>
5:13 pm - Tuesday April 19, 4433

ሰራዊቱ  ከውስጥ የሚንጠውን ፍርሃት ለመሸሽ-የሚፈራም ካገኘ ለማስፈራራት  ታንኮቹን፡ መድፎቹን፡ አሰልፎ እየፎከረ ነው

 መሳይ መኮንን

ከእንቅልፌ መንቃቴ ነው። ዛሬ አድማ እንደሚኖር ያወቀው መንፈሴ በወጉም እንቅልፍ እንዳይኖረኝ አድርጎታል። እናም የነቃሁት ሌሊት ነው። ማህበራዊ ሚዲያዎችን ጎብኘት ሳደርግ ሀገሩ በአድማ ቀጥ ብሎ ጠበቀኝ። ቄሮዎች ቃላቸው መሬት ጠብ ብሎ አያውቅም። ያሉትን አደረጉት።

መንገዶች ጭር ብለዋል። ሱቆች ተዘግተዋል። ትራንስፖርት ቆሟል። ከወለጋ እስከ ሀረርጌ፡ ከባሌ እስከ አምቦ አድማው በታቀደው መሰረት እየተካሄደ ነው። ድሬዳዋም ተቀላቅላለች። አዲስ አበባ ዳር ዳር እያላት ነው። ወዳጃችን አንዋር አንዋር ከአዲስ አበባ እንደነገረን በቀራኒዮ አከባቢ የተኩስ ድምጽ ይሰማል። ከአድማው ጋር ስለመገናኘቱ ግን እርግጠኛ አይደለንም። በአማራው አከባቢ ገና ነው። ምናልባት ሞቅ ሲል መቀላቀላቸው አይቀርም።

ፋና ደግሞ አንድ ዜና እንካችሁ ብሎናል። መቼም አድማውን ለማስቆም ታስቦ ሊሆን ይችላል። እነበቀለ ገርባ ክሳቸው ተቋርጦ እንዲፈቱ መወሰኑን በፋና በኩል ሰምተናል። እነ ቦንቱ በቀለ ገርባ አባታቸውን ከቤት አግኝተው እስኪነግሩን ለጊዜው ደስታችንን ቆጥበናል። ቢሆንም ትግሉ ይቀጥላል። ሁሌም እንደምንለው የታሰሩት ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ የታሰሩለት ዓላማ ሳይፈታ የሚመለስ ትግል አልተጀመረም።

ከሀማሬሳ ዛሬም ጥቃት መኖሩ እየተሰማ ነው። ይሄ መጥፎ ዜና ነው። ትላንት የተገደሉ ወገኖቻችን ሀዘን እያንገላታን ሌላ ዙር ግድያ ማንዣበቡን ስንሰማ በቄሮዎች ጀግንነትን የሞቀውን ልባችንን በወገኖቻችን ስቃይና ሞት እያቀዘቀዘው እንዳይሆን ስጋት አለኝ። ለማንኛውም ሰኞን ጀምረናታል። ይሄ ሳምንት ትግሉ አንድ ምዕራፍ ጠጋ የሚልባቸው ክስተቶች የሚስተናገዱበት ይመስለኛል። የእስረኞቹ መፈታት ይጠበቃል። በተለይም ዋና ዋና የፖለቲካ መሪዎች በዚህ ሳምንት መፈታታቸው የማይቀር ነው። አገዛዙ የስንግ ተይዟል። ከያቅጣጫው የመጣበትን ጫና የሚቋቋመው አልሆነም።

የኤች አር 128 ጫና የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባርን መንደር ብርክ አሲዞታል። የመከላከያ ሰራዊት ዓመታዊ በዓል በሚል የመሳሪያ ጋጋታ፡ የሰራዊት ሰልፍና ትርዒት በየከተሞቹ በማሳየት የተጠመደው ያለምክንያት አይደለም። ከውስጥ የሚንጠውን ፍርሃት ለመሸሽ፡ የሚፈራ ህዝብ ካገኘም በዚያው ለማስፈራራት በሚል ሰሞኑን ሰራዊቱን፡ ታንኮቹን፡ መድፎቹን፡ አሰልፎ እየፎከረ ነው። በእውን ፍርሃትን ለተገላገለ ህዝብ ይህ ግርግር ምኑ ነው?

አዎን! የህዝቡ የማያቋርጥ እምቢተኝነት አገዛዙን ትንፋሽ አሳጥቶ ውድቀቱን እያቃረበው ነው። እስከአሁን አሜሪካ ላስቀመጠችው ቀነ ገደብ ምላሽ አልስጠም። ፌብሯሪ 28 ሁለት ሳምንት ቀርቶታል። በእነዚህ ቀናት ውስጥ የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ያለአንዳች ተጽዕኖ በፈለገው ቦታና ጊዜ ምርመራ እንዲያደርግ በትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር በኩል ፍቃደኝነቱ ካልተገለጸ ረቂቅ ህጉ ለኮንግረስ ይቀርባል። በውጤቱም የአገዛዙ ባለስልጣናት በቡድንና በተናጠል ማዕቀብ ይደረግባቸዋል። ያኔ እጃቸው ተጠምዝዞ፡ አፍንጫቸው ተይዞ ከተጣበቁበት ወንበር ይነቀላሉ።

የህዝቡ ትግል መቆም የለበትም። እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ወደ አመጽና ተቃውሞ እየተቀየረ አገዛዙን ፋታ ማሳጣት ይገባል። ይህ የህዝብ ትግል ኤች አር 128ን ፈጥሯል። የእነለማን ቡድን አምጦ ወልዷል። የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባርን ትዕቢት ኩምሽሽ እንዲል አድርጓል። የህዝቡ ትግል የምዕራብያውያን መንግስታትን ከተኙበት አንቅቷል። ለአሜሪካን ኮንግረስ ረቂቅ ህግ ጉልበት ሆኗል። ለእነለማ ብድን ምርኩዝ፡ ነዳጅ፡ እህልና ውሃቸው ሆኗል።

እናም መቀዝቀዝ የለበትም። ለአፍታም መቆም አይኖርበትም። ያ ከሆነ አደጋው ከባድ ነው። ኤች አር 128 በመጣበት ፍጥነት ወደ ኋላ ሊመለስ ይችላል። እነለማን ማዳከሙ አይቀርም። ለትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር አፈር ልሶ የመነሳት ዕድል ሊሰጠው ይችላል። ይህ እንዳይሆን የህዝቡ ትግል በማንም ይጠራ፡ ይትም ይጠራ፡ መቀጠሉ ዋስትናችን ነው። ደብረታቦር ይሰማል? ጎንደር እንዴት ናችሁ? አርባምንጭ ምን አለ?

Filed in: Amharic