>

እስክንድር ነጋ - ስለ እስር ቆይታው፣ ፕሬስና ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ

• አዲሱ ጠ/ ሚኒስትር የተረጋጋች ሀገር የመፍጠር ኃላፊነት አለበት

• ህዝቡ ከኢህአዴግም ሆነ ከፖለቲካ ድርጅቶች ቀድሞ ሄዷል

• ኢትዮጵያዊ ዴክለርክ ወይም ኢትዮጵያዊ ጎርባቾቭ ያስፈልገናል

• አርአያ ልንሆናቸው የሚገቡ ሃገሮች፣ለኛ አርአያ መሆን ችለዋል

ከ6 ዓመት ተኩል የእስር ጊዜ በኋላ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት በቅርቡ የተፈታው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፤ስለ እስር ቤት ቆይታው፣ስለ አገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ፣ስለ ቀጣዩ ጠ/ሚኒስትር ሚና እንዲሁም ስለ ቀጣይ ዕቅዱ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አነጋግሮታል፡፡ እነሆ፡

ከእስር ቤት ውጪ ያለውን የሀገሪቱን ሁኔታ እንዴት አገኘኸው?

የህዝቡ የለውጥ ፍላጎት ከጫፍ ደርሷል፡፡ ገና የስርአት ለውጥ ባናይም የአስተሳሰብ ለውጥ ግን በሰፊው አለ፡፡ የፍርሃቱ ድባብ እየተገፈፈ ነው። ህዝቡ ከፍርሃት እየወጣ ነው፡፡ ይሄን ለማየት በመብቃቴ በጣም እድለኛ ነኝ፡፡ እኛ አምባገነናዊ ስርአቱን ስንታገል፣ በዋናነት አብረን ስንታገል የነበረው ፍርሃቱን ነው፡፡

እንደ ጋዜጠኛነትህ፣ የነጻ ፕሬስ መቀጨጭን በተመለከተ ምን ትላለህ?

ያው ከስርአቱ ጋር የተያያዘ ችግር ነው፡፡ ወደ ነፃነቱና ዲሞክራሲው የምንሄድ ከሆነ፣ የፕሬሱም ነፃነት በዚያው ደረጃ ይጎለብታል፡፡ ወደ አፈና የምንመለስ ከሆነ ደግሞ በመዳፈን ሂደት ውስጥ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ በዚህ መሃል ብቅ ያለው አንዱ መልካም አጋጣሚ፣ የማህበራዊ ሚዲያው ነው፡፡ ይህ የማህበራዊ ሚዲያ መስፋፋት እያንዳንዱ ዜጋ መረጃ አቀባይና ተቀባይ በመሆን፣ “ሲትዝን ጆርናሊዝም” ለምንለው ዘርፍ አስተዋፅኦ ያደርጋል። ስለዚህ ህጋዊ ፕሬሱን ሙሉ ለሙሉ መዝጋት ቢቻል እንኳ “ሲትዝን ጆርናሊዝም”ን መዝጋት አይቻልም። የትግልና የነፃነት መንፈሱ እስካለ ድረስ ደግሞ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር አይኖርም፡፡ አሁን ያለውን መሠረት ማስፋት ብቻ ነው የሚፈለገው፡፡

ጋዜጠኝነትን ብቻ ለመተግበር ምቹ ሁኔታ ስለሌለ በዲሞክራሲና በመብት ንቅናቄ በመሳተፍ ትግሌን እቀጥላለሁ፤ ብለሃል፡፡ ምን ማለትህ ነው? እስቲ አብራራልን?

