>

አሰብና አልፋሽቃ፤ የዐብይ አሕመድ የወቅቱ ማጭበርበሪያወች!  (መስፍን አረጋ)

አሰብና አልፋሽቃ፤ የዐብይ አሕመድ የወቅቱ ማጭበርበሪያወች! 

መስፍን አረጋ


“የኤርትራን ነጻነት የሚዳፈርን ማናቸውንም ኃይል ከኤርትራውያን በላይ በጽኑ የምንታገለው እኛ ወያኔወች ነን፡፡”  ስብሐት ነጋ

ዐብይ አሕመድ የአማራን ሕዝብ አይንቁ ንቀት ንቆታል፡፡  የአማራ ሕዝብ በዐብይ አሕመድ እንደተናቀ፣ ማንም ሕዝብ ተንቆ አያውቅም፡፡  በዐብይ አሕመድ ኦነጋዊ እሳቤ መሠረት ኦሮሞነታቸውንና ትግሬነታቸውን ከኢትዮጵያዊነታቸው የሚያስቀድሙት ጎጠኞቹ ኦሮሞወችና ትግሬወች የፖለቲካ ብልጦች ወይም ልሂቆች ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያዊነቱን ከአማራነቱ የሚያስቀድመው የጦቢያ ብሔርተኛው የአማራ ሕዝብ ግን የፖለቲካ ቂል ወይም ማይም ነው፡፡  ስለሆነም፣ በዐብይ አሕመድ እሳቤ መሠረት የአማራ ሕዝብ ምንም ብታደርገው ምንም አያመጣም፡፡    

የዐብይ አሕመድ የተግባር ዘይቤ (modus operandi) በአማራ ሕዝብ ላይ መፈጸም የሚፈልገውን ማናቸውንም ዓይነት ወንጀል ከፈጸመ በኋላ ኢትዮጵያን የሚያንቆለጳጵስ ባዶ ዲስኩር በመደስኮር ብቻ የአማራ ሕዝብ የተፈጸመበትን ወንጀል ሙሉ በሙሉ ረስቶ ከሱ ጎን እንዲቆም ማድረግ ነው፡፡  ባለመታደል ይህ የዐብይ አሕመድ የአማራን ሕዝብ የማጭበርበሪያ ዘይቤ እስካሁን ድረስ ለዐብይ አሕመድ በደንብ ሠርቶለታል፡፡  የአማራን ሕዝብ አይንቁ ንቀት የናቀውም በባዶ ዲስኩር የሚታለል ሞኝ ሕዝብ ነው ብሎ ስለሚያስብና እስካሁንም ድረስ ሁኖ ስላገኘው ነው፡፡  ሾርት ሚመሪ እያለ የሚሳደበውም ሌላ ማንንም ሳይሆን የአማራን ሕዝብ ነው፡፡    

እንደ እውነቱ ከሆነ ደግሞ ዐብይ አሕመድ የአማራን ሕዘብ በባዶ ዲስኩር እያጭበረበረ ሕልውናውን ጥያቄ ውስጥ አስገብቶ አንድ ሐሙስ እንዲቀረው ስላደረገው፣ የአማራን ሕዝብ እንደ ሕዝብ ቢንቀው አይፈረድበትም፡፡  አለበለዚያማ የአማራ ሕዝብ ዐብይ አሕመድ የሚባለውን ኦነጋዊ አውሬ ከጫንቃየ ላይ ሳላወርድ እቤቴ ብገባ አማራ አይደለሁም ብሎ እንደ አብናቶቹ (አባቶቹና እናቶቹ) ምሎ መገዘት የነበረበት ከሰኔ 15ቱ የባሕርዳር ጭፍጨፋ ማግስት ሰኔ 16 ላይ ነበር፡፡  የአማራ ሕዝብ በባዶ ዲስኩር ተጭበርባሪ ባይሆን ኖሮ፣ ጀነራል አሳምነውን በግፍ የገደለው ዐብይ አሕመድ፣ ሦስት ዓመት ሙሉ ስልጣን ላይ ሊቆይና ጀነራል ተፈራን ለማሳፈን ሊበቃ ባልቻለ ነበር፡፡  

ጀነራል ተፈራን ያሳፈነው ደግሞ የአማራን ሕዝባዊ ሠራዊት በማጥፋት የአማራን ሕዝብ ሕልውና ለማክተም በከፈተው ከፍተኛ ዘመቻ መሠረት ነው፡፡  ይህ የዐብይ አሕመድ ፀራማራ ዘመቻ ግን በገጠመው ከፍተኛ ተቃውሞ ሳቢያ ዐብይ አሕመድ በሚፈልገው ፍጥነት ሊከናወን አልቻለም፡፡  ስለዚህም ዐብይ አሕመድ ለዚህ ዘመቻው የሚጠቅሙትን የወቅቱን የአማራን ሕዝብ ማማለያ ካርዶች መዟል፡፡  እነዚህ ወቅታዊ የአማራ ሕዝብ ማማለያ ካርዶች ደግሞ አልፋሽቃ (al-fashqua) እና አሰብ ናቸው፡፡  ካርዶቹ የአማራን ሕዝብ ይበልጥ እንዲያማልሉለት ደግሞ የመዘዛቸው የአማራ ለምድ በለበሰው በፀራማራው ተኩላ በደመቀ መኮንን አማካኝነት ነው፡፡      

