>
5:18 pm - Sunday June 15, 1208

ለአቶ ገዱ የቀረበው ጥያቄ የምሁራንና የአክቲቪስቶች (የስሉጣን) ወይስ የኦነግና ኦነጋውያን? (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው )

ጥቂት ምሁራንና አክታቪስቶች (ሥሉጣን) የተባሉ የሚበዙት የኦሮሞ ተወላጆች የሆኑ ግለሰቦች የኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርት ወያኔ የአማራ ክልል በሚለው የሀገራችን ክፍል እንዲሰጥ እንዲደረግ ለአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የጻፉትን ደብዳቤ በድረገጾች ተለቆ አግኝተን አንብበናል፡፡
ደብዳቤው በርካታ ግራ የሚያጋቡ ነገሮች ያሉበት ደብዳቤ ነው፡፡ ለምሳሌ ጥያቄው የቀረበበት ምክንያት ተብሎ የተጠቀሰው “የአማራ ክልል የግእዝ ፊደልን ቅርስነት የመጠበቅ ተቀዳሚ ኃላፊነት መወጣት ስለሚገባው!” የሚል ነው፡፡ እንግዲህ ልብ በሉ! ይሄንን ነጥብ ምክንያት ካደረጉ በኋላ ምን ጥያቄ አቀረቡ “ኦሮምኛ በክልሉ እንዲሰጥ ይደረግ!” የሚል ጥያቄ አስከተሉ፡፡ አሁን እስኪ እነኝህኝ ሁለት ነገሮች ምን አገናኛቸው??? አማርኛ ትምህርት በሌላ ቋንቋ ፊደል ተሰጥቶ ቢሆን ክልሉ የተጠየቀው እሽ፡፡ ይሄ ባልሆነበት ሁኔታ ሁለቱን ነገሮች ምን ያገናኛቸዋል???
ነው ወይስ ሰዎቹ ወያኔ የኦሮሚያ ክልል ሲል ለሚጠራው መሥተዳድር ጻፍን ብለው በስሕተት ወያኔ የአማራ ክልል ወደሚለው ጽፈውት ይሆን??? ምክንያቱም ያቀረቡት ምክንያትና ጥያቄያቸው ተስማምቶ የሚገኘውና አግባብ የሚሆነው ጥያቄው የኦሮሚያ ክልል ለሚሉት ቢቀርብ ነውና ነው፡፡ አየ የኛ ምሁራንiii
የገረሙኝ ሌሎቹም አብረው መሰለፋቸው ነው፡፡ ይመስለኛል “ይሄ መደረጉ ለሁለቱም ሕዝቦች ፍቅርን አንድነትን መግባባትን ይፈጥራል!” የሚል የኤለመንተሪ (የወጣኒ) አመክንዮ አቅርበውላቸው ይመስለኛል የደለሏቸው፡፡ እውነታው አንዱ የሌላውን ቋንቋ ማወቁ የተባለውን ፍቅር አንድነት ያመጣል ወይ ነው ጥያቄው??? የሚያመጣ ቢሆን ሶማሊያ፣ ሊቢያ፣ የመን፣ ሶሪያ ወዘተረፈ. ሀገራት ያውም አንድ ቋንቋ አንድ ባሕል አንድ ሃይማኖት ይዘው በቀውስ ይናጡ ይመሰቃቀሉ ነበር ወይ ምሁሮቻችን??? እሽ ይሄ ከሆነ አመክንዮአቹህ ጥያቄያቹህን ለምን የአማራ ክልል ለምትሉት ብቻ አቀረባቹህ??? ለምንስ ኦሮምኛን ብቻ አላቹህ??? ምድረ ቅጥረኛ እንኳን ይች ይች የዝንብ ጠንጋራ እንኳ አትጠፋንም፡፡
ወገኔ ሆይ! ይህች ነገር እውነት እንዳትመስላቹህ ተማክረው ከጨረሱ በኋላ ነው ጥያቄው ከሕዝብ የመጣ ለማስመሰል ይህች ተንኮል የተጠነሰሰችው፡፡ ምናለ አምሳሉ ትሉኛለቹህ በአዱ ቅጥረኛው ብአዴን መሰንበቻውን ውሳኔ ያስተላልፍና ይሄንን ጥያቄ ተግባራዊ ለማድረግ ሲንደፋደፉ ታዩዋቸዋላቹህ፡፡ የዚህ ተግባር ዓላማም የአማራን ተማሪ ሆን ተብሎ በተሠራበት ሸፍጥ የትምህርት ጥራቱ እንዲህ ጉድ በሚያሰኝ ደረጃ አሽቆልቁሎ ተማሪው እንኩቶ መሆኑ ሳያንሰው ፋይዳ በሌለው የትምህርት ዓይነት በመጥመድ፣ ትኩረት ሊሰጣቸው ለሚገቡ የትምህርት ዓይነቶች በቂ ትኩረት እንዳይሰጥ በማድረግ ጊዜውን በመሻማት ከምንም ሳይሆን እንዲቀር ለማድረግ ሲሆን አንዱ ዓላማ፡፡
