>

በብአዴን የተከዳው የኦሕዴድ አሳዛኝ ፍጻሜ! አስቸኳይ ጥሪ ለኦነግና ኦነጋውያን!!! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

ኦሕዴድና ብአዴን በወያኔ ላይ ፊታቸውን አዞሩ ተብሎ ሁለቱ መዋሸማቸውን ይፋ ካደረጉበት የባሕርዳሩ ጉባኤያቸው ጀምሮ በጻፍኳቸው ጽሑፎች ብአዴንና ኦሕዴድ ያለ ወያኔ ፈቃድ እንዲያ ዓይነቱን ጉባኤ ሊያደርጉ እንደማይችሉ፣ ወያኔ ኦሕዴድና ብአዴን ፊታቸውን ያዞሩበት አስመስሎ በማቅረብ ሕዝቡ የነሱን እንቅስቃሴ ተስፋ አድርጎ እንዲዘናጋ ለማድረግ….. ሆን ብሎ የፈጠረው ትወና እንደሆነ ገልጨ ነበረ፡፡
በወቅቱ የኦሕዴድንና የብአዴንን እንቅስቃሴ እንድጠራጠር አድርጎኝ የነበረው  “የወያኔ ድራማ ጣራ የነካበት የውጥረት ሰዓት!” በሚለው ጽሑፌ ላይ እንደገለጽኩት “… ኦሕዴድና ብአዴን የሚባለውን ያህል በሕዝብ ተወካዮች አባሎቻቸውና
በካድሬዎቻቸው (በወስዋሾቻቸው) ደረጃ የዓላማና የአቋም አንድነት ያላቸው ከሆነ
ታዲያ ኢሕአዴግ ላይ ለሚያነሡት የጥገናዊ ለውጥ ጥያቄያቸው
ያለ ጥርጥር በወያኔ ሊያስበላቸው እንደሚችልና ከዚህም የተነሣ ይህ እያደረጉት ነው የሚባለው እንቅስቃሴ እውነተኛ ቢሆን ላለመበላትና የሕዝባቸውንና የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ከለላ፣ ጥበቃና ጥብቅና ለማግኘት ሲሉ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን በመጠቀም ለአገዛዙ ያላቸውን መተማመኛ ድምፅ በመንፈግ ወይም በማንሣት ሕወሓትን ሽባ አድርገው የኢሕአዴግን ሥልጣን መቆጣጠር፣ ሥልጣንን ከወያኔ መረከብ የሚያስችላቸውንና ስር ነቀል ለውጥ ሊመጣ የሚችልበትን እርምጃ መውሰድ ሲኖርባቸው ይሄንን መንገድ ያልመረጡት ለምን ይመስላቹሀል???
ኦሕዴድና ብአዴን ወያኔን ጠየቁ የሚባለውን ጥገናዊ ለውጥ
መጠየቅ ለእያንዳንዳቸው ለኦሕዴድና ብአዴን አመራሮች ምን ያህል አደገኛና በፈንጅ ላይ የመራመድ ያህል መሆኑን ያጡታል ብሎ የሚገምት ሰው ካለ የመጨረሻ ቂል ነው፡፡ ስለዚህም እንቅስቃሴያቸው እውነተኛ ቢሆን ኖሮ ጥገናዊ ለውጥ መጠየቅን ፈጽሞ አይሞክሩትም ነበረ፡፡ ሰዎቹ
የእውነት የሚወራውን ያህል የቆረጡ ከሆኑ ሊያደርጉ የሚችሉት ለወያኔ ጊዜ ሰጥቶ እነሱን ቀረጣጥፎ እንዲበላቸው
የሚያስችለውን ጥገናዊ ለውጥ ሳይሆን ሊያደርጉ የሚችሉት ሕጋዊ መብታቸውን ተጠቅመው ከወያኔ የአጸፋ እርምጃ ለመዳን ለመጠበቅ ዕድል የሚሰጣቸውንና ስር ነቀል ለውጥ ሊመጣ የሚችልበትን ስር ነቀል እርምጃ ነበር ሊወስዱ የሚችሉት!” የሚል ነበረ፡፡
