¤ የመጀመሪያው ምክንያት ሶስት ሺህ አመት ሳይነካ የኖረ ውበት ስለተነካ
በተለይ ሪቨርጋድ፣ “ስልብ” በሆነውና እና እጅግ አስገራሚ ተሰጥኦ ባለቤት በሆነው “ታይታ” በሚባል ገፀ-ባህሪ ላይ የተመሰረቱት የዊልበር ስሚዝ መፀሐፎች ላይ ያለው ይህ ሰው ፣ የግብፅ ፒራሚዶች በተሰሩበት ዘመን እንዴት ተሰሩ በምን አይነት መንገድ እና ለምን ተሰሩ ከሚለው እንዲሁም በጣም ስለሚያስገርመው የእርከን እና የውሃ መስመር ስራቸው ብሎም ከሱ ጋር የሚያያዘውን አባይ ላይ ያለውን ከሃይማኖት የሚልቅ አምልኮ ይዳስሳል፣ በተጨማሪም ግብፃዊያን ፈርኦኖች እና ልኡሎች ዘ-ሂኮስ በመባል ታሪክ ከሚያነሳቸው ኑቢያዊያን ጋር ስለነበራቸው ከፍተኛ ትግል እንዲሁም ግብፅን የሚያጠጣት ወንዝ፣ አባይ እስከሚነሳበት ምድር፣ የዛሬዋ አገራችን ኢትዮጵያ ድረስ ያደርጉ የነበሩትን ፣ የመንፈሳዊነት ይዘት ያለውን ጉዞ ሳይቀር፣ “ታውረስ” በሚባል ጦረኛ ልኡል ገፀ-ባህሪ የሚያስገርም እና መሳጭ ፍሰት ያለው ታሪክ በ1994 አስነብቧል፡፡
በሪቨር ጋዱ ገፀ-ባህሪ ታይታ ስራዎች ላይ በሚያተኩር አርኪዎሎጂካል ፍለጋ ላይ በኋላም ፣ ግኝቶቹን በመፍታት ፣ የታይታ ቀመሮች ድብቅና ሚስጥራዊ መልእክቶች ወደሚመሯቸው አቅጣጫ እንዲሄዱ የሚያደርጋቸው ሁለተኛው የዊልበር ስሚዝ ዘ-ሰቭንዝ ስክሮል መፀሐፍ ፣ እኔ ባንድ ወቅት ተቀጥሬ ከሰራሁበት ሪፍት ቫሊ ሳፋሪስ የተሰኘ በማስጎብኘት እና በስፖርታዊ የአደን ስራ ላይ የተሰማራ ድርጅት ባለቤት እስከ ስዬ አብረሃ እና ሌሎች የወቅቱ የመከላከያ ኮሎኔሎች ሳይቀር የተካተቱበት እጅግ አስገራሚ መፀሐፍ ነው፡፡
የዚህ ደራሲ ዋጋ እና የፃፈው መፀሐፍ ፋይዳ ለእኔ ይብስ ሰማይ የሚደርሰው ደግሞ፣ ፀሐፊው የታይታን ምጡቅ ገፀ-ባህሪያዊ አእምሮ ተጠቅሞ ከሶስት ሺህ አመታ በፊት ፣ ከአባይ ወንዝ ፏፏቴ አካባቢ (በኢትዮጵያዊያን ነዋሪዎች) በገጠማቸው ከፍተኛ ጦርነት ወቅት ፣ የአባይን ፏፏቴ በአርባስምንት ሰአት ውስጥ ፣ አቅጣጫውን ቀይሮ እንዲፈስ በማድረግ ከመጣባቸው የጠላት ጥቃት እና አደጋ እጅግ ውድ ዋጋ ያላቸውን ይዞታዎቻቸውን ፣ ከአባይ ፏፏቴ ውስጥ እንዴት እንደሸሸገ፣ ከዚያም መልሶ ፏፏቴውን ከስፍራው የመለሰበትን ሁኔታ ላነበበ ሰው፣ ዛሬ ላይ ከሶስት ሺህ አመታት በኋላ ያለውን የአባይ ፏፏቴን ተጨባጭ ሁኔታ ስመለከት ስለሚገርመኝ እና በዚያው ልክ ስለሚያበግነኝም ጭምር ነው፣ የመፅሓፍ ማስታወቂያ እስኪመስል ድረስ የዊልበር ስሚዝን መፀሐፍ ዝርዝር ውስጥ ገብቼ መናገር ያስፈለገኝ!