በዲሞክራሲና በመብት ጉዳዮች ላይ ትግል የሚያስፈልገው፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ስላልተከበረ ነው፡፡ ሌሎች መሰረታዊ መብቶችም እንዲረጋገጡ መታገል ያስፈልጋል፡፡ ወደ ጋዜጠኝነት ስራ ስንገባ፣ ኢህአዴግ የተቀበለን መጀመሪያ በግሰፃ ነው፡፡ ነፍጠኞች ናቸው፤ ጠባቦች ናቸው፣ የድሮ ስርአት ናፋቂዎች ናቸው በሚል ነው። ይሄ ተግሳፅና ዘለፋ አልሰራ ሲለው ወደ ጥፊ ነው የሄደው፣ ጥፊው ደግሞ ወደ ካልቾ፣ ካልቾው ወደ ድብደባ አድጎ፣ በኋላም ድብደባው ገልብጦ ወደ መግረፍ ነው የሄደው፡፡ ገልብጦ መግረፉ አልሰራ ሲል ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ፕሬሱን ወደ መዝጋት ነው የተገባው። የኢትዮጵያ ፕሬስ የተወለደው በዚህ ሂደት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፕሬስ የትግል ፕሬስ ነው፡፡ ሙያውን በሰከነ መንገድ ለመተግበር ጊዜ አላገኘም። የኢትዮጵያ ፕሬስን፣ ለመብቱና ለነፃነቱ ካደረገው ትግል ነጥሎ ማየት አይቻልም፡፡
ይሄ አስቸጋሪ ሁኔታ ባይኖርና ዲሞክራሲያዊ ስርአት ቢኖር ኖሮ፣ ከየትኛውም የአፍሪካ ሃገር በተሻለ እውነተኛ ፕሬስ መገንባት እንደምንችል ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ዳገት ሆኖ የቆየው ትግሉ ነው፡፡ ይሄ ትግል ደግሞ በዓለም ደረጃ የተወደሰ ትግል ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ያደረጉት ትግል ለዓለም ምሳሌ ነው፡፡ በጋዜጠኞች የተደረገን የዓለም ተሞክሮ ብንመለከት ወይም በዚህ ዙሪያ የሚሰሩ ተቋማትን ብንጠይቅ፣ እንደ ሞዴል የሚያነሱት የኢትዮጵያን ጋዜጠኞች ትግል ነው፡፡ ልክ እንደ ኢትዮጵያ ተማሪዎች ትግል ሁሉ ለአፍሪካውያንም ሞዴል ነው፡፡ የተማሪዎች ትግል ከሁሉም የአፍሪካ ሃገራት በመጨረሻ ላይ የመጣ ቢሆንም የጎላ ታሪክ የፃፈ ነበር፡፡ የኛ ፕሬስም አፍሪካ ውስጥ ከተመሰረቱ ፕሬሶች በመጨረሻ የመጣ ነው፡፡ ግን የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ትግል፣ ለአፍሪካም ለዓለምም ሞዴል መሆን የቻለ ነው፡፡ ሁኔታዎች ቢመቻቹ ደግሞ ለአፍሪካም ለዓለምም ሞዴል መሆን የሚችል ነፃ ፕሬስ መገንባት እንችል ነበር፡፡ የክህሎት ችግር የለብንም፡፡ የኛ ችግራችን የዲሞክራሲ ነው፡፡ ይሄን ዳገት ለማስተካከል የከፈልነውና የሚከፈለው መስዋዕትነት ግን አርአያ ሆኖ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡
ለኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች፣ እንደ ምዕራቡ ዓለም አይነት ሚዲያ መገንባት፣ በጣም ቀላል ነበር፡፡ ነገር ግን የጎደለን ዲሞክራሲ ነው፡፡ አሁን ለዚህ እውን መሆን ትግል ላይ ነን፡፡ መጨረሻ ላይ የሚመጣው ውጤት ግን የበለጠ አርአያ መሆን እንደሚችል ተስፋ አለኝ፡፡ ለኛ ወሳኝ የሚዲያ ስርአት መገንባት ቀላል ነው፤ ዋናው የዲሞክራሲው መምጣት ነው፡፡ ሙያዊ ጋዜጠኝነትን መገንባት፣ ለኛ ባለሙያዎች ቀላል ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካና ኬንያ አርአያ መሆን የሚችሉ ፕሬሶች መገንባት ከተቻለ፣ ለኛ ሀገር የበለጠ ቀላል ነው፡፡

በህዝብ ተቃውሞና አመጽ መነሻነት ከተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ፣ መውጪያው መንገድ ምንድን ነው ትላለህ?

