጵያ ምሰሶ ወድቆ ኢትዮጵያ ትቆማለች ብሎ የሚያስብ ደነዝ አማራ አለ፡፡  አማራ ሁኖ ….

አዲሱ ለገሰ፣ ተፈራ ዋልዋና፣ ከበደ ጫኔ አማራ መስለው አማራን እንዲያስጠቁ ወያኔ የአማራ ስም ያወጣላቸው የቁጩ አማሮች ናቸው፡፡  በአዲሱ ለገሰ፣ ተፈራ ዋልዋና ከበደ ጫኔ እግር ተተክተው የኦነግን ፀራማራ ፖሊሲ በከፍተኛ ስልጠት (efficiency) እየተገበሩ ያሉት ደግሞ ቆንጆ ያማራ ስም ያላቸው፣ የቁጩ አማሮች የሆኑት ደመቀ መኮንን፣ ተመስገን ጡሩነህ፣ አበባው ታደሰ፣ ይልቃል ከፋለ፣ ብናልፍ አንዷለምና መሰሎቻቸው ናቸው፡፡ 

ለምሳሌ ያህል ደመቀ መኮንንን ብንወስድ፣ አማራዊነት ሳይኖረው አማራን እንዲወክል ተደርጎ የወያኔን ፀራማራ ሕገመንግሥት በማርቀቅ ከፊተኛ ሚና የተጫወተና በመጫወቱ የሚኮራ፣ ትምህርት ሳይኖረው የትምህርት ሚኒስቴር ተደርጎ በአማራ ታዳጊወች ላይ ይቅር የማይባል እጅግ ከፍተኛ ወንጀል የፈጸመ፣  ቅንጣት የመሪነት ብቃት ሳይኖረው የአማራ ቅንጡ መሪ ተደርጎ የአማራን ሕልውና ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ፀራማራ ነው፡፡ 

ደመቀ መኮንን በትምህርቱ ብዙም ያልገፋ ከመሆኑም በላይ ራሱን በራሱ የሚያስተምር ዓይነት ሰው አይደለም፡፡  በዚያ ላይ ደግሞ የሚያውቃትን በደንብ መግለጽ የማይችል አንደበተ ግድር (challenged) ከመሆኑም በላይ በራስ መተማመን የሚባል ነገር ምናምኒትም እንደሌለው በግልጽ ያስታውቅበታል፡፡  ይባስ ብሎ ደግሞ ኃላፊነት መውሰድን እንደ ጦር የሚፈራ የዣግሬነት ሰብዕና (follower mentality) በጽኑ የተጠናወተው፣ ለጀሌነት እንጅ ለመሪነት ያልተፈጠረ ግለሰብ ነው፡፡  

ይህን በእውቀትና በመንፈስ ደካማ የሆነ የምድረገነት (ከሚሴ) ግለሰብ፣ ላኮመልዛ (ወሎ) የኦሮሞ ነው በሚለው የኦነጋውያን የፈጠራ ትርክት አጭበርብሮ ወደ ቀንደኛ ኦነጋዊነት ለመቀየር፣ ላጭበርባሪው ዐብይ አሕመድ እጅግ በጣም ቀላል ነው፡፡  የደመቀ መኮንን ተግባር በግልጽ የሚያመለክተው ደግሞ ግለሰቡ በዐብይ አሕመድ ኦነጋዊ ስብከት ታውሮ፣ ከወያኔነት ወደ ኦነጋዊነት ተቀይሮ፣ ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ እንዲሉ ከራሱ ከዐብይ አሕመድ በላይ ጽንፈኛ ኦነጋዊ ሁኖ፣ የኦነጋውያንን ፀራማራ አጀንዳ ከዐብይ አሕመድ በላይ እያራመደ መሆኑን ነው፡፡  የአማራ ሕዝብ መሪ ነኝ እያለ፣ አማራ ሕዝብ በኦነግ ሲጨፈጨፍ ዝንብ የሞተ ሳይመስለው ድመጹን አጥፍቶ የተቀመጠው የአማራን ለምድ የለበሰ ኦነጋዊ ተኩላ በመሆኑ ብቻ ነው፡፡   

የሰኔ አስራምስቱ የባሕርዳር ጭፍጨፋ ሚስጥር ቁልፉ ያለው ደመቀ መኮንን የአማራን ለምድ የለበሰ ኦነጋዊ ተኩላ መሆኑን በመረዳትና በጭፍጨፋው ወቅት ቦሌ አየር ወደብ ውስጥ ጃኖች መንፈላሰሻ  (vip lounge) ተቀምጦ ምን ሲያደርግ እንደነበር አጥብቆ በመጠየቅ ነው የሚባለውም በዚሁ ምክኒያት ነው፡፡  ደመቀ መኮንን በራስ መተማመን  እጥረት የሚሰቃይ ሰው ስለሆነ፣ እነከሌ በማንነትህና በምንነትህ ይንቁሃል ብሎ በመስበክ ለበቀል እንዲነሳሳ ማድረግ ለሐሳዊ ተዋኙ (con artist) ለዐብይ አሕመድ የሕጻን ጨዋታ ያህል ቀላል ነው፡፡  የፈሪ ብትር ሆድ ይቀትር እንዲሉ፣ እንደ ደመቀ ዓይነት ቱርቂ ለበቀል ከተነሳሳ ደግሞ ብትሩ በጣም አሰቃቂ ነው፡፡  ዐብይ አሕመድ ደመቀ መኮንንን በበቀል ስሜት አነሳስቶ ባሕርዳር ላይ ለፈጸመው አሰቃቂ ወንጀል ግብራበሩ ካደረገው ደግሞ፣ ወንጀለኛነቱን እንደ ማስፈራርያ በመጠቀም ሲጠራው ወዴት፣ ሲልከው አቤት፣ ዝቀጥ ሲለው እስከየት የሚል፣ አፋሽ አጎንባሽ ሎሌው ያደርገዋል፣ አድርጎታልም፡፡  