ያልኩትም አልቀረ ለወያኔ ጊዜ የሰጠ እንቅስቃሴያቸው ጉድ ሠርቷቸዋል፡፡ ኦሕዶድ ከብአዴን ጋራ ሊወስደው ለፈለገው እርምጃ በወቅቱ በብአዴን ላይ እምነት መጣል የሚያስችለውን ቁርጠኝነት ስለገኘ ከነበረ ወዳጅነቱንና አጋርነቱን የጀመረው በዚያውኑ ወቅት አፋጣኝ ውሳኔ ወስነው ከኢሕአዴግ ግምባር መለየታቸውን መውጣታቸውን በማወጅ እርምጃ ወስደው ቢሆን ኖሮ የሕዝብንና የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ከላላ በማግኘት ከወያኔ የበቀል እርምጃ መጠበቅ በቻሉ፣ ብአዴንም ኦሕዴድን ባልከዳ ነበረ፡፡
ጊዜ በመስጠታቸው ግን ብአዴን በጌታው ቁጣ ተለውጦ የወያኔ ሰላይ ሆኖ ኦሕዴድን ሲሰልል ቆይቶ ወሳኝ ሰዓት ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማጽደቅ በተጠራው ስብሰባ ላይ እንደታየው ኦሕዴድን ሊከዳውና አሳልፎ ሊሰጠው ችሏል፡፡ ብአዴን እንኳንና ኦሕዴድን እወክለዋለሁ የሚለውን የአማራን ሕዝብ እንኳ የከዳ ለአንድ ቀንም እንኳ ቢሆን ለአማራ ሕዝብ ቆሞ የማያውቅ የወያኔ አህዮች መንጋ በመሆኑ ኦሕዴድ በዚህ በብአዴን ክህደት ሊገረም ሊያዝን ሊከፋ አይገባም፡፡ ኦሕዴድ የተከዳው በብአዴን ብቻ አይደለም ከፊሉ የራሱ የተወካዮች ምክርቤት አባላቶቹም ከድተውታል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ኦሕዴድ ተቀረጣጥፎ ወደ ወያኔ ሆድ ውስጥ አልገባም እንጅ በወያኔ አፍ ግን ተጎርሷል፡፡ ከወያኔ አፍ አስተፍቶ ተቀረጣጥፎ ከመዋጥ የሚያስጥለው አንዳች ተአምር ይፈልጋል፡፡
አሁን መፍረሱ የታየው የኦሕዴድንና የብአዴንን ወዳጅነትና አጋርነት ከአማራ ሕዝብ ጥቅም አኳያ ያየነው እንደሆነ ቀድሞውንም ቢሆን ይሄ የኦሕዴድና የብአዴን ወዳጅነት ተሳክቶ ቢሆን ኖሮ አጋርነቱ ወዳጅነቱ ተጠቃሚ የሚያደርገው የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅም እንጅ የአማራን ሕዝብ ጥቅም ማስጠበቅ የሚችል አጋርነት አይሆንም ነበረ፡፡
የዚህም ምክንያቱ 1ኛ. ኦሕዴድ ከጀርባው ኦነግንና የእነጃዋርን ቡድን አዝሎ የነበረ በመሆኑ ሲሆን፡፡ 2ኛ. ብአዴን ከአንድም የአማራ ሕዝብ የነጻነት ትግል ድርጅት ጋር ምንም ዓይነት የስውርም ይሁን የምን ግንኙነት የሌለው ከመሆኑም በላይ ከአማራ ሕዝብ ጋር የሆድና ጀርባ የሆነ ግንኙነት ያለው የጥፋት ኃይል በመሆኑ፣ በተፈጥሮው ፀረ አማራ አቋምና አስተሳሰብ ያለው በመሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም ተጠቃሚ ይሆኑ የነበሩት ብልጡ ኦሕዴድ፣ ያዘላቸው እነ ኦነግና እነ ጃዋር ናቸው ተጠቃሚ ይሆኑ የነበሩት፡፡
ኦሕዴድም ሆነ ኦነግና የነጃዋር ቡድን አጉል ብልጥ የሆኑ መስሏቸው ሊያቋርጥ የማይችል አቋራጭ መንገድ መረጡ እንጅ ከሁለት ዓመት በፊት  “ለኦነግና ኦነጋዊያን! የወያኔን ዓላማ አንግቦ ወያኔን ለመውጋት የእንተባበር ጥሪ አይሠራም!!!” በሚለው ጽሑፌ የሰጠኋቸውን ምክር ሰምተው ቢሆን ኖሮ ነገሩ እስከአሁን ተቋጭቶ ሀገራችንንና ሕዝባችንንም ነጻ ማውጣት ችለን ነበረ፡፡