¤ ሁለተኛው ምክንያት የኢትዮጵያን ውበት
ታዲያ አቶ አባዱላ ገመዳ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት በነበሩበት ጊዜ ፣ ሁለት እስራኤላዊያን ባለሃብቶች ፣ አንድ “ሪ” ያለበት ነገር፣ እንጆሪ ወይ ደግሞ መንደሪን ሊያለሙ ቦታ ጠይቀው ከባቢሌ ጥብቅ ስፍራ (ሳንክቹዋሪ) ተቆርሶ ሲሰጣቸው፣ በፕሬዝዳንቱ ድርጊት ግራ የተጋቡ አንድ ትልቅ የዘርፉ ምሁር፣ “እንደው ጌታዬ ዝሆኖቹ የት ወስደን እንጠብቃቸው፣ ይኸው ነው የቀረቀቸው የተፈጥሮ መኖሪያ ስርፋቸው እና፣ ከርስዎ ባላውቅም ሌላ ቦታ ጠፍቶ ነው! ብለው ቢጠይቋቸው፣ “ህዝባችንን ከድህነት የምናወጣው በግብርና ነው፣ ለዚያ ደግሞ በዝሆን ሳይሆን በበሬ ነው የምናርሰው” ብለው በመልሳቸው እኚህን ክቡር የዘርፉ ባለሞያ ጥንብርኩሳቸውን አውጥተው አባርረዋቸዋል፡፡
ታዲያ የሚገርመኝ መመሳሰል ያለው እንደዚህ አይነቱ የኢትዮጵያ የወቅቱ መሪዎች አስገራሚ እርምጃዎች አቋም ላይ እና ከዚያ በኋላ የሚሰጡትን መልስ ውስጥ የሚታየው የህዝብ ንቀት፣ ትምክህት ከሁሉ በላይ ልክ የሌለው የእውቀት ማነስ ፣ ተሳስተው ሳይሆን ሆን ብለው የሚያደርጉት እንደሆነ ያሳየናል፡፡ እዚህ ጋር አንድ በስም የማላስታውሳቸው የባህር ዳር ከተማ መስተዳድር ሰው ከሶስት አመት በፊት፣ በጢስ አባይ ሁለት የሃድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ምክንያት ስለተሰወረው የአባይ ፏፏቴ ፣ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ጋዜጠኛ ተጠይቀው የሰጡትም ምላሽ ፣ ድርጊቱ እንዲፈፀም ፊረርማቸውን ካኖሩት እኩል ባይሆንም በንግገራቸው ብቻ በህዝብ ላይ ከፍተኛ ወንጀል ሰርተዋል አስብሎኛል፡፡ እንዲህ አሉ፣ “ የአባይ ፏፏቴ አንድ አምፖል አያበራም ለባህር ዳርም ሆነ ለዚህ ለጭስ አባይ አካባቢ ነዋሪ- ለዚህም ነው እዚህ ፏፏቴው ጋር ከመድረሱ በፊት ጠልፈል ወስደን ሃይል እንዲያመነጭ የምናደርገው !”
አባዱላ የዝሆን ጥብቅ ስፍራ ለምን ለእንጆሪ እርሻነት ተሰጠ ሲባሉ፣ “ የአገራችንን ህዝብ ከድህነት ለማውጣት በዝሆን ሳይሆን በበሬ ነው የምናርሰው” ይሄኛውም አገር በዚህ ስሟ ሳትጠራ በፊት የነበረን የአለም ውበት፣ “ ለባህርዳር ህዝብ የአባይ ፏፏቴ አንድ አምፖል አያበራም” ከዚህም በፊት እንዲሁ፣ ከነዚህ ሹመኞች የስልጣን አባት እና አጥማቂ በላይ በዚህ አርእስትን ያለጭብጥ እና ሃቅ በቃላት የማፈናጠቅ ሊቅ በሆኑ ሟች መለስ፣ ከታሪካዊውና ታላቁ የኤርትራ መገንጠል አስፈላጊነት ጥያቄ ( ከወረቀት መቀደድ ጋር ያመሳሰሉበትን ) ንግግራቸው እስከ የነገነት ዘውዴንና ዩናትድ ተባረክና ቤተሰቦቹ ሽርክና ኢትዮጵያን 245 ሚሊዮን ብር ያስወጣውና (የፕላዝማ ቴሌቭዥን ) በኋላ በወጉ ሶስት አመት ሳያገለግል በየትምህርት ቤቱ መጋዘን ተጥለው የቀሩትን ግዢ በተመለከተ፣ የቅንጦት ቴሌቭዥን በመሆኑ የት ሊሰቀል ታስቦ እንደሆን ሲጠየቁ፣ ካስፈለገ ዛፍ ላይ እንሰቅለዋለን ብለው ፓርላማ መሃል እንዳላገጡበት፣ እነኚህም አርአያቸውን በመከተል መልካቸው ቁርጥ ነው፡፡
ላጠፉት እና ለተሳሳቱት ማንኛውም ታሪካዊ ስህተት መከላከያነት የሚሰጡት ምላሽ፣ ቀን አልፎ የሚያስጠይቃቸው እንካ አይመስላቸውም፣ በራሳቸው ተፀፅተው አሊያም አርመው ወደፊት ለመሄድ እና የህዝብ ወገንተኝነትን ለማሳየት! ከአባይ ፏፏቴ መጠለፍም ጀርባ ያለው ይኸው ንቀት እና የህዝብ ወገንተኝነት መጥፋት ነው!!