ሌላኛው ዓላማ ደግሞ ኦሮምኛ ቋንቋ ከኦሮሞዎች ውጭ ሌላ ተናጋሪ ስለሌለውና ይሄም ደግሞ ኦሮምኛን የማዕከላዊ (የፌዴራል) መንግሥት የሥራ ቋንቋ የመሆኛ አንደኛውን መስፈርት ስለሚያሳጣው ይሄንን ውስንነቱን ለመቅረፍ የተሴረ ሴራ ነው፡፡ ደግሞ በጣም የገረመኝ ነገር ቢኖር እነኝህ ጥያቄውን አቅራቢዎቹ “በአማራ ክልል ነዋሪዎች በተደረገ የናሙና ጥናት የክልሉ ነዋሪ የኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርት መማር እንደሚፈልግ አረጋግጠናል!” ማለታቸው ነው፡፡
ሰው ያምነናል ብለው በድፍረት ይሄንን ማለታቸው የሰዎቹን ቅሌትና በቁም ቅዠት ላይ ያሉ ቀባጣሪ መሆናቸውን አያሳይም ትላላቹህ??? በአንድ በኩል “በአማራና በኦሮሞን ሕዝብ መሀል መስማማትን፣ መግባባት፣ ፍቅርን፣ አንድነትን ለመፍጠር፣ ለመመሥረት ስለሚረዳ!” ይላሉ፡፡ ይሄ ዓይነት ችግር በሁለቱ ሕዝብ መሀከል ካለና በዚህም ምክንያት ከሆነ ኦሮሚያ በሚሉት “አማርኛ የሚባል ቋንቋ መማር አንፈልግም!” ተብሎ የተተወው እንዴት ሆኖ ነው ታዲያ እናንተ እንዳላቹህት “በሳይንሳዊ መንገድ ናሙና በመውሰድ (ወላጆችን፣ የትምህርት አስተዳደር ሠራተኞችን፣ መምህራንንና ተማሪዎችን) በተደረገው በዚህ ጥናት የተገኘው ውጤት የኦሮምኛ ቋንቋ በክልሉ ትምህርት ቤቶች በሁለተኛ ቋንቋነት እንዲሰጥ በአንደኛነት መመረጡን ነው!” የሚል ውጤት ልታገኙ የቻላቹህት የኛ ምሁራን??? ቢያንስ እንኳ ማቄል ከፈለጋቹህም እንኳ ምናለ አቂያቂያሉን ብትችሉበት??? ችሎታው ከሌላቹህም ከምትቀሉ፣ ቅጥረኝነታቹህን በቀላሉ ከምታጋልጡ ምናለ ብትተውት???
በጣም የሚገርመው ደግሞ ምን አሉ የጠየቁት ነገር በዓለም የተለመደና የሚሠራበት መሆኑን ምሳሌ ሲጠቅሱ “ይህ አሠራር በሠለጠኑት ሀገራት በተለይም በአውሮፓ የተለመደ አሠራር ነው። ለምሳሌ በፈረንሳይ የትምህርት ፖሊሲ እያንዳንዱ ዜጋ ከፈረንሳይኛና ከእንግሊዘኛ በተጨማሪ ሌላ ሦስተኛ ቋንቋ በምርጫ እንዲማር ይደረጋል። አንዳንዶቹ ጀርመንኛ አንዳንዶቹ ራሺያኛ፣ አንዳንዶቹ ጣሊያንኛ… ይመርጣሉ!” ብለው አረፉት! አይገርሙም???
አሁን የሀገራችንንና ፈረንሳይን የትምህርት ጥራት፣ የተደራሽነት አቅም፣ የሠለጠነ የመማር ማስተማር ሒደት፣ ምቹ ሁኔታ፣ የትምህርት መርጃና ተያያዥ ነገሮች አቅርቦት፣ የሠለጠነ የሰው ኃይል ወዘተረፈ. ምን የሚያገናኛቸው፣ የሚያቀራርባቸው፣ የሚያመሳስላቸው ነገር ኖሮ ነው ለኛ ፈረንሳይ በምሳሌነት የምትጠቀሰው??? ምን ነክቷቹሃል ሁለቱ ሀገራት እኮ የሰማይና የመሬት ያህል ልዩነት አሏቸው፡፡ ለጨቅላ ጎረምሳ ምሳሌ ሆኖ ይቀርባል እንዴ???
