>
5:21 pm - Sunday July 20, 7000

ቴዎድሮስ እና ማርቲን ...!!! (አሳፍ ሀይሉ)

ቴዎድሮስ እና ማርቲን …!!!

አሳፍ ሀይሉ

የብሪታንያው ልዩ ልዑክ ሆርሙዝድ ራሳም፣ ከአፄ ቴዎድሮስ ህልፈተ-ህይወት አንድ ዓመት በኋላ፣ ‹‹ወደ አቢሲኒያ ንጉሠ ነገሥት ቴዎድሮስ የተደረገው የብሪታንያ ዘመቻ ዝክር›› በሚል ርዕስ ያሳተመው የታሪክ ማስታወሻ አለ።
ሆርሙዝድ ራሳም ማነው? ባጭሩ ለማስታወስ ራሳም ማለት ወደ ንጉሠ ነገሥት ቴዎድሮስ በንግሥት ቪክቶሪያ የተላከውና የአፄው መልካም ወዳጅ ለመሆን የበቃው፣ (ነገር ግን ኋላ መልካም ወዳጅነቱ እንደተጠበቀ፣ ምቾቱም ሳይጓደልበት፣ የቴዎድሮስን አውሮፓውያን የቁም እስረኞች የተቀላቀለው)፣ የንግሥቲቱ ልዩ መልዕክተኛ ነው።
የእንግሊዞች ጦር አፄ ቴዎድሮስ ወደ መሸጉበት የመቅደላ አፋፍ እየተጠጋ በመጣ ጊዜ – ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ቴዎድሮስ ራሳምን አስጠርተው የነገሩትን ቃል፣ በማስታወሻው ቃል-በቃል አስፍሮታል፡፡ ከብዙ በጥቂቱ ቴዎድሮስ ለራሳም ካሉት ውስጥ እንዲህ የሚል ንግግር ይገኝበት ነበር፡-
“‘ነገ እዚህች አምባ ላይ ወይ እኔ
ወይ ደግሞ ያንተ ወገኖች
መውደቃችን የማይቀር ነገር ነው፣
እኔ ያ አያሳስበኝም፣ በዚህች ዕለት
እንደ ቀድሞዬ ኢትዮጵያ ሁሉ-በእጄ
ሆና ብንገናኝ ነበር የምመኘው፣
ምን ይደረግ ብለህ ነው?
“ሀገሩ ሁሉ አመፀኛ ሆኖ ከዳኝ፣
አሁን በእጄ የቀረኝ 7ሺህ ወታደርና
ይቺ የአለት ተራራ ብቻ ናት፡፡ ህይወቴ
ብታልፍም ይህን እንደምታስተውል
እርግጠኛ ነኝ፣
“እስከመጨረሻዋ ሰዓት እንክብካቤዬን
ሳላጓድል በክብር ይዤያችኋለሁ፣
ከዚህም በኋላ ምንም እንደማይደርስ
ባችሁ ቃሌን እሰጥሃለሁ፣ ለእናንተም
ሆነ ለንግሥታችሁ በልቤ ጥላቻ
ያላሳደርኩ ሰው መሆኔንም ሳታውቀው
አትቀርም፣ …
” ‘እ… የናንተ ሰዎች እዚህ አምባ ላይ
ወጥተው ሲያዩኝ፣ እና ጥቁር መሆኔን
ሲመለከቱ እንደማይጠሉኝም ተስፋ
አደርጋለሁ መቼም! አምላክ ሲፈጥረን
ለሁላችን የሰው ልጆች የሰጠን አንድ
ዓይነት ጭንቅላትና አንድ ዓይነት
ልብ ነውና…’
“ብለው በመልካም መስተንግዶ አሰና
ብተውኝ፣ ታች ማዶ በሳላምጌ ወደ
ተከሉት የጦር ካምፓቸው ወረዱ፡፡…”
በማለት ከአፄ ቴዎድሮስ አንደበት በመጨረሻዋ ሰዓት የሰማውን ለታሪክ አስፍሮ አስቀምጦልናል።
ለአሁኑ ትኩረቴን የሳበችውን የአፄ ቴዎድሮስን የመጨረሻዋን ዐረፍተ ነገር በራሱ በሆርሙዝድ ራሳም ቪክቶሪያዊ እንግሊዝኛ እንደተፃፈችው ባቀርባት ደስ ይለኛል። የመጨረሻዋ ክፍል እንዲህ ትነበባለች፦
“…‘I hope, Mr. Rassam,’ Theodore
added, ‘that when your people
arrive they will not despise me
because I am black; God has
given us all the same faculties
and heart.’ With this the interview
closed and Theodore descended
again to his camp at Salamgie.”
