ትለቃለህ አትለቅም ???!!!
******
“አንት ክፉ፣ ለመሆኑ ስምህ ማን ይባላል?›› አባ መስቀላቸውን ወደመኒት ግንባር አስጠጉ፡፡
‹‹አቃጠሉኝ! አቃጠሉኝ አባ፣ አቃጠሉኝ!›› የሆነ የወንድ ድምጽ በመኒት አንደበት ውስጥ ሲጮህ ተሰማ፡፡ ‹‹ፋታ ይስጡኝና እናገራለሁ፡፡ ትንሽ መስቀሉን ከኔ ላይ ራቅ ያድርጉልኝ አባ!››
‹‹እኮ ይህቺን ሰው ይዘህ እንዲህ እየጠጫወትክባት፣ እሷም ባገሩ ላይ እንድትጫወትበት ያደረካት ሰይጣን ስምህ ማን ይባላል?››
‹‹ብል፣ ብል ይባላል፡፡››
‹‹ለመሆኑ የት ነው የያዝካት?››
‹‹ስትዋሽ፣ ስትዘርፍ ፣ስትክድ፣ ስትገድል ስታስገድል ፣አይኔን ግንባር ያድርገው ስትል፣ ያማረ ነገር በሙሉ ስትጠላ ፣ህዝብ ስትነቅል ስታፈናቅል ፣ ያማረን ስታከፋ ፣ ነባሩን ስታጠፋ እና ትምህርት አምርራ ስትጠላ፣ ያኔ ነው ትኩረቴን የሳበችው፡፡ እንዴት ያለች ፈረሴ መሰለችዎ አባ!! ድንቅ ፈረስ ናት፡፡ ድንቅ ባዝራ!! እኔም እሷን እንደልቤ እጋልባታለሁ፤ እሷም ህዝቡን በኮቴዋ ደህና አድርጋ ትረመርመዋለች፣ ትደቀድቀዋለች፡፡ ጋልቤአት ደከመኝ፣ ጭኜአት ሰለቸኝ የማትል አመለሸጋ ባዝራ ነበረች፡፡ ምን ያደርጋል አሁን እርሶ ከዚች ፈረሴ ጋር ሊያፋቱኝ ይኼው መስቀል ይዘው መጡብኝ፡፡››
‹‹የፈረስህ ጥልቅ ምኞት ምንድን ነው?››
‹‹ፈረስ ደግሞ የምን ጥልቅ ምኞት ነው ያለው? እኔ የጫንኳትን ተሸክማ እንደማናቸውም አጋሰስ ከመንጋፈፍ በስተቀር የኔ የምትለው ምን ምኞት አላትና?›› ብሎ ያ አስቀያሚ የወንድ ድምጽ ሁለት እጥፍ ማስጠሎ የሆነ ሳቁን አሰነካው፡፡ አባም መስቀላቸውን ይብስ ወደመኒት ግንባር ሲያስጠጉ ከላይዋ ላይ ሆኖ ሲለፈለፍ እና አሁን ደግሞ ቅጥ ያጣ ሳቁን እያስነካው የነበረው ሰይጣን በእርብትብት ድምጽ ፣ ‹‹መስቀሉን፣ መስቀሉን፣ መስቀሉን ብቻ ትንሽ ራቅ ያድርጉልኝ አባ፤ እንዲህ ያለ መረን የወጣ ሳቅ አይለምደኝም፡፡››
‹‹የምታደንቀው ሰው ወይም ድርጅት አለን?››
‹‹እንዴታ! አለንጂ!››
‹‹ማን ወይም ምንድነው ነው ?››
‹‹ሲሪላንካን ለአመታት ረግጠው ሲገዙ የከረሙት አራት ወንድማማቾችን ከማንምና ከምንም በላይ አደንቃለሁ፡፡››
‹‹እነማናቸው እነሱ?››
‹‹የራጃፓክሳ ወንድማማቾች ይባላሉ፡፡ አንዱ ጠቅላይሚኒስትር፣ አንዱ ፕሬዚደንት፣ አንዱ አፈጉባኤ፣ አንዱ ወሳኝ በሚባሉ የተለያዩ የሚኒስቴር መስሪያቤቶች ላይ እንዳስፈላጊነቱ በጆከርነት እየተሾመ ሲሪላንካን ላመታት በደረቁ ላጭተው፣ ደሟን መጠው፣ ስጋዋን በቁሟ ጠብሰው ሲበሉ የኖሩት የራጃፓክሳ ልጆችን ለእስከዎዲያኛው አደንቃለሁ፡፡››
