አርቲስት ዳምጠው አየለ በሰላም ከሚያከብረው ሕዝቡና ከሚያፈቅራቸው ቤተሰቦቹ ጋር ተቀላቅሏል ጋዜጠኛ ኣበበ ደመቀ-ኖርዌ
ምክትል መቶ አለቃ አርቲስት ዳምጠው አየለ ለ8 ዓመታት በስደት ከቆየባት ከኖርዌይ ባለፈው ሰኞ ጁን 16 ወደሚወዳት ሃገሩ በክብር ተሸኝቶ፤ከሚያከብረውሕዝቡና ከሚያፈቅራቸው ቤተሰቦቹ ጋር በሰላም ተገናኝቷል።
የምክትል መቶ አለቃ አርቲስት ዳምጠው አየለ የጤና ሁኔታ አሳሳቢነትና ፤ የሃገሩ ፣ የሕዝቡና ፣ የቤተሰቡ ናፍቆት ታክሎበት ወደ ሃገሩ መመለሱን የመረጠው አርቲስት ዳምጠው አየለ ፥ በስደት ቆይታው ወቅት ባፈራው ተወዳጅነት ፣ ሃገር አፍቃሪነትና ባህል አክባሪነት በኖርዌይ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ታላቅ ክብርንና ፍቅርን ያተረፈ ሲሆን የኢትዮጵያውያን ኮሚዩኒቲ በኖርዌይ ተወዳጁን ባለሙያ በተለያየ መልኩ ለመደገፍ በአስቸኳይ 8 አባላትን የያዘ ግብረ ሐይል በማቋቋም ከፍተኛ የሆነ የገቢ ማሰባሰቢያ ያደረገ ሲሆን የያሬድ ባህል ባንድ እና በፈቃደኝነት የተሰባሰቡት አርቲስቶች በቦታው በመገኘት በማስተባበርና በመምራት ፤ የተለያዩ የብሔር ብሔረሰቦችን ጨዋታ በማሳየት እምቅ ችሎታቸውን በማውጣት የሙያ አጋርነታቸውን በብቃት የተወጡ ሲሆን ፤ በቦታው የስነ ግጥም እና ጨረታም ተካሂዷል።
በአጠቃላይ ለዚህ ወገናዊ ጥሪ የእድሜ ፣ የፆታ ፣ የብሔር ፣ የሃይማኖት፣ የፖለቲካ አጥር ሳይገድባቸው ለዚህ አመርቂ ክንውን በገንዘባቸው በጉልበታው በእውቀታቸው ድጋፋቸውን ላበረከቱ ሁሉ የኮሚውኒቲው ሊቀመንበር አቶ ፋሲል ያመሰገኑ ሲሆን ፥አርቲስቱም በአጠቃላይ የኖርዌይ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ላደረገላቸውና ላሳያቸው ፍቅር እግዚአብሔር ዋጋችሁን ይክፈላችሁ በማለት መልካሙን ተመኝተዋል ። የኢትዮጵያ ማህበር በኖርዌይ ለሰጠው አፋጣኝ ተግባራዊ ምላሽ ፡ በኢትዮጵያውያን ዘንድም ታላቅ ስኬት ተብሎለታል ።