እኔ በጣም ነው የገረመኝ! ግን እርግጠኞች ናቹህ ይሄንን ደብዳቤ የጻፉት በስም የተጠቀሱት ግለሰቦች ናቸው??? እኔ አንድ የበሰለ ነገር እንኳ ባጣበትና ለተጠቀሱት ግለሰቦች ከነበረኝ ግምት አኳያ እነሱ ጻፉት ብየ ለማመን እጅግ ተቸግሬያለሁ፡፡
በስም ተዘርዝራቹህ ስማቹህ የተጠቀሰ ፦
1. ዶ/ር አበራ ሞላ
2. ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ
3. ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ
4. ዶ/ር ባዬ ይማም
5. ፕሮፌሰር ሃይሌ ላሬቦ
6. አትሌት ገዛኸን አበራ
7. የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ
8. አቶ ያሬድ ጥበቡ
9. አቶ ሰይፉ ኣዳነች ብሻው
10. አቶ ተፈራ ድንበሩ
11. አቶ ሙሉጌታ ዉዱ
12. አቶ አበባየሁ ደሜ
13. አቶ ብርሃኑ ገመቹ
14. አቶ አብርሃም ቀጄላ
15. አቶ ሃብታሙ ኪታባ
16. አቶ ግርማ ካሳ
ምን ዓይነት አደገኛ ስሕተት እንደፈጸማቹህ ፈጽሞ የገባቹሁ አልመሰለኝም፡፡
ያለጥርጥር ከመሀላቹህ ለጠላት የተቀጠረ ሰው አለ፡፡ አብዛኞቻቹህ በቅጥረኞቹ ተነድታቹህ የገባቹህ እንደሆናቹህ እንዲሁ መገመት ይቻላል፡፡ እነኝህ ተነጅዎቹ ምን ዓይነት አደገኛ ስሕተት እንደተሳሳቱ ያወቁ የገባቸው አልመሰለኝም፡፡ በመሆኑም ነው የተባበሯቸው፡፡
ቢገባቹህ ይሄንን ፈጽሞ አግባብነት የሌለው በጣም ያልበሰለ ጥያቄ በማቅረባቹህ የኦሮሞን ሕዝብ መጥፎ ትምህርት አስተምራቹህታል፣ ቢገባቹህ በዚህ ድርጊታቹህ የሀገራችንን ፖለቲካ ካለበት በባሰ ሁኔታ እንዲወሳሰብ አድርጋቹህታል፣ ቢገባቹህ የኦሮሞን ሕዝብ “አማራ ቋንቋህን ካልተማረ፣ ካላወቀልህ በስተቀር ቋንቋውን እንዳታውቅለት፣ እንዳትማርለት፣ አክብሮትና ፍቅር እንዳትሰጠው!” የሚል አደገኛ ትምህርት ነው እያስተማራቹህት ያላቹህት፡፡ ፍጹም ኃላፊነት የጎደለውና ያልበሰለ ሥራ ነው የሠራቹህት፡፡
ከዚህ ቀደም ኦነግ በተሳሳተ ስሌት የኦሮሞ ሕዝብን አብላጫ (majority) ልብ በሉ 50+1 ቁጥር ላይ ያልደረሰ ቁጥር ማጆሪቲ (አብላጫ) አይባልም፡፡ እነሱ ግን እንደሆኑ በማስመሰል በዚህ ምክንያት “ከኦሮምኛ በተሻለ ለሀገሪቱ ተቀዳሚ የሥራ ቋንቋ የመሆን መብት ያለው ቋንቋ የለምና ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ኦሮምኛ የሀገሪቱ የሥራ ቋንቋ ይሁን!” የሚለው የእነ ኦነግ ጥያቄ ከዲሞክራሲያዊ (ከመስፍነ ሕዝባዊ) መብት፣ ከፖለቲካዊ (እምነተ አሥተዳደራዊ) ፣ ከእኩልነት፣ ከኢኮኖሚያዊ (ጥሪታዊ) ፣ ከማኅበራዊ፣ ከፍትሕ ጉዳዮች አንጻር በሰፊው በመተንተን ጥያቄው በእጅጉ አግባብነት የሌለው ጥያቄ መሆኑን በማሳየት “ኦሮምኛ ከአማርኛ በተጨማሪ የሥራ ቋንቋ ሊሆን ይገባል ወይ? በቋንቋ አጠቃቀም ላይ የቡድንና የግለሰብ መብት እንዴት ይጠበቃል?” በሚል ርእስ በጻፍኩት ጽሑፍ መጻፌ ይታወሳል፡፡ ለምንና እንዴት አግባብነት እንደማይኖረው ሊንኩ (ይዙ) ይሄውና ጽሑፉን አንብባቹህ ተረዱ፡፡
