>

የሕዝብ ኩባንያዎች ነባርና የጊዜው ፈተና፤ በጨረፍታ

የሕዝብ ኩባንያዎች ነባርና የጊዜው ፈተና፤ በጨረፍታ

ከይኄይስ እውነቱ

የሕዝብ ኩባንያዎች (Public Companies) የሚባሉት በኢትዮጵያ ንግድ ሕግ መሠረት ቊጥራቸው ቢያንስ አምስቱ በሆኑ አባላት (የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት በተሰጣቸው አካላት) ለንግድ ዓላማ ብቻ በመመሥረቻ ጽሑፍየሚቋቋሙ፣ አክሲዮናቸው ለሕዝብ ክፍት የሆኑ የአክሲዮን ማኅበራት ነው፡፡ ባንጻሩም የአክሲዮን ማኅበር ለሕዝብ ክፍት ሳይሆንም በአባላቱ ተወስኖ ሊቋቋም ይችላል፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ስለ ሕዝብ ኩባንያዎች ጠለቅ ያለ ሕጋዊና ሕገ ነክ ያልሆኑ ትንተናዎችና ማብራሪያ ለመስጠት አይደለም፡፡ ከባሕሩ በማንካ እንደሚባለው በተግባር የሚታዩ ጥቂት ተሐዝቦቶችን (observation) ለማካፈል ነው፡፡ መነሻም የሆነኝ አንድ ወዳጄ ባለ አክሲዮን የሆነበትና እኔም በሕጋዊ ወኪልነት የምገኝበት የአክሲዮን ማኅበር አሠራር ነው፡፡በፋይናንሱ ዘርፍ በአገር አቀፍ ደረጃ ተቋቁመው የሚንቀሳቀሱት የአክሲዮን ማኅበራት አደረጃጀትም ሆነ አሠራር ተመሳሳይነት ስላለው በዚህ ጽሑፍ የሚቀርበው መረጃና አስተያየት እንደ ሁናቴው ከጥቂት ማስተካከያዎችም ጋር ለአብዛኛዎች ተፈጻሚነት ኖረው ይችላል፡፡ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ ያደረግሁት አክሲዮን ማኅበር በንግድ መዝገብ ከገባ አምስት ዓመታትን ያስቆጠረው ጎሕ የቤቶች ባንክ የሚባለው አክሲዮን ማኅበር ነው፡፡

ለገለጣ እንዲመች ተግዳሮቶቹን ወይም ፈተናዎቹን ውስጣዊና ውጫዊ ብሎ መክፈል ይቻላል፡፡

1/ ውስጣዊ፤ ከአደራጆች ጀምሮ ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ የማኅበሩ አመራር፣ የኩባንያው ተቀጣሪ ሠራተኞች እና በተራው ባለአክሲዮኖች የሚታዩ ድርጊቶችና ጠባዮችን ይመለከታል

1.1 በማኅበሩ አደራጆች ከመመሥረቻ ጉባኤው ጀምሮ የሚታዩ ተገቢ ያልሆኑ ተጽእኖዎች፤

የሚግባቡ ግለሰቦች ዕውቀታቸውን፣ ልምዳቸውን፣ ጊዜአቸውን፣ ማኅበራዊ ትሥሥራቸውን ተጠቅመውና ሕዝብን አስተባብረው ከምንም ተነሥተው አንድ የንግድ ማኅበር እንዲመሠረት ማድረግ ትጋትን የሚጠይቅ÷ ሊመሰገን÷በይፋ ዕውቅናና ዋጋ ሊሰጠው የሚገባ ታላቅ ተግባር ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እነዚሁ አደራጆች ከማኅበሩ መመሥረቻ ጉባኤ ጀምሮ የማኅበሩ ማቋቋሚያ ሰነድ በጥልቀት እንዲፈተሽ ጊዜ አለመስጠት፣ በጽሑፍ የሚሰጥ አስተያየትንም ከግምት አለማስገባትና ለመቀበል ዝግጁነትና ፍላጎት አለመኖር፣ በጉባኤውም በአካል የሚነሡ ማሻሻያ አሳቦችን እንደ ፖለቲካ ድርጅታዊ አሠራር በየማዕዝኑ የራሳቸውን ሰዎች (‹ካድሬዎች›) አስቀምጠው ባወጣው ገንዘብ ልክ የማኅበሩ ባለቤት የሆነውን ባለአክሲዮን አፍ አፉን ማለትና ውሳኔዎች ተድበስብሰው እንዲያልፉ ማድረግ በፍጹም ተቀባይነት የሌለው አሠራር ነው፡፡ መመሥረቻ ጽሑፍና መተዳደሪያ ደንብ(በዐዲሱ የንግድ ሕግ መሠረት የማኅበሩ ‹መተዳደሪያ ደንብ›ንም ይይዛል) በዝርዝር ታይቶ አሳማኝ ማሻሻያ ካለ ተካትቶ መጽደቅ ሲገባው ጊዜ የለም በሚልና ‹ድርጅታዊ› በሚመስል አሠራር ተውተፍትፎ እንዲያልፍ ማድረግ ማኅበሩን ከጅምሩ በድቡሽት ላይ እንዲመሠረት ከማድረጉ በተጨማሪ የወደፊቱንም አምባገነናዊ አሠራር ጠቋሚ ነው፡፡ ይሄ እኔ በታዘብሁትም ሆነ ባብዛኛዎቹ አክሲዮን ማኅበራት ከጅምሩየሚንፀባረቅ አሠራር ነው፡፡

