>

ኣሳዛኝ ዜና፥ ኣርቲስት ዳምጠው ኣየለ በሚወዳት ሃገሩ ህይወቱ ኣልፏል

Artict Damtew Ayeleኣርቲስት ዳምጠው ኣየለ ለስምንት ዓመታት ከቆየባት ኖርዌይ ሃገር፤ ህመሙ  ጠንቶበት ነበር ወደ ሃገር ቤት የሄደው።  በስደት ከቆየባት ከኖርዌይ ባለፈው ሰኞ ጁን 16 ወደሚወዳት ሃገሩ በክብር ተሸኝቶ ከሚያከብረው ሕዝቡና ከሚያፈቅራቸው ቤተሰቦቹ ጋር በሰላም ተገናኝቶ መቀላቀሉንም ዘግበን ነበር። ሃገር ወዳዱና ተወዳጁ ኣርቲስት ዳምጠው ኣየለ፤  በኣዲስ ኣበባ ቅዱስ ገብር ኤል ሆስፒታል ህክምናውን ሲከታተል የነበረ ቢሆንም፣  ህመሙ እየጸናበት ስለሄደ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወደ መኖሪያ ቤቱ ገብቶ በህክምና እንደ እግዚኣብሔር ፈቃድ ሲረዳ ቆይቶ፤ በዛሬው ዕለት ጁላይ 7 ቀን 2014 የድንቅየው ኣርቲስት ህይወት ማለፉን ለማወቅ ችለናል። በዚሁ ኣጋጣሚ ኢትዮ ሪፈረንስ የኣርቲስት ዳምጠው ኣየለን ነፍስ በገነት እንዲያኖርልን ፣ ቤተሰቦቹንም ለመጽናናት ያበቃልን ዘንድ ምኞታችን ነው።

አርቲስት ዳምጠው አየለ በሰላም ከሚያከብረው ሕዝቡና ከሚያፈቅራቸው ቤተሰቦቹ ጋር ተቀላቅሏል ጋዜጠኛ ኣበበ ደመቀ-ኖርዌ

ምክትል መቶ አለቃ አርቲስት ዳምጠው አየለ ለ8 ዓመታት በስደት ከቆየባት ከኖርዌይ ባለፈው ሰኞ ጁን 16 ወደሚወዳት ሃገሩ በክብር ተሸኝቶ፤ከሚያከብረውሕዝቡና ከሚያፈቅራቸው ቤተሰቦቹ ጋር በሰላም ተገናኝቷል።

የምክትል መቶ አለቃ አርቲስት ዳምጠው አየለ የጤና ሁኔታ አሳሳቢነትና ፤ የሃገሩ ፣ የሕዝቡና ፣ የቤተሰቡ ናፍቆት ታክሎበት ወደ ሃገሩ መመለሱን የመረጠው አርቲስት ዳምጠው አየለ ፥ በስደት ቆይታው ወቅት ባፈራው ተወዳጅነት ፣ ሃገር አፍቃሪነትና ባህል አክባሪነት በኖርዌይ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ታላቅ ክብርንና ፍቅርን ያተረፈ ሲሆን የኢትዮጵያውያን ኮሚዩኒቲ በኖርዌይ ተወዳጁን ባለሙያ በተለያየ መልኩ ለመደገፍ በአስቸኳይ 8 አባላትን የያዘ ግብረ ሐይል በማቋቋም ከፍተኛ የሆነ የገቢ ማሰባሰቢያ ያደረገ ሲሆን የያሬድ ባህል ባንድ እና በፈቃደኝነት የተሰባሰቡት አርቲስቶች በቦታው በመገኘት በማስተባበርና በመምራት ፤ የተለያዩ የብሔር ብሔረሰቦችን ጨዋታ በማሳየት እምቅ ችሎታቸውን በማውጣት የሙያ አጋርነታቸውን በብቃት የተወጡ ሲሆን ፤ በቦታው የስነ ግጥም እና ጨረታም ተካሂዷል።

Damtew Ayele 4ምክትል መቶ አለቃ አርቲስት ዳምጠው አየለ በኢትዮዽያ ማህበር በኖርዌይ ቆይታቸው በነበራቸው ፤ ሃገራዊ ፍቅር ባህላችንን በማስተዋወቅና ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ጠብቀንና አክብረን እንድንቀጥል ታላቅ በሆነው ሙያዊና ፡ የካበተ ልምዳቸውን በማካፈል ላደረጉት አስተዋፅኦና ላበረከቱት አገልግሎት አቶ ፋሲል አለባቸው የኢትዮጵያ ኮሚዮኒቲ ሊቀመንበር ለአርቲስቱ የምስክር ወረቀት ጁን 9/2014 በክብር ሰጥተዋል ።

በአጠቃላይ ለዚህ ወገናዊ ጥሪ የእድሜ ፣ የፆታ ፣ የብሔር ፣ የሃይማኖት፣ የፖለቲካ አጥር ሳይገድባቸው ለዚህ አመርቂ ክንውን በገንዘባቸው በጉልበታው በእውቀታቸው ድጋፋቸውን ላበረከቱ ሁሉ የኮሚውኒቲው ሊቀመንበር አቶ ፋሲል ያመሰገኑ ሲሆን ፥አርቲስቱም በአጠቃላይ የኖርዌይ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ላደረገላቸውና ላሳያቸው ፍቅር እግዚአብሔር ዋጋችሁን ይክፈላችሁ በማለት መልካሙን ተመኝተዋል ። የኢትዮጵያ ማህበር በኖርዌይ ለሰጠው አፋጣኝ ተግባራዊ ምላሽ ፡ በኢትዮጵያውያን ዘንድም ታላቅ ስኬት ተብሎለታል ።

 

Filed in: Amharic