እስካሁን ድረስ ህዝቡ የፖለቲካ እስረኞች መፈታት ጉዳይን አንዱ የመታገያ አጀንዳው አድርጎ፣ ትግሉን እዚህ አድርሶታል፡፡ በቀጣይ መሆን ያለበት፣ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች ያሳተፈ ድርድር ማካሄድ ነው፡፡ ይሄ መፍትሄ ለኢትዮጵያ ብቻ የተፈጠረ አይደለም፡፡ ሌሎች በተመሳሳይ ቀውስ ውስጥ የነበሩ ኃይሎች ሞክረውት መፍትሄ አግኝተውበታል፡፡ ለዚህ ዓይነተኛ አርአያ ደቡብ አፍሪካ ነች፡፡ በደቡብ አፍሪካ በአፍሪካን ናሽናል ፓርቲና በአፓርታይድ ስርአቱን ባቆመው መንግስት መካከል የነበረው ልዩነት፣ በጣም ሰፊ እንደነበር እናውቃለን፡፡ ያንን ሰፊ ልዩነት የፈቱት ሁሉንም ፓርቲዎች ባሳተፈ ድርድር ነው፡፡ ያንን ውስብስብና ሰፊ ችግር በዚያ መንገድ መፍታት ከተቻለ፣ የኛ ችግር ደግሞ ከዚያ ያነሰ በመሆኑ ለመፍትሄው ይቀላል፡፡ የዲሞክራሲ ስርአት ችግር በነበረባቸው ሃገሮች በሙሉ፣ ይሄ የመፍትሄ መንገድ ተሞክሮ ውጤት አምጥቷል፡፡ ከዚህ የመፍትሄ አማራጭ ውጪ፣ በራሱ በኢህአዴግ ውስጥ በሚደረግ የስልጣን ሽግሽግ መፍትሄ ማበጀት አይቻልም፡፡

አሁንም የህዝብ ጥያቄ አልቆመም፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ይገለጻል?

ኢህአዴጎች በአሁኑ ወቅት በአንድነት እየተጓዙ አይደለም፡፡ ሁሉንም የፖለቲካ ደርጅቶች ያሳተፈ የፖለቲካ መፍትሄ ያስፈልጋል የሚለው፣ በኦህዴድ ደረጃ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባውን ሲያጠናቅቅ፤ ይሄን ሁኔታ እንደሚቀበል መግለጫ አውጥቷል፡፡ ይሄ አቋም ግን በኢህአዴግ ደረጃ እስካሁን ተቀባይነት አላገኘም። ይሄ የሚያሳየን ደግሞ በኢህአዴግ ውስጥ ይሄን አማራጭ የማይቀበል ኃይል እንዳለ ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተጠቅሞ፣ በኃይል የኢህአዴግን የበላይነት ለማስጠበቅ የሚደረግ ጥረት አለ፡፡ ይሄ የሚያመለክተን፣ በራሱ በኢህአዴግ ውስጥ ማለቅ ያለበት ትግል መኖሩን ነው፡፡ ይሄ ወዴት አቅጣጫ እንደሚሄድ አይታወቅም፡፡ በእርግጥ ለለውጥ የተዘጋጀ ኃይለ አለ፡፡ ህዝብ ከከፈለው መስዋዕትነት በተጨማሪ የዚህ የለውጥ ኃይል የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። ህዝብ ግን ከፍርሃት ነፃ ወጥቷል፤ ከዚህ በኋላ በኃይል ሊገዛ አይችልም፡፡ ምናልባት ለጊዜው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዝም ማሰኘት ይቻል ይሆናል። ይሄ ግን ዘላቂ አይደለም፡፡ ህዝቡ ከኢህአዴግም ከፖለቲካ ድርጅቶችም ቀድሞ ሄዷል፡፡ ይሄን ህዝብ ከዚህ በኋላ በኃይል እንገዛዋለን ማለት፣ አደገኛ ውጤት ነው የሚያመጣው፡፡ ለሀገሪቱም አደጋ ነው። ህዝቡ የአስተሳሰብ አብዮት ውስጥ ገብቷል። ህዝቡ የማይቻል ነገር አይደለም እየጠየቀ ያለው። እየጠየቀ ያለው ዲሞክራሲ፣ በአፍሪካ ውስጥም ታይቷል። በማላዊ ውስጥ በተግባር ዲሞክራሲን ማየት ይቻላል። በጣም ውስብስብ ችግር ባለበት በደቡብ አፍሪካ ውስጥ መዋል የቻለን ዲሞክራሲ ነው፣ ህዝቡ እየጠየቀ ያለው፡፡ የማይቻል ነገር ሳይሆን የሚቻል ነገር ነው እየተመኘን ያለነው፡፡ እኛ አርአያ ልንሆናቸው የሚገቡ ሃገሮች፣ ዛሬ ለኛ አርአያ መሆን ችለዋል፡፡ ቢያንስ እነሱ ላይ እንድንደርስ ነው፤ የህዝቡ ጥያቄ፡፡

