>

"ወንድና ሴት ዕኩል ናቸው!" ያለው ማን ነው? በፍጹም አይደሉም! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

ዛሬ የካቲት 29 (March 8) በዓለም አቀፍ ደረጃ የሴቶች ቀን ተከብሮ ውሏል፡፡ “እህህ!” አለ ሰውየው! እንዲህ እየደለላቹህ አታሏቸው እንጅ እናት እኅቶቻችንን፡፡ ያለንበት ዘመን 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ነው፡፡ በጣም በሚገርም ሁኔታ ያልሠለጠነውን የዓለማችን ክፍል እንተወውና (ከሀገራችን በስተቀር) በሠለጠነው የዓለማችን ክፍል እንኳ እስከዛሬ ድረስ ሴቶች ከወንዶች ጋር ዕኩል የመታየት የመስተናገድ መብትና ዕድል አላገኙም፡፡

በእነኝህ ሠለጠኑ በሚባሉ ሀገራት ሴቶች የመምረጥ የመመረጥ፣ ከቤት ወጥቶ የመሥራት የመሳሰሉ  መብታቸውን ያገኙትም አሁን ሩቅ በማይባል ጊዜ ነው፡፡ እስከአሁንም ድረስ ግን በብዙ የሥራ ዘርፎች ሴቶች ከወንዶች እኩል ተከፋይ መሆን አልቻሉም፡፡ እኩል ተከፋይ ለመሆንም እየታገሉ ይገኛሉ፡፡ ይሄም ማለት ዓለም የሴቶችን እኩልነት ገና አልተቀበለችም ማለት ነው፡፡

ከላይ ከእኛ በስተቀር ማለቴ ከረጅሙ የሀገራችን ታሪክ መረዳት እንደሚቻለው ሀገራችን  ከመጀመሪያው ጀምሮ በታሪኳ ከንግሥት ማክዳ ወይም ንግሥተ ሳባ በፊትም ሆነ በኋላ እስከ ንግሥት ዘውዲቱ ድረስ በርካታ ሴቶችን ለመጨረሻው ሀገርን የመምራት የማሥተዳደር የሥልጣን ደረጃ ያበቃች ሀገርና ያበቃን ሕዝብ በመሆናችን ገና ከጥንቱም ዛሬ ሠለጠንን ከሚሉ ነገር ግን በታሪካቸው አንዲት እንኳ የሴት መሪ ዓይተው፣ ሰጥተው፣ አብቅተው ከማያውቁ ሀገራትና ሕዝቦች የላቀ የሠለጠነ  የአስተሳሰብ ደረጃ ላይ የነበርን ወይም ያለን በመሆኑ ነው ከእኛ በስተቀር ብየ መናገሬ፡፡

ሴት ከወንድ እንደምታንስ በወንዶች ሲሰበክ ኖሯል፡፡ አሁን ግን ቢያንስ በወሬ ደረጃ እኩል እንደሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ እውነታው ግን ወንድ ሴትን የሚበልጥበት ብቸኛ  መለኪያ ቢኖረው ጉልበት ወይም ጡንቻ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ባለው ነገር ሁሉ ግን ወንድ ከሴት ከምኗም አይደርስ፡፡ የእግሯን እጣቢ ያህልም እንኳ አይሆን፡፡ በጭንቅላት ብትሉ ኃላፊነትን በመወጣት በመሸከም ብቃት፣ ለችግሮች መላ መፍትሔ በማመንጨት ችሎታ፣ በአንድ ነገር ላይ ባላቸው ጽናት፣ በአሥተዳደር ችሎታና አቅም ወዘተረፈ. ሴት እጅግ የላቀ አቅምና ችሎታ አላት፡፡

ይሄንንም ወንዶች አሳምረን እናውቃለን፡፡ ስለማናውቅ እንዳይመስላቹህ “ታንሳለች!” ስንል የኖርነው አሁን ደግሞ “እኩል ናት!” እያልን ያለነው፡፡ ታውቃላቹህ? እኛ ወንዶች ስንባል ሸፍጠኞች ነን! በተፈጥሯችን ሽንፈትን ማስተናገድ አንወድም፡፡ አብሶ ደግሞ በሴት መሸነፍን በፍጹም ልንቀበለው የማንፈልገው ነገር ነው፡፡ ከጾታ ተቃራኒነት የመጣ ተፈጥሯዊ የመቀናቀን ስሜት ነው እንዲህ ያደረገን፡፡ ብዙ ሰው ልብ የማይለውና የማያውቀው ነገር አለ፡፡ ሴት ልጅ በተፈጥሮዋ ወንድን እንድታሸንፍ ተደርጋ የተፈጠረች መሆኗን፡፡ ወንድነት መቸም፤ በምንም ተአምር ቢሆን ሴትነትን ሊያሸንፍ አይችልም! እኛ ወንዶች ሴቶች በእኩል መድረክ የመፎካከር ዕድል ቢያገኙ ፈጽሞ እንደማንችላቸው ውስጣችን ስለሚያውቅ ሴቶችን በምንበልጥበት በአንዲቱ ጉልበታችን በመጠቀም ሴት ያላትን ተፈጥሯዊ አቅም ኃይልና ችሎታ ተጠቅማ ወንድን እንዳታሳፍር፣ በወንድ ላይ እንዳትሠለጥን አስሮ የሚያስቀምጥ በአድልኦ የተሞላ የባሕል የወግና የመሳሰሉትን የአሥተዳደር ሥርዓት በመፍጠር  የመፎካከር ዕድሉን ከነአካቴው እንዳያገኙ አድርገን ቆይተናል ወደፊትም ይህ ሸፍጠኛና ኢፍትሐዊ አሠራር ሳይለወጥ በዚሁ እንደሚቀጥል ቅንጣት ታክል አልጠራጠርም፡፡

