>

ድብ እና ቀበሮ!! (እንግዳ ታደሰ - ኖርዌይ)

በዓለም ላይ ያሉ አገሮች የየራሳቸው የተረት አፈ ታሪኮች አሏቸው፡፡ ከኖርዌጅያን አፈ ታሪክ ያገኘሁት ተረት ለምን እንደሆነ አላውቅም ከህወሃት እና ኦነግ/ ኦህዴድ ጋር ተገናኘብኝ ፡፡ ኦህዴድን ለምን ከኦነግ ጋር አገናኘኽው የሚል ጥያቄ እንደሚነሳ አውቃለሁ ፡፡ ኦነግን በማጃጃል ከጨዋታ ውጭ ያደረገችው ህወሀት አሁን ደግሞ ኦህዴድ ላይ ጨዋታ እየጎነጎነች እንደሆን እየታየ ያለው ሁኔታ ከተረቱ ጋር ስለተመሳሰለብኝ ነው ይህን የኖርዌይ ተረት አንባብያን በምሳሌና በንፅፅር እንዲያዩት የፈለግሁት ፡፡ ወደ ተረቱ ልግባ ፡፡

 ትልቁ ድብና ብልጧ ቀበሮ በአንድ ወቅት የገና በዓልን በጋራ ለማክበር ይረዳቸው ዘንድ አንድ ጣባ ሙሉ ለጋ ቅቤ ገዝተው ከአንድ ጥቅጥቅ ካለ ደን ውስጥ የጸሃይ ብርሃን እንዳያቀልጠው በማለት ቅቤው እንዲበስል ደብቀው ያስቀምጣሉ ፡፡ ቅቤውን በአስተማማኙ ቦታ ካስቀመጡ በኋላ ለምን ከወንዝ ዳር ሄደን ፀሃይ እየሞቅን ሰውነታችንን አናፍታታም የሚል ጥያቄ ቀበሮዋ ለድቡ ታቀርብለታለች ፡፡ ድቡም ይስማማል ፡፡ ጸሃያቸውን እየሞቁ ሳለ ድንገት ቀበሮዋ ከተኛችበት ብድግ ትልና ሰውነቷን በማርገፍገፍ   ወዬ ! መጣሁ እያለች ወደ ጫካው ወረደች ፡፡ ከጫካው እንደደረሰች ወደ ቅቤው በመሄድ ሁለት ሶስተኛውን ቅቤ ከበላች በኋላ አፏን ጠርጋ ጸሃይ ይሞቁበት ወደነበረው ቦታ ትመጣለች ፡፡

ድቡ ምን እንደተፈጠረና ለምንስ ካጠገቡ እንደሄደች ? ተመልሳም ስትመጣ ቦርጯ ጨምሮ ለምን እንደመጣ አፋጦ ይጠይቃታል ፡፡ እንዴ ምን ማለትህ ነው ! አራስ ቀበሮ እንደሆንኩ አታውቅም እንዴ? ልጆቼ ጡት አምሯቸው ሲጠሩኝ ሰምቼ ላጠባቸው ሄጄ ነው ፣ ጡቴ አግቶ ነው ትለዋለች ፡፡ የልጆችሽ ስም ማለቴ የመጀመርያው ማን ተብሎ ነው የሚጠራው ይላታል ፡፡ ስሙ ! « ገና መጀመሩ » ይባላል የመጀመሪያው ልጄ ብላ ከነገረችው በኋላ እንደገና ተንጋለው ጸሃያቸውን ይሞቁ ጀመር ፡፡

ጸሃያቸውን እየሞቁ ድቡ የሰመመን እንቅልፍ እያንጎላጀው እንደሆነ የተረዳችው ቀበሮ ልክ እንደቀድሞው ሰውነቷን በማንጠራራት ብድግ ካለች በኋላ ፣ ወዬ ! መጣሁ ብላ እንደገና ወደ ጫካው ትወርዳለች ፡፡ ከገበታው ቅቤ ውስጥ ቀሪውን ከበላች በኋላ እንደተለመደው አፏን አብሳ ወደ ድቡ ትመለሳለች ፡፡ አሁን ደግሞ የት ነበርሽ ? የሚል ጥያቄ በድጋሚ ሲያቀርብላት ! እንዴ ! ቅድም ነገርኩህ እኮ ልጆቼ ርቧቸው ጠርተውኝ ነዋ ! በማለት ትመልስለታለች ፡፡ አሁን ደግሞ ርቦት የጠራሽ የልጅሽ ስም ማነው ?                     « ግማሹ ተበላ » ይባላል ትለዋለች ፡፡ ድቡም በጥርጣሬ መልክ ወደ ቀበሮዋ እያየ ምን አይነት ገራሚ ስም ነው ልጆችሽ ያላቸው እያለ በማዛጋት እንቅልፍ ጭልጥ አድርጎ ወሰደው ፡፡ እንደተለመደው ለሶስተኛ ጊዜ ወዬ ! መጣሁ በማለት ወደ ቅቤው ሄዳ ቀሪውን ሙጥጥ አድርጋ በልታ ወደ ድቡ ተመለሰች ፡፡

