መንደርደርያ
ኢትዮጵያ በታሪክ የእርስ በርስ ጦርነትን እንደ ትልቅ ታሪክ የምትዘክር ሀገር ሆና አታውቅም።እንደዚያ ቢሆን ኖሮማ ዘመነ መሳፍንት የብዙ የእርስ በርስ ጦርነቶች ባለ ታሪክ ነበር።ሆኖም ግን የወቅቱ የሀገራችን መሪ ግዜያዊ ድል ሲያገኝ የእኔን ማሸነፍ የኢትዮጵያ ታሪክ አድርጉልኝ ሲል አልተሰማም።ጉዳዩ የእርስ በርስ ጦርነት ነዋ! በተቃራኒው ግን ኢትዮጵያ ለነፃነቷ እና ለአንድነቷ የሞቱላትን ከህወሓት በፊት የነበሩት የኢትዮጵያ መሪዎች ትልቅ ቦታ ሰጥተውት ኖረዋል።እነኝህ መሪዎች ከጣልያን ጋር የነበረውን ትንቅንቅ ዘከሩ እንጂ ለስልጣን የተደረጉ ውግያዎችን የኢትዮጵያ ትልቁ ታሪክ ነው ብለው አልተሟገቱም።ህወሓት ግን ያለፉትን ለኢትዮጵያ የሞቱትን እየነቀፈ እና እየወቀሰ ሲመቸው ደግሞ ለማደብዘዝ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ እየከፈተ ኢትዮጵያ የተፈጠረችው ደደቢት ላይ ነው መሰል ንግግር ሊያሰማን ይዳዳዋል።
ፖለቲከኞችን ማሳመን ያልቻለው ህወሓት ለአርቲስቶች ምን ነገራቸው?
ሰሞኑን አርቲስቶችን አሳፍሮ ደደቢት ላይ የከረመው የወያኔ አመራር ቡድን 150 ሚልዮን ብር ወጪ(ለፀጥታ ጥበቃ፣ትራንስፖርት፣ለሁሉም አርቲስቶች የቀን አበል፣የምሽት እራት እና ዳንስ ወዘተ) መውጣቱን የውስጥ አዋቂ ዘገባዎች ዘግበዋል።አርቲስቶቹም ድራማ ሲሰሩ ከርመዋል።ሰው ለሰው ድራማ በዋና አክተሩ ተወክሏል፣የህወሓት የዛሬ የአዲስ አበባ እና መቀሌ ህንፃ ባለቤቶች ሲደንሱ ታይተዋል።ለአርቲስቶቹ በእርስ በርስ ጦርነት ወቅት እንዴት ድልድይ እንደፈረሰ፣የቱ ጋር ትግራይን ለመገንጠል እንደተዶለተ፣የቱ ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ለሻብያ የምፅዋ ጦርነት የትግራይ ልጆች እንዲላኩ እንደተወሰነ፣የቱ ጋር ስለ ብሔር ብሔር በሚል ሽፋን የኢትዮጵያ ጉድ የሆኑትን ጉድ የብሔር ድርጅቶች ለመፈልፈል ህወሓት እንደዶለተች ተነገረ።
ለአርቲስቶቹ ከተናገሩት ውስጥ አቶ ስዩም መስፍን፣አቦይ ስብሐት እና ሳሞራ የኑስ እንዴት ኢህአፓን እና ኢድዮን እንዴት ከትግራይ እንዳስወጡ ተተረከ።አቦይ ስብሃትም በመሃል የሚያስቆማቸውን ሳል እየሳሉ ሲቀጥሉ እንዲህ አሉ ”የቀድሞዎቹ ተቃዋሚዎች ሁሉም የተሰገሰጉት የቀደመውን ስርዓት ለመመለስ የሚፈልጉ ነበሩ” ካሉ በኃላ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር የብሔር ችግር ነው ካሉ በኃላ የብሔር ችግርን ”የማይታረቅ ቅራኔ” ሲሉ ስደመጡ ተሰብሳቢውን አስደንግጧል።
ቀጥሎ ከተናገሩት ውስጥ አቶ በረከት ነበሩ።አቶ በረከት አቦይን የወረፉበት ንግግር አቦይን ”ድራማቲክ” አቀራረብ ያለው ሲሉ ተደምጠዋል። አቶ በረከት የገለጡበት መንገድ እንዲህ ይነበባል -”የአቦይ ስብሐት አይነት ድራማቲክ አቀራረቦች ስንሰማ ልንዋጥ እንችላለን።በታሪክም ልንጠፋ እንችላለን” በማለት ነበር።የሁሉም ንግግሮች ያጠነጠኑት ትግራይ በሌላው ኢትዮጵያ ላይ የበላይ እንደሆነ ማብራራት ነበር።ደደቢት ላይ ህወሓት ባይመሰረት ኖሮ ኢትዮጵያ ትጠፋ እንደነበር ለመግለፅ መድከም ሌላው ለማስተላለፍ የታሰበው መልዕክት ነበር።