እናም ተቆርቋሪ መሳይ ምሁራንና ስሉጣን ሆይ! እውን እንደምትሉት ተቆርቋሪ ከሆናቹህ የአማራ ክልል በምትሉት የሀገራችን ክፍል ኦሮምኛ ቋንቋን በተመለከተ በአማራ ክልል ኦሮሚያ ዞን በምትሏቸው አካባቢዎች ኦሮምኛ ትምህርት እንዲሰጥ በማድረግ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት በሚባለውም ተወካይ እንዲኖራቸውና ሐሳባቸውን በኦሮምኛ እንዲገልጹ በማድረግ እንደ አገዛዙ ሕግ መሆን ያለበት ተግባር በሚገባ እየተፈጸመ ያለ ነው፡፡
ከዚህ በላይ ሊፈጸም የሚችል አግባብነት ያለው ጥያቄ ስለሌለ ማሰብ የምትችሉና ኃላፊነትም የሚሰማቹህ ከሆነ በአገዛዙ አኀዛዊ መረጃ መሠረት ዐሥራ አንድ ሚልዮን (አእላፋት) አማራ ባለበት ኦሮሚያ በምትሉት የሀገራችን ክፍል አንድም የአማራ ዞን ለሌለበት፣ ይሄንን ያህል የአማራ ሕዝብም የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት በምትሉት አንድም ተወካይ እንዳይኖርና በቋንቋው በአማርኛ ሐሳቡን እንዳይገልጽ ላደረገው፣ በዜግነቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የማወቅ ግዴታ ያለበትን የሀገሪቱን ወይም የማዕከላዊ መንግሥትን (የፌዴራሉ መንግሥትን) የሥራ ቋንቋን የኦሮሞ ተማሪዎች እንዳይማሩ እንዳያውቁ ላደረገው፣ በታወረ ጥላቻ በመነሣሣት የሀገሪቱን ፊደል በመተው አመች ያልሆነውንና እጅግ አባካኙን የላቲን የባዕድ ፊደል አገለግሎት ላይ እንዲውል ላደረገው ወዘተረፈ. በርካታ ዓይነት ታሪክ ይቅር የማይለውን ግፍ በደልና ስሕተት ለፈጸመውና እየፈጸመ ላለው የኦሮሚያ ክልል ለምትሉት መሥተዳድር እነኝህን ችግሮች እንዲያርም፣ እንዲያስተካክልና በእነኝህ ድርጊቶች ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮች እንዲቀረፉ እንዲወገዱ የሚጠይቅ ጥያቄ አቅርቡ፡፡ መፍትሔው ይሄ ነው፡፡
በእርግጥም ወያኔ ባመጣው የጥላቻ ፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) ምክንያት ኦሮምኛ፣ አፋርኛ፣ ሴማሊኛ የመሳሰሉ ቋንቋዎች የራሳችንን የሀገራችንን ፊደል ጥለው የባዕዳንን ፊደል እንዲጠቀሙ መደረጋቸው አሳዛኝና አሳፋሪም ነው፡፡ እነሱ የሚሉት “የአማርኛው ፊደል አንዳንድ የኦሮምኛ ድምፆችን የሚወክል ፊደል ስለሌለው ለምሳሌ በደ እና በጰ መሀከል ላለች ድምፅ ፊደል አለመኖሩ፣ ለሚጠብቅ ለሚላላ ለሚሳብ ድምፅ ምልክት አለመኖሩ፣ የአንዳንድ የኦሮምኛ የድምፅ ቤቶች ርባታ እስከ ዘጠኝ የሚደርሱ በመሆናቸው!” የሚሉ ምክንያቶችን ይጠቅሳሉ፡፡
ችግሮች ተብለው የተጠቀሱት ሁሉም ግን መፍትሔ ያላቸውና ለከፊሎቹ ችግሮች እንዲያውም ገናድሮ መፍትሔ የተሰጣቸው ችግሮች ሲሆኑ ለቀሪዎቹም ችግሮች መፍትሔያቸው ቀላል በመሆኑ የቀረበው ምክንያት አሳማኝ አልነበረም፡፡ በተለይም ደግሞ የመረጡት የላቲን ፊደል በርካታ የኦሮምኛ ድምፆች የሌሉት ከመሆኑም በተጨማሪ ፊደሉ እንደኛ ፊደል sillabery  ማለትም አናባቢንና ተነባቢን በአንድ ድምፅ የሚወክል ባለመሆኑና alphabetical ወይም አናባቢንና ተነባቢን አንድላይ በመደርደር የሚፃፍ በመሆኑ ይሄም አፃፃፍ እጅግ አባካኝና ለአነባበብም አስቸጋሪ አሻሚ በመሆኑ ወደላቲኑ የተደረገው ሽግግር ምክንያት ገቢራዊ (ቴክኒካል) ሳይሆን ፖለቲካዊ መሆኑን አጋልጧል፡፡
