>

7ቀን በአሜሪካ፦ አሜሪካኖች የቀድሞ መሪዎቻቸውን ያከብራሉ፣ ኢትዮጲያኖች ይራገማሉ! (ስዩም ተሾመ)

በዚህ ዓመት መስከረም ወር ላይ በአሜሪካን ሀገር የዋሽንግተን ዲሲ በነበረኝ የአንድ ሳምንት ቆይታ የታዘብኳቸውን ነገሮች በፎቶ አስደግፌ “እንሆ በረከት” ልላችሁ ወደድኩ። በዚህ ፅሁፍ የማቀርበው በግሌ የተሰማኝንና የታዘብኩትን እውነት ብቻ ነው፡፡ እንደምትወዱት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ከላይ ያለው ያለው ፎቶን የተነሳነው በአሜሪካን የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት የነበረን ስብሰባ እንደተጠናቀቀ ነው። ከዚያ በኋላ እኔና ከታች ባለው ፎቶ ላይ አንድ ወንድና ሦስት ሴቶች፣ ከእኔ ጋራ አምስት ሆነን የሊንከን ሜሞሪያል ለመጎብኘት ሄድን። ሴቶቹን ፎቶ የሚያነሳው አስጎብኚያችን ሲሆን የሩሲያ ጎረቤት ከሆነቸው ጆርጂያ የመጣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነው። ሴቶቹ ድግሞ፤ ከግራ ወደ ቀኝ፤ ከኤልሳቫዶር፥ ፓኪስታንና ኮስታሪካ የመጡ ናቸው። በፎቶው ላይ እንደምታዩዋት ፓኪስታናዊቷ የእኔ ብጤ ቦርጫም ናት። ከኤልሳቫዶር የመጣችዋ ደግሞ የምትናገረው እንግሊዘኛ ይሁን ላቲን መለየት ይከብዳል።

በስብሰባው ወቅት በካምቦዲያ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ነበር። ከካምቦዲያ የመጣው የመብት ተሟጋች ምሳ ላይ አብረን ነበር። የሀገሪቱ መንግስት በዜጎች ላይ ስለሚፈፅመው ግፍ አጫውቶኛል። ወደ ሊንከን ሜሞሪያል ለመሄድ ከውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ስንወጣ ደግሞ ካምቦዲያዊያን ከመስሪያ ቤቱ ፊት ለፊት የተቃውሞ ሰልፍ ሲያደርጉ ተመለከትኩ። ከታች በፎቶው ላይ እንደምትመለከቱት ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሰዎች የፖሊስን መኪና ተደግፈው ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው። በፎቶው ላይ በደንብ ይታይ እንደሆነ እኔ’ጃ፣ ነገር ግን በመኪናው ውስጥ ፖሊስ እንደነበረ አስታውሳለሁ። ይህን ጉዳይ የማነሳው የተለየ ነገር ሆኖ አይደለም። ሰልፈኞቹን እንዲህ ከፖሊስ መኪና ጎን ተቀምጠው ስመለከት ሰላማዊ ሰልፈኞች በጥይትና ቆመጥ የሚቀጠቅጡ የሀገሬን ፖሊሶች በአይነ-ህልናዬ እየመጡ ቢያስቸግረኝ ነው እንጂ…

ከአብርሃም ሊንከን ሜሞሪያል ስንደርስ ከታች እንደምታዩት ከውጪም፥ ከውስጥም ብዙ ሰዎች ተኮልኩለዋል። ሕፃናት፣ ወጣቶች፥ አዛውንትና አረጋዊያን አሜሪካኖች በሀገራቸው ታሪክ ትልቅ ክብር የሚሰጡትን ፕረዜዳንት ማስታወሻ ይጎበኛሉ።

በቀኝ በኩል ባለው የፕረዘዳንቱ ሃውልት ከላይ በኩል የተፃፈው ፅሁፍ እንዲህ ይላል፡-

“IN THIS TEMPLE AS IN THE HEARTS OF THE PEOPLE FOR WHOM HE SAVED THE UNION THE MEMORY OF ABRAHAM LINCON IS ENSHRINED FOREVER”

በግሌ አብርሃም ሊንከንን በጣም አደንቀዋለሁ። ስለ እሱ ለማወቅ ካለኝ ጉጉት የተነሳ ለፕረዜዳንትነት ሲመረጥ ያደረገው ንግግርን ሳይቀር አንብቤያለሁ። የፅሁፉ ጥልቀት የፖለቲካ ፍልስፍና እንጂ በፍፁም በፕረዜዳንትነት ሹመተ-በዓል ላይ የቀረበ ንግግር አይመስልም። ለአብርሃም ሊንከን ካለኝ አድናቆት በተጨማሪ አሜሪካ መሄዴን አመኖ መቀበል ለከበዳቸው አንዳንድ ወዳጆቼ ማስረጃ ይሆን ዘንድ እኔም ከሃውልቱ ፊት ቆሜ የተነሳሁትን ፎቶና በአደራሹ አንድ ጥግ የተመለከትኩት የፕረዜዳንቱን ምስል እንሆ…

