>

ነገሪ ሌንጮ፣ አቦይ ስብሃት በሙስና መታሰራቸውን ይንገሩን (ክንፉ አሰፋ)

azeb_mesfinየነጋዴዎች አድማ ዛሬም እንደቀጠለ ነው። ገዥው ፓርቲ ከየአቅጣጫው በመወጠሩ – የችግሩን ትኩረት አቅጣጫ ማስቀየር አለበት። የተለመደ የፉገራ ካርዳቸውን መዘዝ አድርገው ለዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ሰጡዋቸው።

ኦቦ ነገሪ ሌንጮ 34 የመንግስት ባለስልጣናት እና ነጋዴዎች በሙስና ተጠርጥረው መታሰራቸውን ለመገናኛ ብዙሃን ትናንት ምሽት  አብስረዋል።   እነማን እንደታሰሩ ግን አልገለጹም።  ታሳሪዎቹን ሊያውቁዋቸው ስለማይችሉ ሊገልጹ እንደማይችሉ ግልጽ ነው።     እንደወትሮው ተጽፎ የተሰጣቸውን ከማንበብ ውጭ አማራጭ የላቸውም።  የፕሮፌሰር መረራ ጉዲናን መታሰር  እንደማንኛውም ተራ ሰው በዜና የሰሙት ነገሪ ሌንጮ ምን አፍ ኖሯቸው ስለ ባለስልጣናት መታሰር ይነግሩናል?  ስራዎቼን ሁሉ በግምት ነው የምሰራው – መረጃ እንኳን አይሰጡኝም የሚሉ ጠቅላይ ሚኒስትርስ ምን አቅም ኖሯቸው ጉዳዩን ያስፈጽሙታል?

የሙስና ጉዳይ በየአመቱ ነው የሚነሳው። ችግር ሲመጣ እየጠበቁ ለአቅጣጫ ማስቀየርያ ይለቁብናል። አንዳንዴ በሙስና ታሳሪ ገጸ-ባህርያትን ይፈጥሩና አስቂኝ ድራማ ያሳዩናል። ሌላ ግዜ ደግሞ የንግድ ባላንጣዎቻቸውን ለመበቀል ይጠቀሙበታል። አንዳንዴም ለመታመን ሲሉ ተራ የመንግስት ሰራተኞችን እና ነጋዴዎችን ይዘው ያጉሯቸውና ግርግሩ ሲረሳሳ ደግሞ ይለቋቸዋል።

sibhat-negaበእርግጥ የሙስና ተጠርጣሪዎችን ማሰር ቢያስቡ-  መጀመርያ አቦይ መስፍንን ወይንም አዜብ መስፍንን በማሰር ያሳዩን ነበር።  ጸረ-ሙስናው ዘመቻ እውን ቢሆን ኖሮ የህወሃት የጦር አለቆች በሙሉ መኖርያቸው ቂሊንጦ በሆነ።  የአቶ ስብሀት ነጋ ልጅ ተከስተ ስብሀት ነጋ እና  እህት ቅዱሳን ነጋ ህልቕ መሳፍርት ንብረት ቢታገድ ነበር ጸረ-ሙስና ዘመቻ ተጀመረ ምንለው።

የሙሰኞች ንብረት ታገደ የምንለው የጄነራል  ሳሞራ የኑስ፣  የሌ/ጄ ታደሰ ወረደ፣  የሌ/ጄ ገዛኢ አበራ፣ የሌ/ጄ ብርሃነ ነጋሽ፣ የሌ/ጄ ሳእረ መኮንን ቦሌ ላይ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ቤቶች ሲታገዱ ነው።

ሌ/ጄ ገዛኢ አበራ፣ ሌ/ጄ ብርሃነ ነጋሽ ፣  ሌ/ጄ ሳእረ መኮንን ፣  ሌ/ጄ አበባው ታደሰ፣   ሜ/ጄ አብርሃ ው/ገብርኤል ፣ ሜ/ጄ ዮሃንስ ገ/መስቀል፣  ሜ/ጄ ስዮም ሃጎስ፣  ሜ/ጄ ሃየሎም አርአያ፣  ሜ/ጄ ገ/እግዚአብሄር መብራቱ፣  ብ/ጄ ታደሰ ጋውና፣  ብ/ጄ ተክላይ አሽብር፣  ብ/ጄ ፍስሃ ኪዳነ፣ ብ/ጄ ፓትሪስ፣ ብ/ጄ መስፍን አማረ፣  ብ/ጄ ምግበ ሃይለ፣ ብ/ጄ ሃለፎም ቸንቶ፣  ኮ/ል ታደስ ንጉሴ፣  ኮ/ል ጸሃየ መንጁስ በህዝብ ገንዘብ በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ያሰሩዋቸው  በሚሊዮኖች የሚገመቱ ቤቶች  በወር ደሞዛቸው እንዳልሆነ  ፖሊስና አቃቤ ህግ ሳያውቁት ቀርተው ነው?

