>

የኢትዮጵያ ህዝብ ተራበተራ መታረዱን እንደቀጠለ ነው (ሉሉ ከበደ)

…ዛሬ ደግሞ ሃረር ሃማሬሳ ላይ ወያኔ ዳግመኛ ባዲስ የጭፍጨፋ ግንባር ከፍቷል።አንድ ሚሊዮኖችን አፈናቅለው ሺዎችን ገድለው ኦሮሞ አልተቀጣም ብለው አስበዋል ይመስላል። ግድያውን ባዲስ ጀምረውታል።ሆን ብለው ፋታ እየሰጡ በሁሉም የሃገሪቱ አቅጣጫ ያለውን ህዝብ የሚያነሳሳ ነገር እየፈጠሩ ህዝቡ ድንገት በግብታዊነት ፍንቅል ብሎ ሲነሳ አጨዳውን ይጀምራሉ።በዚህ አይነት ስልት የህዝቡን ቁጥር ለመቀነስ እቅድ ያወጡ ሳይሆን አልቀረም። ብሶቱ ምሬቱ በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ እንዳለ ሆኖ ተቃውሞዎች የሚነሱት ድንገትና አንድ ጊዜ ካንድ ጥግ ሌላ ጊዜ ከሌላ ጥግ ነው። ተቃውሞዎችም የሚነሱት ህዝቡ መክሮና አቅዶ ባንድ ላይ ሳይሆን በተለያየ ጊዜና ቦታ በድንገት ነው። ገዢዎቹ ሆን ብለው እራሳቸው አንድ ነገር ያደርጉና ለዚያ ምላሽ ህዝብ በቁጣ ድንገት ሲነሳ መሳሪያ አቀባብለው እየጠበቁ ነውና ተኩሰው የቻሉትን ያህል ይገላሉ። አንድ ቦታ ይህ ሲደረግ ሌላ ቦታ ያለው ሰው ይሰማል።ወደሱ እስኪመጡ ከመጠበቅ በቀር ግን አይነሳም።