1.2 ቃት ያላቸው የአክሲዮን ማኅበሩን አባላት ፕሮፋይል በመረጃ ቋት (በዳታቤዝ) ይዞ ለጠቅላላው ጉባኤ ተደራሽ የማድረግ ዘመናዊ አሠራር ተግባራዊ ማድረግ ሲቻል፤ የአክሲዮን ማኅበሩ አባላት የሆኑ አደራጆች በቀጣይም የዲሬክተሮች ቦርድ አባላት ባለአክሲዮኖች አይተዋወቁም በሚል ተገቢ ያልሆነ ምክንያት የዲሬክተሮች ቦርድ አባላትእና የተለያዩ ኮሚቴዎች ምርጫ ራሳቸው ወይም ከነሱ ትውውቅ ውጭ እንዳይሆን የሚያረጋግጡበት ‹ድርጅታዊ› አሠራር የተለመደ ሆኗል፡፡ የውጭ ኦዲተሮችም አሰያየም ከዚህ አሠራር የጸዳ አይደለም፡፡ ሥራውን በትውውቅ ካገኙት ከማናቸውም ተጽእኖ ‹ነፃ› ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በኩባንያዎቹ የሚደረጉ የሠራተኞች ቅጥር (የቅጥር ማስታወቂያ እንደ ፎርማሊቲ የሚወጣ ቢሆንም እንኳን ከኃላፊ እስከ ተራው) ከተወሰኑ የቦርድና የሥራ አመራር አባላት እና ተጽእኖ ፈጣሪ ባለአክሲዮኖች ጋር የተያያዘና መጠቃቀሚያ ነው፡፡ ድርጅታዊ የካድሬ አሠራርም ተግባራዊ እየተደረገ ያለው በዚህ መልኩ በቅጥር በገቡ ‹መሸጦዎች› ነው፡፡
1.3 እንደሚታወቀው በንግድ ሕጉና በኩባንያ መመሥረቻ ጽሑፍ መሠረት በጠቅላላው ጉባኤ ብቻ የሚወሰኑ ጉዳዮች ተለይተው ተመልክተዋል፡፡ የዲሬክተሮች ቦርድ አባላት ጠቅላላ ጉባኤውን የሚፈልጉት በዋናነት በጉባኤው የግድ የሚወሰኑ ጉዳዮች በመኖራቸው እንጂ አሳትፎ የተሻለ ግብዓት ለማግኘት አለመሆኑን በተግባር ይታያል፡፡ እንዲያውም ጊዜ የለንም በሚልና አብዛኛው ባለአክሲዮን ዕውቀቱም የለውም በሚል ምክንያት አሳቦችን ማፈን የተለመደ አሠራር ሆኗል፡፡ በዓመታዊ የጠቅላላ ጉባኤ ዋናው አጀንዳ የዲሬክተሮችና የውጭ ኦዲተሮች አበልና ጭማሪ ነው፡፡ ቊርጡን ለመናገር ስብሰባዎች ድራማ እስኪመስሉ ድረስ ተቀነባብረው አልቀው መድረክ ላይ የሚተወኑ ይመስላሉ፡፡
1.4 በዲሬክተሮች ቦርድ የሚቀርቡ ዓመታዊ ሪፖርቶች በመጨረሻ ረቂቅነት ደረጃ እንጂ ያለቀላቸው የመጨረሻ ሆነው አይቀርቡም፡፡ ለስብሰባ የሚያስፈልጉ ሰነዶች ለባለአክሲዮኖች በጊዜው አይደርሱም ወይም ጥያቄ ሲቀርብ ለመስጠትም ፍላጎቱ የለም፡፡ በስብሰባ ጥሪ መግለጫ ላይ በጥልቀት መፈተሽ ያለበት ሰነድ በኩባንያው ድረ ገጽ ላይ እንደሚገኝ ይጠቁምና ድረ ገጹ ላይ ስብሰባው ጥቂት ቀናት ሲቀረው ወይም ካለፈ በኋላ ወይም እስከነአካቴው ላይለጠፍ ይችላል፡፡ በስብሰባው ዕለት ሪፖርቱን መስጠት ትርጕሙ ምን ይሆን? አስቀድመው ያለቀላቸው አጀንዳዎችንና ውሳኔዎችን አጨብጭባችሁ ካጸደቃችሁ በኋላ ሰነዱ ለታሪክ ይዛችሁ ሒዱ የሚሉ ይመስላል፡፡
1.5 ከባለአክሲዮኖች ስለ ዓመታዊ ሪፖርቶቹ በተለይም ከውጭ ኦዲተሮች ስለሚቀርቡ የፋይንናስ ሪፖርቶች በአካልም ሆነ በጽሑፍ የሚቀርቡ ጥያቄዎች ግልጽ መልስ አያገኙም፡፡
1.6 አክሲዮን ማኅበሩ በሁለት እግሩ ሳይቆምና ሳይጸና በ‹ኢንቨስትመንት› ስም ለዛውም በንግድ ሕጉ ግንኙነቱ ጥንቃቄ እንዲደረግበት ከተደነገገውና ከማኅበሩ ጋር ‹‹ቅርበት ያላቸው ሰዎች››/ሪሌትድ ፓርቲስ (እንደ ቦርድ አባላት፣ ሥራ አስኪያጅ/ሥራ አስፈጻሚ፣ ኦዲተር፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ አባላት፣ የማኅበሩ ጸሐፊዎች) ሚባሉት ጋር በሚሊየን ሚቆጠር ብርስምምነት ማድረግ ከጥርጣሬ በላይ የሚያጠያይቅ ነው፡፡