ይሄን ፖለቲካዊ መሻሻልና ለውጥ ማን ነው የሚያመጣው? ገዥው ፓርቲ? ህዝቡ ወይስ ሌሎች ኃይሎች?

የለውጡ ባለቤት ህዝቡ ራሱ ነው። የሚገለጠው ግን በፖለቲካ ድርጀቶች ነው። ጥያቄው በየትኞቹ ይገለጥ ከሆነ፣ ኢህአዴግን ጨምሮ በሁሉም መከወን አለበት፡፡ የሚመጣው አብዮት፣ ወይም ዲሞክራሲያዊ ለውጥ፣ ኢህአዴግም ቦታ የሚያገኝበት መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ፡- የደቡብ አፍሪካ የዲሞክራሲ አብዮት፣ ለአፓርታይድ አራማጁ፣ ናሽናል ፓርቲ ቦታ ነበረው፡፡ ናሽናል ፓርቲ፣ የአፓርታይድ ስርአትን ለ48 ዓመታት፣ በደቡብ አፍሪካ የተገበረ ነው፡፡ በኋላ ግን የደቡብ አፍሪካ ዲሞክራሲ የተገለፀው፣ እሱን ጨምሮ በሁሉም ፓርቲዎች ነው፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የህብረተሰብ የፖለቲካ አስተሳሰብ መገለጫዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ሁሉንም የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያሳትፍ የሽግግር ቀመር ስናወጣ፣ በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ አስተሳሰቦች በሙሉ የሚወከሉበትን ሁኔታ ፈጥረናል ማለት ነው፡፡ ለውጡ መምጣት ያለበት በአንድ ወይም ሁለት ድርጅቶች ሳይሆን በሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች በኩል ነው፡፡

በዚህ ሂደት የፓርቲዎች የተለያየ ርዕዮተ ዓለም እንዴት ሊጣጣም ይችላል?