እነ ብርሃኔ ገብረ ክርስቶስ፣   አባዲ ዘሙ፣   ስብሃት ነጋ፣ ሽመልስ ኪዳኔ፣  አርከበ እቁባይ፣  አባይ ጸሃዬ፣  ገብረ መድህን ገብረ ዮሃንስ፣ ደብረጽዮን ገብረ ሚካአኤል, ቴዎድሮስ ሃጎስ፣   ታደሰ ሃይሌ፣   ሰምሃል መለስ ዜናዊ ከባህር ማዶ ያከማቹት በቢሊዮን የሚቆጠር የህዝብ ገንዘብ እስቲ ይታገድ እና ነገሪ ሌንጮን እንመን።

ይህን መራራ ሃቅ የሚክድ የለም። ራሳቸውም የሚሉት ነው።  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲፈሩ ሲቸሩ “ሙስና አለ – ማስረጃ የለም” ብለውናል። አቦይ ስብሃት ደግሞ በሰንደቅ ጋዜጣ አዳልጧቸው  “መቶ ሚልዮን የሰረቁና ያስዘረፉ፤ 10ሺህ ብር የሰረቀውን ሲያገላብጡት ሲያስፈራሩት ይታያሉ”  ብለው ነበር።  የየሃገራቱን የሙስና መጠን ደረጃ  በየአመቱ የሚዘግበው  ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለዉ ተቋም ኢትዮጵያ   ከፍተኛ ሙስና ከሚፈፀምባቸዉ ሃገራት አንዷ መሆኗን አመልክቷል። እንደ ተቋሙ ዘገባ ከሆነ ከኢትዮጵያ በህወሃት ዘመን ተዘርፎ የወጣው ገንዘብ 17 ቢሊየን ዶላር ይደርሳል።  ጥናት ከተደረገባቸው 174 ሃገሮች መካከል ኢትዮጵያ 113ኛ ቦታን ይዛለች። ይህ  ቁጥር መንግስታዊ ሙስናው ሃገሪቱን ምን ያህል እንደ መዥገር እመጠጠ መሆኑን ያሳየናል።   በታቦ ኢምቤኪ የመሩት ሌላ ጥናት ደግሞ በአምስት ዓመታት ዉስጥ ብቻ ከኢትዮጵያ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ 10 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ወደ ዉጭ እንዲወጣ ተደርጓል።

በአንድ ወቅት በጸረ-ሙስና ኮሚሽን የባለስልጣናቱን ንብረት የመመዝገብ ደንብ ወጣና ስራውን ጀመረ። ብዙ የተወራለት ይህ ኮሚሽን  ወደ ጀነራል ሳሞራ የኑስ ቤት ነበር ቀድሞ ያመራው። አይተ ሳሞራም የጸረ-ሙስናውን ቡድን አስቀምጦ “ስራችሁን አደንቃለሁ። ጥሩ  ጅምር ነው። ግን ከላይ ጀምሩ” ብሎ ወደ  አዜብ መስፍን መራቸው።  ንብረት መዝጋቢዎቹ ወደ አዜብ ቤት  ሳይደርሱ ግማሽ መንገድ ላይ እንደጠፉ ይነገራል።  አዲዮስ ፌደራል የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን!

የሲቪክ ማኅበራት በነፃነት መንቀሣቀስ  በማይችሉበት፣  የፕሬስ ነጸነት በታፈነበትና  የህግ የበላይነት በሌለበት ሃገር ሙስናን እናጠፋለን ማለት በህዝብ ሳይሆን በራስ ላይ መቀለድ ነው የሚሆነው። አላማው ከችግሩ አቅጣጫ ለማስቀየር ከሆነ ደግሞ ሌላ ካርታ መጠቀሙ የሚበጅ ይመስላል። ደጋግማችሁ በተባላ ካርታ  አትጫወቱ።

Filed in: Amharic