  — Hormuzd Rassam, Narrative of the British Mission to Theodore, King of Kings of Abyssinia (Murray, 1869); quoted in Alan Moorehead, The Blue Nile, pp 251, 1962.)
እኚህ የሀበሻ ንጉሥ በዚያን ዘመን (ከ150 ዓመት በፊት) ስለ ሰው ልጅ እኩልነት የነበራቸውን ያልተዛባ አስተሳሰብ ስመለከት በጣም ገረመኝ፡፡
በአጋጣሚ ሆኖ ዛሬ የአሜሪካኖች ታላቁ የፀረ-ዘረኝነት ትግል አራማጅ የማርቲን ሉተር ኪንግ ጁንየር የልደት መታሰቢያ ተከብሮ የሚውልበት አጥቢያ ቀንም ነው::
ማርቲን ሉተር ጃንዋሪ 15/1929 (ማለትም በእኛ የዘመን አቆጣጠር በጥር 7 ቀን 1921 ዓ.ም.) ነው የተወለደው። አፄ ቴዎድሮስ ደግሞ በጥር 6 ቀን 1811 ዓ.ም. ነው የተወለዱት፡፡ እንግዲህ አፄ ቴዎድሮስ በጥር 6 በተወለዱ በ110ኛ ዓመታቸው ላይ፣ ማርቲን ሉተር በጥር 7 ተወለደ እንደማለት ነው! ምርጥ የጥር ልጆች! አስገራሚ ግጥምጥሞሽ!
ይበልጥ የሚገርመው ግጥምጥሞሽ ደግሞ፣ የኛው አፄ ቴዎድሮስ የጥቁርንና የነጭን ወይም የሰውን ዘር ሁሉ እኩልነት ከተናገሩ ከክፍለዘመን በኋላ፣ ማርቲን ሉተርም ያንኑ የእሳቸውን ቃል እንደ መፈክር ይዞ ለእኩልነት ትግል መነሳቱ ነው።
“የሰው ልጅ በምግባሩ እንጂ ጥቁር ነጭ ተብሎ በዘሩና በቆዳ ቀለሙ እየተለየ ማንነቱ እንዳይዳኝ” አጥብቆ ህልሙን የተናገረበት በጣም የምወደው የማርቲን ሉተር ትንቢት የመሰለ ንግግር አለ፡፡
ነገር ግን ማርቲን ሉተር በ1964 የሚናገረው ከእርሱ 100 ዓመት በፊት አፄ ቴዎድሮስ ለሆርሙዝ ራሳም የነገሩትን እና በክብር የሞቱለትን የነፃነት መርህ ነው፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግ እንዲህ ነበር ያለው፡-
“ሕልም አለኝ፡፡ አንድ ቀን አራቱ ልጆቼ እንዳሁኑ
በቆዳቸው ቀለም፣ በዘር ሃረጋቸው፣ ወይ በፀጉራቸው
ሳይሆን፣ በውስጣቸው በያዙት፣ እና አውጥተው
በሚያንፀባርቁት የባህርይ ታላቅነት ወይም ወራድነት
ብቻ ማንነታቸው የሚመዘንበት አንድ የነፃነት ቀን
እንደሚመጣ ሕልም አለኝ፡፡”
የማርቲን ሉተርን ኦሪጂናል ንግግር ከድረገፅ ላይ ከሚገኘው “I have a dream” ንግግሩ ላይ በፅሑፍም በቪዲዮም እየተናገረው የተቀረፀውን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል። በራሱ ቃል እንዲህ ነበር ያለው ማርቲን፦
(“…I have a dream that my four
little children will one day live in
a nation where they will not be
judged by the color of their skin
but by the content of their character.”)