እኔ በግሌ ከአምስት ዓመታት በፊት የአማርኛ ወይም የግእዝ ፊደላችን ያለው አቅም የየትኛውም ሀገርና ሕዝብ ቋንቋ ፊደል ፈጽሞ ሊደርስበት በማይችል ደረጃ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ይሄንን አቅሙን ለማሳየት ኦሮምኛን፣ ሶማሊኛን፣ አፋርኛን ብቻ ሳይሆን ላቲን ፊደል ተጠቃሚ ለሆኑ የዓለም ቋንቋዎች እንዲሁም ሌሎችም በፊደሎቻቸው ምክንያት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እየተጋፈጡ ላሉ የዓለም ቋንቋዎች በሙሉ ማገልገል እንዲችል ለማድረግ በማሰብ  ባለው ፊደላችን ላይ የሚጨመሩ 182 አዳዲስ ፊደሎችን፣ ዓለም እየተጠቀመበት ያለው የዓረቡ ቁጥር ለማጭበርበር የተመቸ በመሆኑና በርካታ ችግሮችን እየፈጠረ በመሆኑ ፈጽሞ ለመጭበርበር የማይችሉ ለመጻፍ የተመቹ ቁጥሮችን፣ ዐሥር ሽህ ዜሮ (ባዶ) ያለውንና ምዕራባውያኑ የዓለማችን ስም ያለው የመጨረሻውን ቁጥር እያሉ የሚኩራሩበትን Googolplexian የተባለውን ቁጥራቸውን አራት መቶ ጊዜ እጥፍ የሚበልጥ የቁጥር ስሞችን፣ ሁነታዊ የስሜት ምላሽ ለሆኑ ነገር ግን ፊደል ለሌላቸው የአማርኛ ድምፆች እነኝህን ሁሉ ፈልስፌ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ (መካነ ትምህርት) የኢትዮጵያ ባሕልና ቋንቋዎች አካደሚ (መካነ ጥናት) ለፊሎሎጅ ዲፓርትመንን (ለሥነ ልሳን ክፍለ ጥናት) አቅርቤ ነበረ፡፡
ወያኔ ቀጭን ትዕዛዝ በማስተላለፉ አካደሚው (መካነ ጥናቱ) ለሦስት ወር ሲያጠናውና ሲመረምረው ከቆየ በኋላ “ከቋንቋዎች የተለያየ ከሥነ ድምፅ ተፈጥሮ አኳያ የአንድ ቋንቋን ፊደል ለሌላ ቋንቋ ማድረግ አይቻልም!” የሚል አስቂኝ ምክንያት በመጥቀስ አካደሚው የምርምርና የፈጠራ ሥራየን እንደማይቀበለው ገልጾ ሸኘኝ፡፡
እኔም የሬዲዮ (የነጋሪተ ወግ) ዝግጅት በማመቻቸት በብዙኃን መገናኛ ላይ ቀርበን እንከራከር ብየ ጥያቄ ባቀርብላቸውም በሰጡኝ ምላሾች የማያፍሩና የሚተማመኑ ስላልነበሩ ፈቃደኛ ሳይሆኑልኝ ቀሩ፡፡ ጉዳዩም በዚያው ተረስቶ ቀረ፡፡ የፈጠራ ሥራዬን ጥቂት ክፍል ግን በሐመር መጽሔት ላይ እንዲወጣ አደረኩት፡፡
ወደ ቀደመው ነገራችን እንመለስና እናም በስም ተጠቅሳቹህ ጥያቄውን አቀረባቹህ የተባላቹህ ግለሰቦች ሆይ! እንደቀላል ነገር የተነፈሳቹህት ነገር ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ልትገምቱት ከምትችሉት በላይ የዚህች ሀገርንና ሕዝቧን ችግር ይበልጥ የሚያወሳስብና ችግር የሚፈጥር በመሆኑ መጠቀሚያ ከመሆናቹህ በፊት ጥያቄያቹህን ትስቡ ዘንድ እንጠይቃለን!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
Filed in: Amharic