ህወሓት የፖለቲካ ማሳመኛው ፍልስፍናው ሁሉ ተሟጦ የቀረው የደርግ ዘመንን ደጋግሞ ማንሳት ብቻ ሆኗል።አሁን ኢህአዴግን ፖሊሲህ ዘመን ያለፈበት በቂም፣በዘር እና በበቀል የታሸ ነው የሚለው ደግሞ ኢህአዲግ አዲስ አበባ ሲገባ ገና በእግራቸው መቆም ያልቻሉ ሕፃናት የነበሩ ወይንም ገና ያልተወለዱ ናቸው።ህወሓት የኢትዮጵያን ሕዝብ ዲሞክራሲ የነጠቀ፣በጠራራ ፀሐይ ድምፄ ተሰረቀ ያሉ ወጣቶችን በጥይት የቆላ፣ብሔር ከብሄር በማጋጨት ከእራሱ የወጡ አባሎቹ የመሰከሩበት፣አባላቱ በሙስና በሰበሰቡት ገንዘብ መሃል አዲስ አበባ እና መቀሌ ላይ ባለ ሰባት ፎቅ ሲገነቡ እፍረት የማይሰማቸው አባላት ያሉት ወንጀለኛ ድርጅት መሆኑን የሚሞግቱት አሁንም ወያኔ አራት ኪሎ ቤተ መንግስትን ሲቆጣጠር በእናታቸው እቅፍ ሆነው ጡት የሚጠቡቱ ናቸው። በመሆኑም ተከራክሮ የማያሳምነውን ትውልድ ሸሽቶ ስለፖለቲካ ቢናገሩ እናንተን አይመለከትም ለማለት የሚቀሉትን አርቲስቶችን መማፀኑ ካለተከራካሪ የእኔን ብቻ ስሙኝ ስልት መሆኑ ነው።
ህወሓት ለአርቲስቶች ያልነገራቸው
- አቦይ ስብሐት፣አቶ ስዩም እና አቶ በረከት ቢቢሲ ስላረጋገጠው ህወሓት ለትግራይ ሕዝብ በ 1977 ዓም እረሃብ የመጣውን የዕርዳታ እህል ሱዳን እየተወሰደ ይሸጥ እንደነበር እና የጦር መሳርያ ይገዛበት እንደነበር አልነገሩትም።
- በደርግ ዘመን በአሶሳ የአማራ ተወላጅ ናችሁ ተብለው በአንድ ቤት ተከተው በእሳት ስለተቃተሉት ምንም አላሉም።
- ኤርትራ ከኢትዮጵያ ትለይ ብለው እስከ ምፅዋ እና ከረን ድረስ የትግራይ ተወላጆች ደም እንዲገብሩ መላካቸውን አላነሱትም።
- ህወሓት እስካሁን ድረስ በአሜሪካ የሽብር መዝገብ ላይ እንደሰፈረ መሆኑን ትንፍሽ አላሉም።
- በህወሓት የተሳሳተ ፖሊሲ ሳብያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሴት እህቶቻችንን ለአረብ ሀገር መከራ መዳረጋቸውን ያነሳ የለም።
- በህወሓት ውሳኔ በሺህ የሚቆጠሩ ሕፃናት ለጉድፈቻነት መዳረጋቸው እና በለውጡ ህወሓት ብዙ ሚልዮን ዶላር ማትረፉን ትንፍሽ ያለ የለም።
- ህወሓት ከተሞች በጎዳና ተዳዳሪዎች፣ወጣቶች ለጫት እና ለሽሻ፣የዩንቨርስቲ ምሩቃን የኮብል ስቶን ሥራ ሰራተኛ እንዲሆኑ የተደረጉት በዘመነ ህወሓት መሆኑን ለመናገር የደፈረ የለም።
- በከተሞች የሚኖሩ ብዙ ሺዎች የገዛ ቤታቸው በግሬደር ሲፈርስ እና የጎዳና ተዳዳሪ የሆኑት በህወሓት ዘመን መሆኑን ህወሀቶች አላነሱትም።
- ገበሬው ለዘመናት ከኖረበት ቦታ በጎሳ እና በቋንቋ እየለዩ ለዘመናት ከኖረበት ቦታ የተፈናቀለው በዘመነ ህወሓት መሆኑን ያወሳ የለም።
- አስራሶስት የህወሓት አመራሮች በስዊድን ዓለም አቀፍ የጦር ፍርድ ቤት በዓለም አቀፍ ወንጀለኛነት ከተከሰሱ ገና ቀናት እየተቆጠሩ መሆናቸውን ሊያስታውሱ አልፈለጉም።