>
5:13 pm - Monday April 19, 3993

‹‹ለህዝባዊ እምቢተኝነት ሁኔታዎች ተመቻችተዋል›› የእስክንድር ነጋ መልዕክት ከቃሊቲ እስር ቤት

Eskindr Nega

ነገረ ኢትዮጵያ

በሰላማዊ ትግል ውስጥ ሁለት አብይት የትግል ስልቶች አሉ፡፡ አንደኛው ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማትና ህግጋት ባሉበት ነባራዊ ሁኔታ የሚደረግ ህዝብን ያሳተፈ ምርጫ ነው፡፡ ምርጫ ሲባል ዝም ተብሎ ለማስመሰልና የአምባገነኖችን የስልጣን እድሜ ለማራዘሚያነት የሚደረገውን አይጨምርም፡፡ ምርጫ ሲባል ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ያሉት ነው፤ መመዘኛዎችን ባሟላ መልኩ የሚደረግ ምርጫ፣ ምርጫ ሊባል ይችላል፡፡ 

አምባገነን ስርዓቶች ምርጫ ሲያደርጉ አስተውለናል፤ ግን የይስሙላ ነው፡፡ ግብጽ በሙባረክ ጊዜ ምርጫ ታደርግ ነበር፡፡ ብዙ አምባገነኖች ምርጫ አደረግን ይላሉ፡፡ ኢህአዴግም ምርጫ አደረግሁ ይላል፡፡ በእነዚህ ስርዓቶች የተደረጉት ምርጫዎች ግን ዴሞክራሲያዊ ሆነው አላየናቸውም፡፡ በዚህ ምክንያት ምርጫን እንደ ሰላማዊ የትግል ስልት አማራጭ አድርገው ይመለከቱ የነበሩ ዴሞክራሲያዊ ኃይላት ፊታቸውን ወደ ሌላኛው ስልት እንዲያዞሩ ይገደዳሉ፤ እሱም ህዝባዊ እምቢተኝነት ነው፡፡ በግብጽ የሆነው ይኸው ነው፡፡
አንድ ነገር ማስተዋል አለብን…የምርጫ ስልት ተዘጋ ማለት ሰላማዊ ትግል አበቃለት ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንስ ወደሌላኛው ምዕራፍ ተሸጋገረ ማለት እንጂ፡፡ ምርጫ ሲያበቃለት ህዝባዊ እምቢተኝነት አማራጭ ይሆናል፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ሁኔታዎች ለህዝባዊ እምቢተኝነት ተመቻችተዋል፡፡ አሁን ህዝቡ በምርጫ ላይ ያለውን አሰራር አስረጅ ሳያስፈልገው ራሱ አይቶታል፡፡ ስለሆነም ከዚህ በኋላ አማራጩ ህዝባዊ እምቢተኝነት እንደሆነ መገንዘብ ግድ ይለናል፡፡ ህዝባዊ እምቢተኝነት ህጋዊና ሰላማዊ የትግል ስልት መሆኑን ዓለም ይገነዘባል፡፡
በዚህ ወቅት ስለህዝባዊ እምቢተኝነት የሚሰሩ አካላት ካሉ መንገዳቸው ልክ ነው፤ ሊገፉበትም የሚገባ ነው፡፡ በእርግጥ ህዝባዊ እምቢተኝነት ላይ በቅድሚያ መግባባት ላይ መድረስ ያለባቸው አካላት አሉ፣ ዋነኛዎቹ ‹አክቲቪስቶች› ናቸው፡፡ አክቲቪስቶች መግባባት ላይ ደርሰው ህዝቡን የማነቃነቅ ስራቸውን በጋራ ቢያከናውኑ አንድነቱን ያጠናከረ እንቅስቃሴ መተግበር ይቻላል፡፡
እስካሁን በተገለጸው የ2007 ‹‹ሀገራዊ ምርጫ›› (በትምህርተ ጥቅስ አስገባልኝ) ውጤት እጅግ ደስተኛ ነኝ፡፡ አዎ፣ የተለያየ ፍላጎትና ጥቅም ያላቸው ኢትዮጵያውያን በሙሉ ተስማምተው አንድ ፓርቲ መረጡ ቢባል ለሰሚውም ቀልድ ነው፡፡ ይህ ተፈጥሯዊ ያልሆነ ውጤት ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ኢህአዴግ ለማጭበርበር እንኳ አቅም እንዳጠረው ነው፡፡ ለዚህም ነው በውጤቱ ደስ የተሰኘሁት፡፡ ውጤቱ በግልጽ የሚነግረን ከዚህ በኋላ ለሚመጣው ህዝባዊ እምቢተኝነት ዋናው ገፊ ምክንያት ኢህአዴግና የኢህአዴግ ስርዓት መሆኑን ነው፡፡ እናም ህዝባዊ እምቢተኝነት በኢትዮጵያ ‹ጀስቲፋይድ› ነው፡፡
በእርግጥም አሁን ያለው የኢህአዴግ ስርዓት ለራሳቸው ለኢህአዴግ አባላት እንኳ አሳፋሪ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ የማስመሰል ካባው እንኳ አላስፈለገውም፤ ሁሉንም ነገር ከርችሞታል፡፡ እናም ቀጣዩ ትግል የነጻነት ትግል ነው፡፡ ይህን የነጻነት ትግል ዳር የሚያደርሰው ማሳረጊያ ደግሞ ህዝባዊ እምቢተኝነት እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ህዝባዊ እምቢተኝነት ኢህአዴግ ራሱ መርጦ ለህዝቡ የተወው እንደሆነ መረዳት አለብን፡፡ የታፈነ ህዝብ ሲነሳ ማዕበል ነው፣ አምባገነኖችን ይጠራርጋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አፈና ህዝባዊ እምቢተኝነት አይቀሬነቱን በግላጭ ያረጋግጣል፡፡

 

Filed in: Amharic