ተመስገን ጡሩነህ ደግሞ ዐብይ አሕመድን ለማስደሰት እንጦረንጦስ ለመውረድ ዝግጁ የሆነ፣ በዐብይ አሕመድ ስም ምሎ የሚገዘት፣ የዐብይ አሕመድ ባልደረባ ሳይሆን ጃንደረባ ነው፡፡  ተመስገን ጡሩነህ ሲፈጠር ጀምሮ አማራዊነት የሌለው ወይም ደግሞ አማራዊነቱን በዐብይ አሕመድ የተሰለበ የዐብይ አሕመድ ደንገጡር ነው፡፡  ተመስገን ጡሩነህ ለሰኔ አስራምስቱ የባሕርዳር ጭፍጨፋ ከዐብይ አሕመድ ቀጥሎ ዋናው ተጠያቂ ወንጀለኛ ነው፡፡  ተመስገን ጡሩነህ ከኦነጋውያን በላይ ኦነጋዊነት የሚሰማው የአማራ ለምድ የለበሰ ኦነጋዊ ተኩላ ነው፡፡  ተመስገን ጡሩነህ  የአማራ ጥላቸው ከውስጡ እየገነፈለ ግንባሩ ላይ ተንጨፍጭፎ እፊቱ ላይ በመከልበስ በግልጽ የሚነበብበት፣ አማራ ጨፍጫፊወችንና አስጨፍጫፊወችን ለማመስገንና ለመሸለም የሚቀድመው የሌለ ወደር የሌለው አማራጠል ነው፡፡  ተመስገን ጡሩነህ ፋኖን ሳያጠፋ ላያንቀላፋ በጌታው በዐብይ አሕመድ ስም ምሎ የተገዘተ ፀረፋኖ ነው፡፡  ተመስገን ጡሩነህ እመራዋለሁ የሚለውን የአማራን ሕዝብ ‹‹ወንጀለኞችን የሚያወድስ ማሕበረሰብ›› በማለት ሸንጎ ላይ በይፋ በመሳደብ የአለምነው መኮንንንየሽመልስ አብዲሳንና የታየ ደንድኣን ስድብ የደገመ፣ በአማራ ሕዝብ ላይ ዐብይ አሕመድ የጫነው ትልቅ መርገምት ነው፡፡    

አበባው ታደሰ ደግሞ በወያኔ ጊዜ ልዩ ተልእኮ እየተሰጠው አማራዊ የጦር መኮንኖችን ያሳድድ እንደነበርና በዚህም ምክኒያት በሹመት ዳብሮ በሐብትና በንብረት እንደናረ ሟቹ ደራሲ ተስፋየ ገብረአብ አሳምሮ ተርኮለታል፡፡  በወያኔ ዘመን የጀመረውን ተልዕኮ በኦነግ ዘመን አጠናክሮ እንዲቀጥል ደግሞ የብርሃኑ ጁላ ሎሌ እንዲሆን በዐብይ አሕመድ ተሹሟል፡፡  የብርሃኑ ጁላ ሎሌ ሆኖ በመሾሙ ደግሞ አባዱላ ገመዳ ሎሌነት ያዳብር ብሎ መርቆታል፡፡  ስለዚህም የወያኔንና የኦነግን ፀረፋኖ ዘመቻ እንዲመራ የተመረጠው ይህ የአማራ ጥላቻ የሚያብከነክነው፣ የአማራ ለምድ የለበሰ ፀራማራ ተኩላ መሆኑ ምንም አያስገርምም፡፡      

ኤርትሬው በረከት ስምዖን በአማራ ሕዝብ ላይ የሠራው ትልቁ ወንጀል፣ ብአዴንን የሞላው የደመቀ መኮንን፣ የተመስገን ጥሩነህና የአበባው ታደሰ ዓይነቶችን፣  በማንነት ቀውስ የተጠቁ የመንፈስ መፃጉወችን (hunchbacks) በማሾ እየፈለገ መሆኑ ነው፡፡  ዐብይ አሕመድ አማራን ቀረጣጥፎ እየበላ ያለ ኦነጋዊ አውሬ ሲሆን፣ ጥርሶቹ ደግሞ ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ የአማራ ለምድ የለበሱ ፀራማራ ተኩላወች ናቸው፡፡  ከጥርሶቹ ውስጥ ደግሞ ክራንቻወቹ (ማለትም አማራን የሚዘነጣጥልባቸው በግራና በቀኝ ያገጠጡት ሁለቱ የፊት ጥርሶቹ) ደመቀ መኮንን እና ተመስገን ጥሩነህ ናቸው፡፡  ስለዚህም የአማራ ሕዝብ በኦነጋዊው አውሬ በዐብይ አሕመድ ተቀረጣጥፎ ከማለቁ በፊት ብአዴናዊ ጥርሶቹን ማወላለቅ፣ በተለይም ደግሞ ክራንቻወቹን ማፍለስ የግድ ነው፡፡

 Email:  መስፍን አረጋ mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic