>

የቴዎድሮስ አሟሟት-በአለቃ ወልደማርያም፤ (ውብሸት ሙላት)

የታጠቅ አሰያየም፤
የቡዳ ጅብ በመቅደላ፤
የማይነበብ ደብዳቤ አጻጻፍ፤
የቴዎድሮስ አሟሟት-በአለቃ ወልደማርያም፤
(ውብሸት ሙላት)
150ኛው መቅደላ የተያዘበትን ማስታወሳችንን ቀጥለናል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዋቢ ደግሞ አለቃ ወልደማርያም (የሸዋ ምሁይ ቆላ ሰው) ዜና መዋእል ነው፡፡ መቅደላ የነበሩ ናቸው፡፡ የጻፉት ዐጼ ቴዎድሮስ ራሳቸውን በጀግንነት መስዋእት ባደረጉ በ13ኛው ዓመት ነው፡፡ ከዚህ መጽሐፍ ላይ አራት አጫጭር ታሪኮች ተመርጠዋል፡፡
ተዋበች የታጠቅ ሰያሚ
የዐጼ ቴዎድሮስ የመጀመሪያ ባለቤታቸው እቴጌ ተዋበች አሊ ናቸው፡፡ የታናሹ ራስ አሊ ልጅ፡፡ ካሳ ኃይሉ ልጅ እያለ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ተማረ፡፡ ውትድርናም ከደጃች ጎሹ ዘንድ ገብቶ ተማረ፡፡ ከዚያም ከራስ አሊ ጋር መኖር ይጀምራል፡፡
ወዳጆቹም “እንግዲህ አግባና ትዳር ያዝ” ይሉታል፡፡
እሱም “ተዋበች ካልሆነች ማንን አገባለሁ?” ይላል፡፡
እነሱም “እንዴት አንድ ተራ ወታደር የራስ አሊን ልጅ ያገባል?” ይሉታል፡፡
ውሎ አድሮ ነገሩ ከራስ አሊ ዘንድ ደረሰ፡፡
ራስ አሊም “እንዴት አንድ ጭፍራ ልጄን ላግባ ይላል?” በማለት አለቅጥ ተናደዱ፡፡
የራስ አሊ እናት ወይዘሮ መነን ግን “ክርስቶስ ባለው ይሁን፤ በሀብቱ ያሳድራት፤ እንስጠው፡፡” ብለው ተዋበችን ይገባል፡፡
ኑሮውም ደብረ ታቦር ከአማቶቹ ጋር ሆነ፡፡ አንድ ቀን መድኃኒት ወስዶ “ምግብ ላኩልኝ” ቢል የወርች ሥጋ ተላከለት፡፡ “ገምቦኛ አይደለሁም፤ ወርች አልበላም” ብሎ መለሰው፡፡ ተዋበችም ይህንን ተመለክታ “አገር የለህም ታጠቅ እንሂድ!” ብትል “ምነው የለኝ” ብለው ወደ ቋራ ወረዱ፡፡
በዚሁ ምክንያት የፈረስ ስማቸው አባ ታጠቅ ተባሉ፡፡
የቡዳ ጅብ በመቅደላ፤
ደጃች ውቤ የስሜኑ ገዥ የነበሩትና ከእቴጌ ተዋበች ሞት በኋላ የዐጼ ቴዎድሮስ ባለቤት የጥሩወቅር አባት በመቅደላ ነበሩ እና እሳቸው የሞቱ ዘመን በመቅደላ ብዙ ችግር ተከሥቶ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ የቡዳ ጅብ እና ነብር ዋነኛው ነበር፡፡ አለቃ ወልደማርያም ጅብና ነብር ሰውን አስቸገረ፡፡  ብዙ ጭንቅም በሆነ ጊዜ አምባው ነፍጠኛ ተመካከሮ ቢተኩስ ብዙ ጅቦች ተገደሉ፡፡