ወልቃይትና ራያን ለወያኔ ለማስረከብ ከወያኔ ጋር በአማራ ሕዝብ ስም በአማራ ሕዝብ ጀርባ እየተደራደረ ያለው ፀራማራው ተኩላ ደመቀ መኮንን፣ አሁን ላይ በድንገት ብድግ ብሎ አልፋሽቃን ከሱዳን እናስመልሳለን እያለ ባዱ ጉራ መንፋት ጀምሯል፡፡  ኢትዮጵያን ባሕር በር ዐልባ ያደረጋትን ፀራማራውን መለስ ዜናዊን በትምህርት ሚኒስቴርነትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴርነት በፍጹም ሎሌነት በማገልገሉ ከፍተኛ ኩራት የሚሰማው ይህ ፀራማራ ተኩላ፣ አሁን ላይ ግን በድንገት ብድግ ብሎ የኢትዮጵያ የባሕር በር እጦት እንቅልፍ የነሳው ማስመሰል ጀምሯል፡፡  ይህን ሁሉ የሚያደርገው ግን ለአልፋሽቃ ወይም ለአሰብ ግድ ኑሮት ሳይሆን፣ የአማራን ሕዝብ በባዶ ዲስኩር ደልሎ የትኩረት አቅጣጫውን በመቀየር፣ በፋኖ ላይ የተከፈተውን መጠነ ሰፊ ዘመቻ በስኬት ለማጠናቀቅ ሲል ብቻና ብቻ ነው፡፡    

ሰፊው የአማራ ሕዝብ ሆይ፡፡  አሁን ላይ ያንተ አንገብጋቢ ጥያቄ የመኖር ያለመኖር ጥያቄ ስለሆነ ሙሉ ትኩረትህን ማድረግ ያለብህ በሕልውና ጠላቶችህ በወያኔና በኦነግ ላይ ብቻና ብቻ ነው፡፡  እየየም ሲደላ ስለሆነ፣ አሁን ላይ አልፋሽቃና አሰብ ላንተ የቅንጦት ቃሎች ናቸው፡፡  ዝንጀሪት እንዳለቸው በመጀመርያ የመቀመጫየን ነው፡፡  ስለዚህም፣ ወያኔና ኦነግ ብአዴንን ከፊት አሰልፈው፣ በራስህ ምድር ላይ በማንነትህ እየጨፈጨፉህ ባሉበት ሰዓት፣ ስለ ጦቢያ የባሕር በር መጨነቅ ቀርቶ ማውራት የለብህም፡፡  ፀራማራው ተኩላ ደመቀ መኮንን አልፋሽቃን አስመልስልሃለሁ እያለ ሊያነሆልልህ ሲሞክር ደግሞ፣ እንደምታወራው እውነትም አስመላሽ ከሆንክ፣ ወደ ሱዳን ከመዞርህ በፊት አንተው ራሰህ ከወያኔና ከኦነግ ጋር ተመሳጥርህ ያስወሰደክብኝ ራያንና ደራን አስመልስልኝ በማለት አሳፍረህ መልሰው፡፡

ሰፊው የአማራ ሕዝብ ሆይ፡፡  እዚህ ግቡ ይባሉ ያልነበሩት ወያኔና ኦነግ ያንተን የጀግናውን የአማራን ሕዝብ ሕልውና ከጥያቄ ውስጥ ሊያስገቡ የቻሉት ምዕራባውያን ቅኝናፋቂወች (neocolonialists) (በተለይም ደግሞ ያሜሪቃና የእንግሊዝ ቅኝናፋቂወች) በሚሰጧቸው ሙሉ የቁሳቁስና የቱልቀዳ (propaganda) ድጋፍ ነው፡፡  ምዕራባውያን ቅኝናፋቂወች አንተን የአማራን ሕዝብ ነክሰው የያዙህ ደግሞ ላፍሪቃ (ብሎም ለመላው ጥቁር ሕዝብ) ነጻነት ፋና ወጊ በመሆንህ ነው፡፡  የሕልውና ጠላቶችህ ወያኔ፣ ኦነግና የአማራ ለምድ የለበሱት የብአዴን ፀራማራ ተኩላወች ብቻ ሳይሆኑ፣ ምዕራባውያንም ጭምር ናቸው፡፡      

