>

የወያኔ ፓትርያርክ ምሕላ የመጥራት የእምነት/ሞራል ብቃት የለውም (ከይኄይስ እውነቱ)

የሃይማኖት አባት አድርገህ የማትቀበለውን ሰው ለለበጣ ‹አቡነ› እና ‹ብፁዕ› እያሉ መጥራት ለራስ
አለመታን በመሆኑ አልፈቀድኩትም፡፡ ጊዜው የወሬ ባለመሆኑ መልእክቴን ባጭሩ አቀርባለኹ፡፡የማኅበር/የሕዝብ ጸሎት (ምሕላ) የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ለዘመናት ስትገለገልበት የቆየችና በቊዔት/ጠቀሜታ ያለው ታላቅ ሥርዓተ ጸሎት ነው፡፡ በተለይም አገር በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋ (ድርቅ፣ ቀጠና፣ቸነፈር፣ ሀገር-አቀፍ ደዌያት ሕዝብን ሲቀጥፍ፤ ደሀ ሲበደል÷ ፍርድ ሲጓደል፣ ከሁሉም በላይ ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ላለፉት 27 ዓመታት ምድራዊ ገሃነም ባደረገ÷ራሱን ‹መንግሥት› ነኝ ባለ የጥቂት ዘረኞች ወንበዴዎች ቡድን አገርና ሕዝብ የጥፋት አደጋ ሲያጋጥመው ወዘተ.) ሲያጋጥም በእውነተኛ የቤተክርስቲያን አባቶች ነት በየአድባራቱና ገዳማቱ የምሕላ ጸሎት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ መንጋውን ለመጠበቅ በኖላዊነት (እረኝነት) ከተሰየሙ የሃይማኖት አባቶች የሚጠበቅ ነው፡፡

ወያኔ/ሕወሀት በሚባል አሸባሪ ቡድን አገር ወደ ገደል እየተገፋችበት ባለበት፣ በሕዝባችን ላይ እልቂት
በታወጀበትና በንጹሐን ላይ ግድያ እየተፈጸመ ባለበት፣ በዚህ ግቢ ነፍስ ውጪ ነፍስ በሚያሰኝ ቀውጢ ሰዓት የምሕላ ጸሎት ማድረግ ተገቢነት የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ አገር ለመውረር የመጣው የጣልያንን ጦር ቡራኬ ሰጥቶ እንደላከው የግብር አባታቸው የሮም ‹ጳጳስ› ሕዝባችንን በጎሣ አጥር አለያይቶ እርስ በርስ ሲያናቊር፣ አንድነታችንን በጽኑ ሲያናጋ፣ ወገንን በጅምላ ሲጨፈጭፍ፣ አገራዊ ሀብትን ሙልጭ አድርጎ ሲዘርፍ፣ ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት ምሎ ተገዝቶ ለመጣ ቡድን አበጀህ በጎ አደረግክ ብሎ ቡራኬ ሲሰጥ የቆየና ለዚሁ ዓላማ የተቀመጠ የወያኔ ‹የነፍስ አባት› ምሕላ እንዲደረግ ጥሪ ሲያደርግ ያምማል፡፡ አንዳንዶች ‹ለበጎ› እስከሆነ ድረስ ማንም ጥሪ ቢያደርግ ክፋት የለውም ብለው ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ የውጤትን ያህል ውጤቱን ለሚያስገኘው ሥነ ሥርዓታዊ ሂደትም እኩል ልንጨነቅ ይገባናል፡፡ እንዲህ ሲሆን ውጤቱ ዘላቂና አስተማማኝ ይሆናል፡፡

ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ለአገርና ለሕዝብ አስበው ነው ወይ ብሎ መጠየቅም ተገቢ ነው፡፡ወያኔ በጻዕረ ሞት ላይ በሆነበት ጊዜ ኹሉ የመጨረሻ ሕቅታውን ለማራዘም በደጀንነት ብቅ የሚሉ መናጆዎች – እነ ፃድቃን ገ/ትንሣኤ፣ አበበ ተ/ሃይማኖት፣ አማረ አረጋዊ፣ ስዬ አብርሃ እና ባንዳው ልደቱ አያሌው የመሳሰሉ ሐሳውያን የሰላም መልእክተኞች› ውስጣቸው ግን ነጣቂ ተኩላዎች – በፖለቲካው መስክ እንዳሉ ኹሉ፤ ብአዴን የተባለ የቁም ሙቶችን ቡድን ሕወሀት ‹የአማርኛ ክፍሉ› ተጠሪ እንዳደረገ ኹሉ፤ እያጠፋንው ነው በሚሉት በኦርቶዶክስ ክርስትና በኩል ደግሞ ‹አቦይ ማትያስን› እና በየአድባራቱና ገዳማቱ ከመንፈሳዊ ሕይወት ጋር ፍጹም የተጣሉ፣ ክህነት የሌላቸውን/ያፈረሱ ምልምል ካድሬዎችን አስቀምጧል፡፡ እነ አቦይ ማትያስ አንድነትን የምትሰብክ
ቤ/ክርስቲያን እመራለኹ እያሉ ወያኔ ሕዝቡን በጎሣ ሲከፋፍልና ሲያጋጭ÷ ‹ክልል› የተባለ የአትድረሱብኝ አጥር ሲያቆም ምን አሉ፤ በቆሙለት አገዛዝ ደሀ ሲበደል ፍርድ ሲጓደል ምን አሉ፤ ሕዝብ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎ ሜዳ ላይ ሲወረወር ምን አሉ፤ ሕፃናትና አረጋውያን ሲገደሉ ምን አሉ፤ ወጣቶች አገር አልባ ተደርገው በየበርሃው ቀልጠው÷ በባሕር ሰጥመው ሲቀሩ ምን አሉ፤ እልፍ አእላፋት አገዛዙ በፈጠረው የዝርፊያና የንቅዘት ሥርዓት በጠኔ ሲያልቁ ምን አሉ፤ ወዘተ. ዛሬ ‹አቦይ ማትያስ› የምህላ ጥሪ አደረጉ የተባሉት ‹የነፍስ ልጆቻቸው› ወያኔዎች በአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዝናት በደል ባንገፈገፈው፣ ነፃነት በጠማው የሕዝብ ዓመፃ ዛንጅር ተይዘውና በተቃወሞ አውታር ተወጥረው እንዳሉ በማወቃቸው፣ መንፈሳዊውን የጦር መሣሪያ (ምሕላ) ተጠቅመው ነውረኛውን አገዛዝ ከገባበት አጣብቂኝ ለማስወጣትና ፋታ እንዲያገኝ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ሳይገባቸው (‹ገ› ጠብቆ ይነበብ) በነ አቡነ ጴጥሮስ መንበር ላይ የተሰየሙት የወያኔው አቦይ ማትያስ እንደ ነውረኛ ልጆቻቸው እሳቸውም ሕዝበ ክርስቲያኑን በእምነት ሽፋን የሕዝቡን የተቃውሞ መንፈስ ለማዳከም ተልእኮአቸውን ለመወጣት እየጣሩ ነው፡፡ እግዚኦ እንደዚህ እንዝቀጥ፡፡ በነገራችን ላይ በ‹ሃይማኖት አባቶች› ላይ (አይደሉም እንጂ) በድፍረት የምንናገረው ኢትዮጵያዊ ጨውነትና ባህልን ዘንግተንው አይደለም፡፡ ግፍና በደልን በእምነት ሽፋን እንድንቀበል የሚገፋንን የትኛውንም ኃይል መቀበል ከሰብአዊነት መፋታት÷ከሕገ እግዚአብሔርም ውጭ ስለሆነ እንጂ፡፡

ወገኔ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም የሚመለከታችሁ ሕዝበ ክርስቲያን፣ የአገርና የሕዝብ ህልውና ካልተከበረ
ሥርዓተ አምልኮታችንን በኅብረት መፈጸም የማይታሰብ ነው፡፡ ወራቱ የዐቢይ ፆም መሆኑ ይታወቃል፡፡ ያለ አቦይ ማትያስ ጥሪ ምህላችንን ለአገራችን ህልውናና ለሕዝባችን ደኅንነት እናደርጋለን፡፡ እያደረግንም ነው፡፡ ይህንንም እያደረግን ጎን ለጎን፣ የወያኔ አረመኔያዊ አገዛዝ ከኢትዮጵያ ምድር ተነቅሎ የሕግ የበላይነት የነገሠበትና ሁሉንም ኢትዮጵያው በእኩልነት የሚያስተናግድ መንግሥተ ሕዝብ በኢትዮጵያችን እስክንተክል ቃውሞአችንን እንቀጥላለን፡፡ መንፈሳዊ አባቶቻችን ‹‹ብዙ ሕዝብ እግዚአብሔር ነው፡፡›› ይላሉ፡፡ ሕዝብ የጀመረውን ሰላማዊ እምቢተኝነት በአንድነት መንፈስ በመላ ኢትዮጵያ ከቀጠለ የነፃነት ቀን ቅርብ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር እውነት፣ የፍትሕና ርትዕ አምላክ ነውና፡፡

አምላከ ኢትዮጵያ ያንዣበበብንን የጥፋት ደመና በቸርነቱ ይበትንልን፡

Filed in: Amharic