ከአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት የተሰጠ መግለጫ!
ለአማራ የህልውና ትግል ፈተና የሆኑ አካላት በህዝብ እና ታሪክ ይጠየቃሉ!
(ሚያዚያ 20፣ 2017 ዓ.ም)
የአማራ የኀልውና ትግል ግቡን እንዲመታ አማራዊ ድርጅትን መሠረት ማድረግ አለበት፡፡ ይህን እውነታ መሠረት አድርጎም፣ የህልውና ትግሉ ሂደት የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅትን በራሱ ግዜ ወልዶታል፡፡ ይህም የህልውና ትግሉ የተጎናፀፈው የበሰለ የእድገት ደረጃ ነፀብራቅ ሆኗል።
አፋሕድ፣ ብቸኛው የአማራ ሕዝብ ተቋማዊ የትግል ድርጅት እንደመሆኑ መጠን፣ ትግሉ አቅጣጫውን እንዳይስት በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በአንፃሩ፣ ትግሉን ወደኋላ በመጎተት ላይ የተጠመዱ እና እራሳቸውን”4ቱ የፋኖ አደረጃጀቶች” ብለው የሚጠሩት ኃይሎች፣ በትላንትናው ዕለት፣ ማለትም፣ ሚያዚያ19፣2017 ዓ ም ባወጡት መግለጫ ፣ የድርጅታችንን ስም እንደወትሮው ጭቃ ለመቀባት ባዝነዋል ፡፡
የ4ቱ አደረጃጀቶች ጥቂት አመራሮች ያወጡት መግለጫ እንደተለመደው በሐሰት ትርክትና ፍረጃ የተሞላ ብቻ ሳይሆን፣ ከራሱ ይልቅ የሌሎች ፍላጎት ማስፈሚያ ነው፡፡ በእኛ በኩል፣ እንዲህ ዓይነት የሐሰት ፕሮፖጋንዳዎችን በአብዛኛው በዝምታ የምናልፍ ቢሆንም፣ አንዳንዴ ምላሽ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፣ ምላሻችን የሰከነ፣ ጨዋ እና የተመጠነ መሆኑን የምናረጋግጥ ከመሆኑም ባሻገር፣ “ያለ አማራ ድርጅት የአማራን የህልውና ትግል እንመራለን” የሚሉ ወገኖች ቆም ብለው የሚያስቡበት ልቦና እንዲሰጣቸው በጅምላ በሚጨፈጨፈው የአማራ ህዝብ ስም ፈጣሪን እንደምንለምንላቸው ሁሌም በማሳሰብ ነው፡፡ ልክ እንደ ህዝባችን፣ እኛም በፋኖ ስም የሚራገቡ የጎንዮሹን ፍትጊያዎችን አምርረን ነው የምንጠየፈው።
መላው ህዝብ ከሰሞኑ ዜናዎች ጠንቅቆ እንደሚያውቀው፣ በአፋህድ ላይ ጀግናውን የህዝብ ልጅ አርበኛ ከፍያለው ደሴ እና ሌሎች አያሌ አርበኞችን የበላ ጦርነት ከተከፈተበት ሰንባብቷል። በጦር ኃይል የተመኙትን መጨበጥ የተሳናቸው የ4ቱ አደረጃጀቶች እፍኝ የማይሞሉ መሪዎች፣ በመገናኛ ብዙሃን በኩል በከፈቱት የሥነ ልቦና ጦርነት በርካታ ውሸቶችን ተናግረዋል። ለተሰነዘሩት ውሸቶች በሙሉ ምላሽ መስጠት እራሳችንን ብቻ ሳይሆን የአማራ ህዝብንም ማቅለል ስለሚሆን፣ በህልውናው ትግል ውስጥ ያሉት9 እውነታዎች ከዚህ በታች የተሰነዘሩት ናቸው:-
1ኛ. 4ቱ አደረጃጀቶች ከ8 ወራት በፊት፣ “በሳምንታት እውን እናደርገዋለን” ብለው ቃል የገቡትን የአንድነት ድርጅት እስካሁን መመሥረት ባለመቻላቸው፣ በአጥፍቶ-መጥፋት መንፈስ ብቸኛውን የአማራ ድርጅት የሆነውን አፋህድ ለማፍረስ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለህልውና ትግሉ መራዘምና መወሳሰብ ዋነኛ ምክንያት እንዳደረጋቸውና በህዝብ እና በታሪክ እንደሚጠየቁ፣
2ኛ. አንድ ድርጅት መመስረት ያቃታቸው በስልጣን በመጣላት እንደሆነና፣ ከዚህ በፊት በምርጫ ሲሸነፉ አፋህድን ረግጠው የወጡትም የስልጣን ጥያቄ በማንሳት እንደነበር፣