ለነገሩ ሴቶችም ብትሆኑ ለሌላ ሳይሆን በዋነኛነት ለራሳቹህ ጥቅምና ደኅንነት ሲባል ከወንድ ጋር ዕኩል የመፎካከር መብትና ዕድል እንዲኖራቹህ እንዲሰጣቹህ ባትጠይቁ መልካም ነው፡፡ ይሄንን መብትና ዕድል ብታገኙ በተፈጥሯቹህ የተሰጣቹህን አቅም ኃይልና ችሎታ በፍጹም ልትቆጣጠሩት ስለማትችሉና በውጤቱም ተሸናፊው ወንድ አጠገባቹህ ሊቆም ስለማይችል ስለሚርቅና ባል የማግኘት ዕድል ልታገኙ ስለማትችሉ በዚህም ደግሞ የማኅበረሰብ ቀጣይነት ሊቋረጥ ስለሚችል በዚህ በዚህ ነገር ተጠቃሚ ስለማትሆኑ በባሰባቸው ደናቁርት ወንዶች የሚፈጸምባቹህን የቤት ውስጥ ጥቃት ግፍና በደል እንዲቆም፣ መሠረታዊ የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩላቹህ ሳትታክቱ ሳትሰለቹ ታገሉ እንጅ እባካቹህ ከወንድ ጋር ዕኩል የመፎካከር መብትና ዕድል እንዲሰጣቹህ በፍጹም አትጠይቁ አትታገሉ? ያላቹህ ኃይል ችሎታና አቅም ከፍተኛ በመሆኑ ከወንድ ጋር የምትፎካከሩበት ዕኩልና ነጻ መብትና ዕድል ብታገኙ የማኅበረሰብን ቀጣይነት አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ከፍተኛ አደጋ ሊፈጠር እንደሚችል ስለሚታወቅም ነው ሃይማኖትም በሴቶች ላይ ገደብ የጣለው እኮ!

እናም ለራሳቹህም ጥቅምና ደኅንነት ስትሉ ይሄንን መብትና ዕኩልነት መጠየቁን ተውት? ለነገሩ ብትጠይቁም አታገኙም! መግቢያየ ላይ እኛ ወንዶች ሸፍጠኞች ነን አላልኳችሁም? ገፍታቹህ ከመጣቹህ ያው ወረቀት ላይ ያሠፍሩላቹህና ይመልሷቹሀል፡፡ ይህ ወረቀት ላይ የሠፈረ መብትና ዕድል ግን በምንም ተአምር ተግባር ላይ ይውላል ብላቹህ ተስፋ እንዳታደርጉ፡፡ እንዲህ እያደረጉ ሲያሿቹህ ይኖራሉ እንጅ መቸም ቢሆን ዕኩል ዕድልና መብት በፍጹም የምታገኙ  አይመስለኝም፡፡ ይህች ዓለም የአንባገነኖቹ፣ የሸፍጠኞቹ፣ የአረመኔዎቹ፣ የተሸናፊዎቹ፣ የሥርዓት አልበኞቹ የወንዶች ናት! የፈለገ ነገር ብታደርጉ በምንም ተአምር ይሄንን ልትለውጡት አትችሉም! ቢለወጥም ተጎጂ እንጅ ተጠቃሚ አትሆኑም፡፡ ቀላል  ምሳሌ ልስጣቹህ በመላው ዓለም አንድ ነገር ታዘቡ ያሸነፈች ሴት ትዳር ሲዘልቅ አይታቹህ ታውቃላቹህ? በፍጹም! ሴት ልጅ አውቃ ስትሸነፍና የማትገዳደር፣ የማትፎካከር፣ የማትቀናቀን ስትሆን ብቻ ነው ትዳሯ ዘላቂና ሰላማዊ የሚሆነው፡፡ ተሸንፋም እንኳ ስንት ችግር አለ! እና? እናማ ……

ሰላም!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com

Filed in: Amharic