አሁንም አጥብተሽ መጣሽ ? አሁን ደግሞ የጠባው ልጅሽ ስሙ ማነው ብሎ ይጠይቃል ? የዚህኛው ስሙ « ላስኩት ስሩ ድርስ »  ይባላል ትለዋለች ፡፡ ትንሽ እንደተኙ ድቡ ከንቅልፉ በመንቃት እስቲ ቅቤያችንን ወደ ጫካው ወርደን እንየው በሰሎ እንደሆን በማለት ለቀበሮዋ ጥያቄ በማቅረብ ተያይዘው ቅቤውን ወደአስቀመጡበት ስፍራ ሲደርሱ ቅቤው የለም ፡፡ ይህኔ ! ድቡ ወቀሳውን ወደ ቀበሮዋ ላይ ለጠፈ ፣ ቀበሮዋም በምላሹ በድቡ ላይ ማላከክ ጀመረች ፡፡ ቀላል ነው የበላውን ለማወቅ !! ከሁለታችን አንዳችን እንደበላን ለማወቅ ቀላል ነው ለማወቅ እያለች ቀበሮዋ ያዙኝ ልቀቁኝ አለች ፡፡ የበላውን ለማወቅ አሁንም በጀርባችን ተኝተን ጸሃይዋ ፊት ፊታችንን ስትመታን አገጫችን እና ቆዳችን በወዝ ከተጥለቀለቀ ያኔ ፊቱ የወዛውና ቆዳው የወዛው ነው የበላው በዚያ ይታወቃል በማለት ቀበሮዋ ሃሳቡን ታመነጫለች ፡፡ በህሊናው ነጻ የሆነው ቅቤውን ያልበላው ድብ በሃሳቡ ተስማምቶ ከጸሃይዋ ፊት ለፊት ሁለቱም ይተኛሉ ፡፡ ድቡ ድብን ያለ እንቅልፍ እንደወሰደው ያወቀችው ቀበሮ ከአጠገቡ ቀስ ብላ በመነሳት ቅቤው ወደነበረበት በመሄድ በስንጥር ከጣባው ስንጥቅጣቄ ውስጥ ያለውን ቅቤ በመዛቅ ድቡ ወደተኛበት ቦታ ስትመለስ ድቡ ጭራሽ እያንኮራፋ እንቅልፉን ይለጥጣል ፡፡ ከዚያም በስንጥሮች ይዛ ካመጣችው ቅቤ የድቡን አገጭ እና ከንፈር ፣ እንዲሁም ቆዳውን ሁሉ ለቅልቃ ስትጨርስ ድቡ ከንቅልፉ ይነቃል ፡፡ ምንም እንዳልተፈጠረ በመሆን ቀበሮዋም ከንቅልፏ እንደተነሳች በማስመሰል ቁጭ ትላለች ፡፡ ጸሃይ ጥሩ አድርጋ የመታችው ድብ ሲታይ አፉ አካባቢና ቆዳው ሁሉ በቅቤ ርሶ ይታያል ፡፡ ቀበሮም የበላኽው አንተ ነህ ! የበላኽው አንተ ነህ ! በሚል ክሷን ድቡ ላይ ለጠፈች ይላል ተረቱ ፡፡