በዓለም ላይ ያለው የዲሞክራሲ ፍልስፍና የተለያየ አይደለም፡፡ አንድ ነው፡፡ እርግጥ አብዮታዊ ዲሞክራሲ አለ የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ግን በሂደት እነዚህ ሁሉ ተቀባይነት እንደሌላቸው በታሪክ ታይቷል፡፡ ዲሞክራሲ አንድ አይነት ነው፡፡ ወጥ ነው። ለምሳሌ በአሜሪካና በጃፓን መካከል የማህበራዊ መሰረት፣ የባህል ልዩነት አለ። የስልጣኔ መስመራቸው ይለያያል፡፡ ነገር ግን ጃፓን ውስጥ እና በአሜሪካ የሚሰራው ዲሞክራሲ አንድ አይነት ነው፡፡ እርግጥ ነው ሁለቱ ሀገሮች በማህበራዊ መሰረታቸው የተለያዩ ናቸው፡፡ ህንድንም ብንመለከት፣ ማህበራዊ መሰረቱ፣ የሂንዱ እምነትና ባህል ነው፡፡ ነገር ግን ህንድ ውስጥ እና አሜሪካ ያለው ዲሞክራሲ አንድ አይነት ነው። ስለዚህ የሚሰራውን ዲሞክራሲ እናውቀዋለን፡፡ ህንድ ውስጥ፣ አሜሪካ ውስጥም ሆነ ማላዊ ውስጥ የሰራው ዲሞክራሲ፣ ሊበራል ነው፡፡ ይሄ ማለት የፖለቲካ ስርአቱ አይደለም። የፖለቲካ ፕሮግራም አይደለም። በዓለም ላይ የምናውቀው ሊበራል ዲሞክራሲ ነው፤ እሱን ነው ማምጣት ያለብን፡፡ የህዝብ ዲሞክራሲ (Peoples’ democracy) እና አብዮዊ ዲሞክራሲ የሚባሉ አሉ፤ ግን አልሰሩም፡፡ እነዚህ አስተሳሰቦች የነበሩባቸው ሃገሮች፣ አምባገነናዊ ስርአት የነገሰባቸው ነበሩ። ኢህአዴግም በዚህ መስመር ነው የተጓዘው፡፡ ከዚህ መስመር ወጥተን፣ ወደ ብቸኛው የዲሞክራሲ መስመር ውስጥ መግባት አለብን። ይሄ የኒውክለር ሳይንስ አይደለም፡፡ በቀላሉ ብዙ የአፍሪካ ሃገሮች በሄዱበት መንገድ መሄድ ነው። እነ ቦትስዋና፣ ማላዊ፣ ናሚቢያ፣ ደቡብ አፍሪካ በሄዱበት መንገድ መሄድ ነው፡፡ ይሄ ትልቅ ምስጢር አይደለም፡፡ በቀላሉ መሆን፣ መፈፀም የሚችል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሞዴል መሆን የሚችል ዲሞክራሲ የመገንባት አቅሙ አላት፡፡ ለምን ከተባለ፣ ከሌሎች የአፍሪካ ሃገሮች የተሻለ የታሪክ መሰረት አለን፡፡ ትምክህት አይሁንብኝ እንጂ የተሻለ የባህል መሰረትም አለን ብዬ አምናለሁ፡፡ የረጅም ጊዜ የመንግስትነት ታሪክ አለን፡፡ በአንፃሩ ዛሬ ዲሞክራሲን የገነቡ የአፍሪካ ሃገሮች፣ ከቅኝ ግዛት በኋላ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ሀገራዊ ባህሎችና እሴቶች ተዛብቶባቸዋል። የኛ ግን አሁንም አለ። ይሄ ጥሩ መሰረት ይሆናል፡፡ የፖለቲካ ስርአት የሚገነባው በባህልና በታሪከ መሰረት ላይ ነው። እንደ አፍሪካ ህብረት መቀመጫነታችን ደግሞ የአፍሪካ የዲሞክራሲ ሞዴል የመሆን ኃላፊነት አለብን፡፡ የአፍሪካ ገፅታ የሚገነባው በኛ በኩል ነው ካልን፣ ለኛ ብቻ ሳይሆን ለአህጉሪቱም በኃላፊነት ማሰብ አለብን ማለት ነው፡፡ አፍሪካ በዓለም ላይ ያላትን ገፅታ ለመለወጥ፣ የኛ ድርሻ እጅግ የሰፋ ነው፡፡

ከቀጣዩ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ምን ዓይነት አመራር ይጠበቃል?

ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚጠበቀው ትልቁ ነገር፣ ኦህዴድ የተቀበለውን እውነት በኢህአዴግ ደረጃ ተቀባይነት እንዲያገኝ ማድረግ ነው፡፡ ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ለመስራት፣ ለመደራደር ፍቃደኛ ነን ማለት፣ ለዚህም ሁኔታውን ማመቻቸት ነው፡፡ በመጀመሪያ የኦህዴድን አቋም የኢህአዴግ አቋም ማድረግ፣ ቀጥሎ የመንግስቱ አቋም ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሄን ማድረግ ካልቻለ ሀገሪቱን ማረጋጋት አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያን ማረጋጋት ካልተቻለ ደግሞ ልማቱን ቀጣይ ማድረግ አይቻልም፡፡ በመጀመሪያ የተረጋጋች ሀገር የመፍጠር ኃላፊነት ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለበት፡፡ ሌላው በሙሉ በሁለተኛ ደረጃ የሚመጣ ነው፡፡ ህዝብም ሆነ የፖለቲካ ተከታታዮች በሙሉ የሚጠብቁት ይሄንን ነው፡፡ የዓለማቀፍ ዲፕሎማቶች በ27 ዓመት ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሁሉም ፓርቲዎች ጋር ተደራደሩ ብለዋቸዋል፡፡ ይሄ ራሱን የቻለ አብዮት ነው። ከዚህ ቀደም ለጋሽ ሀገራቱ እንዲህ ያለውን አቋም ወስደው አያውቁም፡፡ በፊት “በህገ መንግስቱ ማዕቀፍ ውስጥ ስሩ” ነበር የሚሉት፡፡ በውጭ ያሉትን የፖለቲካ ኃይሎችንም “ህገ መንግስቱን ተቀበሉ” እያሉ ግፊት ያደርጉባቸው ነበር፡፡ አሁን ግን ያንን ትተው፣ ሁሉንም ያሳተፈ ድርድር ያስፈልጋል እያሉ ነው፡፡ ኢህአዴግን “ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተደራደር” እያሉ ግፊት እያደረጉበት ነው፡፡ ስለዚህ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚጠበቀው፣ ሀገሪቱን በዚህ ሂደት ውስጥ ማስገባት ነው፡፡ ዝም ብሎ የስልጣን ሽግሽግ ዋጋ የለውም፡፡ በደቡብ አፍሪካ ሽብርተኛ በተባለው ኤኤንሲ ፓርቲና በዴክለርክ መንግስት መካከል ድርድር ተደርጎ ነው፣ የሃገሪቱ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ የተጀመረው። አሁንም ኢትዮጵያዊ ዴክለርክ ወይም ኢትዮጵያዊ ጎርባቾቭ ያስፈልገናል፡፡ ጎርባቾቭ፤ የኮሚኒስት ፓርቲውን ከህዝቡ የለውጥ ፍላጎት ጋር አስማምቶ ነው ያራመደው፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ እንደዚህ አይነት መሪ እንዲሆን ነው የሚያስፈልገው፡፡

እስቲ አሁን ደግሞ ስለ ማረሚያ ቤት ቆይታህ ንገረን — በማረሚያ ቤት ውስጥ ምን ታዘብክ?