ከላይ ባለው የአብረሃም ሊንከን ምስል ጎን ያለው ፅሁፍ እንዲህ ይላል፡- “The man who gave meaning, honor, and purpose of a nation speaks to us still.” አዎ… የሀገርን ትርጉም፥ ክብርና ፋይዳ የሰጠው ፕረዜዳንት ዛሬም ድረስ ለአሜሪካኖች እየተናገረ ነው። አብርሃም ሊንከን ለአሜሪካ ትርጉም፥ ክብርና ፋይዳ የሰጣት አስከፊውን የአሜሪካ የእርስ-በእርስ ጦርነት በማሸነፍ የሀገሪቱን አንድነት በማስከበር ነው። በዚህ ምክንያት፣ ዛሬም ድረስ ለሀገሪቱ ሕዝብ ይናገራል፣ ዛሬም ድረስ አሜሪካኖች ጆሮና ልባቸውን ሰጥተው ያዳምጡታል።
ኢትየጲያዊያን ግን የአፄ ሚኒሊክን ስም እያነሱ፤ ግማሾቹ እንደ ሰይጣን ሲረግሙት፣ ሌሎቹ እንደ ጣዖት ሲያመልኩት፣ የተቀሩት በማን-አለብኝነት ሰምተው እንዳልሰማ ሲያልፉት ይውላሉ። የሀገሪቱን መስራች ከመስማት ይልቅ አፅሙን መቀስቀስ፥ ሃውልቱን ማፍረስ ያሰኘናል። ለታሪክ ከመማር ይልቅ የቀድሞውን ታሪክ በራሳችን ግንዛቤ ልክ መፃፍ ያምረናል። ታሪክን ማወቅ፣ እውነትን መገንዘብ ተስኖናል። በዚህ ምክንያት የሀገር ትርጉም፥ ክብርና ፋይዳ ጠፍቶብናል።

ከሊንከን ሜሞሪያል እንደወጣን ፓክስታናዊቷን ወዳጃችንን መፈለግ ጀመርን። ምክንያቱም የሊንከን ሜሞሪያል በከፍተኛ ቦታ ላይ የተገነባ ሲሆን ከላይ በፎቶው ላይ እንደምታዩት ደረጃዎቹ ትላልቅ ናቸው። የዕለቱ አየር በጣም ሞቃታማ ስለነበር ፓክስታናዊቷ ወዳጃችን በጣም ደክሟት ነበር። በዚያ ላይ ቅድም እንዳልኳችሁ ከእኔ የባሰች ወፍራም ናት። በዚህ ምክንያት፣ ትላልቆቹን ደረጃዎች በመውጣት ወደ አዳራሹ ውስጥ መግባት አልቻለችም ነበር። በመጨረሻ ከአንዱ ጥግ ቁጭ ብላ ሲጋራ ስታጨስ አገኘናትና ወደ ኮሪያ የጦር ሜሞሪያልን ለመጎብኘት ሄድን።

ኮሪያ የጦር ሜሞሪያል እየሄድን ሳለ አስጎብኚያችን ስለ ኮሪያ ጦርነት ብዙ ነገር ማውራት ጀመረ። ብዙ ሀገራት ደቡብ ኮሪያን ከሰሜን ኮሪያዎች ወረራ ለመታደግ ለከፈሉት መስዕዋት ክብር ሲባል የተገነባ ማስታወሻ እንደሆነ ተናገረ። በመቀጠል የሀገራቱን ስም ዘረዘረና ኢትዮጲያን ዘለላት። ታሪኩን በደንብ ያውቅ እንደሆነ ስጠይቀው በልበ ሙሉነት “በደንብ አውቀዋለሁ!” አለኝ። ከዛ “ታሪኩን በደንብ የምታውቅ ከሆነ ኢትዮጲያን ለምን ዘለልካት?” ብዬ በለበጣ ጠየቅኩት። “ኧረ በጭራሽ…ኢትዮጲያ የለችበትም” አለኝ። አለማወቁ ሳያንሰስ እርግጠኝነቱ አበሳጨኝና “ባክህ ስለማታውቀው ነገር ዝም ብለህ አትቀባጥር” አልኩት። ይባስ ብሎ “ይኸው ደርሰን የለ… አይተህ ማረጋገጥ ትችላለህ!” አለኝ።

