>

አድዋ፦ ሶስተኛው ፍልስፍናዊ አብዮት !!!

አድዋ፦ ሶስተኛው ፍልስፍናዊ አብዮት !!!

<<አድዋ ሶስተኛውን ፍልስፍናዊ አብዮት ትወክላለች፡፡ በጥቂቱ ርእሰነገሩን ለማስረዳት ያህል፣ በአለም ላይ ሶስት ፍልስፍናዊ አብዮቶች አሉ፡፡ ስለመልካም ግብ ግህደት (እውንነት) የነበረውን ሁሉ እንዳልነበረ ያደረጉ፣ በእግሩ የቆመውን በሙሉ በጭንቅላቱ የተከሉ፣ የውስጡን ወደውጪ የገለበጡ፣ተደብቆ የነበረውን ሁለንተና ሀቅ ነጻ ያወጡ እሳቤያዊ አብዮቶች ናቸው፡፡

‹‹የመጀመሪያው አብዮት ኮፐርኒከን ሬቮሉሽን፣ ሁለተኛው አብዮት ካንሺየን ሬቮሉሽን እና ሶስተኛው አብዮት ምኒሊከን ሬቮሉሽን በመባል ይታወቃሉ፡፡ “ኮፐርኒከስ በቶለሚ ተነጽሮ የነበረውንና ምድርን ማእከሉ (ጂኦሴንትሪክ ቪው) ያደረገውን ፍልስፍና ዘ ሳይንስ ወስነፈለክ ከውስጥ ወደውጪ በመገልበጥ ጸሀያዊው ስርአት (ሶላር ሲስተም) በምድር ዙሪያ የሚሽከረከር ሳይሆን ምድር ራሷ ናት በጸሀይ ዙሪያ የምትሽከረከረው፤ በማለት አዲስና ፋና ወጊ የሂልዮሴንትሪክ (ጸሀይን ያማከለ) አብዮትን በስነፈለክ አወጀ፡፡

‹‹ካንት በበኩሉ በስነእወቀት የፍልስፍና መስክ አዲስ አብዮትን ነፍስ ዘራበት፡፡ ነገሩ፣ ቀለል ባለ አገላለጽ እንዲህ ነው፡፡ በህሊናችን ውስጥ ያለውን ይዘት ልምድ አይወስነውም፡፡ ይልቅዬ ልምድን እራሱን የሚወስነው ህሊናችን ነው፡፡ እናም የምንዳስሰው አለም በራሱ ሆኖ የሚገኝ ሳይሆን የአእምሮአችን የተለያዩ ፈርጆች በወቀሩት፣ በሰሩት፣ ባበጃጁት፣ ፈር ባስያዙት፣ ልክ ባገቡት እና በጫኑበት ቅርጽና በለገሱት ስርአት መሰረት የሆነ ነው፡፡ እናም እውነታ ለእኛ ህሊናችን አቡክቶ በጋገረው መሰረት የሚታየው፣ የሚለበበው እና የሚቀርበው ሲሆን፣ እውነታ በራሱ ግን ምን እንደሆነ አይታወቅም፤ በማለት አዲስ የእሳቦት ፈር በስነእውቀት ቀደደ፡፡

‹‹ሶስተኛው አብዮት በፖለቲካዊ ፍለስፍና ዘርፍ በምኒሊክ መሪነት አድዋ ላይ እውን የሆነው አብዮት ነው፡፡ እስከአድዋ ድል ድረስ ከኢትዮጵያ በስተቀር አለም በሙሉ በነጮች ገዢነት፣ በነጮች ፍጹም የበላይነት፣ በነጮች ወሮ ድልአድራጊነት፣ በነጮች ሉላዊ መሪነት፣ በነጮች ብቸኛ ተሰሚነት፣ ፍጹማዊ ፈላጭ ቆራጭነት ስር ስትፍገመገም ኖረች፡፡ ከአድዋ ድል በሁዋላ ግን ይህ ታሪክ በጭንቅላቱ ተተከለ፣ ከፍጹምነት አምድ ወደአንጻራዊነት ወታቦ ተሸኳለለ፤ ከአለማቀፋዊ ገዢ እውነታነት ወደወራዳ ፖለቲካዊ ድስትፊያነት ተንደባለለ፡፡

“ይህ የነጮችን የበላይነት በፍትህ የበላይነት፣ የዘርና የቀለም ልዩነትን መራሄነት በሰው ልጆች ሁሉ ልእልና ገዢ አስተምህሮነት፣ የጥቁሮችን መናቅና ውርደት በሰው ልጆች ሁሉ እኩልነት የተካ ሁለንተናዊ ፖለቲካዊ አብዮት ምንሊከን ሬቮሉሽን ወይም ሶስተኛው ፍልስፍናዊ አብዮት ተብሎ ይጠራል፡፡ ”

ሰውን ናሰው፣ ምእራፍ 1 https://t.me/mndarallewbooks

Filed in: Amharic