ይህ ተረት ወደ በደኖ ወሰደኝ ፡፡ ወደ ወተር የተባለ ስፍራም አደረሰኝ ፡፡ ኦነግ የሽግግሩ ምክር ቤት አባል በነበረ ጊዜ ከህወሃት ጋር በተነሳ አምባ ጓሮ ኦነግ ይዞት የመጣውን በብዙ ሺህ የሚገመት ጦር ከጦር ካምፕ ውስጥ ካስገባህ በኋላ ነው ለተፈጠረው አምባ ጓሮ መደራደርና መፍትሄ የሚገኘው በሚል ቀበሮዋ ህወሃት ድቡን ኦነግ አታላ ከጨዋታ ውጭ በማድረግ እንደ ከብት ነጻ ማጎርያ ስፍራ ካምፕ ውስጥ አጎረቻቸው፡፡ ባላትም ትምክህት የሴት ታጋይ ወታደሮቿን ማራኪ በማድረግ ያን ሁሉ የኦነግ ሠራዊት በሴት ተጋዳላይ ወታደሮቿ እየነዳች በቴሌቪዥኗ መሳቂያ አደረገቻቸው ፡፡ የኦነግ መሪዎችንም በነፋሪት/ አውሮፕላን በመጫን ወደ ሚፈልጉበት የስደት አገራት እንደ ቀበሌ ስኳር አከፋፈለቻቸው ፡፡ እነሆ ! አቶ ሌንጮም የኖርዌይ ብርድ አንዘፍዝፎኛል አገሬ ልግባና በድጋሚ ልታገል ብለው አገር ቢገቡም፣ አንድ ቀን አሳድራ ለብ ለብ ያለ ጸሃይ  ከሸራተን አስመትታ እዚያው በረዶ አገር ኖርዌይ መልሳቸዋለች ቀበሮዋ ህወሀት ፡፡

በበደኖና ወተር ክነነብሳቸው ወደ ገደል የተወረወሩትን አማሮች፣ ኦነግ የተባለው አሸባሪ ድርጅት የፈጸመው አረመኔያዊ ድርጊት ነው ስትል ቀበሮዋ ህወሀት ቅቤዋን ስልቅጥ አድርጋ በልታ ስትጨርስ እንዳደረገችው ተንኮል በስንጥር ይዛ የመጣችውን የአማራ ደም ባንጎላጀውና ሲያንኮራፋ በነበረው በድቡ ኦነግ ከንፈርና ሰውነት ላይ በመለቅለቅ ጦሱን ለኦነግ አሸከመችው ፡፡ ወፍራሙና ግዙፉ ኦነግ ሲያንቀላፋ ቀበሮዋ ህወሃት ከጨዋታ ውጭ አደረገችው ፡፡

ቂመኛዋ ህወሃት መንግስት ብትሆንም ቂም ከጨበጠች እስከመጨረሻው ስለማትለቅ በዚህም በዚያም ብላ ቂሟን ትበቀላለች ፡፡ ለቀበሮዋ ህወሃት ፣ ግለሰብ ወይም ተቋም የለም ፡፡ ቂም ከጨበጠች እንኳን እሷ አይደለችም የስጋ ዘመዶቿ ተራ ካድሬዎችና ተደጋፊ ነጋዴዎቿ ጭምር ቂማቸው ከምሱ ሳይደርስ አይለቁም፡እንደ ግለሰብ ቴዲ አፍሮን ማየት ይቻላል ፡፡ ተሰነይ ላይ ከመለሰ ጋር አመቻችቶ ኦነግን ያስገባውን ለታ ሌንጮን ዛሬ ከነድርጅቱ ምን አድርጋ እንደተበቀለችው ማየት ይቻላል ፡፡

የሰሞኑ የቀበሮዋ ህወሃት ድርጊትስ ኦህዴድን የት ያደርሰው ይሆን !

ኦህዴድ ከኦነግ ስህተት ተምሮ ቀበሮዋ ህወሃት ናና ቅቤ እንደብቅ ፣ ናና ጸሃይ እንሙቅ ጨዋታ ውስጥ የሚገባ ድብ ከሆነላት በዜሮ ድምር አጣፍታ ከጨዋታ ውጭ እንደምታደርገው ሳይታለም የተፈታ ነው ፡፡በዚህ ላይ አባ ዱላ ሂሳብ እንዲያስብላት ከዚያው ኦህዴድ ውስጥ ያስቀመጠችው እንስሳ አባ ሰንጋ ስላለላት አትጨነቅም፡፡ ቀበሮዋ ህወሃት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ብሄረሰብ እስረኞች ቃሊቲ ፣ ቂሊንጦ ፣ ዝዋይን ሲያጣብቡ መሳርያ ሆነው ያገለገሏት አሁን ወደ ህዝባቸው ቀልብ እና ወደ  ኢትዮጵዊነት መንፈስ የተለወጡት ቲም ለማዎች እንደሆኑ ታውቃለች፡፡ የአማራ ህዝብ ገዥ መደብ ነው ንድፈ ሃሳቧን የለም የገዢ መደብ እንጂ ገዥ ህዝብ የለም ብሎ ያፈረሱባትን ቲም ለማዎችን ሳትበቀል አትተኛም ፡፡ ከኦሮሚያ ክልል ብሄር የሚለውን መታወቂያ ስላነሱባት እልህ የገባችው ቀበሮ አሁን ወደ ሽንፈቷ አካባቢ ከህዝብ መታረቂያ መንገድ እና እነ ቲም ለማን ለማሰጠላትና ለማስጠቆር ብሎም ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ የፈበረከቻቸውንም ሆነ ያላትን ካርዶች እንደ በደኖው ክስ በነለማ ቲም ላይ ከማውረድ አትመለስም ፡፡