3ኛ. በመካከላቸው ያለው አለመግባባት ሲያበሳጫቸው እና ተስፋ ሲያስቆርጣቸው፣”አፋህድን አፍርሳችሁ እንደ ጠቅላይ ግዛት አንድ እንሁን፣ የአማራ ድርጅት አያስፈልግም” የሚል ኋላቀር የዘመነ-መሳፍንት ቀመር ይዘው”በቀጠና (በጎጣዊ) ትስስር” ስም ብቅ ማለታቸውንና፣ በእኛ በኩል፣”በጎጣችን ስም አልተጨፈጨፍንም፣ አልተፈናቀልንም፣ አልተጨቆንም” የሚል ምላሽ የሰጠናቸው መሆኑን፣
4ኛ. “በየጠቅላይ ግዛቱ ከአንድ አደረጃጀት በላይ መኖር የለበትም፣ በኃይል እናጠፋቸዋለን” ብለው በተደጋጋሚ በአደባባይ የተናገሩት የ4ቱ አደረጃጀቶች መሪዎች ብቻ መሆኑን ማንኛቸውም ሰው ከማህበራዊ ሚዲያ በቀላሉ ማረጋገጥ እንደሚችል፣ ይህም የአገዛዙ አጄንዳ መሆኑን፣
5ኛ. በተመሳሳይ መንገድ ፣ የአፋህድ መሪዎች ሁሌም ስለ አንድነት እንደሚናገሩ ከዚያው ከማህበራዊ ሚዲያ ሁሉም ሰው ማረጋገጥ እንደሚችል፣
6ኛ. የ4ቱ አደረጃጀት መሪዎች በአደባባይ በተናገሩት መሠረት፣ በየጠቅላይ ግዛቱ አንድ አደረጃጀት ብቻ እንዲኖር ለማድረግ የሚያስችል ወታደራዊ አቅም እንፈጥራለን ብለው፣ ወልቃይት እና ራያን በኃይል አስመልሳለሁ ከሚለው ፅንፈኛው እና ጦረኛው የወያኔ አንጃ የፋይናንስ እና የጦር መሣሪያ ድጋፍ በመቀበል በ4ቱም ጠቅላይ ግዛቶች በአፋህድ ላይ ወታደራዊ ጥቃት መሰንዘራቸውን፣ በዚህም በጥቅሉ በአማራ፣ በተለይ ደግሞ ላለፉት35 ዓመትት በስቃይ በኖሩት የወልቃይት እና የራያ ህዝብ ላይ ክህደት መፈፀማቸውን፣
7ኛ. አፋህድ ከየትኛውም ወገን የሚፈፀምበትን ወታደራዊ ጥቃት የመከላከል ተፈጥሯዊ መብት እንዳለው እና አማራጭም እንደሌለው፣
8ኛ. በ4ቱ አደረጃጀቶች መግለጫ ላይ በተጠቀሱት አውደ ውጊያዎች ሁሉ የአፋህድ ኃይሎች አስቀድመው ተኩስ ያልከፈቱ መሆናቸውን እና እራሳቸውን ለመከላከል ብቻ የተንቀሳቀሱ መሆናቸውን፣
9ኛ. አፋህድ ጦርነት ተከፍቶበት ብዙ ጉዳት የደረሰበት ቢሆንም፣ በ4ቱ አደረጃጀቶች በሚዲያ የሚደረጉ ስም ማጠልሸቶ እና የሚራገቡ ውሸቶች ብልጽግናን ከመርዳታቸው ባሻገር ህዝባችንን እያወዛገበ፣ የአማራን ክቡር እና ጨዋነትን እያኮሰሰ በመሆኑ፣ አደረጃጀቶቹ ወደቀልባቸው ተመልሰው ልዩነታችንን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆናችንን በህዝብ እንዲታወቅልን እንፈልጋለን።
በመጨረሻም፣ በጅምላ የተጨፈጨፈውን አማራ አክብረን ልናስከብረው ይገባል። የህልውና ትግሉ የወለዳቸውን መሪዎቹን አዋርደን ልናስከብረው አንችልም። መሪዎቹ በሀሰት ተሰድበው ለሰዳቢ፣ በሀሰት ተዋርደው ለአዋራጅ እየተሰጡ ናቸው። ይህ እንዲሆን4ቱ አደረጃጀቶች የተጫወቱት የፈር ቀዳጅነት ሚና በእጅጉ የሚያሳዝን ነው።
አማራ ኃይማኖተኛ፣ ጀግና፣ሀገር ወዳድ፣ ታሪክ አክባሪ፣ ይሉኝታ ያለው መሆኑን ወዳጁም ጠላቱም ሲመሰክርለት ኖረዋል። በዚህ ልክ ያልቆመ የፋኖ አደረጃጀት ፈፅሞ ህዝባዊ ሊሆን አይችልም። ጨዋነት ለአማራ ፋኖ አማራጬ አይደለም። ተፈጥሮው ነው። ሁሉም በዚህ ልክ ለመገኘት በያለበት ይትጋ። አሁንም ግዜ አለ።
ድል ለአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት!
ድል ለአማራ ህዝብ!
ድል ለኢትዮጰያ ህዝብ!
ሚያዝያ 20/2017 ዓ.ም.