ኩባንያው በዚህ ድንጋጌ ቅርበት ያላቸው ከተባሉ ሰዎች ጋርየሚያደርጋቸው ስምምነቶች የጥቅም ግጭት ሊያስከትሉ እናኩባንያውንም አደጋ ላይ ሊጥሉ ስለሚችሉ በከፍተኛ ጥንቃቄየሚታዩ ናቸው፡፡ በተቻለ መጠን ይህ ዓይነት ስምምነትለኩባንያው የግድ ያስፈልጋል ካልተባለ  ቢቀር ይመረጣል፡፡በዚህ ረገድ በማዕከላዊ ባንኩም መመሪያ ወጥቶ ተግባራዊሆኗል፡፡ ኩባንያዎች ቅርበት ያላቸው ከሚባሉ ሰዎች ጋርየሚያደርጓቸው ስምምነቶች (ትራንዛክሽንስ) በገንዘብ መጠንየተገደቡ፣ ለኦዲተር ማሳወቅ የሚጠይቁ፣ የቦርድ ውሳኔንየሚፈልጉ፣ አንዳንዶቹም የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤካላጸደቋቸው ተግባራዊ የማይሆኑ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ጥቂትበማይባሉ ኩባንያዎች ከሕግ ውጭ ባለ አፈጻጻም ኩባንያዎችለአደጋ ሲጋለጡ ይስተዋላል፡፡

በዚህ ረገድ ጎቤባ ... 2022 በቀረበው የማኅበሩባለአክሲዮኖች በመጀመሪያው ዓመት የሥራ ዘመኑ የባንኩየቦርድ ዲሬክተሮች አባል ከሆነው ኢትዮላይፍ ኤንድ ጄኔራልኢንሹራንስ .. ጋር (በተለይም የብሔራዊ ባንክ መመሪያ ልዩትኩረት የሚሰጥበት ሆኖ እያለ) ስምምነት ፈጽሟል፡፡“Investment Securities” በሚል በውጭ ኦዲተሮች (የሂሳብመግለጫ ማስታወሻ) ሪፖርት ላይ መመልከት ይቻላል፡፡

1.7 ተጽእኖ ፈጣሪ በሚባሉትም ሆነ በተራው ባለአክሲዮን የተፈረሙ አክሲዮኖች በሕጉ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ አይከፈሉም፡፡ በዲሬክተሮች ቦርድ ማሳሰቢያ በጽሑፍ ከመላክ ባለፈ የሚወሰዱ ሕጋዊ ርምጃዎች የሉም፡፡ በፋይናንስ ተቋማት አክሲዮን ማኅበራት ጠቅላላ ጉባኤዎች የብሔራዊ ባንክ ተወካዮች እንደሚገኙ ይታወቃል/ይጠበቃል፡፡ በዚህ ረገድ ብሔራዊ ባንክ የንግድ ባንኮችን አሠራር ለመቆጣጠር የተሰጠው ሥልጣን ተጠቅሞ የወሰደው ርምጃ የለም፡፡የተፈረመው አክሲዮን ተጠናቅቆ ሳይከፈል ከዓመት ዓመት እየተንከባለለ ይገኛል፤ በሕጉ መሠረት ርምጃ ተወስዶ ኩባንያው የወሰዳቸውን አክሲዮኖች (forfeited shares) ለሽያጭ ቢቅረቡምእነዚህም አለመገዛታቸው ባለ አክሲዮኖችም ሆኑ ሕዝቡ በኩባንያው አፈጻጸም ላይ ስላለው መተማመን ብዙ ይነግረናል፡፡በተጠቀሰው የአክሲዮን ማኅበር መተዳደሪያ ደንብ የተፈረሙ ነገር ግን ያልተከፈሉ አክሲዮኖች ሙሉ በሙሉ ተከፍለው መጠናቀቅ ያለባቸው በ18 ወራት ሲሆን፣ በያዝነው 2018 ዓ.ም. መገባደጃ ላይ ማኅበሩ በንግድ መዝገብ ከገባ 5 ዓመት ይሞላዋል፡፡ በተራ የንግግር ቋንቋ ማኅበሩ በ‹‹ጨበጣ›› የሚንቀሳቀሱ (ጨከን ብለን ከተናገርን ‹‹የሚቆምሩ›› ነገር ግን ተጽእኖ ፈጣሪ የሚል ስያሜ የተሰጣቸውን ባለአክሲዮኖች ይዞ ቀጥሏል ማለት ነው፡፡
1.8 ሌላው የአክሲዮን ማኅበሩ (ባንኩ) የግል የቤቶች /ሞርጌጅ/ ባንክ ተብሎ ቢቋቋምም፣ የተወሰነው ባለ አክሲዮንም በዚህ ረገድ ልዩ ጥቅም አገኛለሁ ብሎ ባንኩን የተቀላቀለ ቢሆንም፣ ከባንኩ ባለአክሲዮንነት ውጭ ላለው ሕዝብም እንደ ቀድሞው የሞርጌጅ ባንክ በዝቅተኛ ወለድ በርካታ ዜጎችን የቤት ባለቤት ያደርጋል ተብሎ ተስፋ የሚጣልበት አይደለም፡፡ ባንኩን ከስሙ በስተቀር የቤቶች የሚያሰኘው የተጨበጠ ምክንያት ፈልጎ ለማግኘት ይቸግራል፡፡ በዋናነት ለባለአክሲዮኖችም ሆነ ለጠቅላላው ሕዝብ የሚሰጠው ብድር ወለድም ሆነ የአከፋፈሉ ሥርዓት ከሌሎች ባንኮች የተለየ አይደለምና፡፡ በመሆኑም አመዛኙ ባለአክሲዮን የማኅበሩ አባል የሆነው እንደማናቸውም የግል ንግድ ባንኮች የትርፍ ድርሻ ለመካፈል ሲሆን፣ በዚህም ረገድ እጅግ ቅር መሰኘት ብቻ ሳይሆን ተስፋ እየቆረጠ ይገኛል፡፡ ለአብነት እ.አ.አ. በ2022/23 ከግብር በፊት ብር 84 ሚሊዮን እንዳተረፈ ቢነገርም በኦዲተሮች የፋይናንስ ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው የዲሬክተሮች ቦርድ ከተጣራው ትርፉ ሕጋዊ ተቀናሾች ከተደረጉ በኋላ ለባለአክሲዮኖች እንዲከፋፈሉ አልወሰነም፡፡ ይልቁንም ሕጋዊ መሠረቱ ምን እንደሆነ በማይታወቅ ርእስ ትርጕም የሌለው የይስሙላ – እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው – የሚመስል (nominal amount) ለጥቂት ባለአክሲዮኖች ፈጽሟል፡፡
