የፅምዶ ስትራቴጂያዊ ፍላጎቶች እና ፅምዶን የተቀላቀለው የአፋብን ክንፍ!

ጥላሁን ጽጌ

በሻዕቢያ እና በአንደኛው የህወሓት አንጃ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት የተፈጠረው ይህ ጥምረት በቅድሚያ “ራማ” ተብሎ በሚጠራው የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ራሱን ለሕዝብ ይፋ አደረገ። ቀጥሎ በኢትዮጵያ ያሉ ሌሎች የታጠቁ ቡድኖችን ማካተት ቻለ። በፖርት ሱዳኑ ጉባኤ ደግሞ ቀጠናዊነቱን አወጀ። የዚህ ጥምረት ዘለቄታዊ ፍላጎቶች ያን ያህል አከራካሪ አይደሉም።

ፅምዶን በበላይነት ከሚመሩት አካላት ፍላጎት አንፃር ጥቅል ፍላጎቶቹን ከዚህ በታች ነጣጥለን እንመለከታለን። በአቋም ደረጃ መሀል ሰፋሪ ለመሆን የሚመች ባለመሆኑ ወይ ጥምረቱን አምነህበት ትደግፋለህ ወይም ታቃውመህ ትቆማለህ።

አንደኛ፦ የአማራ ክልልን የእጅ አዙር ጦርነት ሜዳ ማድረግ!

ፅምዶን የፈጠሩት ሻዕቢያ እና ህወሓት እንደዚሁም ዘግይተው የተቀላቀሉት ጁኒየር ፓርትነሮች ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ቁርሾም ጦርነትም ውስጥ የገቡ ናቸው። የዐቢይ አህመድ መንግሥት ከኤርትራ ወይም ከህወሓት ጋር ወደ ጦርነት ቢገባ “ጦርነቱ የት ይካሄዳል?” የሚለውን ጥያቄ መመለስ ፅምዶ ቀድሞ ካስቀመጣቸው ፍላጎቶች አንደኛው ነው። በዚህም አማራ ክልል ለጦርነት ሜዳ እንዲውሉ ከታጩ አካባቢዎች ዋነኛው ነው። ይህ ፍላጎት ከአንድ ዓመት ወዲህ በወሎ ራያ በኩል ሙከራ ላይ ውሏል። በቤንሻንጉል ጉሙዝ የሚመጣውን ኃይል ለመቀበልም “ድግሥ ነው ድግሥ ነው፤ ዛሬ ፋሲካ ነው” እየተባለ ነው።

ሁለተኛ፦ ፋኖን “Junior Partner” እና ረባሽ ኃይል ብቻ ማድረግ!

የፅምዶ ፈጣሪዎች ፋኖን የሚፈልጉት መተኮስ የሚችል ማሸነፍ ግን የማይችል ኃይል እንዲሆን ማድረግ ነው። የተሳካላቸውም ይመስላል። በዚህም ምክንያት ፋኖ ጦርነቱን ከአማራ ክልል ማስወጣት እንዳይችል ለማድረግ ተችሏል። በተለይም ፅምዶን እንደወረደ የተቀበለው በኤርትራ ሐሬና የተመሰረተው የቀድሞው አፋብኃ ስብስብ “upper hand” መያዝ በመቻሉ “ፋኖን ረባሽ ኃይል ማድረግ” የሚለውን ዕቅድ ማስኬድ ተችሏል። “ህወሓት 17 ዓመታት ተዋግቷል ስለዚህ እኛም እንደዛ እንዋጋለን” የሚሉትም የረዥም ጊዜ ረባሽ ለመሆን ብቻና ብቻ ነው።

እንደ ኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ያሉ ኃይሎች ወደ አማራ፣ ቤንሻንጉል፣ ጋምቤላ፣ አፋር፣ እና አዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች መንቀሳቀስ እንደሚችሉ በተግባር አይተናል። በአንፃሩ “በቅድሚያ ቀበሌዎችን እንቆጣጠራለን፤ ቀጥሎም በክልል ደረጃ የሽግግር መንግሥት እንመሰርታለን” በሚለው የአፋብኑ መሪ “ድንቅ የትግል ስልት” ምክንያት የፋኖ እንቅስቃሴ ከአማራ ክልል መውጣት አልቻለም። መሪዎቹ ከአማራ ክልል ይወጣሉ ጦርነቱ ግን አይወጣም። በዚህም ፋኖ በፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ እና ወታደራዊ ዘርፎች እዚህ ግባ የሚባል ተፅዕኖ የሌለው ኃይል እንዲሆን ተደርጓል።

አሁን ላይ ፋኖ የአፍሪካ ቀንድ ተገዳዳሪ ኃይል እንደሆነ የሚነገረው ፕሮፓጋንዳ በተጨባጭ የሌለ ነገር ነው። ትናንት ግን ነበር። ትናንት ፋኖ አስፈሪ እና ተስፋ ሰጭ ኃይል ነበር። ቢያንስ ቢያንስ የመንግሥትን እጅ ለድርድር መጠምዘዝ የሚያስችል አቅም ነበረው። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ተጠሪ የነበረችው አምባሳደር Molly Phee የአማራ ክልሉን ጦርነት ከሱዳኑ እኩል አሳሳቢ እንደሆነ እስከመግለፅ ደርሳ ለፋኖም ጥሪ አቅርባ እንደነበር አይዘነጋም። የዛሬው የአፋብን ትክክለኛ ቁመና ግን እዚህ ምስል ላይ እንዳለው የድርጅቱ ሊቀመንበር አቀማመጥ ነው! እየመረራችሁም ቢሆን ዋጡት!