በእርግጥ እስር ቤቶች የሚለወጡት ስርአቱ ሲስተካከል ነው፡፡ እስር ቤቶችን ያበላሸው የኃላፊዎች ክፋት አይደለም፡፡ አሰራሩ ነው፡፡ በእስር ቤት የሚታየው የስርአቱ ባህሪ ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲኖረን፣ ሰብአዊ መብት የሚከበርባቸው እስር ቤቶችን እናያለን፡፡ አሁን በእስር ቤቶቻችን ሰብአዊ መብቶች የማይጠበቁት፣ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ስለሌለን ነው፡፡ እኔ ስታሰር ለ8ኛ ጊዜ ነው። በመጀመሪያ እስሮቼ ወቅት ከዘለፋ ጀምሮ ገልብጦ እስከ መገረፍ፣ አስከፊ ጥቃት ደርሶብኛል። በነገራችን ላይ አሁን ስታሰር ምንም አይነት ድብደባም ሆነ ዘለፋ አልተፈፀመብኝም፡፡ ከዚያ በፊት በነበሩት ግን ተገርፌያለሁ፡፡ ይሄን ስል፣ አሁን ተሻሽሏል እያልኩ አይደለም፡፡
በእስር ቤት ቆይታዬ መፅሐፍ ቅዱስ እንዲገባልኝ ጠይቄ ተከልክያለሁ፡፡ ወረቀት፣ እስክሪብቶ፣ ተከልክያለሁ፡፡ መፅሐፍቶቼ በሙሉ ተሰብስበው ተወስደዋል፡፡ እኔ በእርጅና ዘመኔም ቢሆን መቼውንም የማልረሳው፣ መፅሐፍ ቅዱስ መከልከሌን ነው፡፡ የእስር ቤት ትልቁ ትዝታዬ፣ መፅሐፍ ቅዱስ እንዳይገባልኝ ተከልክዬ፣ ማንበብ አለመቻሌ ነው። ወረቀት ባይገባ እኛ በኬክ መጠቅለያ፣ በካርቶን፣ በሳሙና ወረቀቶች ላይ እንፅፍ ነበር፤ ይሄን እንዳላደርግ በተደጋጋሚ ቢነገረኝም፣ እምቢ ስላልኩ፣ መጨረሻ ላይ እልህ ይዟቸው፣ መፅሐፍ ቅዱስ እንዳይገባልኝ ነው የከለከሉኝ፡፡ ይሄ በእውነቱ የልቦና መታወር ነው፡፡ ለኔ የስርአቱን ዝቅጠት ከሚገልፅልኝ አንዱ ይሄ ነው፡፡ በእርግጥ ህፃናትም በጠራራ ፀሐይ፣ በጥይት ሲሞቱ አይተናል። እኔ ምናልባት ለእስር ቤቱ ዲሲፕሊን አልተገዛሁም ይሆናል፤ ግን መፅሐፍ ቅዱስ በመከልከል የተደረገብኝ ቅጣት ለነሱም ነገ የሚቆጫቸው እንደሚሆን አልጠራጠርም። ምናልባት ወረቀት በመከልከላቸው ላይፀፀቱ ይችሉ ይሆናል፤ መፅሐፍ ቅዱስ እንዳላነብ በመከልከላቸው ግን ለወደፊት ይፀፀቱበታል፡፡ ለእነሱም ለራሳቸው፤ ”ለወደፊት ትፀፀቱበታላችሁ” ብያቸዋለሁ፡፡
በፍ/ቤት ንብረትህ መታገዱ ይታወቃል፡፡ የሱ ጉዳይስ ምን ደረሰ?
የታገዱብኝ ሁለት ቦታ የሚገኙ ቤቶቻችንና በባለቤቴ ስም የተመዘገበ መኪና ነው፡፡ ምን እንደሚሉ ባላውቅም፣ እግዱን እንዲያነሱልን እንጠይቃቸዋለን። ይቅርታ ሳንፈርም ነው የወጣነው። ምን መልስ እንደሚሰጡን አናውቅም፡፡ እኔም ሆነ ባለቤቴ፣ ያኔም ቢሆን አልተከራከርናቸውም፡፡ አሁንም ያን ያህል አንከራከራቸውም፡፡ ይሄን የምለው ሀብታም ሆኜ ሳይሆን አንድ ቀን ዲሞክራሲያዊ ስርአት እውን ሲሆን ንብረቴን እንደማገኝ እርግጠኛ ስለሆንኩ ነው።

አሁን ምን ለመሥራት ነው ያቀድከው?

የኢትዮጵያ ህዝብ የደም መስዋዕትነት ከፍሎ ከእስር ስላስፈታን፣ ውለታው አለብን፡፡ አሁንም ከእስር የወጣነው ለትግል ነው፡፡ አሁንም የኔ ኃላፊነት፣ በሰላማዊ መንገድ መታገል ነው፡፡ በአንድ በኩል ጋዜጠኝነቱን እየሰራሁ፣ በሌላ በኩል ለዲሞክራሲና ለሰብአዊ መብቶች መከበር መታገሌን እቀጥላለሁ፡፡ በምንም መንገድ ወደ ኋላ አልልም፡፡

Filed in: Amharic