1.9 ባንኩ ይህ ከፍ ብሎ ከጠቀሰው ትርፍ በስተቀር ስኬት ብሎ የሚያነሣው ቅርንጫፎች መክፈቱን ነው፡ የተፈረመ ካፒታል ማስከፈል ሳይችል፣ ዋናውን ጽ/ቤት ጨምሮ በየቅርንጫፎቹ ለሚቀጥረው የሰው ኃይል ሥራ ማስኬጃ (overhead cost) የሚያውጣው ወጪ የባንኩ ከፍተኛው ወጪ ሆኖ በቀጠለበት ሁናቴ፣ ገና በሁለት እግሩ ሳይቆም በተራ ቊ. 1.6 የተጠቀሰውን ‹‹ሴኩሪቲ ኢንቨስትመንት›› ማድረጉ ወዘተ. በሒደት የኩባንያውን ካፒታል ቅ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ በብሔራዊ ባንክ መመሪያ እንዲያሟላ የሚጠበቅበትን የተከፈለ ካፒታል ብር 5 ቢሊየን ለማሟላት የሚያስችል ዐቅም ይኖረዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡
1.10 ሌላው አንድ ባለአክሲዮን አባል በሆነበት የአክሲዮን ማኅበር (ባንክ) ሂሳብ መክፈት መብት መሆኑ ቀርቶ በግዴታ እንዲከፍት ተግባራዊ የሆነው አሠራር በእጅጉ የሚገርም ነው፡፡ የሚሰጠው ምክንያት በካፒታል ገበያ ባልሥልጣን ታዘናል የሚል ነው፡፡ ማኅበሩ ትርፍ አግኝቶ እንኳን ባለአክሲዮኑ የሚደርሰውን የትርፍ ድርሻ በፈለገው የባንክ ሂሳብ እንዲላክለት መጠየቅ እንደማይችል በተግባር ታይቷል፡፡ ይህ አካሔድ ባለአክሲዮኑ በትርፍ ድርሻው ማዘዝ እንደማይችል ጠቋሚ ይመስላል፡፡ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን በተባለው መ/ቤት ትእዛዝ ባለአክሲዮኖች የ‹ኢንቨስትመንት ሂሳብ› መክፈት አለባችሁ የሚለው ሕገ ወጥ ትእዛዝ  ከፍ ብዬ ያነሳሁትን ሥጋት የሚያጠናክር ነው፡፡ በንግድ ሕጉ የአክሲዮን ሰርቲፊኬት እንደ ሁኔታው በተለመደው መልኩ በሰነድ እና ግዑዝ አልባ (በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ) ሊሆን ይችላል፡፡ ምንም እንኳን የአክሲዮን ማኅበሩ በባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ የአክሲዮን ሰርተፊኬቱን ከሰነድነት ሙሉ በሙሉ ወደ ኤሌክትሮኒክስ አሠራር መቀየር እንደሚቻል የንግድ ሕጉ ቢያስቀምጥም፣ በሰነድ (ወረቀት) መልክ የሚሰጠውን የአክሲዮን ማስረጃ ጎን ለጎን መጠቀም የሚከለክል ወይም የሚያስቀር አይደለም፡፡ በመሆኑም በወረቀት የሚሰጠውን የአክሲዮን ሰርቲፊኬት ለባለአክሲዮኖ መከልከል ብሎም አስቀድሞ ለወሰዱት አይሠራም ዋጋ የለውም የሚለው አባባል ሕጋዊ መሠረት ወይም ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ የሚያዘው የአክሲዮን ሰርቲፊኬት የ‹ኢንቨስትመንት ሂሳብ› በተባለውና ከኩባንያው ውጪ የ‹ኢንቨስትመንት ባንኮች› በሚባሉት ተቋማት የሚያዝ ከሆነ ግለሰብ ወይም ተቋማዊው ባለአክሲዮን ለባለቤትነቱ ዋስትናው ምንድን ነው?

2/ ውጫዊ፤ የአገዛዙ ጣልቃ ገብነት፣ በሕግ ሽፋን በ‹መንግሥት ተቋማት› የሚደረጉ ሕገ ወጥ ወይም የማያላው አሠራሮች

2.1 አጠቃላይ አመቺ ያልሆነ ከባቢ

የግለሰቦችና ድርጅቶች ሕጋዊ የባንክ ሂሳቦች እንዲሁም የፋይናንስ ተቋማት አሠራር ዋስትና የሌለበት አገር ውስጥ ነው ያለነው፡፡ አገዛዙና በኅቡዕ ያደራጃቸው ‹የታችኛው ዓለም ወንጀለኞች› የድርጅቶችንና የግለሰቦችን የባንክ ሂሳቦች የግል ኪሣቸው አድርገውታል፡፡ የግለሰቦችና የድርጅቶች የባንክ ሂሳብ ያለ ሕግና ዳኝነት አካል ውሳኔ መታገድ የተለመደ አሠራር እየሆነ መጥቷል፡፡ የግለሰቦች ሂሳቦች መረጃዎች በውስጥ ዐዋቂዎች ለዘራፊዎች እየተሰጠ ሰዎች ታግተው ዦሮን ጭው የሚያደርግ የማስለቀቂያ ገንዘብ (Ransom) የሚጠየቅበት ውንብድና ከአገዛዙ ዕውቅና ውጭ የሚፈጸሙ አይደሉም፡፡ ለሕዝቡ የሽመልስም ሆነ የጃል መሮ ‹ኦነጎች› ልዩነት የላቸውም፡፡ ሁለቱም አገዛዝ-መር ሽብር ፈጣሪዎች ናቸውና፡፡ ፌዝ አይቀርምና አገዛዙ ‹የፋይናንስ ደኅንነት› የሚል ተቋም አቋቁሞ የአገር ሀብት በከንቱ ይባክናል፡፡

ባንኮች በጠራራ ፀሐይ በሚዘረፉበትየሕዝብ ባንኮች ተዘርፈው ሌሎች ልዩ ጥበቃና ጥቅም የሚሰጣቸው ‹‹የወንጀል ውጤቶች የሆኑ ባንኮች›› የሚቋቋሙበት አገር ውስጥ ነው ያለነው፡፡ አንጋፋው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክዘራፊዎቹ (ወያኔና ኦሕዴድ/ኦነጎች – ግዙፍ በሆነ በማይመለስ ብድር ጭምር) ሙልጩን አስቀርተውት እንደገና ‹እየዳኸ› ያለው በብሔራዊ ባንክ በተመደበለት ብድር መሆኑ የዐደባባይ ምስጢር ነው፡፡ የሕዝብ ሀብት በመሆኑ ምክንያት ለረዥም ዓመታት ከመንግሥት የነበረውን ልዩ ድጋፍ ከባንኩ ተነሥቶ ዛሬ ኦሮሚያና ሲንቄ ለሚባሉት በዝርፊያ ለተቋቋሙ የጐሣ ‹ባንኮች› ተላልፏል፡፡ ዛሬ ወያኔ በፈጠረው ‹ኦሮሚያ› (ዐዲስ አበባን በቀለበት ባሰራት ‹ሸገር› በተባለው የውንብድና ከተማ)በሚባለው ግዛት ዜጎች ማናቸውንም ክፍያ በነዚህ የዝርፊያ ባንኮች ብቻ እንዲፈጽሙ በግዳጅ ተወስኖ ተግባራዊ ከሆነ ውሎ አድሮአል፡፡ ጐሣን መሠረት አድርገው የተቋቋሙ ባንኮች በሙሉ ባንድም ሆነ በሌላ መልኩ የጐሠኛነት ሥርዓትና ‹ፖለቲካ› ደጋፊዎችና የአገር አንድነት ጠንቆች መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡

ሕጋዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሌለበት፣ ከየትኛውም ዘርፍ ምርትና አገልግሎት ኖሮ አገራዊ ገቢ የለም ብለን በድፍረት የምንናገርበት ሁናቴ ውስጥ በመሆናችን፣ የአገዛዙ ዓይኖች የግለሰብ ድርጅቶችና ዜጎች ሀብትና ንብረት ላይ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ከቀበሌ እስከ ክ/ከተማ፤ ከማዘጋጃ እስከ ገቢዎች፣ ባጠቃላይ በተለያዩ ለሕዝብ መገልገያ ተብለው በተቋቋሙ ተቋማት በሚጠየቀው ማቆሚያ ሌለው የገንዘብ አምጡ ሕገ ወጥ ትእዛዝ/ዝርፊያ በማያለውሰው አሠራር ምክንያት በአ.አ. ብልጭ ድርግም ከሚለው ንግድና አገልግሎት እየወጡይገኛሉ፡፡ፋይናንሱም ዘርፍ ‹የአክሲዮን ገበያ ባልሥልጣን› የሚባል ለዚሁ መሣሪያነት የሚያገለግል ተቋም መሥርቶ የአክሲዮን ማኅበራትን ሀብት ለመዝረፍ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ ድርጅት ጋር በተያያዘ ውክልና ተሰጥቷቸዋል የሚባሉት ‹የኢንቨስትመንት ባንክ› (አንዱ ወጋገን ሲሆን፤ በወንጀል ውጤት በተገኘ ሀብት የተቋቋመ መሆኑን ያስታውሷል) በሕግ ሽፋን የዝርፊያው ማስፈጸሚያ አካል ነው፡፡