ሁኔታወች በግልጽ እንደሚያመለከቱ ደግሞ ባሁኑ ሰዓት ባቅራቢያህ የሚገኘው ያንተ የአማራ ሕዝብ ወዳጅ አንድና አንድ ብቻ ሲሆን፣ እሱም የኤርትራው መሪ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ነው፡፡  ይህን ሊታበል የማይችል ሐቅ ደግሞ እያነቀህም ቢሆን መዋጥ ይኖርብሃል፡፡  እርግጥ ነው፣ አቶ ኢሳያስ የሚወድህ ሊወድህ ፈልጎ ሳይሆን ሊወድህ ስለተገደደ ሊሆን ይችላል፡፡  ይህ ግን ሊገርምህም ሊያስገርምህም አይገባም፣ ፖለቲካ ማለት እከከኝ ልከከህ ነውና፡፡  

በሌላ በኩል ደግሞ ኤርትሬወች እንደ ወያኔወችና ኦነጎች በጎጣቸው ሳይሆን፣ ልክ እንዳንተ እንደ አማራ ሕዝብ ባገራቸው ኩሩ ስለሆኑ፣ ከኤርትሬወች ጋር በመከባበር ላይ የተመሠረተ ትብብር ከፈጠርክ፣ ትብብሩ ጊዜያዊ ሳይሆን ዘላቂ የመሆኑ እድል ከፍተኛ ነው፡፡  ከኤርትራወች ጋር ባስተሳሰብ ተመሳሳይ ስለሆንክ፣ ቅራኔ ቢኖርህም ቅራኔው የሚሆነው በጥቅም ላይ የተመሠረተ ቅራኔ ነው፡፡   ይህ ዓይነት ቅራኔ ደግሞ በውውይትና ሰጥቶ በመቀበል የሚፈታ መሠረታዊ ያልሆነ ቅራኔ ነው፡፡  

ከወያኔና ከኦነግ ጋር ያለህ ቅራኔ ግን በማንነትህ ላይ የተመሠረተ መሠረታዊ ቅራኔ ስለሆነ፣ ቅራኔው የሚፈታው ወይ አንተ እነሱን ስታጠፋቸው ወይ እነሱ አንተን ሲያጠፉህ ብቻ ነው፡፡  ከወያኔ ጋር መቸም የማትታረቅ ዓይንና ናጫ፣ ከኦነግ ጋር ደግሞ መቸም የማትደባለቅ እሳትና ጭድ መሆንህን መቸም መዘንጋት የለብህም፡፡   

ዐብይ አሕመድ ደግሞ አማራን የሚበላ የሚናገር አውሬ ነው፣ ጭካኔው ወደር የሌለው ኦነጋዊ አውሬ፡፡    ስለዚህም ወልቃይትና ራያን ሊነጥቅህ ከወያኔ ጋር የተፈራረመው ዱርየው ዐብይ አሕመድ፣ በደንገጡሩ በደመቀ መኮንን አማካኝነት ስለ አልፋሽቃና አሰብ የሚደሰኩርልህ፣ ፊትህን ወደ አልፋሽቃና አሰብ ስታዞር ማጅራትህን በቆንጨራ ቆርጦ፣ ደምህን መጦ፣ ሥጋህን ግጦ፣ አጥንትህን ቀጥቅጦ አጣጥሞ ሊበላህ መሆኑን ተረድተህ ለሱ በሚገባው በዱርየ ቋንቋ ፋራህን ብላ በለው፡፡ 

በወያኔና በኦነግ ትብብር ሕልውናህ ከጥያቄ ውስጥ የገባው ሰፊው የአማራ ሕዝብ ሆይ፡፡  ለራስህ ሕልውና ስትል የኤርትራን ሕልውና ከወያኔና ከኦነግ አውሬወች ጠብቅ፡፡  የወያኔው አውሬ አቶ ስብሐት ነጋ ባንድ ወቅት  “አማራን ኤርትራን ሊወጋ ቢሞክር፣ ከኤርትራውያን በላይ በጽኑ የምንዋጋው እኛ ወያኔወች ነን” የሚል መልዕክት ያዘለ ንግግር ተናግሮ ነበር፡፡  አሁን ላይ ደግሞ አንተም በተራህ “ኤርትራን የነካ አማራን ነካ” በማለት ከማን ጋር እንደቆምክ ለሕልውና ጠላቶቸህን ለአውሬወቹ ለወያኔና ለኦነግ በግልጽ አሳውቃቸው፡፡  

ዐብይ አሕመድ ዐሊ የኦነጉ ኦቦ

አፉና ምግባሩ ሐራምባና ቆቦ፡፡

ባንደበቱ መስሎ የኢትዮጵያ ሙሴ

በምግባሩ ሆነ የኦነግ ራምሴ፡፡

በመውረስ ያገኘው ከወያኔ አባቱ

መዋሸት ማጭበርበር ነውና ፍጥረቱ፣

አንዴ ቢሸውደን የሱ ነው ኀፍረቱ

ሁለቴ ቢደግም የኛ ነው ጥፋቱ፡፡

Email:  mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic