ኢትዮጵያን አትርሱ! በፖለቲካ በዘረኝነት አትታለሉ አትጭበርበሩ። አጥር አታብዙ። ድንበር አታብዙ። ልዩነት አታብዙ። ውደዷቸው ይውደዷችሁ። ለምሳሌ ጎንደሮዎች ስታገቡ ኦሮሞዎችን ትግሬዎችን ወሎዬዎችን አግቧቸው። ገበሬ ይመስል ዘር አትምረጡ። እኛኮ ክፋታችን አንድ ዓይነት ደግነታችንም አንድ ዓይነት ነው። የእኛ ሕዝብኮ እንኳን ምግብ፤ መድኃኒህም ቢሆን አብሮ ይጠጣል ከፍቅሩ ፅናት የተነሳ፤ ሓኪም ሳያዘው በትብብሩ! እና ያ ፍቅራችን የት ገባ? ያ መዋደድ የት ገባ? ሽማግሌዎችስ የት አሉ? የትግራይ የኦሮሞ የአማራ የሲዳማ ሽማግሌዎች የት አሉ? ባልህበት እርጋ የሚሉ፣ ደም የሚያደርቁ?
***
እባካችኩ ተረጋግታችሁ አስቡ! #አንድ_ሕዝብ ነን። ልዩነት ኃጢአት ነው ወይ? አይደለም! እኔ ይገርመኛል ልክ መለያየት እኛ ሀገር ብቻ ያለ ይመስል፤ ናይጄርያ ሀገር ውስጥ 100 ዓይነት ቋንቋ ይነገርበታል። እኛ ሀገር 80 ነው በ20 ይበልጡናል። ነገር ግን ናይጄርያ ሀገር ሁና እየቀጠለች ነው ከነ ችግሯ! ቻይና ውስጥ ብዙ መቶ ቋንቋዎች ይነገርባታል። አንድ ቢልዮን ሕዝብ እየመሩ ዛሬ ሆዳቸው ሞልቶ ለኛም እርዳታ እየላኩልን ነው። እኛ 80 ሚልዮን ሆነን እንኳን እርዳታ ልንልክ እርዳታ ለመቀበል እንኳን መግባባት አልቻልንም። ስለዚህ እባካችሁ እንግባባ ምዕመናን!
***
ትግርኛ ሕይወታችን ነው ቋንቋችን ነው! ኦሮምኛም ሕይወታችን ነው ቋንቋችን ነው! አማርኛም ሕይወታችን ነው ቋንቋችን ነው! እነዚህ ሁሉ ቋንቋዎች አንድ አድርጎ የሚተረጉማቸው ደግሞ #ኢትዮጵያ የሚባል የቋንቋዎች ሁሉ ቋንቋ ደግሞ አለ። ይሄንን ሁሌም እናገራለሁ። ምክንያቱም ለማምለክም ሀገር ያስፈልጋል። ለመኖርም ሀገር ያስፈልጋል። ተበታትነን ፈራርሰን እንቀራን ወገኖቻችን! ደግሞም ማፍረስ እንደ መገንባት አድካሚ አይደለም። እስኪ ለምሳሌ፦ ዶክተሮች ሆድ ይቀዳሉ አይደል በኦፕራሲዮን? አንድ ዶክተር ሆድ ሲቀድ ተጠንቅቆ፣ አጥንቶ፣ መቀደድ አለበት ወይ? ብሎ፣ ተዘጋጅቶ፣ ነርሶቹም እቃ እንዳይረሳ መቀሱን ቆጥረው፤ በጣም ጥንቃቄ ተደርጎ ነው። እንዴው አንድ ዱርዬ ግን የሰውን ሆድ ሲቀድ ዝግጅት ያደርጋል? አያደርግም! ከየትስ እንደሚጀምር ያውቀዋል? አያውቀውም! ምክንያቱም መልሶ አይሰፋውም! ዘርግፎ መሄድ ነው የእርሱ ዓላማ።… አንድነትም በጥንቃቄ ሊያዝ ይገባል። ምክንያቱም አንድ ጊዜ ከተቀደደ መስፊያው ከባድ ነው ወገኖቼ! አባቶቻችን በብዙ ጥንቃቄ ነው ይህንን የሰፉት! ስለዚህ አንለያይ እንግባባ! በማርያም ተዋደዱ።
ምንጭ:- ቢኒያም ዘ ክርስቶስ
Binyam ZeChristos /የካቲት 13 – 2010/