¤ ሶስተኛው ምክንያት ይህንን የአባይን ውበት
በተፈጥሮ አቀማመጧ ኢትዮጵያ፣ ከሶሪያ ተነስቶ ሞዛምቢክ ድረስ የሚወረወረው የስምጥ ሸለቆ መስመር ከላይ ካናቷ እስተ እታችኛው ክፍሏ ድረስ ፣ ሁለት በምእራብና በምስራቅ እንደተንጣለሉ የሚቀሩ ከፍ ያሉ ደጋ ስፍራዎች እንዲኖሯት አድርጎ ሰንጥቆ ፣ መሃሏን በረባዳማ አቀማመጥ ይዘው ዝቅ ባሉ የስምጥ ሸለቆ ውብ ተፈጥሮ ፣ እንዲሁም እምቅ ለሃይል ማመንጫነተት ሊሆኑ የሚችሉ እዛም እዚም እያጓሩ የሚርመሰመሱ ወንዞችን የታደለች አገር ናት፡፡ የአባይ ወንዝም እንዲሀ በፈሰሰበት ሁሉ አስገራሚ መልክአ-ምድርን ሰንጥቆ እየፈጠረ ስለሚጓዝ ጭስ አባይ ፏፏቴ ሆኖ ከሚወረወርበት ስፍራ ትንሽ ዝቅ ሲባል እንዲሁ ተመሳሳይ የውሃ አወራረድ እና መልክአ-ምድራዊ አቀማመጥ ማየት ይቻላል፡፡
በፈረንጆች አቆጣጠር በ1973 ለመጀመሪያ ጊዜ የጭስ አባይን የጎበኘው የኤምኤስኤንቢሲ ፕሮዲዩሰር ሪቻርድ ባንግሰ በአራት መቶ ሜትር ስፋት እና በአርባ አምት ሜትር ርዝማኔ ወደ ምድር ተወርውሮ በቪክቶሪያ ሃይቅ ከሚፈጠረው ፏፏቴ ለጥቆ የአፍሪካ ግርማ እስከመባል የበቃውን ጭስ አባይን የገለፀበት ቋንቋ በማርች 2004 (Stealing Nile-“Famous fall No More”) ልክ ከ200 አመት በፊት ጄምሰ የገለፀውን ውበት ሳይቀየር አገኘሁት ብሎ (ስኮትላንዳዊ አሳሽ ጄምስ ብሩስ እንደፃፈው) የአባይን ፏፏቴ ከነውበቱ እንዳገኘው ይናገራል፡፡ እ አ አ በ2004፣ ለአይማክስ ፊልም ቀረፃ ከቡድኑ ጋር አብሮ የመጣው ሪቻርድ በፏፏቴው ላይ ያየውን አሳዛኝ ድርጊት በከፍተኛ ሃዘን በዚሁ ፅሁፉ፣ (Stealing Nile-“Famous fall No More”) ዘርዝሮ ይናገራል፡፡
ከአስር አመታት በላይ በፊት ስልሳ ሶስት (63 )ሚሊዮን ዶላር ገደማ ወጥቶበት ለባህር ዳር ከተማ የመብራት ፍላጎት 450 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል እንዲያመነጭ ታስቦ በችኮላ እና ለርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ሲባል የተገነባው የጭስ አባይ ሁለት ፕሮጀክት፣ ተዳክሞ የነበረውን የፏፏቴውን መጠነኛ የውሃ ጠለፋ ከናካቴው፣ ጭል ጭል ወደምትል ጉድ የቀየረ አሳዛኙን የኢትዮጵያን መንግስት በአላዋቂዎች የተሞላ አመራር ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡
ጭስ አባይ ከተማዋ ውስጥ አንድ ቀን አብሮኝ ያሳለፈ የዛው ከተማ ተወላጅ እና አሁን ጭል ጭል እያለች የምትወርደዋን ጅረት ጋይድ ሆኖ በማስጎብኘት ስራ ላይ ያለ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ከጥቂት ወራቶች በፊት ህዝቡ ውስጥ ያለውን ምልልስ እንዲህ ነበር ያስቃኘኝ፡፡