ቀበሮዋ ህወሃት አሁንም እጇ አልዛለም ፡፡ ከእህት ድርጅቶች ውስጥ ባሏት ሆድ አደር አሽከሮቿ ረዳትነት በአባ ዱላ ቀመር ሸቃቢነት በውሽልሽል ባለፈው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የክልል መሪዎችን ፣ የክልል ቃል አቀባዮችን ከጨዋታ ውጭ በማድረግ ኮማንድ ፖሳቱ ብቻ የማይከሰስ ፣ የማይገሰጽ መብት እንዳለው አዋጅ በማወጅ አገሪቱን በፍርሃት ቆፈን አጥምቃለች ፡፡ ያለክልሉ መንግስት እውቅና እኛ ጉልበት አነሰን ብለን ሳንጠይቅ የፌዴራል መንግስቱ ከኛ እውቅና ውጭ ጦር ክልላችን ውስጥ አስግብቶብናል ብሎ በይፋና በድፍረት የተናገረው አቶ ለማ መገርሳ ዛሬ በኮማንድ ፖስቱ ጡንቻ ስር ወድቋል ፡፡ ደፋሩ የኦሮሚያ ቃል አቀባይ አቶ አዲሱ ድምጹ ከጠፋ ሰነባብቷል ፡፡ እንደነገሩ ቢሆንም የብአዴኑ ቃለ አቀባይ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ከህወሃቱ ሰው ከአቶ ዘራይ አስገዶም ጋር ያደረገው ትንቅንቅ ዛሬ የለም ፡፡ ሁሉንም በኮማንድ ፖስቱ አዋጅ ስር ጸጥ አድርገዋቸዋል ፡፡ ኦህዴድ ጥርስ አውጥቶ ቀበሮዋን ህወሃት ሲገዳደር የአምቦው ከንቲባ ጭምር ሳይቀር ነበር ህወሃትን መጫወቻ ያደረጋት ፡፡ አልተኛችም ፡፡ አሰበች ፣ ውስጥ ውስጡን መከረች ፡፡ ኮማንድ ፖስቱን ይዛ ብቅ አለች ፡፡ ቀበሮዋ ህወሃት ፕሮፌሰር መረራ ከዚህ በፊት እንዳሉት ሶስት በትር ብቻ አይደለም አሁን ያላት፡፡ አራት ነው ፡፡ ደህንነቱ ፣ ጦር ሃይሉ ፣ ምርጫ ቦርድ ፣ አሁን ደግሞ ኮማንድ ፖስቱ ፡፡

በኮማንድ ፖስቱ ልቅ ስልጣን መሰረት እነሆ የኦሮሚያ ክልል የፖሊስ አዛዦች እየተለቀሙ ነው ፡፡ ኮማንደሮቹ ሲታፈኑ ትእዛዝ ወደ ታች የሚያወርድ አካል ክንፉን በመመታቱ ወታደሮቹ  እንደ ባቢሎኑ ፎቅ ቋንቋው ስለሚደበላለቅባቸው ትጥቃቸውን ይፈታሉ ፡፡ ትጥቅ እየፈቱም ነው ፡፡ ቂመኛዋ ህወሃት የኢሊአባቦራን የፖሊስ አዛዥ ስትይዝ ቂም ደርባ ነው ፡፡ በኢሊአባቦራ የቀበሮዋ ህወሃት የስጋ ዘመዶች የኦነግን ባንዲራ ሲያከፋፍሉ እጅ ከፍንጅ በመያዛቸው እዚያው እስር ቤት ይህ የፖሊስ አዛዥ ስላሰራቸው ነው ቂመኛዋ ቀበሮዋ ህወሃት ቂም በመደረብ ይህንንም ሰው ያሰረችው ፡፡ በዚህ ከቀጠለ በግልጽ እንደሚታየው በግልጽ አልተነገረም እንጂ በነ ቲም ለማ ላይ በኮማንድ ፖስቱ በኩል ኩዴታ እየተሰራላቸው ነው ፡፡ እንደ ድቡ ተንጋሎ ጸሃይ እየሞቁ  በቀበሮዋ መሸውድ ? ወይስ በፍጥነት ኦህዴድን ከኢሃዴግ ማስወጣት ? በጊዜ የምናየው ትንቅንቅ ነው፡፡

Filed in: Amharic