>

ሕወሃት "ትጠብ-ኪስ" ነው! ''ትጠብ-ኪስ'' ግን ምንድነው? (ስዩም ተሾመ)

የኢህአዴግ መንግስት ላለፉት 10ና 15 አመታት የአፈፃፀም ግምገማ ባደረገ ቁጥር ወይም እንደ ባለፈው አመት አጣዳፊ የሆነ ፖለቲካዊ ቀውስ ባጋጠመው ቁጥር “ለመንግስታዊ ስርዓቱ አደጋ” በሚል የሚጠቅሳቸው ሶስት ችግሮች በዋናነት በሶስቱ አባል ድርጅቶች ያነጣጠሩ ናቸው፡፡ ትምክህተኝነት በብአዴን አባላትና አመራሮች፣ ጠባብ_ብሔርተኝነት በኦህዴድ አባላትና አመራሮች፣ እንዲሁም ኪራይ_ሰብሳቢነት በሕወሃት አባላትና አመራሮች ላይ ያነጣጠሩ ናቸው፡፡ ነገር ግን፣ የሶስቱን ቃላት ፍቺ ስንመለከት ነገሩ ሁሉ የተገላቢጦሽ ይሆናል፡፡

1ኛ) “ትምክህተኛ” ማለት “ለሁሉም ነገር እኔ አውቃለሁ” የሚል ሲሆን በኢትዮጲያ ፖለቲካ ውስጥ ከሕወሃት በላይ ትምክህተኛ ቡድን ፈልጎ ማግኘት ይከብዳል፡፡ ለምሳሌ፣ የሕወሃት የሰሞኑ አጀንዳ ብአዴንን ከኢህአዴግ ውስጥ አስወጥቶ፥ ሱማሌንና ቤኒሻንጉልን አስገብቶ፣ ደህዴንን ለሁለት ሰንጥቆ፣ … እየተባለ ይዶለታል፡፡ ከዚህ በላይ “እኔ አውቃለሁ” የሚል የትምክህተኛ አመለካከት ብአዴን ሆነ ኦህዴድ ውስጥ ከቶ አይገኝም፡፡

2ኛ) “ጠባብ ብሔርተኛ” የሚለው ቃል “ፍቺ ስለ ራስ ብሔር ብቻ ማሰብና ማዳላት፣ ለሌሎች ጥላቻ ማሳየት” የሚል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከሕወሃት የበለጠ ማሳያ መጥቀስ ይከብዳል፡፡ ከፓርቲው አመሰራረት እስከ ፌደራሊዝም ስርዓት በግልፅ የሚስተዋለው የሕወሃት ጠባብ ብሔርተኝነት ነው፡፡ ሕወሃት ሰራሹ ኦህዴድ ቀርቶ #ኦነግ እንኳን የብሔርተኝነት አጀንዳው ወደጎን ሲገፋ አሁንም ድረስ ከዚህ ሸውራራ እይታ መውጣት የተሳነው #ሕወሃት ብቻ ነው፡፡

3ኛ) ስለ ሕወሃት “ኪራይ_ሰብሳቢነት” ብዙም ማለት አያስፈልግም፡፡ “Rent Seeking” ማለት ያልተገባ ጥቅም መፈለግ ነው፡፡ ያልተገባ ጥቅም ማለት፣ ለምሳሌ በጋምቤላ ክልል በግብርና ስራ ላይ ለመሠማራት መሬት ከሊዝ ነፃ ወስደህ፣ የአከባቢውን አርብቶ አደሮች ከመሬታቸው ሲፈናቀሉ ምንም ያልተሰማህ፣ ኢንቨስተሮቹ ከኢትዮጲያ_ልማት_ባንክ ብድር በማግኘታቸው ደስ ብሎህ… ባንኩ በራሱ የብድር አስተዳደር ፖሊሲና መመሪያ መሠረት ለኢንቨስተሮቹ ስለ ሰጠው ብድር ያወጣው ማስታወቂያ የሕወሃት ደቃፊዎችን (የሕወሃት ደጋፊዎች እና ተቃዋሚ መሳይ ደጋፊዎች) የሚያንጫጫ ከሆነ በእርግጥ ይሄ የኪራይ_ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር መገለጫ ነው፡፡

በአጠቃላይ፣ የኢትዮጲያ_ልማት_ባንክ ሃላፊዎችን ስምና_ፎቶ ልክ እንደ ልዩ ዕውቀት በማን_አለብኝነት በሕወሃት ደጋፊዎች ድረገፅ ላይ ታትሞ ስትመለከት ሕወሃት ማለት ”ትጠብ-ኪስ” (ትምክህተኛ፣ ጠባብ ብሔርተኛ፣ ኪራይ_ሰብሳቢነት) መሆኑን ይጠቁምሃል!

ስለዚህ፣ የኢህአዴግ መንግስት ላለፉት 10ና 15 አመታት “ለመንግስታዊ ስርዓቱ አደጋ” በሚል የሚጠቅሰው ‘ትጠብ-ኪስ’ ነው፡፡ “ትጠብ_ኪስ” ማለት ሕወሃት፣ “ሕወሃት” ትጠብ_ኪስ ነው!! ስለዚህ፣ ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ ሕልውናውን ለማስቀጠል የትጠብ_ኪስን ችግር ከውስጡ ማስወገድ አለበት! ኢህአዴግ ሕልውናውን ለማስቀጠል ሕወሃትን ከውስጡ ማስወገድ አለበት፡፡

Filed in: Amharic