ሦስተኛ፦ ሀገረ ትግራይን ማዋለድ!

ህወሓት የአፋብኑ ቃል አቀባይ አስረስ ማረ እና አቶ ገዱ አንዳርጋቸው “ትብብሩ መሬት ሲነካ አገዛዙ ያከትማል” የሚል ሃሳብ በተመሳሳይ ሰዓት “ኢትዮ ኒውስ” እና ኢኤምኤስ” ላይ ቀርበው ባደረጉት ቃለምልልስ ላይ የነገሩንን አይነት ዕቅድ የለውም።ዛሬ ላይ Semi-autonomous ትግራይን የያዘው ህወሓት ከዚህ በኋላ የሚታገለው ነፃ ሀገር ለመመስረት ብቻና ብቻ ነው። ይሄንን እውን ለማድረግ ሁለት ነገሮችን ይፈልጋል።

የመጀመሪያው……!

ወልቃይት እና ራያን ሙሉ በሙሉ መልሶ መቆጣጠር ነው። የአማራን መሬቶች አሳልፎ የመስጠት የካበት ልምድ ያላቸውን አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን የፅምዶ አምባሳደር ያደረገው የእነ ምሬ ወዳጆ እና ሔኖክ ኪዳኔ ቡድን ራያን “ስላሌው ጉማ” እያለ ለህወሓት አሳልፎ ከሰጠ ሁለት ዓመታት አልፈዋል።

ይልቃል ጌትነትን ሌላኛው የፅምዶ አምባሳደር አድርጎ የሰየመው የእነ ዘመነ ካሴ እና አስረስ ማረ ቡድን ደግሞ ህወሓት ወልቃይትን መልሶ እንዲቆጣጠር “ደመንማኔው” እያለ መሸለል ከጀመረ ስድስት ዓመታት አልፎታል። ወልቃይትን ለማሳነስ እና ለህወሓት መንገድ ለመጥረግ ብዙ የተደከመ ቢሆንም የጎንደር ልሂቅ በወልቃይት ጉዳይ ልዩነት ስሌለለው የብረት አጥር ሆኖ ወልቃይትን ማስጠበቅ ተችሏል። “የደመንማኔው” ቡድን ወደፊትም ቢሆን በወልቃይት ጉዳይ ምንም ነገር ማሳካት አይችልም።

ሁለተኛው……!

ለሀገረ ትግራይ እውን መሆን ሌላኛው ተፈላጊ ጉዳይ የእውቅና ሂደት ነው። ለዚህ ደግሞ የአፍሪካ ቀንድ ጅኦ-ፖለቲካዊ ፍትጊያ ምቹ ሜዳ ነው። እስራኤል ለሶማሌላንድ ለሰጠችው እውቅና ትይዩና አፀፋዊ ምላሽ መስጠት የሚፈልጉ ሀገራት አሉ። ለዚህ ደግሞ ትግራይ ታጭታለች። እውቅና ሰጭ ሀገራትን አንደኛ ግብፅ ሁለተኛ እከሌ ሦስተኛ እከሌ እያላችሁ ራሳችሁ ቀጥሉበት።

አራተኛ፦ የኤርትራን ሀገራዊ ኅልውና በተለመደው መንገድ ማስቀጠል!

ሻዕቢያ የኤርትራ ኅልውና የሚከበረው በጎረቤት ሀገራት በተለይም በኢትዮጵያ ውስጣዊ መዳከም ነው ብሎ ያምናል። ይህ ትራዲሽናልና ዛሬም የቀጠለ አቋም ነው። የቅርቡን ጊዜ ብንመለከት እንኳን በቅድሚያ በፕሪቶሪያው የሠላም ስምምነት የ”Spoiler” ሚናን ተጫወተ። ቀጥሎ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የተፈጠሩ ቀውሶችን እና ቡድናዊ ስንጥቃቶችን አሰፋ። በመጨረሻም ፅምዶን አዋለደ። ለዚህ ሂደት የዐቢይ አህመድ መንግሥት የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አለው። የአማራ ልዩ ኃይልን ማፍረሱ እንደዚሁም የትግራይ ፖለቲካዊ ሽኩቻ ለሻዕቢያ ፍላጎት ምቹ እንዲሆን ማድረጉ ተጠቃሾች ናቸው።

አምስተኛ፦ የግብፅን ጅኦ-ፖለቲካዊ ፍላጎት ማሳለጥ!

ኤርትራን፣ ሶማሊያን፣ እና ጅቡቲን አጋር ማድረግ የቻለችው ግብፅ ሱዳንን ምሽግ አድርጎ በኤርትራ በበላይነት የሚመራውን ፅምዶን በሚገባ እየተጠቀመችበት ነው። የዓባይ ወንዝ እና የቀይ ባሕር አጀንዳዎች የግብፅ ዓይን ማረፊያዎች ናቸው። ቀጠናዊ ተገዳዳሪነትን ማሳደግ ሌላኛው ስልታዊ ፍላጎቷ ነው። ስለዚህ እንደ ፅምዶ አይነት ጥርነፋ ለግብፅ ነባር ፍላጎት ምቹ ነው። እየደገፈችውም ነው።

በጥቅሉ ፅምዶና ፍላጎቱ ይሄንን ይመስላል። የተዳከመች ኢትዮጵያ፣ የተከበበች ሀገር፣ ተላላኪ እና ግዛቱን የእጅ አዙር ጦርነት ማፋፋሚያ ሜዳ የሚያደርግ የአማራ ኃይል፣ ግዛቶቹን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተነጠቀ አማራን እውን ማድረግ። ይህ የአማራ የትግል Cause ነው? በፍፁም!

 

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.