አለቃ ዘነብ የሚባለው የዐጼ ቴዎድሮስ የተወደደ ፀሐፊም ብቻውን አስራ አንድ ጅብ ከደጁ ላይ ገድሏል ይላሉ፡፡ ነብርም እንዲሁ አስቸገረ፡፡ ድመትም ሆነ አይጥ ቤት ውስጥ ሲያንኮሻኩሽ ድንጋጤ በዛ፡፡ አንድ ነብር ተገድሎ ከሁለት ተክፍሎ ቢቀበር በማግስቱ ተቆፍሮ እንደወጣ ታየ፡፡ ጅቦቹ የቡዳ መሆናቸው የሚታወቀው በጆሮውና በአንገቱ በሚኖር ምልክት እንደሚታወቅ ይናገራሉ፡፡
የማይነበብ የምሥጢር ደብዳቤ፤
ጳጳሱ አቡነ ሰላማ ከዐጼ ቴዎድሮስ ጋር ከተጣሉ በኋላ በመቅደላ በቁም እስር ይኖሩ ነበር፡፡ ኋላ ላይ ወደ ሸዋው ንጉሥ ምኒልክ መምጣት እና ለዚህም እርዳታ እንዲደረግላቸው ደብዳቤ መላክ ይፈልጋሉ፡፡ ይኽንኑ ጉዳይ ለአለቃ ወልደማርያም ቢያማክሩት ጽፎ ወደ ሸዋ ለማድረስ መንገድ ላይ ቢያዝም  የመጣው ይምጣ ብሎ ይስማማል፡፡
ኋላ እንደውም የጥበብ ቀለም አብጅቶ ከመንገድ ቢያዝና ከዐጼ ቴዎድሮስ ቢቀርብም በተጻፈው ወረቀት የጽሑፉ ቀለም እንዳይታይና እንዳይነበብ በማድረግ ከዚያ ደግሞ በጥበብ እንዲገለጥ በማድረግ ጽፈው በገብረ ሥላሴ እጅ ተላከ፡፡ ምንም እንኳን ከጥቂት ወራት በኋላ ጳጳሱ ቢያርፉም፡፡
ዐጼ ቴዎድሮስ አሟሟት በመቅደላ፤
የእንግሊዝ ጦር መቅደላ አቅራቢያ አረጌ ላይ ጦርነት አድርጎ እነ ገብርዬ ይሞታሉ፡፡ ጦርነቱ እየበረታ መጥቶ የመቅደላ አምባ የታችኛውን በር በሚጠብቁበት ወቅት ዐጼ ቴዎድሮስ ብቻቸውን ሔደው ሁለት የእንግሊዝ ወታደሮችን ገድለው ተመለሱ፡፡ በዚህን ጊዜ እንግሊዞቹ ወደ ንጉሡ አልተኮሱም፡፡ ንጉሥን እግዚአብሔር የቀባው ነውና መግደል ተገቢ አይደለም የሚል መርሕና ትእዛዝ ስላለባቸው፡፡ የመጨረሻ ዓላማቸውም በሕይወት እንዳሉ መውሰድ ይመስላል፡፡
ጦርነቱ እየበረታ ሲሄድ እሳቸውም አምባው ወጥተው በሩ ተዘጋ፡፡ 1860 ዓ.ም. የፋሲካ (የትንሳኤ) በዓል ማግስት ሰኞ ላይ በሩ በመድፍ ተሰበረ፡፡ የእንግሊዝ ወታደሮችም በሩን ሰብረው ሲገቡ ዐጼ ቴዎድሮስ ከላይኛው በር እልፍ ብለው ነበር የተቀመጡት እና ወታደሩ “ማፊሽ”  አለ፡፡ “የለም” ለማለት ነው፡፡ ንጉሡን እየፈለገ ወደሳቸው ሲቀርብ ቢያዩት ጊዜ:-
 “ይህስ ይዞ አስሮ ሊወስደኝ ሞቴ ይሻለኛል” ብለው “በራስዎ ፈርደው እንደ አመጸኛ ጠበንጃ አሶጡበት” በራሳቸው ፈርደው ጭንቅላታቸው ላይ ጠበንጃ ደግነው ተኮሱበት ሲሉን ነው አለቃ ወልደማርያም፡፡
ራሳቸውን የሰውት ሰኞ ቢሆንም በዚህን እለት ሙሉ ሥዕላቸው ሲሳል ውሎ ማክሰኞ መቅደላ መድኃኔ ዓለም ተቀበሩ፡፡
አሟሟታቸውንም በተመለከተ ከተገጠሙላቸው ውስጥ አንዱ ይህ ነው፡፡
“አያችሁትን ወይ ያንበሳውን ሞት፤
በሰው እጅ መሞትን ነውር አድርጎት፡፡” ተባለ፡፡
Filed in: Amharic