ወሎ ወልደያ የጥምቀት እለት ራሳቸው ተንኩሰው ያስነሱትን ህዝብ እስከቆቦና ሰሜን ወሎ ከልጅ እስካዋቂ የጨፈጨፉትና ያቆሰሉት ሳያንስ ህዝቡ ከታገሰ በኋላም አፈሳና ቅጥቀጣውን ተረጋግተው በመቀጠል ላይ እያሉ ነው ሌላው ቡድናቸው ደሞ በሃረር ሀማሬሳ በኩል የጀመረው።
ህዝባዊውንም አመጽ ራሳቸው ህዝቡን እየተነኮሱ ፤ እያነቆሩ ነው የሚቀሰቅሱት ፤ 2016፡17 የሶማሌ ክልል ጦር አዝምተው በሶማሌ ክልል አዋሳኝ ያሉ ንጹሀን ኦሮሞ አርሶ አደሮችንና ነዋሪዎችን መጨፍጨፍ ጀመሩ። በተለያዩ ኦሮሚያ ከተሞች ህዝቡ ለምን ብሎ ለተቃውሞ ተነሳ ። የሚፈልጉት ያን ነበርና እስከሚበቃቸው ገደሉ። ከዛ በፊት ባዲሳባ ማስተር ፕላን ሰበብ ያርሶአደሩን መሬት ቀምተው ሊሸጡ ሲሉ ህዝቡ ” መውደቂያ አታሳጡን ” ብሎ ተነሳ ። ያኔም እስከሚበቃቸው ገደሉ። ከዚያ ወደ ባህርዳር እናም ጎንደር ሄዱ ። የሚበቃቸውን ያህል ደም አፈሰሱ። ወሎ ወልደያ ተሻገሩ ። ያሻቸውን ያህል ደም አፈሰሱ። ፋታ ስላላቸው እንደገና ወደ ሃረር ተመልሰዋል። እስከመቼ? እስከመቼ? ተራ እየተጠበቀ መገደል ይቀጥላል?
ይህን ህዝብ የሚታደገው ሀይል ጠፋ። እራሱን እንዳይከላከል የሚመራው የሚያስተባብረውም የሚያስታጥቀውም ጠፋ።በመላ ሀገሪቱ ያለው ህዝብ ጭቆና፤ ግፍና መከራ፤ ሰብአዊ መብትረገጣ፤ የኑሮ ውድነት፤ የህይወት ዋስትና ማጣት ፤አንገፍግፎታል።ለዚህም ነው ትንሽ ሲነካኩት ፍንቅል የሚለው። ይህን የከፋው ህዝብ አስተባብሮ አንድ አቅጣጫ ይዞ አንድ ላይ ታግሎ ቶሎ ለውጤት እንዲበቃ ለማድረግ ወደፊት የሚመጣ ድርጅት ጠፋ። በውስጥም በውጭም ያሉ ተቃዋሚ ነን የሚሉ በዲስኩርና በመግለጫ ከማደንቆር በቀር ከምንም ነገር ህዝቡን ሊያስጥሉት አልቻሉም።በሰላም ተቀምጠው ህዝቡ ሞቶ አንድ ድል ቢያመጣ ለነሱ እንዲሸልማቸው ይጠብቃሉ።
ወያኔ በፈለገው ሰአት የፈለገውን አይነት ውሸት ለህዝቡ ይመግባል። በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ከፍተኛ ንቀት አድሮባቸዋል።እስረኛ እንፈታለን እገሌን እገሌን እንለቃለን ብለው ያውጃሉ። ህዝቡ እውነት እየመሰለው ሲጠብቅ እስረኛው ጋ ሄደው ያልሰራውን ወንጀል “ሰርቻለሁ ” ብለህ ፈርም ይሉታል። የፈለጉት ይፈታል። ያልፈለጉት እዚያው ይቀራል። ሌላም በላይበላይ እየመጣ እስርቤቱን ያጨናንቀዋል። ማንን ፈርተው እውነት ይናገሩ። ይህን ሁሉ የሚያደርጉት በህዝቡ ላይ ካላቸው ንቀትና ጥላቻ የተነሳ ነው።
ሀያ ሰባት አመታት ሙሉ ሀገር ወዳድ ዜጎች “አንድ እንሁን፥ አንድ እንሁን ፤እንተባበር ” ይላሉ። በሌላ በኩል ደሞ ዘረኛ የሆኑ ቆሻሻ ግለሰቦችና ድርጅቶች የወያኔው አልበቃ ብሎ ከፋፋይ፤ መርዘኛ ፤ የጥላቻና የልዩነት ፕሮፓጋንዳቸውን በህዝቡ ውስጥ ይረጫሉ። የኢትዮጵያን ህዝብ ውዥንብር ውስጥ ስለጣሉት አንድ መሆን አቅቶት ለወያኔ ጥቃት ክፉኛ ተጋለጠ። በዚ ህዝብ ላይ ለደረሰው ግፍና እልቂት ከወያኔ እኩል ተጠያቂ የማደርገው ዘረኛ የፖለቲካ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን ነው። ህዝቡ አንድ ልብ ቢሆን ፤ ባንድ አቅጣጫ እንዲጓዝ ብናደርገው ኖሮ ሀያሰባት አመት ሙሉ ያ ሁሉ ሰው ተገሎ አያልቅም ነበር። ወያኔም እስካሁን እየገደለና እየዘረፈ አይኖርም ነበር።
አሁንም ቢሆን ማምሻም ቢሆን እድሜ ነው እንደሚባለው በቀረን ጊዜ ህዝቡን በቶሎ አንድ እናድርገው። የለማ መገርሳንና የዶክተር አብይን ጥረት መደገፍና ማጠናከር ከጎናቸው መቆም የመላው ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነው። ይህ የህልውና ጉዳይ ነው።ይህ ስርአት መፍረስ አለበት ።ህውሀት የሚባል ድርጅት ጥልቅ ጉርጓድ ውስጥ መቀበር አለበት። የዘር ፖለቲካ ከነፈጣሪው ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከርሰመቃብር መውረድ አለበት። ሁሉም ነገር ፈርሶ ባዲስ መሰራት አለበት።ብዙ ስራ ይጠብቀናል። እስከዛሬ ላለቁት ወገኖቻችን ፍትህን እንሻለን።እስከዛሬ የተዘረፈውን ያገርና የግለሰብ ሀብት የማስመልውስ ስራ ይጠብቀናል።
ሰራዊቱ .። ይህ ቃታ እየሳበ ወግኖቹን በመግደል ላይ ያለው ፥ አምሮው ከጭቃ ይሆን የተሰራው? ይህ ሰራዊት ከኢትዮጵያ ህዝብ አልተወለደም? ትክክለኛና ትክክለኛ ያልሆነ ትእዛዝ መለየት የሚያስችል ጤናማ አእምሮ የለውም? አንድም ጀግና የአማራ ልጅ ፤ አንድም ጀግና የኦሮሞ ልጅ ፤ አንድም ጀግና የደቡብ ልጅ፤ አንድም ጀግና የኢትዮጵያ ልጅ የለም? አፈሙዙን በአዛዦቹ ላይ መልሶ ህዝቡን የሚያድን ወንድ ጠፋ? ህውሀት ሁሉንም ትጥቃቸውን አስፈትቶ ሲረሽናቸው እንዳናይ ፈራሁ። ህዝቡን ማዳን ቀርቶ ራሳቸው ህዝቡን አድነን እንዳይሉ ፈራሁ። ብረት ተሸክመው ወታደሮቹ ልጆቻችን።
ቄሮዎችም ፋኖዎችም ካላችሁ እስቲ ተቀናጁና አንድ ቋንቋ ተናገሩ.ተናበቡና አንድ ነገር አድርጋችሁ አሳዩን። ህዝቡ ተአምር ሊሰራ ነዶ፤ አሮ ፤በስሎ፤ ተዘጋጅቷል። እስቲ አንድ ቀንበር ፍጠሩና በአንድ አቅጣጫ አንቀሳቅሱት። ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰአት ያላት ጠላት አንድ ነው። የትግሬው ነጻ አውጭ የሚመራው ፋሺሽት ገዢ ቡድን። ሞት ለወያኔና ተላላኪዎቹ። ድል የህዝብ ነው። እምዬ ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!

Filed in: Amharic