ያኔ ብያቸው የነበረው እነ ኦነግና እነ ጃዋር የፈለገውን ያህል የኦሮሞን ሕዝብ በዐመፅ ማነቃነቅ ቢችሉ እንኳ የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብም በተለይም የአማራ ሕዝብም በዐመፁ ካልተባበረ በስተቀር የኦሮሞን ሕዝብ ከማስጨረስ ውጭ ምንም ነገር ሊለውጡ እንደማይችሉ፣ የአማራን ሕዝብ በዐመፁ እንዲቀላቀል ለማድረግ ደግሞ ኦነግና ኦሕዴድ ከወያኔ ጋር በመተባበር በአማራ ሕዝብ ላይ ለፈጸሙት ኢሰብአዊ ግፍ ይቅርታ ጠይቀው ያለበትን ጥርጣሬና ሥጋት ማንሣት ማስወገድ የግድ አስፈላጊ መሆኑን፣ በኦሮሚያ ለኦሮሞ ቅኝት ያበደ በተፈጥሮው ኢዲሞክራሲያዊና ኢሰብአዊ የሆነውን የጠባብ ዘውገኝነት ፖለቲካን ጥለው የሠለጠነ የዕኩል ዜግነትንና ሰብአዊ መብትን ያከበረ መሠረት ያደረገ ሀገር አቀፍ ፖለቲካዊ አቋም አስተሳሰብ መያዛቸው የግድ አስፈላጊ መሆኑን፤ ይሄንን ማድረግ ከተቻለ ነገሩ ቀላል መሆኑን በጥልቀት በመተንተን አበክሬ አሳስቤ ነበረ፡፡
እነ ኦሕዴድ/ኦነግ እነ ጃዋር ግን እኔ እንዴት እንደሚያስቡና ምን እንደሚፈልጉ አላውቅም የአማራ ሕዝብ በእነሱ ላይ ያለበትን ጥርጣሬና ሥጋት ከማስወገድና በአንድነት እንዲሰለፍ እንዲታገል ከማድረግ ይልቅ ሾላ በድፍኑ ዓይነት መንገድ በመምረጣቸው ጭራሽ እንዲያውም እስከአሁንም ድረስ በተለያየ መንገድ እያንፀባረቁት እንደምናያቸው ጥርጣሬውን የሚጨምሩ የሚያብሱ ድርጊቶችን ማድረግ በመቀጠላቸው የአማራ ሕዝብ እንዲሁም የአዲስ አበባ ሕዝብ ዐመፁን በቁርጠኝነትና በሙሉ ልብ እንዲቀላቀል ማድረግ ሳይቻል ቀርቷል፡፡
እነ ኦነግ ይሄንን እርምጃ ቢወስዱ ኖሮ የአማራ ሕዝብ ዐመፁን ለመቀላቀልና ወያኔን ለማስወገድ ዝግጁ መሆኑን በተደጋጋሚ ዐመፅ በማድረግ ፍላጎቱን፣ ቁርጠኝነቱንና አጋርነቱን አሳይቶ ነበረ፡፡ እነ ኦሕዴድ/ኦነግ የቤት ሥራቸውን አጠናቀው ቢሆን ብአዴንን መለማመጥ ሳያስፈልጋቸው ነገሩን በአጭሩ መቋጨት ይቻል ነበረ፡፡
እነ ኦነግ ግን ለዚህ የአማራ ሕዝብ ፍላጎትና አጋርነት የሰጡት ምላሽ አዎንታዊና አስተማማኝ መሆን አልቻለም፡፡ በመሆኑም ይሄው እንደምታዩት ምንም ነገር መለወጥ በማይችል ዐመፅ ሕዝብ በከንቱ እያስጨረሱ ይገኛሉ፡፡ ማን ይምከራቸው ይሆን??? እንዴትስ ተደርጎ ቢነገራቸው ይሆን የሚገባቸው??? ኧረ ተው ተው እሽ በሉና የሚጠበቅባቹህን የተጠየቃቹህትን ወሳኝ እርምጃ በመውሰድ በአንድነት አብረን ተሰልፈን ወያኔን ለመቅበር አስችሉን??? ተው ተው ብልጥ ሁኑ አስተውሉ??? አርቃቹህ አስቡ??? ዓላማቹህ ሌላ ሆኖ ካልሆነ በስተቀር ለሀገርና ለሕዝቧ ከሆነ ሐሳባቹህ እንዴት ይሄንን ነገር ማድረግ ይሳናቹሀል??? እያልነው ያለነው ነገር እንዴት አይገባቹህም??? ስታስቡት ከፍተኛ ሥጋትና ጥርጣሬ እያለበት ማን እንዴትስ ብሎ ነው አብሯቹህ ሊሰለፍ የሚችለው???
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው 
Filed in: Amharic