>

ደኢህዴን - የወቅቱ የህወሓት “ምርጥ ባርያ” (ዶ/ር ታደሰ ብሩ)

 የህወሓት መሰሪ የአገዛዝ ስልት የባርያ አሳዳሪ ሥርዓትን ይመስላል።
ህወሓት በመላው ኢትዮጵያ አገልጋዮች አሉት። እነዚህ አገልጋዮች ጌታቸው ህወሓት ያዘዛቸውን ይፈጽማሉ፤ ውረሩ ሲባሉ ይወራሉ፤ ግረፉ ሲባሉ ይገርፋሉ፤ ግደሉ ሲባሉ ይገድላሉ፤ ዝረፉ ሲባሉ ይዘርፋሉ። ህወሓት እነዚህን በቁጥር የበዙ አገልጋዮቹን የሚቆጣጠረው ከእነሱ በላይ ታማኝ በሆኑ “ምርጥ ባርያዎቹ” አማካይነት ነው። ጌታው ህወሓት ያለብዙ ድካም ኢትዮጵያዊያንን በአገልጋዮቹ፤ አገልጋዮቹን ደግሞ በምርጥ ባርያዎቹ እየተቆጣጠረ ይገዛል።
የህወሓት “ምርጥ ባርያዎች” ራሳቸውን ነፃ ለማውጣት ጥረት የሚያደርጉ አገልጋዮችን ይሰልላሉ፤ ያጋልጣሉ። መሰሪው ህወሓት ታማኝ አገልጋዮቹ “ለምርጥ ባርያነት” እንዲፎካከሩ በማድረግ ባሮችን በባሮች ይገዛል።
ከነፃነት እሳቤ አንፃር ሲታይ ከባርነት የከፉ ነገር ማሰብ ይከብዳል። ባርነት ሰው በመሆንና እንስሳ በመሆን መካከል ያለ ድንበር ነው። ይሁን እንጂ ባርያ መሆን ባርነት ተቀብሎ የመኖርን ያህል የከፋ አይደለም። የህሊና ነፃነት ያለው ባሪያ ነገ ነፃ ሰው የመሆን እድል አለው። ባርያነቱን የተቀበለ ባርያ ግን በአካልም፤ በመንፈስም ባሪያ ነው፤ ነፃ ሰው የመሆን እድል የለውም። ባርነትን ከመቀበል ባለፈ ከባርያ አሳዳሪው ጋር ተሻርኮ ሌሎች የሚሰልል፤ የነፃነት ትግልን የሚያደናቅፍ ባርያ ደግሞ ከባርያ አሳዳሪው በላይ የነፃነት ጠላት ነው።
ዛሬ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞልራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ያለበት ሁኔታ ይህንን ይመስላል።
ደኢህዴን ባርነትን በፀጋ የተቀበለ ድርጅት መሆኑ አሳፋሪ ነው። ይህ ሳያንስ ራሳቸውን ከባርነት ነፃ ለማውጣት የሚጥሩ ድርጅቶችን ትግል የሚያሰናክል መሆኑ ደግሞ ከህወሓት በላይ የትግሉ ዒላማ እንዲሆን ያደርገዋል።
በተለይም የደኢህዴን የወቅቱ መሪዎች ሽፈራው ሽጉጤ፣ ሲራጅ ፈጌሳ፣ ደሴ ዳልኬ፣ ተስፋዬ በልጅጌ፣ ተሾመ ቶጋ፣ ሬድዋን ሁሴን፣ መኩሪያ ኃይሌ፣ መለሰ ዓለሙ፣ ሙፈሪሃት ካሚል፣ ታገሰ ጫፎ፣ አስፋው ዲንጋሞ፣ …. የወቅት የህወሓት “ምርጥ ባርያዎች” ናቸው።
በእነዚህ የደኢህዴን መሪዎች ተግባራት የሚሸማቀቁ የደኢዴን አባላት አሉ ብዬ አምናለሁ። በሌሎች የኢህአዴግ ድርጅቶች እንደሆነው ሁሉ በደኢህዴንም ውስጥ ህሊና ያላቸው ወገኖች አሉ ብዬ አምናለሁ።
ለእነዚህ ወገኖች ጥሪ ማቅረብ እሻለሁ። “መሪዎቻችን” በምትሏቸው ሰዎች መሸማቀቃችን መቆም አለበት። “መሪዎቻችን” የምትሏቸው ሰዎች የሁላችንም ማፈሪያዎች ናቸው። ያለ እነሱ ምርጥ ባርነት የህወሓት አገዛዝ ኢትዮጵያችን ላይ ይኸን ያህል ጉዳት ማድረስ ባልቻለም ነበር። ራሳቸው ነፃነት የሌላቸው መሆኑ ሳያንስ ሌሎች ለነፃነት የሚያደርግትን ትግል እያወኩ ነውና ከህወሓት በላይ ተጠያቂዎች ናቸው። ይህ ሀቅ የሚቆጠቁጣችሁ ሁሉ ራሳችሁን ከእነሱ አርቁ። ደኢህዴን የተባለውን አሳፋሪ ድርጅትንም ግደሉት።
Filed in: Amharic