‹‹ ሌላስ የምታደንቀው የአንድ ወላጅ ውላጆች የሆኑ በላኤ ህዝብና በላኤ ሀገር የሆኑ አሉን ?››
‹‹አሳምሮ፣ አሳምሮ!››
‹‹እነማን ይባላሉ?››
‹‹በአጂቦክስ ሪፐብሊክ የሚገኙት አራቱ እህትማማቾች ይባላሉ፡፡ እትማማች ገዢዎች ናቸው፡፡ አገርን ሲግጡ፣ ደምዋንም ሲመጡ የኖሩ፣ በህዝብ እጣ ፈንታ ሲያላግጡ የከረሙ ናቸው፡፡ ታዲያንላችሁ…በመሀሉ ተጣሉ፡፡››
‹‹ምን አጣላቸው?›› አባ ጠየቁ፡፡
‹‹ጥቅም ነው የአጣላቸው፡፡››
‹‹እንዴት ማለት?››
‹‹ከአራቱ እትማማቾች ታላቅዬዋ ዘራፊ ናት፡፡ የተቀሩት ሶስቱ ደግሞ ሌቦች ናቸው፡፡››
‹‹ዘራፊና ሌባን ምን ለየው?››
‹‹መጠን ብቻ ነው የሚለየው፡፡ ጠባቸውም የመጣው በሚሰረቀው የሀገር ሀብትና ንብረት መጠን በእጅጉ መለያየት የተነሳ ነው፡፡ ታላቅዬዋ መሸከም ከምትችለው በላይ ስትዘርፍ ሶስቱ ታናናሾችዋ ደግሞ ኪሳቸው የሚችልላቸውን ያህል ብቻ እንዲሰርቁ በመሆኑ ነው የጠባቸው መነሻ፡፡››
‹‹ከዛስ ምን ሆነ?››
‹‹ሶስቱ እህትማማቾች አድመው፣ ታላቃቸውን ከመንበርዋ አነሱዋት፡፡ ከዚያም እነሱም ልክ እንደታላቃቸው መሸከም ከሚችሉት በላይ መዝረፉን ተያያዙት፡፡ በሜካፕ ተያያዙት፡፡በሜካፕ ማለትም በማካካሻ ፕሮግራም ዘረፋውን አጦፉት፡፡ እንግዲህ በዘራፊና በሌባ መሀል ያለው ልዩነት ይኼው ነው፡፡ ግን የአራቱ እትማማቾች ነገር ከአራቱ የራጃፓክሳዎቹ ወንድማማቾች የሚለይበት ቦቃ አለው፡፡ ራጃፓክሳዎቹ እንዳሉ እንደሌሉ ተጠራርገው ከስልጣን ሲባረሩ፣ እትማማቾቹ ግን ታላቃቸውን አባረው የተቀሩት ሶስቱ የራሷን የታላቅ እህታቸውን ተግባር አሻሽለው የገፉበት መሆናቸው ነው፡፡ ይብላኝለት በነሱ ጠብ የተነሳ መከራውን ለሚገፋውና አበሳውን ለሚጠብሰው ህዝብ እንጂ፣ እነሱስ፣ ጠባቸው አህያ ላህያ ቢራገጥ ጥርስ አይሳበርም የሚባል ነው፡፡
እናም እርቃቸው የዘመድ ጥል የስጋ ትል በሚለው መርህ ይፈጸማል ፡፡
አሁንም በስርቆት ላይ ይስማማሉ፡፡ ለጥቀውም በዝርፊያ ላይ በአንድ ቂጥ እንራ ይላሉ፡፡ ከዛያ በሁዋላ ሀብት ክፍፍል ላይ እንደገና ይጣላሉ፡፡ለአዲስ ዝርፊያ ቃል ሲገባቡ እንደገና ይታረቃሉ፡፡ የሌቦች ዲያሌክቲክስ ውሀ ቅዳ ውሀ መልስ፤ ደም ቅዳ ደም አፍስስ፡፡ …………..”
የፍትህ ስርቅታ ምዕራፍ 29
https://t.me/mndarallewbooks
ምንዳር አለው ፍልስፍና