>
5:21 pm - Wednesday July 21, 2488

የዘመኑን ጎልያድ ዓይኑን ጨፍኖ ''የአጥፍቶ መጥፋት'' መስመር ላይ  ሽምጥ እየጋለበ ነው (መሳይ መኮንን)

ትልቅ አደጋ ከፊታችን ተደቅኗል። የፊታችን ዓርብ የሚሰበሰበው ፓርላማ አስቸኳይ አዋጁ ላይ የሚሰጠው ውሳኔ የኢትዮጵያ ሀገራችንን ቀጣይ ቀናት፡ ሳምንታትና ወራት የሚለይለት ያደርገዋል። ይህ አስቸኳይ አዋጅ ካልተስረዘ አደጋው ከባድ ነው። ምናልባትም ወደ ከፍተኛ የእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ ሊከተን ይችላል። ምንም እንኳን የለማ ቡድን በትግራዩ አገዛዝ የተበተነውን የዘር መርዝ በማምከኑ በተወሰነ ድረጃ ስጋቱን የቀረፈ ቢሆንም አሁንም ግዙፍ ዕልቂትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ጉዳዮች እንደተወሳሰቡ ናቸው። የትግራዩ አገዛዝ ዓይኑን ጨፍኖ ”የአጥፍቶ መጥፋት” መስመር ላይ ወጥቶ ሽምጥ እየጋለበ ነው።
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚያስገኘው አንዳችም ሰላምና መረጋጋት አይኖርም። አዋጁ የትግራዩን አገዛዝ ዕድሜ በጉልበት ለማስቀጠል የተወሰደ እርምጃ ነው። የህወሀት ባለሀብቶችና ከስርዓቱ ጋር የተጣበቁ ሰዎችን ንብረት ለመጠበቅ በሚል የታወጀ እንደሆነም ይታመናል። ይህ አዋጅ ኢትዮጵያውያን ላይ የተሰነዘረ የዕልቂት በትር ነው። መንግስት በሚባል አካል ህዝብ ላይ የታወጀ ጦርነት ነው። ነቀምት ላይ ተጀምሯል። ደምቢዶሎ ላይ ተፈጻሚ ሆኗል። በእርግጥ ለነጻነቱ ቁርጠኛ ውሳኔ ላይ የደረሰ ህዝብን ወደኋላ የሚመልሰው ምንም ሃይል አይኖርም። አዋጁን ህዝቡ አልተቀበለውም። ጥሶታል። በየቦታው የህዝብ ንቅናቄ የሚቆም አልሆነም።

አስቸኳይ አዋጁ በምክር ቤት አባላት አብላጫ ድምጽ ውድቅ ካልተደረገ ነገሩ አደገኛ ይሆናል። ለመሞት የቆረጠ ህዝብና ለመግደል የተዘጋጀው የትግራዩ አገዝዝ ተፋጠዋል። ህዝቡም ከመሞት፡ አገዛዙም ከመግደል የሚመለሱ አይደሉም። ይህ ደግሞ ወደ ህዝብ ለህዝብ ጦርነት የማምራት ዕድሉ ሰፊ ነው። የትግራዩ አገዛዝ ሃላፊነት የጎደለው በመሆኑ ይህን ከማድረግ የሚመለስ አይደለም። አጥፍቶ ለመጥፋት ወስኗል። አሁን ኳሷ ያለችው በፓርላማ አባላት እግር ስር ነው። ኢትዮጵያ ወደ ዕልቂት እንዳታመራ ማድረግ ይችላሉ። በፓርላማው ማዕቀፍ ስር በአስቸኳይ አዋጅ ስም ህዝብ ላይ የተጠራውን የሞት ድግስ ማስቀረት ካልቻሉ ታላቅ ታሪካዊ ጥፋት ሆኖ ይመዘገባል።ዓርብ ወሳኝ ቀን ነው። የፓርላማ አባላት ከህዝባቸውና ከጨቋኙ አገዛዝ አንዱን ለመመረጥ ይሰየማሉ። ከወዲሁ ከትግራዩ አገዛዝ ጫናና ማስፈራሪያ እያደረሰባቸው ነው። ግን ከህዝብ የሚበልጥ ነገር የለም። በስልጣን ካልቆየሁ አጠፋችኋለሁ ብሎ የተነሳን የዘመኑን ጎልያድ በመፍራት ህዝብ ላይ የታወጀውን ጦርነት ይሁንታ ሰጥተው ያጸድቁታል ብዬ አልጠብቅም።ለ27 ዓመታት የትግራይ አገዛዝ አዳማቂ መሆናቸው በራሱ ትልቅ ወንጀል ነው። እናም ታሪካዊ ውሳኔ በእጃቸው ላይ ወድቋል። ዓርብ ዕለት።

ከአንድ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የደረሰን የውስጥ ማስታወሻ
”እያስፈራሩን ነው። ጄነራሎቹ ራሳቸው በአካል መጥተው ነው ያነጋገሩኝ። በግልጽ ማስፈራራት አደረጉብኝ። አዋጁን መጽደቅ አለባችሁ። ይህ ለእናንተም የሚበጅ ነው። አለበለዚያ ፓርላማውን አፍርሰን እያንዳንዳችሁ ላይ እርምጃ እንወስዳለን ነው የሚሉት። ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለጓደኞቼም ተመሳሳይ ነገር ነው የነገሯቸው። አንዳንዶቹ ጓደኞቼ ደንግጠዋል። ምን ሊሆን እንደሚችል አላውቅም።” 

 

Filed in: Amharic