እኔና እሱ ደግሞ በእልህ ወደ ኮሪያ የጦር ሜሞሪያል በጥድፊያ መራመድ ጀመርን። ሁለቱን ሴቶች ጥለናቸው ሄድን። የኮስታሪካዋ ቆንጆ ግን ከኋላችን ቱስ..ቱስ እያለች ነው። ልክ ከቦታው እንደ ደረስን የሀገራት ስም የተፃፈበት ጡብ ላይ አፈጠጥን። በእንግሊዘኛ ፊደል ተራ ቅደም ተከተል “Denmark” ይልና “Ethiopia” ይላል።

“ሃሃሃ…” ብዬ በኩራት ትንሽ ተንቀባረርኩበት። እንዳናደደኝ ትንሽ ላናድደው ፈለኩና “የሩሲያ ታንኮች በአንድ ሰዓት ከዳር እስከ ዳር በሚሮጡባት፣ ከዚያች የእጅ መዳፍ ከምታክል ሀገር መጥተህ ‘ኢትዮጲያ የለችም!’ ትለኛለህ?” አልኩትና ከሃውልቱ ስር ያለውን ጽሁፍ በተመስጦ ማንበብ ጀመርኩ፡-

“OUR NATION HONORS HER SONS AND DAUGTHERS WHO ANSWERED THE CALL TO DEFENED A COUNTRY THEY NEVER KNEW AND A PEOPLE THEY NEVER MET. 1950. KOREA. 1953” KOREA WAR MEMORIAL, WASHINGTON DC, USA

ፅሁፉን ደግሜ-ደጋግሜ ሳነበው የሀገራችን የኮሪያ ዘማቾች በዓይነ-ህልናዬ መጡ። እነዚህ የሀገሬ ዘማቾች በአንድ ወቅት ከማያውቁት ሀገር እና በአካል ከማያውቁት ሕዝብ የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው ለሰዎች ነፃነትና እኩልነት መስዕዋት ከፍለዋል። አሁን ያሉት የሀገራችን ወታደሮች በሁለት አመት ውስጥ ብቻ ከ1200 በላይ ንፁሃን የሀገራቸውን ዜጎች እንደ ጠላት ጦር በጥይት ተኩሰው ገድለዋል። ለማያውቁት ሀገርና ሕዝብ መስዕዋት ከመሆን የራስን ሕዝብ መስዕዋት ወደ ማድረግ ከመሸጋገር ይልቅ ወታደሮቹን እንደ ወራሪ ጦር ሰራዊት ማየት የሚቀል ይመስለኛል። በእርግጥ በዚህ አመት ብቻ በአምቦ፥ ጨለንቆ፥ ወልዲያ፥ ቆቦ፥ ሲሪንቃ፥… በዜጎች ላይ የተፈፀመውን ግፍና ጭፍጨፋ ለተመለከተ “የውጪ ሀገር ወራሪ ጦር ቢሆንስ ከዚህ በላይ ምን ሊያደርግ ይችላል?” ያሰኛል።

ከአቀረቀርኩበት ቀና ስል አስጎብኚው ሰውዬ ለካስ በንዴት ጦፎ፥ የኮስታሪካዋን ቆንጆ ጠልፎ ጥሎኝ ሄዷል። ወደኋላ ዞር ብዩ ስመለከት የኤልሳቫዶሯ ተብታቤ እና የፓኪስታኗ ድንቡጬ ገና ኮሪያ ሜሞሪያል ጋር አልደረሱም። በፎቶው ላይ እንደምታዩት ገና ከሩቁ በድካም እንደ ዶሮ እያለከለኩ እንደሆነ ያስታውቃል። እኔ ጋር እንደደረሱ “ሁለቱ ወደየት ሄዱ?” አሉኝ። የማርቲን ሉተር ሜሞሪያልን ለመጎብኘት እንደሄዱ ነገርኳቸው። እኛም ወደዛ እንሂድ ልላቸው መስሏቸው መዝለፍለፍ ሲጀምሩ “እኔ ወደ ሆቴል መመለስ እፈልጋለሁ” አልኳቸው። ሁለቱም በእፎታ ቁጭ ብለው ማለክለክ ጀመሩ።

ያ መናጢ ጆርጂያዊ ከጎኔ የሞጨለፋትን ኮስታሪካዊ ቆንጆ እያሰብኩ ከኋላ ወዳለው ሳር ስሄድ ሌላ ቆንጆ አገኘሁ። ከዚህች ቆንጆ ጋር የደራ ጨዋታ ጀመርኩ። የእጄ ጣት ላይ ምራቄን አድርጌ ስሰጣት አንዴ በአፏ ነካችኝ! ደስ አለኝ! የሳመችኝ መሰለኝ። ይቀጥላል…

Filed in: Amharic