2.2 በጥቅሉ ‹‹ገበታ›› የሚባለው ‹‹ከበላይ አካል›› የሚመጣ የመዋጮ ትእዛዝ፤

የወያኔና ኦሕዴድ/ኦነግ አገዛዞች ዓይነተኛ መለያ ጠባያቸው መካከል ሰውን በተለይም ሕዝብ የሚወዳቸውንና ላገር በተለየ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ተብለው የሚታሰቡን ሰዎች፣ በአግባቡ በጥናትና ምርምር ታግዘው በተግባር ቢውሉ የሕዝብንም ሕይወት ሆነ አገርን በበጎ ሊለውጡ የሚችሉ ታላላቅ ሐሳቦችን እና በሚያስፈልጉበት ጊዜ ቢቋቋሙ ለሕዝና ላገር ሊጠቅሙ የሚችሉ ተቋማትን ማርመጥመጥ÷ ማምክን ወይም ማኮላሸት ነው፡፡ ይህንን ሲፈጽሙ የቆዩትና አሁንም እየፈጸሙ ያሉት ከጥልቅ ጥላቻና ምቀኝነት÷ ከድንቊርና(ያርመጠመጡአቸውን ሐሳቦችና ተቋማት) ሥልጣንን ተገን አድርገው እኛ ሠራንው በሚል በየትኛውም መመዘኛ የማይገባቸውን ዕውቅና ከመሻት (take undue credit) የመነጨ ነው፡፡ ታሪክ ግን እነዚህ የጥፋት ኃይሎች የሠሩአቸውን ነውሮችና ወንጀሎች ሁሉ መዝግቦታል፡፡የሚያስታውሳቸውም ተወዳዳሪ በማይገኝለት ውንብድናቸው ነው፡፡

እንደማንኛውም ነጋዴ የአክሲዮን ማኅበራት (ምክንያቱ የተለያየ ሊሆን ይችላል) ‹‹ገበታ›› በሚባለው ጥቅል የዝርፊያ ርእስ (ኩባንያዎቹ አላተረፉም እየተባለ) የባለአክሲዮኑን ገንዘብ አሳልፈው በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከፍ ብዬ በተራ ቊጥር 1 ያነሳኋቸውን ውስጣዊ ምክንያቶች የተገነዘበ አንባቢ አክሲዮን ማኅበራት ከአገዛዙ የሚመጣውን እንዲህ ዓይነቱን ጫና የመቋቋም ጫንቃ ይኖራቸዋል ተብሎ አያስብም፡፡ አይጠበቅምም፡፡ አንዳንድ አክሲዮን ማኅበራት እንዲህ ዓይነቱን በግዳጅ የሚመጡ የማያበሩ ጥያቄዎችን ‹‹የኩባንያዎች ማኅበራዊ ኃላፊነት/corporate social responsibility/›› በሚል ርእስ ወይም ሌላ የወጪ ርእስ ፈልገው የሕዝብ ኩባንያዎችን ዕርቃናቸውን እያስቀሩ ይገኛሉ፡፡ መጠነኛ ትርፍ ሲገኝም ለባለአክሲዮኖች የትርፍ ድርሻ ክፍፍል እንዳይደረግ ብሔራዊ ባንክ (እነዚህን ከሕግና ሥርዓት የወጡ የፋይናንስ ተቋማት መቆጣጠር ሲገባው) ራሱ የማያባሩ መመሪያዎችን እያወጣ(አንዳንዶቹም ‹እናት› ሕጎችን የሚፃረሩ) የአክሲዮን ማኅበራት ከተጣራ የትርፍ ገቢአቸው 25 በመቶ ብቻ በሕጋዊ መጠባበቂያ ገንዘብነት እንዲያስቀምጡ (ተቀማጩ ከኩባንያው የተከፈለ ካፒታል እኩል ሲሆን፣ 10 ከመቶ ብቻ እንዲሆን ተቀምጧል) ሚያዘው ሕግ በተጨማሪ ‹ተጨማሪ መጠባበቂያ› በሚል የኩባንያ ባለቤቶች/ባለአክሲዮኖች በተግባር የትርፍ ድርሻ እንዳያገኙ እያደረገ ይገኛል፡፡ በዚህም ለወደፊቱ ማንም ግለሰብ ሆነ ድርጅት የአክሲዮን ማኅበራት ውስጥ መዋዕለ ነዋይ እንዳያፈስ እና በአክሲዮን ማኅበራቱም አመኔታ እንዳይኖረው እያደረገ ይገኛል፡፡