ማርቲን ሉተር ለብዙዎቻችን አርዓያ ሰብዕ የመሆኑን ያህል – ብዙዎቻችን ያለንን የራሳችንን የከበረ ወርቅ ሰብዕና፣ እና ከወርቅም በላይ የነፃ አኩሪ ታሪካችንን የማናውቅ ሆነን እንጂ – ከማርቲን በፊት የእርሱን የነፃነት መርህ በነፍሳቸው ተወራርደው ከፍ አድርገው በመቅደላ አደባባይ በክብር ያውለበለቡት ጀግናና ኩሩ ኢትዮጵያዊ ንጉሥ ደግሞ እንዳሉን በራሳቸው በእንግሊዞቹ ፀሐፊ በመፅሐፍ ታትሞ የተከተበ ሀቅ ነው! እውን ነው! ይህን ስናስብም ደስታችን ወደር የለውም!
ይህች የሀበሻ ምድር፣ እና እኒህ የሀበሻ ነገሥቶች – ለዚህች ላበቀለቻቸው ቅድስት ምድር፣ እና ለሚመላለሱበት የተቀደሰ የነፃነት አየር ምን ያህል ክፉኛ በፍቅር የወደቁ መሆናቸውን ሳስብ – ከእነዚህ ታላቅ የሰው ልጅ የነፃነት ሃዋርያዎች የተመዘዝኩ ታላቅ ኢትዮጵያዊ በመሆኔ – ባለሁበት ሥፍራ – በኢትዮጵያዊነቴ – ከፍ ያለ ክብርና ግርማ ሞገስ በላዬ ሲተንን ይሰማኛል፡፡ ክብር ለኢትዮጵያችን ይሁን!
በነገራችን ላይ የአለን ሙርሄድ መፅሐፍ ስለዚህ ከዘመኑ ቀድሞ ስለተወለደ አርቆ አስተዋይ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አፄ ቴዎድሮስ ብዙ የሚናገረው አለው፡፡
በሀገራችን በመልዕክተኝነት መጥቶ በእስረኝነት ያሳለፈው የንጉሡ ወዳጅ ራሳም እንኳ ከምሬቱና ከእገታው ባሻገር ለአፄ ቴዎድሮስ የነበረው ልዩ አክብሮት ሰማይ ጠቀስ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
እኚህን ትውልዳቸው ያልተረዳቸውን፣ ዘመን ያከበራቸውን፣ ታላቅ የሰው ልጆች እኩልነት ሰባኪ፣ እና ታላቅ የኢትዮጵያ መሐንዲስ፣ ንጉሠ ነገሥት አፄ ቴዎድሮስ ዳግማዊን፣ በዛሬዋ ዕለት እንኳን ተወለዱልን ንጉሣችን ብዬ በአክብሮት 203ኛውን የውልደታቸውን ዝክር በክብር አሰብኩ፡፡
ለታላቁ የአሜሪካ የፀረ-ዘረኝነት ትግል መሪ፣ ለምናከብረው ወንድማችን፣ ለዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁንየርም – 93ኛ የልደት ቀኑ መታሰቢያ ዝክር ይሆንልን ዘንድ በማሰብ ዝክሬን አበቃሁ!
ክብር ለኢትዮጵያ!
ክብር ታላላቅ ሕልሞችን ለሰነቁ ታላላቅ ነገሥቶቻችን!
ክብር ለነፃነታችን!
ክብር ለሺኅ ዘመናት በነፃነት ላስጓዘን ነፃነት-ወዳድ ኢትዮጵያዊ ጀግንነታችን ይሁን!
የበዛ ክብር በፍቅሩ ለምንገዛለት ሁሉን ለፈጠረ ኃያል አምላክ!
Filed in: Amharic