የአማራ ክልል ህዝብን የሚመራው በአዴን ፣ ለበላዮቹ እሺ ብሎ አባይን ሲያዘርፍ፣ ድምፅ በነሳው ድህነቱ ተለጉሞ ጭጭ ያለው የጭስ አባይ ነዋሪ ፣ ጭስ አባይን ናፍቆ ከራሱ እንባ የማትበልጥ ችፍ ችፍ የምትል “የኢሃዲግ ጅረት” ስር ቁጭ ብሎ ፣ “ምን አደረግናቸው ግን እንደው ድሮስ አባይ ፏፏቴውን እያየሁ ነበር ግጥም የምገጥም፣ ዛሬስ ግን ምን ልበል ጎበዝ፡፡
በእኛ ስም የሚጠሩቱ፣ “አባይ ላይ ያለንን ቁጭት ተወጣነ!” “እድሜ ዝንተአለም ወደ ግብፅ ሲፈስ፣ አያት ቅድመ አያቶችህ በቁጭት የሚገጥሙትን ግጥም የሚደብት፣ የሚያሳዝን የሚያስተክዝ ፣ ከዚያም አልፎ አንገት መድፋትን በሚጮኹ ቃላት እየገለፀ ቁስልህን ያባብስብህ የነበረው አይነት ማላዘን፣ ቀን አለፈበት፡፡
ስለዚህ እነዛን የሚያስተክዝና የሚደብት ስሜት የሚፈጥሩብህን ግጥሞች ፣ መቀየሪያ ጊዜው አሁን ነው! ምክንያቱም አባይ ልንገድብ እዚ ግባ የማይባል ጊዜ ብቻ ነው የቀረውና አሉት ለጭስ አባይ ነዋሪ፡፡
ምን ቢል ጥሩ ነው፣ ባህር ዳር ላይ ነው የሚገደበው ወይ? – አይደለም ሱዳን ጫፍ ነው የሚገደበው ሲሉት እና ታዲያ ጭስ አባይን ምን ወሰደው? መልሱ አንድ ነው! በዘር የተለከፈው የኢትዮጵያ መንግስት እያለ፣ እንዲሁም የሚጠላው እና የሚፈራው ብሄር የአባይን ግርማ ፣ ሃብት፣ ውበት እንዲያጣጥም ፈፅሞ ፈቃዱ አይደለም፣ ይህ ነው ሃቁ!
ይነገር ከተባለ! …አባይን ገድቦ የሚያቆም ስፍራ በአማራ ክልል ስላልነበረ አይደለም አባይ ከአማራው ደጃፍ ርቆ እየፈሰሰ ሱዳን ከመግባቱ በፊት ህዳሴ ተብሎ የተገደበው፡፡
መጀመሪያም ቢሆን አባይን ያክል ጉድ ወንዝ ከጣና ፣ ከጎኑ ደግሞ አማራ የሚባል ብሄር ተፈጥሮ ፈቅዳ በማኖሯ ዘላለም የሚያርረው የአውሬ አመራር ቆሽት፡ በዘር ህዝብ ጥላቻ ጥምቀት በፈጠሙ የአመራሩ ፍልፋዮች ሸፍጥ፡ አባይን የወለደውን የአማራን ምድረ-ማህፀን ሾተላይ አድርገው፡ ህዝቡን ባገሩ ካባይ ቆርጠው ማለያየታቸው፣ አባይን አሶሳ ላይ መገደባቸው!፡፡
ለዘመናት ግብፅ የኢትዮጵያዊያንን ቁጭትና እንባ ከአሸዋ እየለወሰች በልታ ስትሳለቅ እንደኖረች እንዲሁ፡- ክፉው የኢትዮጵያ አመራርም፣ ከአማራው ህዝብ ማጣት እና ከቀሪው ኢትዮጵያዊ ላቦት በተቀማ ገንዘብ ፡ ሲሚንቶ ገዝቶ የቂም ግንብ ገንብቶ፡ በገባው ውል መሰረት ወደ ከርሱ ዶላር ሲያጋብስ አማራውን ይህ በወሰኔ የሚለው ካባይ የሚጣቀስ አንዲት ጥሪት ለመቶ አመት እንዳይኖረው መሆኑ ነው እንጂ፡፡ ግና የእሱን ነገር ወደኋላ ተወት አድርገን፣ ፏፏቴውን ለምን ሰለቡት ብለን ብንጠይቅ ምላሹ የዘር ቂም ያመmጣው ጣጣ ነው! ፈጣሪ ኢትዮጵያን ከዚህ ሰውን ከስፍራው ከሚያጎድል ጎጠኝነት አውጥቶ የድሮው ግርማዋ ላይ፣ የአባቶች ሆደሰፊነትን ያድለን እላለሁ!
የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከአለም መስህቦች አንዱ የሆነውን የጭስ አባይን ፏፏቴ፣ ሰው (ለዚያውም ሰንካላ አእእሮ ያለው) እንጂ ተፈጥሮ አላቋረጠችውም!
ኢትዮጵያዊነት ይለምልም!”