2.3 የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የሚባለው ተቋም ከጅምሩ የሚሳየው ሕገ ወጥ ጣልቃ ገብነት፤

ምዕራባውያኑ እና አንዳንድ ያደጉ አገሮች ያደረጉት አይቅርብን በሚል ወይም (ርጥባንና ብድር ለመቃረም) በምዕራባውያኑ አሳዳሪዎቻቸው ታዘው ቀደም ሲል ወያኔ÷ አሁን ደግሞ ውላጁ ኦሕዴድ አገራችንን የማትወጣበት ምስቅልቅል ውስጥ እየከተቷት ነው፡፡ ያለ ልማት (ኢኮኖሚው እግር ተወርች ታስሮ የወንጀል ኢኮኖሚ በነገሠበት አገር፤ በተለይም በትምህርት ታገዘ የሰው ኃይል ልማት በሌለበት፤ ውል በማይከበርበት፣ ሕግና ዳኝነት በሌለበት አገር) ልጥፍ ዘመናዊነት ከንቱ ነው፡፡ከግንጥል ጌጥነትም ባለፈ አደጋ ነው፡፡ ሕዝብ በጠኔ በሚያልቅበት አገር ርጉም ዐቢይ ከዐረብና ቻይና ባስመጣው ብልጭልጭ ተደሰቱ/ተዝናኑ ብሎ እንደ ማፌዝ ይሆናል፡፡ ወያኔ የተከለው ‹‹የምርት ገበያ ባለሥልጣን›› እና ኦሕዴድ/ኦነግ አሁን እየተከለ ያለው ‹‹የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን›› ላገርና ለሕዝብ ልማት ታስበው የተቋቋሙ ተቋማት ሳይሆኑ ባገር ጥፋት የተጠመዱትና በሕዝብ ጥላቻ የሰከሩት የሁለቱ ደናቊርትና ወንበዴ አገዛዞች አገራዊ ምርትን እና የፋይናንስ እንቅስቃሴበመቆጣጠር ለአገዛዙና ዐዲስ ለሚፈጥሯቸው ጥቂት ሀብታሞች ሕገ ወጥ ሀብት ማካበቻ በዚህም ሥልጣንን ተቆናጥጦ አገዛዝን ለማስቀጠል የሚደረገ ዘርፈ ብዙ ሙከራዎች መካከል ዓይነተኛ መገለጫዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያደናቊርት በሆኑ የቤት÷ የተሽከርካሪ እና የልዩ ልዩ ዕቃዎች አጭበርባሪ ‹ደላላዎች› ለዘመናት መጫወቻ ሆና መኖሯና ይኸውም መቀጠሉ ሳያንስ አሁን ደግሞ በዘመናዊነት ሽፋን ዐዲስ ‹የፋይናንስ ደላላዎች› መጫዎቻ ለመሆን እየተዘጋጀች ነው፡፡ ጐሠኞቹ አገዛዞች ካንድ ኩሬ (የምንጭ ውኃ አላልኹም) የተቀዱ በመሆናቸው ራሳቸው ሸተው ረግተው አገርን ጭምር ያሸታሉ፡፡ እነዚህ ካንድ ኩሬ የተቀዱ አገዛዞች ከፍ ብዬ እንደጠቀስሁት ለሕዝብና ላገር የሚጠቅሙ ታላላቅ ሐሳቦችን በመስረቅ (ባግባቡ በጥናትና በምርምር÷ ጊዜንና ዐውድን በመዋጀት፣ ባገር ፍቅርና ባርበኝነት በጋለ መንፈስ እንዳይፈጸሙ) አኰስሰው÷ አርመጥምጠውና አኰላሽተው በማስቀረት የተካኑ ናቸው፡፡

የአሁኑ ጸሐፊ ስለ ምርትም ሆነ ካፒታል ገበያዎች አስፈላጊ ናቸው/አይደሉም የሚለው ክርክር ውስጥ የመግባት ፍላጎቱም ሆነ ሙያው የለውም፡፡ በዚህ ርእሰ ጉዳይ ዝንባሌ ያለው አንባቢካለ ነፍሳቸውን ይማርልንና የዕውቁንና አንጋፋውን ኢትዮጵያዊ የኢኮኖሚ ምሁር÷ ተመራማሪ የዶ/ር በፈቃዱ ደግፌንና እሳቸውን የመሰሉ አገር ወዳድ የአኮኖሚ ጠበብቶችን ሥራዎች ፈልጎ እንዲያነብ ይመከራል፡፡ ዦሮ ያለው መስማትን ይስማ!!!

Filed in: Amharic